“የዋልያዎቹን ስብስብ ዳግም እንደምቀላቀልና ወላይታ ድቻንም ለጥሩ ውጤት እንደማበቃው እርግጠኛ ነኝ” ፅዮን መርዕድ /ወላይታ ድቻ/

በዘንድሮ የክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ወጣቱ ግብ ጠባቂ ፂዮን መርዕድ ባህርዳር ከተማን በመልቀቅ ወላይታ ድቻን ለመቀላቀል ችሏል፤ በአርባምንጭ ምዕራፍ አካባቢ ተወልዶ ያደገው ይኸው ግብ ጠባቂ በክለብ ደረጃ ለአርባምንጭና ለባህርዳር በመጫወት ያሳለፈ ሲሆን ጥሩም ችሎታ እንዳለው ሊያስመሰክርም በቅቷል፤ ለሀገሩ ብሔራዊ ቡድንም ተመርጦ መጫወትን ችሏል፤ ከዚህ ተጨዋች ጋር ሀትሪክ ስፖርት በኳስ ህይወቱ ዙሪያና ሌሎች ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ አጠር ያለ ቆይታን አድርጋ ምላሽ ተሰጥቷታል፤ ተከታተሉት፡፡

ግብ ጠባቂ ከመሆኑ በፊት ምን ይሰራ እንደነበር

“መጀመሪያ በተወለድኩበት የአርባምንጭ ከተማ ስታድየም ውስጥ ኳስ አቀባይ ነበርኩ፤ ኳስ ማቀበልን የጀመርኩትም ልጅ እያለው ነበር፤ ያኔ ጨዋታውን አስታውሰዋለውም፤ ቅ/ጊዮርጊስ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ያደረጉት ነበር፤ እነ አዳነ ግርማን የመሳሰሉ ተጨዋቾችንም ልመለከት የቻልኩት ያን ጊዜም ነበርና በዚህ መነሻነትም ነው ወደ ኳሱ ዓለምም የመጣሁት”፡፡

በቤተሰቡ ውስጥ ስፖርተኛው እሱ ብቻ እንደሆነና ስንት ወንድምና እህት እንዳለው

“እኛ ቤተሰብ ውስጥ ሶስት ልጆች ነው ያለነው፤ ሁለቱም ታናናሾቼ ወንድሞቼ ናቸው፤ ስፖርተኛውም እኔ ብቻ ሳልሆን አንዱ በክልል ክለቦች ሻምፒዮና ላይ ተጫውቶ አሳልፏል፤ አንደኛው ደግሞ ገና የ8 ዓመት ልጅ ቢሆንም ወደ ስፖርቱ ሊያመራ ተዘጋጅቷል”፡፡

ወደ ስፖርቱ ከመምጣት ጋር በተያያዘ በቤተሰባቸው አካባቢ ስላለው አመለካከት

“በዚህ በኩል እንኳን ችግር ሳይኖርብን ነው ያደግነው፤ አባታችን ኳስን በጣም ይወድ ስለነበር ህፃን እያለው ጭምር ነው ሜዳ ይዞኝ በመምጣት ጨዋታን ያሳይ የነበረው፤ እሱ የማንቸስተር ዩናይትድም ደጋፊ ነበር፤ እኛ ልጆቹ ደግሞ የቼልሲ ነን፤ ይህን ተንተርሶም ከስምንት ዓመት በፊት ተካሂዶ በነበረው የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ላይ የቼልሲው ግብ ጠባቂ ፒተር ቼክ የፍፁም ቅጣት ምት መልሶ ቡድኑን ለድል ባበቃበት ጊዜ የእኛም ቤት የመጨረሻው ልጅ ተወልዶ ነበርና ስሙን ቼክ ብሎ ሰይሞለት አሁን በዛ እየተጠራ ይገኛል”፡፡

ወደ ግብ ጠባቂነቱ ሲመጣ አርአያ ስላደረገው ተጨዋች

“በቦታዬ የማደንቀውና ለእኔ አርአያዬ የሆነኝ ግብ ጠባቂ ኢትዮጵያዊ ተጨዋች ስለሆነ ጭምር ሲሳይ ባንጫን ቢሆንም የቅ/ጊዮርጊሱን የቀድሞ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንኮራንም ኳስ አቀባይ በነበርኩበት ዘመን ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተመልክቼው በችሎታው ወድጄዋለውና እሱንም በማከል ነው ሁለቱንም ልወዳቸው የቻልኩት”፡፡

