በዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር አዳማ ከተማ በስንታየሁ መንግስቱ ብቸኛ ግብ ባህርዳር ከተማን 1 – 0 አሸንፏል።
በባህርዳር ከተማ በኩል ወልዋሎ አዲግራትን ከረታው ቡድን የመጀመሪያ አሰላለፍ አንድ ለውጥ በማድረግ ፍፁም ፍትዓለውን በአቤል ማሙሽ ተክተው ሲገቡ በአዳማ ከተማ በኩል በስሁል ሽረ ከተረታው ቡድን ምርጥ 11 ደግሞ ቻላቸው መንበሩ ፣ ሙሴ ኪሮስ ፣ ሙሴ ከበላ እና ጋዲሳ ዋዶን በኤልያስ ለገሰ ፣ ሃይለሚካኤል አደፍርስ ፣ ዳንኤል ደምሴ እና አድናን ረሻድ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።
በሁለቱም በኩል በማጥቃት ፍላጎት ጅማሮውን ያደረገው ጨዋታው ፈጣን የጨዋታ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። ባህርዳር ከተማዎች በይበልጥ ኳሱን ተቆጣጥረው ወደ ፊት ለመድረስ ሲጥሩ አዳማ ከተማዎች በበኩላቸው በፈጣን ሽግግር ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረዋል።
በጨዋታው 10ኛ ደቂቃ ላይ አዳማ ከተማዎች በነቢል ኑሪ አማካኝነት ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ ቢያስቆጥሩም ከጨዋታ ውጪ በሚል በረዳት ዳኛው ተሽሯል። በአጋጣሚው ቢንያም አይተን ግብ ጠባቂውን ጭምር አልፎ ይዞ የገባውን ኳስ ነቢል ኑሪ ከእግሩ ስር ወስዶ አስቆጥሮ ነበር።
- ማሰታውቂያ -
ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ቸርነት ጉግሳ ከተከላካዮች ጀርባ የተጣለለትን ኳስ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ የአዳማ ከተማው ግብ ጠባቂ ዳግም ተፈራ ተቆጣጥሮታል።
በ18ኛው ደቂቃ ላይ የአዳማ ከተማው የፊት አጥቂ ስንታየሁ መንግስቱ ከቢንያም አይተን በግሩም ሁኔታ የደረሰውን ኳስ በአስገራሚ መልኩ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ በባህርዳር ከተማ በኩል ግርማ ዲሳሳ ከቸርነት ጉግሳ ተቀብሎ በግራ መስመር ይዞ የገባውን ኳስጨፍሬው ሰለሞን አግኝቶ ወደ ግብ ሞክሮ ፍቅሩ አለማየሁ ተደርቦ አውጥቶታል።
ሞቅ ባለ እንቅስቃሴ ጀምሮ የነበረው የምሽቱ ጨዋታ ከ25ኛው ደቂቃ እስከ መጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ድረስ ቀዝቀዝ ያለ ከሙከራም ርቆ የቆየ ሆኖ አልፏል።
የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ልክ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ጅማሮ ሁሉ ጥሩ የማጥቃት ሂደት እንቅስቃሴ የተስዋለበት ነበር።
በአጋማሹ የመጀመሪያ የግብ ሙከራ በ47ኛው ደቂቃ ላይ ሲደረግ ሙሴ ኪሮስ ከአድናን ረሻድ የደረሰውን ኳስ በሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ ሆኖ ያደረገው ሙከራ ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ መልሶታል።
በ53ኛው ደቂቃ ላይም ቢንያም አይተን ከስንታየሁ መንግስቱ የደረሰውን ኳስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
የጣና ሞገዶቹም በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ በተለይም መነሻቸውን ከመስመር ባደረጉ ኳሶች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረቶችን አድርገዋል። ቸርነት ጉግሳ እና ፍፁም አለሙ ያደረጓቸው ኢላማቸውን ያልጠበቁ የግብ ሙከራዎች በዚህ ሂደት ተጠቃሽ ናቸው።
ጨዋታው 67ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ የመጀመሪያው ግብ ተቆጥሯል። አድናን ረሻድ ከቀኝ መስመር ወደ መሀል የቀነሰውን ኳስ ነፃ ሆኖ ያገኘው ስንታየሁ መንግስቱ ከመረብ አሳርፎታል።
ከግቡ መቆጠር ጥቂት ሰከንዶች በኋላ ባህርዳር ከተማዎች የቁጥር ብልጫ ወስደው በአዳማ ከተማ ሳጥን በተገኙበት ወቅት ቸርነት ጉግሳ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ በዳግም ተፈራ እጆች ላይ አርፏል።
በ73ኛው ደቂቃ ላይ ነቢል ኑሪ በግራ መስመር አቅጣጫ ይዞ የገባውን ኳስ ወደ መሀል ሲቀንሰው ያገኘው አምበሉ ቢንያም አይተን በቀጥታ ወደ ግብ ልኮት የግቡን ቋሚ ለትሞ ተመልሷል።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ባህርዳር ከተማዎች ይበልጥ ጫና በመፍጠር ቢያንስ ከጨዋታው አንድ ነጥብ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ስኬታማ ሳይሆን ቀርቷል።
በመጨረሻም አዳማ ከተማ የውድድር ዓመቱን ቀዳሚ ድል በባህርዳር ከተማ ላይ ተቀዳጅቷል።
በሶስተኛው ሳምንት ጨዋታዎች ማክሰኞ መስከረም 10(ማክሰኞ) ረፋድ 3:30 ጀምሮ አዳማ ከተማ ከወልቂጤ ከተማ እንዲሁም በዕለቱ ምሽት 1:00 ጀምሮ ባህርዳር ከተማ ከሀድያ ሆሳዕና ይጫወታሉ።