“የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳት ሕልሜ ነበር፤ ይህንንም ከፋሲል ከነማ ጋር በማሳካቴ የማላውቀው አይነት የደስታ ስሜት ተሰምቶኛል” ሱራፌል ዳኛቸው /ፋሲል ከነማ/

ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የአራት ሳምንታት የጨዋታ ጊዜያቶች ቢቀሩትም ኢትዮጵያ ቡና ከወላይታ ድቻ ጋር ያከናወነውን ግጥሚያ በአቻ ውጤት ማጠናቀቁን ተከትሎ ፋሲል ከነማ ሊጉ ሳይጠናቀቅ ከወዲሁ የውድድሩ ሻምፒዮና መሆኑን አረጋግጧል።

በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ የሚመራው ይኸው ቡድን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫውን ማንሳቱን ተከትሎም በቡድኑ ተጨዋቾች፣ አሰልጣኞች፣ ደጋፊዎችና አጠቃላይ አባላቶች አካባቢም ከፍተኛ የደስታ ስሜትን ሊፈጥር ችሏል።
ፋሲል ከነማ ይህን የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ማግኘቱን ተከትሎም ለቡድኑ ጥሩ እንቅስቃሴን ከሚያሳዩት ተጨዋቾች መካከል አንዱ የሆነውን ሱራፌል ዳኛቸውን የሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ሐሙስ ምሽት ላይ ያናገረው ሲሆን ተጨዋቹም በከፍተኛ የደስታ ስሜት ላይ ሆኖ ለቀረቡለት ጥያቄዎች ሁሉ በቂ ምላሽን ሰጥቷል፤ ተከታተሉት።

ሀትሪክ፦ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የአራት ሳምንታት ጨዋታዎች እየቀሩት ሻምፒዮና መሆናችሁን አረጋግጣችኋል፤ በቅድሚያ እንኳን ደስ አለህ?

ሱራፌል፦ አመሰግናለሁ። እናንተንም ባመጣነው ውጤት ለእኛ ከፍተኛ ክብር ሰጥታችሁ የመልካም ምኞታችሁን ስለ ገለፃችሁልን በቡድኔ ተጨዋቾች እና አጠቃላይ የቡድኑ ማህበረሰብ ስም ምስጋናዬን ላቅርብላችሁ እፈልጋለሁ።

ሀትሪክ፦ ፋሲል ከነማ ሻምፒዮና መሆኑን ተከትሎ የመጀመሪያውን የእንኳን ደስ ያለህ የስልክ ጥሪ ከማን ተቀበልክ? ምንስ ተባልክ?

ሱራፌል፦ ከባለቤቴ ሜሮን ሰለሞን ነበር ተደውሎልኝ እንኳን ደስ አለህ? እንኳን ደስ ያላችሁ? የሚል መልዕክትን የተቀበልኩት። ከዛም የልፋታችሁን እና የሚገባችሁንም ድል ነው የተጎናፀፋችሁት ተብዬም የደስታ ስሜቱ በድጋሚ ተበሰረልኝ።

ሀትሪክ፦ ፋሲል ከነማ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮና መሆኑን ረቡዕ ዕለት እንዳረጋገጠ የተፈጠረብህ የደስታ ስሜት ምን ይመስል ነበር? በወቅቱስ የት ነበርክ?

ሱራፌል፦ የፋሲል ከነማ ሻምፒዮና መሆኑ የተረጋገጠው ገና የአራት ሳምንታት ጨዋታዎች በቀሩበት እና ይሄም በሊጉ ሪከርድ በሆነበት እና ተከታዩምኢትዮጵያ ቡና ከወላይታ ድቻ ጋር የነበረውን ጨዋታ በአቻ ውጤት መጨረሱን ተከትሎ በ15 ነጥብ ስለበለጥነው ባረፍንበት ሆቴል ዶርም ውስጥ ነው የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ እየተከታተልን በነበርንበት ጊዜ ግጥሚያው ሲጠናቀቅ ደስታዬን በከፍተኛ ስሜት ላይ ሆኜ ከዶርም ጓደኛዬ ሽመክት ጉግሳ ጋር በቅድሚያ ልገልፅ የቻልኩት። በእግር ኳስ ህይወቴ በመጀመሪያ አልሜ የተነሳሁት የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ነበር። ለፋሲል ከነማም በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጊዜ ለክለቡ ፊርማዬን ሳኖርም ይህን ዋንጫ ከዚህ ቡድን ጋር የግድ ማንሳት አለብኝ ብዬም ስላቀድኩኝ እና ስለተነጋገርንም ይኸው ጊዜ አሁን ላይ ደርሶ በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ቡድን ውስጥ እልሜን ላሳካው ችያለሁና በዚህም ድል የማላውቀው አይነት የደስታ ስሜት ነው ሊሰማኝ የቻለው።