ስለ መጀመሪያ ክለቡና በቡድኑ ውስጥ ስለነበረው ቆይታው

“አርባምንጭ ከተማ የመጀመሪያ ክለቤ ነው፤ ይሄን ቡድን የተቀላቀልኩትም ከፕሮጀክት ተጨዋችነት በመምጣት ነው፤ ወደ ቡድኑ ከገባው በኋላም እኔና ምንተሰኖት አሎም ነበርን ከስር ተተኪው ቡድን ለማደግም የቻልነው፤ በዚህ ቡድን በነበረኝ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታ ያኔ ክለባችን እነ አንተነህ መሳን፣ ጃክሰን ፊጣንና ሌሎችን ግብ ጠባቂዎችን ይዞ ስለነበር ልምድን ስቀስም ነበር የቆየሁት፤ ለሶስት ዓመት ያህልም ከቡድኑ ጋር ነበርኩ፤ በዚሁ ቡድን ቆይታዬ በአባይ ግድብ ዋንጫ ላይ ከአዳማ ከተማ ጋር በነበረው ፍልሚያ የመጀመሪያ ጨዋታዬን ሳደርግ አሰልጣኝ እዮብ ማለ /አሞካቺ/ ወደ ቡድኑ ከመጣ በኋላ ደግሞ ደፍሮ የመጫወት እድሉን ስለሰጠኝ ትላልቅ በሚባሉት ግጥሚያዎች ላይ በተለይም ደግሞ ቅ/ጊዮርጊስንና ኢትዮጵያ ቡናን ባሸነፍንባቸው ጨዋታዎች ላይ ልሰለፍም በቅቻለውና ይሄ ሁሌም የሚያስደስተኝ ነው”፡፡

ለኢትዮጵያ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ስለተመረጠበት አጋጣሚ

“ይህን እድል ያገኘሁት በአሰልጣኝ አጥናፉ አለሙ ጊዜ ነው፤ ስመረጥ በጣምም ነው ደስ ያለኝ፤ ከ20 ዓመት በታች ቡድንም ተመርጬ ነበር፤ ከሩዋንዳ ጋር በተደረገው ጨዋታ ላይም ልጫወት ችያለው”፡፡

ከአርባምንጭ ወደ ባህርዳር ከተማ ስላደረገው ጉዞና በቡድኑ ስለነበረው ቆይታ

“አርባምንጭ ከተማ ከውጤት ማጣት ጋር በተያያዘ ወደታችኛው ሊግ በወረደበት ሰዓትና ቀጥሎም ደግሞ የእኔ የውል ጊዜ በመጠናቀቁ ምክንያት ልጫወትበት ያመራሁበት ቡድን በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ለሚመራው ባህርዳር ከተማ ነበር፤ ለሁለት ዓመትም ፈርሜ ነበር፤ የመጀመሪያው ዓመት ላይ ሀሪሰንም ስለነበር ነገሮች ከብደውኝ ነበር፤ ዘንድሮ ላይ ግን ግማሽ ግማሽ የሚሆነውን ጨዋታ እኔና እሱ የተጫወትንበት አጋጣሚው ስለነበር ጥሩ ጊዜን ነው ለማሳለፍ የቻልኩት፤ ያም ቢሆን ግን በዚህ ቡድን የነበረኝ ቆይታ አንድ ዓመት ቀሪ እያለብኝ ከእነሱ ጋር በስምምነት በመለያየት ወላይታ ድቻን ልቀላቀል ቻልኩ”፡፡
የባህርዳር ከተማ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው
“ከውጤት አንፃር ካስመዘገብነው በተሻለ ጥሩ ውጤት ሊኖረን ይገባን ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮቻችን ብዙ እንዳንጓዝ አድርጎናል”፡፡

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በአዲስ ዓመት ከወላይታ ዲቻ ጋር ስለሚኖረው ቆይታ

“ይሄ ቡድን ለእኛ የትውልድ ስፍራ በጣም ቅርብና የአካባቢ ያህልም ቡድናችን ስለሆነ ጥሩ ጊዜን የማሳልፍ ይመስለኛል፤ በቆይታዬም ክለቡ አስቀድሞ የነበረውን ጥንካሬም እንዲመልስ ከጓደኞቼ ጋር ከፍተኛ ጥረትን አደርጋለው”፡፡

ስለ ወደፊት ግቡና እቅዱ

“ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከታዳጊው አንስቶ እስከ ዋናው ብሔራዊ ቡድን ለመመረጥ ችያለው፤ በተተኪዎቹ ቡድን ቆይታዬም የመጫወትን እድል አግኝቻለው፤ ከዚህ በኋላ ደግሞ የእኔ ዋናው እቅድ ከዚህ በፊት ለዋናው ብሔራዊ ቡድን በአቋም መለኪያ ጨዋታ የተሰለፍኩበትን የመጫወት አድል በማሳደግ በመደበኛው ውድድር ላይ ለመጫወት መቻልና የዋልያዎቹን ስብስብም በፍጥነት መቀላቀል ነውና ያን እልሜን ማሳካት እፈልጋለው”፡፡

እናጠቃል…

“በእግር ኳስ በመጣሁበት ሙያዬ ገና ብዙ ነገር የሚጠበቅብኝ ተጨዋች ነኝ፤ ከዚህ በላይ እንደምጓዝና ጥሩ ደረጃ ላይም እንደምደርስ አውቃለው፤ ለዛ በርትቼም እሰራለው፤ ይህን ካልኩ ለእስካሁኑ ጉዞዬ ፈጣሪዬን፣ ቤተሰቦቼን፣ ከህፃንነቴ እድሜ አንስቶ የረዱኝንና አሰልጥነውኝ ያለፉትን እነ ገረመውን በብሔራዊ ቡድን ደረጃም በብዙ ነገሮች በማሰልጠን እያገዙኝ የቆዩትን አሰልጣኝ ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ፣ ውብሸት ደሳለኝን፣ እንደዚሁም አዳሙ ኑመሮን ለማመስገን እወዳለው”፡፡

hatricksport team

Hatricksport team

Facebook

hatricksport team

Hatricksport team

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *