የ11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ መደረግ ጀምረዋል
የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ መደረግ ሲጀምሩ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በተደረጉት ጨዋታዎች ነገሌ አርሲ ድል ሲቀናው ተጠባቂ የነበረው የደርቢ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
በሳምንቱ መክፈቻ በሆነው ጨዋታ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲን የገጠመው ነገሌ አርሲ በአሸብር ውሮ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ 1 ለ 0 አሸንፏል።
ከቤ ብዙነህ በኪሩቤል ወንደሙ በተሰራበት ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አሸብር ውሮ አስቆጥሮ ነገሌ አርሲን አሸናፊ አድርጓል።
- ማሰታውቂያ -
ነገሌ አርሲ ማሸነፉን ተከትሎ ነጥቡን 16 ሲያደርስ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ በበኩሉ በነበረው 8 ነጥቦች ለመቆየት ተገዷል።
በ12ኛው ሳምንት ነገሌ አርሲ ከድሬዳዋ ከተማ እንዲሁም ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ደግሞ ከባህርዳር ከተማ ይጫወታሉ።
ከ10:00 ጀምሮ በአንፃራዊነት በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ የተደረገው የባህርዳር ከተማ እና የፋሲል ከነማ ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርበት 0 ለ 0 ተጠናቋል።
የጨዋታው የመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች የተቀዛቀዘ የሜደ ላይ እንቅስቃሴ የታየባቸው ሲሆን በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ በሁለቱም ቡድኖች በኩል መሪ መሆን የሚችሉባቸውን የግብ ዕድሎች ፈጥረዋል።
በተለይም የተሻሉ ዕድሎችን መፍጠር ችለው የነበሩት የጣና ሞገዶቹ የፋሲል ከተማን የኋላ ክፍል በሚገባ መፈተን ችለው ነበር።
አማኑኤል ገብረሚካኤል በ21ኛው ደቂቃ ላይ ከወንድወሰን በለጠ ከቀኝ የሳጥኑ አቅጣጫ የተቀነሰለትን ኳስ ሳይደርስበት ቀርቷል።
በ22ኛው ደቂቃ ላይም አማኑኤል ከመሳይ አገኘሁ በረጅም የተሻገረለትን ኳስ በአግባቡ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
በአፄዎቹ በኩል በተለይም በግራ መስመር ባደላው የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው የተጋጣሚያቸውን የኋላ መስመር ለመፈተን ጥረቶችን አድርገዋል።
በ21ኛው ደቂቃ ላይ አቤኔዘር ዮሐንስ ከሳጥን ውጪ ያደረገው እና ዋሳዋ ጄኦፍሪ በ39ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ያደረጓቸው ሙከራዎች ፔፔ ሰይዶን የፈተኑ አጋጣሚዎች ነበሩ።
በሁለተኛው አጋማሽ ባህርዳር ከተማዎች በይበልጥ ተሽለው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ችለዋል።
በፋሲል ከነማ በኩልም በፈጣን ሽግግሮች ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን አድርገዋል።
ነገር ግን በሁለቱም በኩል በተጋጣሚ የሳጥን ክልል ሲደርሱ በተጠበቀው ልክ ጠንካራ የግብ ሙከራዎች አላደረጉም።
መሳይ አገኘሁ በባህርዳር ከተማ በኩል ዳግም አወቀ ደግሞ በፋሲል ከነማ በኩል ከሳጥን ውጪ ያደረጓቸው ጠንካራ የግብ ሙከራዎች በግብ ጠባቂዎቹ ተመልሰዋል።
ውጤቱን ተከትሎ ፋሲል ከነማ ነጥቡን 21 ያደረሰ ሲሆን ባህርዳር ከተማ በበኩሉ 14 ነጥቦች ላይ መድረስ ችሏል።
በ12ኛው ሳምንት የሊጉ መርሐግብር ፋሲል ከነማ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ባህርዳር ከተማ ደግሞ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲን የሚገጥሙ ይሆናል።