ሀትሪክ፦ ፋሲል ከነማ ይህን የሊግ ዋንጫ ለማንሳት ዘግይቷል?

ሱራፌል፦ ብዙም ባይሆን አዎን ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታቶች ይህን ድል ልንጎናፀፍ የምንችልበት ዕድሉ ነበረን ያም ሆኖ ግን አስቸጋሪና ፈታኝ ሁኔታዎች ስለገጠሙን የልፋታችንን ውጤት ማግኘት እየቻልን አላገኘንም። ፈጣሪ ፈቅዶ ግን የእናንተ ጊዜ አሁን ነው በማለት ያለምነውን እንድናሳካ ስላደረገን እጥፍ ድርብ የደስታ ስሜት ነው በውስጣችን እየተፈጠረብን ያለው።

ሀትሪክ፦ ከኢትዮጵያ ቡናና ከወላይታ ድቻ ግጥሚያ መጠናቀቅ በኋላ ልክ ስልክ እንደደወልኩልህ በሆቴላችሁ ውስጥ እየጨፈራችሁ ነበር፤ እስኪ ስለነበረው አጠቃላይ ስሜት አንድ ነገር ብትለን?

ሱራፌል፦ የኢትዮጵያ ቡናን እና የወላይታ ድቻን ጨዋታ ሁሉም የየቡድናችን ተጨዋቾች ባረፍንበት ሆቴል ዶርም ውስጥ ነበር ስንከታተል የነበረውና ግጥሚያው እንደተጠናቀቀና ሻምፒዮና መሆናችን እንደታወቀ ሁሉም ነው የዋንጫ ጥማት ስለነበረበት ከያለበት በመውጣት በሆቴሉ ውስጥና በመንገዱ ላይም ሆኖ ደስታውን ሊገልፅ የቻለው። በኳሱ የምር የእኛ ቡድን ከባድና አስቸጋሪ ጊዜን ባለፉት ዓመታት አሳልፎም ነበርና ይህን ዋንጫ አሁን ስናገኝ የተቃራኒ ቡድኖች ጭምር ናቸው ድሉ እንደሚገባን በመግለፅ እና በከተማው ላይም ሆቴላችን አካባቢ ሆነን ስንጨፍር የየመኪኖቻቸውን ክላክስ በመንፋት ጭምር የደስታችን ተካፋይ የሆኑት።

ሀትሪክ፦ ከቡድኑ ተጨዋቾች ውስጥ ከአንተ ያልተለመደ አይነት የደስታ አገላለፅ ሲታይ ነበር ተብሏል?

ሱራፌል፦ አዎን የእውነት ነው። ልክ ባለድል መሆናችንን እንዳረጋገጥን መጀመሪያ ላይ ባለሁበት ዶርም ውስጥም በሆቴሉ ውስጥም በቁምጣ ወጥቼ ነበር ደስታዬን ከሽመክት ጉግሳ ጋር በመጮህ ጭምር ስገልፅ የነበርኩት ከዛም ሁላችንም የቡድኑ አባላቶች ነጭ በቀይ የሆነውን የጃኖ ማሊያችንን አድርገን በሆቴላችን በር አካባቢ ስንጨፍር እኔ ላይ ይታይ የነበረው ጭፈራና የደስታ አገላለፅ ስሜት ልክ እንደ ደቡቦቹ አይነት የተለየ የሚባል እና ሁሉንም ያስገረመም ነበር። በተለይ በደቡቦቹ ዲሽታ ጊና በሚለው ባህላዊ ዘፈን ወቅት ላይም ወደላይ እየዘለልኩ ስጨፍርም ብዙዎቹ እኔን ከዚህ በፊት ዝም በሚለው ባህሪ ስለሚያውቁኝ እና ይህን ጭፈራ ከእኔ ያልጠበቁትም ስለነበር በተለይ ደግሞ አሰልጣኛችን ስዩም ከበደ ወደ እኔ መጥቶና አጨፋፈሬንም በአግራሞት ተመልክቶት ይሄን ዳንስ እኔም ገብቼ እለማመዳለውም ያለኝንም ፈፅሞ የማልረሳው ነው።

