“ከፋሲል ከነማ ጋር ያሳካሁት የፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫ መታሰቢነቱ ለእናቴ ይሁንልኝ” አሰልጣኝ ስዩም ከበደ /ፋሲል ከነማ/

አዲሶቹ ሻምፒዮኖች

ዋንጫና 1 ሚሊዮን ብር ተሸላሚ ናቸው

አጠቃላይ ሽልማቱ ሊጉ ሲያልቅ እስከ 3 ሚሊዮን ብር ሊደርስ ይችላል

ለ3 አመታት ጠብቀውታል… ጉጉት ትግል የደጋፊዎቻቸው መገለጫ ሆኗል፤ በ 2011 ለዋንጫ ከጫፍ ደርሰው እግር ኳሳዊ ባልሆነ ምክንያት ዋንጫውን እንዳጡ በርካቶች ይናገራሉ፡፡ በ2011 መቐለ 7߀ እንደርታ ዋንጫውን ሲወስድ ጥያቄ ቢያነሱም ተገቢ ምላሽ ያጡ በርካቶች ናቸው በ2012 17 ጨዋታ ተካሄዶ ፋሲል ከነማ የ2011 በደሉን ሊክስ እየመራ ከጫፍ ደርሷል፡፡ እንደ 2011 በቅሬታ የሚናገረው ሳይሆን አለም አቀፍ ችግር በሆነው ኮቪድ 19 ወረርሽኝ መጋቢት 4/2012 ጃፓናዊ ተጓዥ ላይ ቫይረሱ ተገኝቶ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ተጠቂ ሲገኝ መንግስት ትዕዛዝ ሰጠና ከ18ኛው ሳምንት መርሃ ግብር በኋላ ሊጉ ተቋርጦ ፋሲል ከነማ የጓጓለትን የድል ገመድ ሳይበጥስ ለ2ኛ ጊዜ ሃሣቡ ሳይሳካ ቀረ… 2013 ግን የሚታለፍ አልሆነም፡፡

2ኛ ደረጃ ላይ የነበረው ኢትዮጵያ ቡና ከወላይታ ድቻ ጋር ߀ለ߀ መለያየቱን ተከትሎ ቀሪ 4 ጨዋታዎችን ሙሉ ቢያሸንፍ መድረስ እንደማይቻል በመረጋገጡ ፋሲል ከነማ የስዩም ከበደ ተዋጊያዎች… የአፄዎቹ ኩራቶች… ካደረጓቸው 2߀ ጨዋታዎች 15ቱን አሸንፈው በ4ቱ አቻ ተለያይተው 1 ጊዜ ብቻ ተሸንፈው ለዋንጫ ቁርጠኛ አቋም የያዘ ቡድንን አቋም በማሳየት በ49 ነጥብና 22 ግብ ያለምንም ሰበብ በሚታይ ብቃት የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ማንሣቱን አረጋገጠ፡፡ ግንቦት 8/2߀13 ከድሬደዋ ከተማ ጋር ሲጫወቱ የድል አድራጊነታቸውን ዋንጫ ሊረከቡ ቀጠሮ የተያዘላቸው ፋሲል ከነማዎች ኢትዮጵያን በትልቁ የውድድር መድረክ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ መወከላቸው እርግጥ ሆነ፡፡ የ1 ሚሊዮን ብር ተሸላሚ በመሆን /አመቱ ሲጠናቀቅ አንደኛ ሆነው በመጨረሳቸውና በብሮድካስት ክፍያ ትልቁን ገንዘብ እንደሚያገኙ አረጋግጠዋል/ የመጀመሪያው የዲ.ኤስ.ቲቪ ሙሉ ስርጭት በተካሄደበት ጊዜ ማሸነፋቸው፣ ሊጉን ክለቦች ራሳቸው እየመሩት የተገኘ ድል መሆኑ የፋሲል ከነማዎችን ድል ጣፋጭ አድርጎታል፡፡ ደጋፊዎቻቸው ባሉበት ሁሉ ወሬውና ደስታው የአፄዎቹ አባላት ገድል ብቻ ሆኗል፡፡

