በሁለተኛው ሳምንት ሁለተኛ ቀን የመክፈቻ ጨዋታ የተገናቹት ፋሲል ከነማ እና መቐለ 70 እንደርታ አቻ ተለያዩ። ፋሲል ከነማዎች ቅዱስ ጊዮርጊስን ካሸነፈው ቡድን ምንም ቅያሪ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ሲገቡ፣ የዳንኤል ፀሃዬ ቡድን በተቃራኒው 4 ቅያሬዎችን አድርገዋል። መናፍ አወል፣ ዮናስ ግርማይ፣ ተመስገን በጅሮንድ እና ኩሩቤል ሀይሉ ወጥተው አሸናፊ ሃፍቱ፣ ዘርእሰናይ ብርሃነ፣ ሸሪፍ መሐመድ እና ቤንጃሚን ኮቴ ገብተዋል።
የመጀመርያው አጋማሽ የፋሲል ከነማዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው ለመጫወት መቐለ 70 እንደርታዎች ደሞ በረጃጅም ኳሶች እድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ ታይቷል። አፄዎቹ በመሀል ክፍል በኤፍሬም ሃይሉ፣ አፍቅሮት ሰለሞን እና አቤል እንዳለ አማካኝነት በአንፃራዊነት የተሻሉ ቅብብሎች በማድረግ የኳስ ቁጥጥር ብልጫን መውሰድ ችለዋል። በተለይ አፍቅሮት ሰለሞን ከመሃል ሜዳው የግራ ክፍል እየተነሳ ለማርቲን ኪዛ እና ቃልኪዳን ገዛሀኝ ያቀበላቸው ኳሶች የመጀመሪየው 45 የፋሲል ለግብ የቀረቡ እድሎች ነበሩ።
መቐለዎች የፋሲል ከነማን ተከላካይ ክፍል ወደ መሀል ሜዳ መጠጋትን ለማጥቃት ተደጋጋሚ ረጅም ኳሶችን ሲጥሉ ነበር። የዚህ እንቅስቃሴ ውጤትም በ27ኛው ደቂቃ ከተከላካይ ክፍሉ በረጅሙ የተላከውን ኳስ ያሬድ ብርሃነ ከቦና ኣሊ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብለው አሸናፊ ሃፍቱ መትቶት የተተፋውን ኳስ ያሬድ ብርሃነ ማስቆጠር ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኃላ ፋሲሎች ወደ ጨዋታው ለመለለስ ጫና ቢፈጥሩም አቻ ሚያደርጋቸውን ግብ ማግኘት አልቻሉም።
ሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመርያው በተመሳሳይ መልኩ የፋሲል ከነማ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እና የምዓም አናብስቶቹ ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች የታዩበት ነበር።
- ማሰታውቂያ -
መቐለዎች ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ በፈጣን ሽግግሮች ለግብ የቀረቡ እድሎችን መፍጠር ችለው ነበር። በተለይ ያሬድ ከበደ ለአሸናፊ የሾለከለት ኳስ ኣሸናፊ ሃፍቱ መሬት ለመሬት በቀኝ እግሩ መትቶት ከግቡ ቀኝ ለትንሽ የወጠው እንዲሁም ያሬድ ብርሃኑ ከአሸናፊ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ የመታው የዚህ እንቅስቃሴ ማሳያ ናቸው።
የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበራቸው አጼዎቹ: አብዛኞቹ ቅብብላቸው በመቐለዎች ጥብቅ መከላከል እና በሜዳው የመጨረሻ ክፍል በነበራቸው ያልተሳኩ ቅብብሎች ምክንያት ግልፅ የግብ እድሎችን ለመፍጠር እንዲቸገሩ ምክንያት ሲሆኑቧቸው ታይቷል። የመቐለ 70 እንደርታ ተጨዋቾች ሳጥናቸው በቁጥር በዝተው መከላካላቸውን ያዩት ፋሲሎች በአፍቅሮት ሰለሞን እና በረከት ግዛባቸው አማካኝነት ከርቀት በሚመቱ ካሶች እድሎችን ቢፈጥሩም ኢላማቸውን የጠበቁ አልነበሩም።
የፋሲል ከነማዎች ተደጋጋሚ ማጥቃት በ65 ደቂቃ ላይ ፍሬ ማግኘት ችሏል። ከሳጥኑ አጠገብ ቢንየም ላንቃሞ በራሱ ላይ በተሰራ ጥፋት የገኘውን ቅጣት ምት ራሱ ቢንየም ላንቃሞ በሚገርም መልኩ በማስቆጠር ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል። በሁለት ጨዋታዎችም ሁለት የቆሙ ኳሶችን በማስቆጠር ጥሩ በአፄዎቹ ቤት ጥሩ ጅማሮውን አስቀጥሏል።
ከግቡ መቆጠር በኃላ ማጥቃታቸውን የቀጠሉት ፋሲሎች በማርቲን ኪዛ አማካኝነት ያገኙት እድል ጨዋታው ላይ በርካታ ሙከራዎችን ሲያድን የነበረው ሶፈንያስ ሰይፈ መልሶበታል። መቐለዎች በበኩላቸው በረጅም በሚጣሉ ኳሶች አልፎ አልፎ እድሎችን ፈጥረዋል። በተለይ በግብ ጠባቂው ኦቦሳጊ ስህተት ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ ያገኘው ኳስ መቐለን ለአሸናፊነት ያቀረበ እድል ነበር።
በዚህም መሰረት በሁለተኛው ሳምንት የተካሄደው የሰሜን ደርቢ ጨዋታ በአቻ ሊጠናቀቅ ችሏል።