ሀትሪክ፦ ከፋሲል ከነማ ጋር የፕሪምየር ሊግን፣ የጥሎ ማለፍን፣ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን አነሳህ፤ ከዛ ውጪም ከዚህ ቡድን ጋር ሆነህም የኮከብ ተጨዋችነት ክብርን ተጎናፀፍክ። እነዚህን ስኬቶችና ስሜቶቹን እንዴት ተመለከትካቸው?

ሱራፌል፦ በጣም ደስ የሚሉ ናቸው። በኳስ ህይወትህ እንዲህ ያሉ ድሎችን ማግኘት መቻል መታደልም ነውና የአንድ ዓመት ከ5 ወር ዕድሜ ላላት ለልጄ አሜን ሱራፌልም ወደፊት የምነግራት ታሪክ ስላለኝም እየተሰማኝ ያለው ደስታ በጣም ከፍተኛ ነው።

ሀትሪክ፦ በፋሲል ከነማ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታህ ከእነዚህ ስኬቶችህ ውጪ ለብሄራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረጥክበት እና ተመርጠህም ዋልያዎቹን ለአፍሪካ ዋንጫ ከጓደኞችህ ጋር እንዲያልፉ ያደረግክበትም ሁኔታ አለ በዚህ ዙሪያ የምትለው ነገር ካለ?

ሱራፌል፦ የእውነት ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ለብሔራዊ ቡድን የተመረጥኩት በዚህ ቡድን ውስጥ ሆኜ ነው። ተመርጬም ከኮትዲቯር ጋር በተደረገው ጨዋታ ላይም ጎል ላስቆጥር በቅቻለሁ። ልጄ በተወለደችበት ዕለትም ነው ጎሏን ያስቆጠርኩትም። ከዛ ውጪም ዋልያዎቹን ለአፍሪካ ዋንጫ እንዲያልፉ ከእኔ የሚጠበቀውን አስተዋፅኦም አበርክቻለሁ። ከዚህ ጋር ተያይዞም በዚህ ክለብ ውስጥ ባለኝ ቆይታም ብዙ መልካም የሆኑ ነገሮችንም ስለተመለከትኩኝ ለልጄ ስም እስከማውጣት ደረጃ ላይም ልደርስ ችያለሁ”።

ሀትሪክ፦ ልጅህን ማን አልካት ?

ሱራፌል፦ ስሟ አሜን ይሁን እንጂ እኔ ያወጣሁላት እና የምጠራት ዕድል እያልኳት ነው። ምክንያቱም ብዙ ነገሮችን እያገኘው ያለሁት እሷ ተረግዛና ወደዚህ ምድርም ከመጣች በኋላ በመሆኑ ለዛም ነው ስሙን ያወጣሁላት።

ሀትሪክ፦ የዋንጫ ባለቤትነት ክብሩን ከወዲሁ አረጋግጣችኋል፤ ከዚህ በኋላ ያሉትን አራቱን ጨዋታዎቻችሁን በምን መልኩ የምታከናውኑት ይሆናል?

