“ፋሲል ከነማንም እንደ ብ/ቡድናችን ስነ ልቦና አሸናፊ ልናደርገው ዝግጁ ነን”አስቻለው ታመነ

ፋሲል ከነማ በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎው ወሳኙን ጨዋታ ከአል ኢላል ጋር ያደርጋል ፋሲል በዚህ ውድድር ቆይታው ከዚህ ቀደም ካስመዘገበው ውጤት በተሻለና ሌሎች የአገራችን ቡድኖች የያዙትን የ16 ቡድኖች ሪከርድ ውጤትን ለመስበር ብርቱ ተሳትፎ እንደሚያደርግ የቡድኑ አዲስ ፈራሚ ተጨዋች አስቻለው ታመነ ከሀትሪክ ስፖርት ጋር ባደረገው ቆይታ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ ብ/ቡድን የተጨዋችነት ግዴታውን ከተወጣ በኋላ ለሌላ የኢንተርናሽናል ክለብ ተሳትፎ ጨዋታው የፋሲልን የዝግጅት ወቅት የተቀላቀለውን ይኸው ተጨዋች በክለባቸው የኢንተርናሽናል ጨዋታ ተሳትፎ ዙሪያ አጠር ባለ መልኩ አናግረነዋል፡፡

ሀትሪክ፡- ለዋልያዎቹ ወሳኙን የድል ጎል ማስቆጠር ችለህ አሁን ደግሞ ለሌላ የኢንተርናሽናል የክለብ ጨዋታ ተሳትፎ ወደ ቡድንህ ማምራት ችለሀል በዚህ ዙሪያ ምን የምትለው ነገር አለህ..?

አስቻለው፡- በመጀመሪያ ለብ/ቡድናችን በመጨረሻ ደቂቃ ላይ በተገኘች የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ዝምባቡዌን ልናሸንፍ በቻልንበት ጨዋታ በእኔ ውስጥ የተፈጠረው የደስታ ስሜት እጅግ ከፍ ያለ ነበርና ይህ ውጤት ቀጣይ ላለብኝ የፋሲል ከነማ ቡድን ግዴታዬ ትልቅ የሞራል ስንቅ ይሆነኛልና በዚህ ከፍተኛ የተነሳሽነት ስሜት ከፋሲል ከነማ ጋርም ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጅቴን በሚገባ ጀምሬያለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማ በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የውድድር ተሳትፎ ምን ውጤትን ለማስመዝገብ ነው እያለመ ያለው…?

አስቻለው፡- ፋሲል ጠንካራ ቡድን ነው፤ በብ/ቡድን ውስጥም የሚጫወቱ ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾችም አሉት ከዛም ባሻገር ለአዲሱ የውድድር ዘመን ቡድናችንን ሊያጠናክሩልን የሚችሉ ተጨዋቾችንም ለማስመጣት ችለናልና አሁን ከምንሰራው ልምምድ አንፃር በዚህ የውድድር ተሳትፎዋችን ከዚህ ቀደም ካገኘነው ልምድ በመነሣት ክለቡ ከዚህ በፊት ካስመዘገበው ውጤት የሚሻል ብሎም ደግሞ የአገራችን ትላልቅ የሚባሉት ክለቦች ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ያስመዘገቡትን አስራ ስድስት ክለቦች ውስጥ የገቡበትን ሪከርድ ለማሻሻል ከፍተኛ ፍላጎት አለኝ፡፡

ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማ በኢንተርናሽናል ውድድር ተሳትፎ ከወዲሁ ስለተጋጣሚው ያወቀው ነገር አለ…?

አስቻለው፡-የእኛን ተጋጣሚ በተመለከተ አሰልጣኛችን ብዙ ነገሮችን ከወዲሁ መረጃዎች እያሰባሰበ ነው የጨዋታው ቀን ሲቃረብም ለእኛ በቂ ኢንፎርሜሽን ለመስጠትም ዝግጁ ነውና አሰልጣኛችን ከሚሰጠን ታክቲክ በመነሳት በውድድሩ ተሳትፎ ምርጥ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጁ ነን፡፡

ሀትሪክ፡- የፋሲል ከነማ ስብስብን በተመለከተ ምን ትላለህ…?

አስቻለው፡- አሁን ላይ ምርጥ የሆነ ስብስብ ነው ያለን ስብስቡን ብ/ቡድንም በለው፤ ብዙዎቻችን አብረን የቆየንም ስለሆነ ይሄን ቡድን በአገር ውስጥ ተሳትፎም ሆነ በኢንተርናሽናል ውድድር ብዙ ጉዞ እንዲያደርግም እናስችለዋለን፡፡

ሀትሪክ፡- በመጨረሻ ?

አስቻለው፡- ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እና ለቤተሰቦቼ እንደዚሁም ለቡድን ጓደኞቼ መልካም አዲስ አመት እላለሁ፡፡

 

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *