በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ስታዲየም ሁለቱን አሰልጣኝ ያሰናበቱ ቡድኖችን ያገናኘው ጨዋታ በመቐለ አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ሀድያ ሆሳዕናም ድል አድርጓል።
አርባምንጭ ከተማ 0-2 መቐለ 70 እንደርታ
ዘጠኝ ሰአት ሲል ሁለቱን አሰልጣኝ ያሰናበቱ እና በውጤት ረሀብ ውስጥ ያሉ ቡድኖችን ያገናኘው በፌድራል ዋና ዳኛ መስፍን ዳኜ የተመራው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በእንቅስቃሴ በተወሰነ ረገድ አርባምንጭ ከተማዎች የተሻሉ ቢመስሉም በመከላከሉ በሚሰሩት ስህተት ጎል ተቆጥሮባቸዋል። 15ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር አቅጣጫ ፍፁም አለሙ ከቅጣት ምት አሻምቶ ኪቲካ ጀማ በግንባር ጨርፎ የግብ ዘቡ ፂሆን መርዕድ በአግባቡ አለመቆጣጠሩን ተከትሎ ኳሷን ያገኘው ብርሀኑ አዳሙ አሳዳጊ ክለቡ መረብ ላይ በማሳረፍ መቐለን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል ከቆመበት እንቅስቃሴው የቀጠለው የቡድኖቹ ጨዋታ የግብ ዕድሎችን ከመፍጠር አኳያ አሁንም ጊዜያዊ አሰልጣኛቸውን ፀጋዬ ኪዳነማርያምን በወረቀት ጉዳይ በዛሬው ጨዋታ ያላገኙት መቐለ 70 እንደርታዎች ጎል አግኝተዋል። 56ኛው ደቂቃ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ወደ ቀኝ የተለጠጠ ኳስን ያገኘው ፍፁም አለሙ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ በጥልቀት ይዞ በመግባት ወደ ውስጥ ያሻገረውን ኳስ የአርባምንጭ ከተማ ልማደኛ የመከላከል ክፍተት ታክሎበት ጎል ተቆጥሮ ጨዋታው 2ለ0 በመቐለ አሸናፊነት ተጠናቋል። ክለቡም ከናፈቀው ድል ጋር መገናኘት ችሏል።
- ማሰታውቂያ -
ሀድያ ሆሳዕና 2-1 ወላይታ ድቻ
በመቀጠል አመሻሹን ሀድያ ሆሳዕናን ከ ወላይታ ድቻ ባገናኘው መርሀግብር ጠንካራ ፉክክርን ነገር ግን የሀድያ ሆሳዕና ፈጣን ሽግግሮችን በአንፃራዊነት ያስተዋልንበትን የመጀመሪያ አጋማሽ አስመልክቶናል። 15ኛው ደቂቃ ላይ በተሳኩ ረጃጅም ኳሶች ማጥቃትን የጀመሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች ከጦና ንቦቹ አማካይ ኪዳኔ አሰፋ እግር ስር እዮብ አለማየሁ የነጠቀውን ኳስ በግምት ከ25 ሜትር ርቀት አክርሮ በመምታት የቢኒያም ገነቱ መረብ ላይ አስቆጥሮ ነብሮቹን መሪ አድርጓቸዋል። ጨዋታው ቀጥሎ ፋታ በማይሰጥ ሽግግር ወደ መስመር አድልተው በይበልጥ የተንቀሳቀሱት ሀድያ ሆሳዕናዎች የግብ ዘቡ ቢኒያም ገነቱ ፀጋአብ ግዛው ላይ ሳጥን ውስጥ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የዕለቱ ዳኛ ሚካኤል ጣዕመ የሰጡትን የፍፁም ቅጣት ከረጅም ጊዜ ጉዳቱ የተመለሰው አምበሉ ሔኖክ አርፊጮ ሁለተኛ ጎል አድርጓታል።
ከዕረፍት መልስ መጠነኛ መሻሻልን ይዘው ወደ ሜዳ የገቡት ወላይታ ድቻዎች በረጅሙ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በሚላኩ ኳሶች አንዳች ነገርን ለመፍጠር ጥረት ቢያደርጉም አወዛጋቢ በሆነ መልኩ የተሰጠን የፍፁም ቅጣት ምት ብቸኛ ጎላቸውን አስቆጥረዋል። 66ኛው ደቂቃ ሙሉቀን አዲሱ ከቅጣት አሻምቶ ናትናኤል ናሲሩ ጎል ቢያደርገውም የዕለቱ ዳኛ ሚካኤል ጣዕመ ፊሽካቸውን አሰምተው ከሻሩ በኋላ በድጋሚ የፍፁም ቅጣት ምት በሚል ሰጥተው የጦና ንቦቹን ከሽንፈት መታደግ ያልቻለች ጎል መልካሙ ቦጋለ በማስቆጠር ጨዋታው 2ለ1 በሆነ ውጤት ተቋጭቷል።