ሱራፌል፦ ፋሲል ከነማ በዘንድሮው ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው የመጣበት መንገድ በጣም የሚያስገርም ነው። በአብዛኛው ጨዋታዎቹ የማይዋዥቅ አቋሙንም ከውጤት ጋር አሳይቷል። የልፋት ፍሬውንም ዋንጫ በማግኘት ጭምር ሊያረጋግጥ ችሏል። ከዚህ በኋላ ያሉትን ጨዋታዎች በተመለከተ ደግሞ ይህ ቡድናችን በሊጉ ትልቅ የሚባልን ውጤት ማስመዝገብ እና በራሱ ላብም ተጫውቶ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱንም ማረጋገጥ ስለሚፈልግ እንደበፊቱ ሆነን በመጫወት ነው ሁሉንም ግጥሚያዎች ለማሸነፍ ዝግጁ የሆንነው።
ከአራቱ ጨዋታዎቻችን ውስጥ በወራጅ ቀጠና ላይ ካሉት ጋር የምናደርገውም ጨዋታ አለን እኛ ጋር መላቀቅ የሚባል ነገር የለም። ለቡድናችንም ሆነ ለአገራችን እግር ኳስ ስንል እውነተኛና ታማኝ ቡድን ተብለን እንድንጠራም ስለምንፈልግ በሁሉም ነገሮች ላይም ነው ልንነጋር የቻልነው። በወራጅ ቀጠና ላይ ያሉት ሌሎች ቡድኖችሞ አሁን ላይ ከኛ ጋር ሲጫወቱ ማሰብ ያለባቸው በላባቸው ለፍተው እና ጥረው ተጫውተው ከሊጉ ሲተርፉም ነው ደስ የሚለውና ይህን እንዲያደርጉም ልመክራቸው እወዳለሁ።

ሀትሪክ፦ የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ከዋና ስምህ ይልቅ “ነብሮ” በሚል መጠሪያ ሲጠሩ እንሰማለን። ስያሜው እንዴት ወጣልህ? ምንስ ማለት ነው?

ሱራፌል፦ የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች በሜዳ ላይ ከምታሳየው እንቅስቃሴ በመነሳት ለተጨዋቾች ስም ማውጣት ልምዳቸው ነውና ለእኔም ለቡድኑ ከፈረምኩ በኋላ ነው ኳስ በምነጥቅበት ሰዓት አልሸነፍ ባይነትና ደመኛ ተጨዋች መሆኔን ተመልክተው በአንድ ጨዋታ ላይ እያሟሟቅንና ስትሬቺንግም በምንሰራበት ወቅት ተንበርክኬ የተነሳሁት ምስል ልክ እንደ ነብር ቆጣ ያለም ስለነበር ከዛ መነሻነት ጭምር ነው ስሙን ያወጡልኝ። ፋሲል ውስጥ አሁን እኔን ሱራፌል ብሎ የሚጠራኝ ማንም የለም። ነብሮ ብለውም ነው ሁሉም የሚጠሩኝ። ስሙን ያወጡልኝም ደጋፊዎቻችን ናቸው።

ሀትሪክ፦ ወደ ማጠቃለያው እናምራ?

ሱራፌል፦ ፋሲል ከነማ ይህን የሊግ ዋንጫ ለማግኘት ብዙ ለፍቷል። የላቡንም ዋጋ ነው ያገኘው። ይሄ ድል እንዲመጣም ብዙዎቹ ከፍተኛ መስዋትነትንም ከፍለውበታል። መጀመሪያ ጠንካራዎቹ ደጋፊዎቻችን ፀሀይና ብርድ ሳይሉ ለዓመታት እኛን የደገፉበት ሁኔታ ብርታት ሆኖናል። እነዚህ ደጋፊዎቻችን እኛን ለማበረታታት ብለው በመኪና አደጋ ህይወታቸውን እስከመሰዋት የደረሱ አሉ። ሲደግፉን ብዙ የተጎሳቆሉ ደጋፊዎችም አሉና ለእነሱ ስንል ጭምር ይህን የሊግ ዋንጫ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ቡድኑ ስላነሳ በጣም ደስ ብሎኛል። ይሄን ላሳኩትም የቡድናችን ተጨዋቾች አሰልጣኞች እና አጠቃላይ የቡድኑ አባላትና አመራሮችም እንኳን ደስ አላችሁ ለማለትም እፈልጋለሁ።

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website