ቅዱስ ጊዮርጊስ የውድድር ዓመቱ ቀዳሚ ድሉን ወልዋሎ አዲግራትን 2 – 1 በመርታት አስመዝግቧል።
በጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በፋሲል ከነማ በተረቱበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 ዳግማዊ አርአያን እና ተገኑ ተሾመን በአማኑኤል ኤርቦ እና ፀጋ ከድር ተክተዋል። በወልዋሎ አዲግራት በኩል ደግሞ በባህርዳር ከተማ በተረታበት ጨዋታ ከነበረበው የመጀመሪያ አሰላለፍ ናሆም ሀይለማርያም እና ሰመረ ኪዳነማርያም ታዬ ጌታቸው እና ዳዋ ሆጤሳን ተክተው ገብተዋል።
በጨዋታው ቅዱስ ጊዮርጊሶች ተጭነው በመጫወት ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን የፈጠሩ ሲሆን በተለይም ጨዋታው ገና በሰከንዶች ዕድሜ ሳለ ያገኙትን ዕድል ሳይጠቀሙ ቀርተዋል።
የወልዋሎ አዲግራትን የኳስ ምስረታ በማቋረጥ ያገኙትን አጋጣሚ በረከት ወልዴ አግኝቶ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። በዚህ አጋጣሚ ግን የወልዋሎ አዲግራቶቹ ተከላካዮች ኪሩቤል ወንድሙ እና እያሱ ለገሰ ተጋጭተው እያሱ ለገሰ ከባድ ጉዳት አስተናግዷል።
- ማሰታውቂያ -
እያሱ የእግር ስብራት ጉዳት ያጋጠመው ሲሆን ወድያውኑም ለተጨማሪ ህክምና ወደ ሆስፒታል አምርቷል።
ጨዋታው ዳግም ከተጀመረ በኋላ በ7ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ጥላሁን ቅዱስ ጊዮርጊስን መሪ ያደረገ ግብ ከመረብ አሳርፏል። በረጅም የተላከውን ኳስ ተገሙ ተሾመ በግሩም ሁኔታ በአየር ላይ ከተከላካዮች ጀርባ የጣለለትን ኳስ ፍፁም ጥላሁን ከመረብ አሳርፎታል። ፍፁም በቀዳሚው ጨዋታም ግብ ማስቆጠሩም የሚታወስ ነው።
ወልዋሎ አዲግራቶች በጨዋታው አቻ የሚሆኑበትን ግብ ለማግኘት የፈጀባቸው ሰባት ያህል ደቂቃዎች ብቻ ናቸው።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በፋሲል ከነማው ጨዋታ በቀጥታ ከቅጣት ምት ከተቆጠረበት ቦታ ላይ የተገኘውን የቅጣት ምት ጋዲሳ መብራቴ አሻምቶ ኪሩቤል ወንድሙ በግንባር በመግጨት ከመረብ አሳርፏል።
በጨዋታው 19ኛው ደቂቃ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ባህሩ ነጋሽ ጉዳት አስተናግዶ በተመስገን ዮሐንስ ተቀይሮ ወጥቷል።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይም በተለይም ከተገኑ ተሾመ እግር ስር በሚነሱ ኳሶች የሶስተኛው የማጥቃት የሜዳ ክፍል ላይ ጫና ለመፍጠር ጥረቶችን አድርገዋል። ቡድኑ ኳሱን ይዞ በመጫወት ረገድም ከተጋጣሚው የተሻለ አጋማሽ አሳልፏል።
ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ያን ያህል ጠንካራ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያላደረጉት ወልዋሎ አዲግራቶች ኪሩቤል ወንድሙን በጉዳት ምክንያት 34ኛው ደቂቃ ላይ ቀይረው ለማስወጣት ተገደዋል።
በጨዋታው የሁለተኛው አጋማሽ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲጀምሩ ወልዋሎ አዲግራቶች ከቆይታዎች በኋላ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረዋል።
በአጋማሹ ቀዳሚ ዕድል ተገኑ ተሾመ ከቀኝ መስመር አቅጣጫ የቀነሰውን ኳስ በጨዋታው ግሩም እንቅስቃሴ ያደረገው አብርሀም ጌታቸው በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል።
አብርሀም ጌታቸው ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላም ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅለት ቀርቷል።
በ50ኛው ደቂቃ ላይ የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች ጋዲሳ መብራቴ ከመስመር ተሻግሮ ያገኘውን ኳስ ግብ ጠባቂውን አሳልፎ ቢሞክርም ሻሂዱ ሙሰጠፋ አውጥቶታል።
ከሶስት ደቂቃዎች በኋላም ዳዊት ገብሩ ከሰለሞን ጌታቸው የደረሰውን ኳስ በአግባቡ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
በ61ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው አማኑኤል ኤርቦ ቶሎሳ ንጉሴ ከማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ በግንባር በመግጨት በ71ኛው ደቂቃ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስን ሁለተኛ ግብ ከመረብ አሳርፏል።
አማኑኤል ኤርቦ በቅዱስ ጊዮርጊስ ማልያ 12ኛ ቡድን ላይ ግብ ያስቆጠረ ሲሆን በአጠቃላይ በሊጉ ለፈረሰኞቹ ያስቆጠራቸውን የግብ ብዛቶች 14 አድርሷል። የአርባምንጭ ፍሬ የሆነው አማኑኤል ካስቆጠራቸው 14 ግቦች መካከልም ዘጠኙ ከተጠባባቂ ወንበር ተነስቶ ያስቆጠራችው ግቦች ናቸው።
ፈረሰኞቹ ዳግም መሪ ከሆኑ በኋላ በነበሩት ደቂቃዎች ላይ ወልዋል አዲግራቶች በተደጋጋሚ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ደርሰዋል። ነገር ግን በቀላሉ ጠንካራ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ተቸግረው ጨዋታውን አጠናቀዋል።
በመጨረሻም ቅዱስ ጊዮርጊስ 2 – 1 በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን ቀዳሚ ድል አስመዝግቧል።
በሶስተኛው ሳምንት የሊጉ መርሐግብር በመጪው መስከረም 20(ሰኞ) 10:00 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመቀሌ 70 እንደርታ እንዲሁም ሀሙስ መስከረም 23(ሐሙስ) 1:00 ወልዋል አዲግራት ከሲዳማ ቡና ይጫወታሉ።