ድሬዳዋ ከተማ ከአምስት ፤ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ ከሶስት ጨዋታዎች በኋላ አሸንፈዋል
የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ሲደረጉ አዲስ አበባ ላይ በተደረጉት ጨዋታዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ድሬዳዋ ከተማ ጣፋጭ ድሎችን አሳክተዋል።
ከቀን 07:00 ጀምሮ በተደረገው ቀዳሚው ጨዋታ ምድረ ገነት ሽረን የገጠመው የዘሪሁን ሸንገታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ የማታ ማታ ሶስት ነጥብ ይዞ ወጥቷል።
ቀዝቀዝ ያለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የታየበት ጨዋታው ይህ ነው ሊባል የሚችል የግብ ጠባቂዎቹን የፈተነ የግብ ሙከራ ያላስመለከተ ነበር።
- ማሰታውቂያ -

ነገር ግን የጨዋታው መጠናቀቂያ የፊሽካ ድምፅ በሚጠበቅበት ደቂቃ ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ጣፋጭ ሶስት ነጥቦች ያሳኩበትን ጎል አስቆጥረዋል።
ግቡ የተቆጠረው በ90+4 ደቂቃ ላይ ሲሆን ግብ አስቆጣሪው ደግሞ አቤል ሀብታሙ ነው።

ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥቡን 20 አድርሷል።
በ12ኛው ሳምንት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከፋሲል ከነማ እንዲሁም ምድረ ገነት ሽረ ከአዳማ ከተማ ይጫወታሉ።
ከ10:00 ጀምሮ በተደረገው የኢትዮጵያ ቡና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ደግሞ ድሬዳዋ ከተማ ከመመራት ተነስቶ 2 ለ 1 አሸንፏል።
ኢትዮጵያ ቡና የተሻለ በነበረበት የመጀመሪያ አጋማሽ የድሬዳዋ ከተማን የኳስ ምስረታ በጫና በማቋረጥ የግብ ዕድሎችን ጭምር መፍጠር ችለዋል።
በ24ኛው ደቂቃ ላይ ዘላለም አባተ ከቀኝ የሳጥኑ አቅጣጫ የተቀነሰለትን ኳስ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ኳሱን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ አቤል ነጋሽ የቡናማዎቹን ተከላካዮች መዘናጋት ተከትሎ ያገኘውን ዕድል መጠቀም አልቻለም።
ጨዋታው 30ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግን በቡናማዎቹ በኩል የመጀመሪያው ግብ ተቆጥሯል።

አቡበከር አዳሙ በሳጥኑ የግራ ሳጥን መግቢያ ላይ ያገኘውን ኳስ በጠንካራ ምት ወደ ግብ በመላክ ኢትዮጵያ ቡናን መሪ ያደረገውን ግብ ማስቆጠር ችሏል።
የቡናማዎቹ ብልጫ ቀጥሎ በታየባቸው ቀጣዮቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች ላይም በተደጋጋሚ ወደ ድሬዳዋ ከተማ የግብ ክልል መድረስ ችለው የነበረ ቢሆንም ሌላ ግብ ማከል አልቻሉም።
በድሬዳዋ ከተማ በኩል ግሩም መኩሪያ እና አቤል ነጋሽ ያደረጓቸው ሙከራዎች በአጋማሹ የታዩ የግብ ዕድሎቻቸው ነበሩ።
ድሬዳዋ ከተማዎች ተሽለው በታዩበት የሁለተኛው አጋማሽ በተለይም በቀኝ መስመር ያደረጓቸው ተደጋጋሚ የግብ ዕድል መፍጠር ሙከራዎች ፍሬን አፍርተዋል።
በአጋማሹ ቀዳሚ የነበረው ሙከራ አቡበከር አዳሙ በ54ኛው ደቂቃ ያደረገው ሲሆን አብይ ካሳዬ ግብ ከመሆን አድኖታል።
በድሬዳዋ ከተማ በኩል ያሬድ ታደሰ በ58ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር የተሻገረን ኳስ ለመጠቀም ያደረገው ጥሩት ለድሬዳዋ ከተማዎች አስቆጪ አጋጣሚ ነበር።
ተደጋጋሚ ጫና የበረታባቸው ቡናማዎቹ የኋላ ክፍላቸውን ቁጥር በመጨመር የግብ ክልላቸውን ለመጠበቅ ያደረጉት ውሳኔ የኋላ ኋላ ዋጋ ያስከፈላቸው ሆኗል።
በ77ኛው ደቂቃ ላይ ተከላካዩ ጀሚል ያዕቆብ በሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ ይዞ የገባውን ኳስ አክርሮ በመምታት ድሬደዋ ከተማን አቻ አድርጓል።
ከግቡ መቆጠር አስር ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ መሐመድኑር ናስር ከተመሳሳይ አቅጣጫ የተነሳውን ኳስ በእንደሻው እሸቴ መረብ ላይ አሳርፏል።
89ኛው ደቂቃ ላይ በፍቃዱ አለማየሁ የድሬዳዋ ግብ ጠባቂ አብይ ካሳዬን ደርቦ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ሳይቆጠር ቀርቷል።
በተጨማሪ ደቂቃዎች ላይ ድሬዳዋ ከተማዎች 3ኛ ግብ ማስቆጠር የሚችሉበትን ዕድል ቢያገኙም አብዲሳ ጀማል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ድሬዳዋ ከተማ ማሸነፉን ተከትሎ ነጥቡን 16 ማድረስ ችሏል።
በ12ኛው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡና ከመቻል እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ ከነገሌ አርሲ ይጫወታሉ።