በተመዘገበው የዋንጫ ገድሉ ዙሪያ ከሀትሪክ ጋር ቆይታ ያደረገው አሰልጣኝ ስዩም ከበደ የዋንጫ ገድሉን ለእናቴ ለእማሆይ ……… ይሁንልኝ ብሏል፡፡ “በጣም ተደስቻለሁ የልፋታችንን ውጤት በማግኘተችን ኩራት ተሰምቶኛል፤ እናቴ ካረፈች ግንቦት ወር ሲመጣ 2ኛ አመቷን ትይዛለች ከልጅነት እስከ እውቀት በሙሉ ህይወቷ ስትደግፈኝ ኖራለች ይህን ድል ብታይ ደስታዬ እጥፍ ይሆን ነበር ያም ሆኖ ግን የፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫ መታሰቢነቱ ለእናቴ እንዲሆንልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ባለቤቴ ልጄን መላው ቤተሰቤን ከልብ አመሰግናለሁ” ያለው ስዩም ከበደ “ክለቡና ደጋፊዎቹ የሊጉን ዋንጫ ለማንሣት ጉጉታቸው በጣም የላቀ ነበር አብረውኝ የሚሰሩት ረዳቶቼና ተጨዋቾቼ ደግሞ ይህን ጉጉት በማሳካታቸው ደስተኛ ነኝ በዲ.ኤስ.ቲቪ መተላለፉ በጎ ትርጉም አምጥቶ ምርጥ በሆነ አቋም ሁሉንም ባሳመነ መልኩ የተገኘ ድል በመሆኑ ኮርቻለሁ ሙሉ ደጋፊዎቻችንንም እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ… በቀጣይ ባለው የአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግ ላይም የተሻለ ጉዞ ለማድረግ በጥሩ ሁኔታ እንዘጋጃለን የአምናው የኮንፌዴሬሽን ካፕ ተሳትፏችን ጥሩ ልምድ ሰጥቶናል ብለን እናስባለን” ብሏል፡፡ አሰልጣኙ በተገኘው ድል ዙሪያ ባስተላለፈው የምስጋና መልዕክት “አዲስ አበባ ላይ በነበረው ውድድር ላይ ባሳየነው ወጣ ገባ አቋም ከፍተኛ ተቃውሞ ነበር ያ ተቃውሞ ሙሉ የደጋፊው ነው ብዬ ባላምንም በበጎ ጎኑ ተቀብዬዋለው ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ከጎኔ በመሆን አሁን ድረሰ እየደገፉኝ ላሉ የቦርድ አመራር አባላት፣ ቴክኒካል ስታፍና ተጨዋቾቼ የድሉ የአምበሳ ድርሻ የእርነሱ መሆኑን እመሰክራለሁ መላው ፋሲላዊያንን እንኳን ደስ አላችሁ ከህልማችሁ ጋር በመገናኘታችሁ ኮርቻለሁ” በማለት መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

በበርካቶች የሚወደሰውና የደጋፊ እንዲሁም የሙሉ ተጨዋቾቹ ተቀባይነት እንዳገኘ የሚነገርለት የክለቡ የቡድን መሪ ሀብታሙ ዘዋለ በበኩሉ “በተገኘው ድል የተሰማኝን ደስታ መግለፅ ይቸግረኛል፡፡ በውስጤ ትልቅ ደስታ ተፈጥሯል፡፡ ይህን ቀን ለማየት ረጅም ጊዜ ደክመናል ለፍተናል ይህ እንዲሳካ የበርካቶች ባለ ድርሻ አባላት የጋራ ትብብር ውጤት አስተዋፅኦ አድርጓል የክለቡ የቦርድ አመራሮች፣ የደጋፊ ማህበራት፣ የበላይ ጠባቂዎችና የከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ ክቡር ከንቲባችን አቶ ሞላ ምክትል ከንቲባ አቶ አደባባይ፣ ዳሽን ቢራ በፋይናንሱ ረገድ ለነበረው የማይረሳ ድጋፍ፣ የቢሮ ሰራተኞቻችን፣ የክለባችን አሰልጣኞች ስዩም ከበደና ረዳቶቻቸው የቡድኑ አባላትና ተጨዋቾች ስራ አስኪያጁ አቶ አብዮት ብርሃኑን በአጠቃላይ የእናንተ የጋራ ድምር ውጤት በመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ” ሲል ተናግሯል፡፡
የቡድን መሪው ከዚሁ ጎን አፅንኦት ሰጥቶ ምስጋናውን የቸረው ለክለቡ ደጋፊዎችና ለባለቤቱ ለወይዘሮ እስከዳር ምትኩ ነው፡፡ ቡድን መሪው ለሀትሪክ ሲናገር “ብዙ ነገሬን ሸፍና እኔ ወደ የተለያዩ ቦታዎች ከቡድኑ ጋር ስጓዝ የቤቴን ጣጣ በብቃት ተወጥታ የውጪው ስራዬ ስኬታማ እንዲሆን ያደረገችው ባለቤቴን እስከዳር ምትኩን ማመስገን እፈልጋለሁ ለእኔ የማይተካ ትልቅ ድጋፍ አድርጋልኛለች” ሲል አሞካሽቷታል፡፡ ቡድን መሪው ሀብታሙ ዘዋለ ደጋፊውንም አልረሳም “ለረጅም ጊዜ ውጤት ሲጠፋም ሆነ ሲኖር ከጎናችን ሆነው እየተከተሉ በበረሃ ሳይቀር ተጉዘው ከጎናችን ያልጠፉት ብርድና ዝናብ ሳይበግራቸው ማገር ለሆኑት፣ ጊዜና ገንዘባቸውን ለክለቡ ላፈሰሱ መላው ደጋፊዎቻችን እንኳን ደስ አላችሁ ድሉ የእናንተ ነው በግፍ ላጣነው ዋንጫ የዘንድሮው ዋንጫ ካሳችን ጭምር ነው” በማለት የተሰማውን ደስታ ገልጿል፡፡

ፋሲል ከነማዎች ከሐዋሳ ከተማ፣ ከጅማ አባጅፋርና ከመቐለ 7ዐ እንደርታ በመቀጠል አራተኛው የክልል ክለብ ሲሆን በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር መሠረት ዛሬ ቅዳሜ 4 ሰዓት ከወልቂጤ ከተማ ጋር ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport