“ያለ ኢት.ቡና ደጋፊ ጨዋታን ማድረግ ለእኔ ከወዲሁ ከባድ ሆኖብኛል” አቡበከር ናስር

በይስሐቅ በላይ


መግቢያ


የነገ የእግር ኳሱ አልጋ ወራሽና የአጥቂው ክፍል አደራ በማን ትከሻ ላይ ይወድቃል? በሚል መጠይቅ ብትበትኑ ሁሉም “ከአቡበከር ናስር ውጭ ማን ይሆናል?” ብለው ሊመልሱላችሁ ይችላሉ፤ በእርግጥም የነገው የጎል ማሽን እንደሚሆን የተተነበየለት የኢትዮጵያው ቡናው 10 ቁጥር ለባሽ አቡበከር ናስር ከወዲሁ በክለብና በብሔራዊ ቡድን የእነ ሙሉጌታ ከበደ፣ ሙሉጌታ ወልደየስ፣ አሰግድ ተስፋዬና የነሳላሀዲን ሰይድ ግብ የማስቆጠር አደራን በለጋ እድሜው ተሸክሟል፤ አቡበከር ናስር በአዲሱ የውድድር ዘመን አዲስ ነገር ይዞ ብቅ የማለት ትልቅ ህልምም በውስጡ ሰንቋል፤ በርካታ ግቦች ለኢትዮጵያ ቡና በማስቆጠር የፕሪሚየር ሊጉን የኮከብ ግብ አግቢነት ክብርን ከተጎናፀፉትና ታሪክ ከሰሩት ተጨዋቾች ተርታ ለመሰለፍም ቆርጧል፤ ግን ደግሞ ይሄ የሚሆነው “መጀመሪያ ክለቤን ለስኬት ካበቃሁ በኋላ ነው” በማለት የሚናገረው አቡበከር “ከግል ክብሬ ይልቅ የክለቤን ክብርና ስኬት ማስቀደምን እመርጣለሁ” ሲልም ይናገራል፤ አዲሱን የውድድር ዘመን ሲያስብ ተስፋና ስጋት በውስጡ የሚመላለሰው አቡበከር በተለይ ያለ ኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች የሚያደርገው ጨዋታ ነገሮችን ሁሉ ከወዲሁ ፈታኝ አድርገውበታል፤ “አስበህዋል ያለ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ፕሪሚየር ሊጉን ማድረግ ምን መልክ እንደሚኖረው?” በማለት የሚጠይቀው አቡበከር “ከውድድሮች በላይ ከወዲሁ በጣም እያስፈራኝና እየከበደኝ ያለው ያለ ደጋፊዎቻችን የምናደርገው ጨዋታ ነው” በማለት የደጋፊዎች ነገር ትልቅ ስጋት እንደሆነበት ሳይሸሽግ ተናግሯል፡፡ እንዴት ለአራት አመታት የሚቆይ ኮንትራት ልትፈርም ቻልክ? የሚል ጥያቄ በድንገት ከሀትሪክ ኤክስኪዩቲቭ ኤዴተር ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ የቀረበለት አቡበከር ናስር “ኢትዮጵያ ቡና የረዥም ጊዜ ኮንትራት እንድትፈርም ጥያቄ ሲያቀርብልህ ሁለቴ ማሰብም ሰው ማማከርም አያስፈልግህም፤ ቡና ለአስር አመታት ፈርም ቢለኝ እንኳን አይኔን አላሽም” ሲል ፍርጥም ያለ ምላሽም ሰጥቶታል፤ አቡበከር ናስር ከጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ጋር በነበረው ከ40 ደቂቃዎች የበለጠ ቆይታቸው ስለ ብ/ቡድን፣ ግርምትን ስለፈጠረበት ጌታነህ ከበደ፣ ብዙዎች ስላሳነሱት የኒጀሩ የ3ለ0 ድላቸው፣ ስለ አፍሪካ ዋንጫ ምኞቱ፣ ስለ ኢትዮጵያ ቡና ዝግጅት፣ ስለ አዲሱ የውድድር ዘመን ህልሞቹ አንዳችም ሳይሰስት በውስጡ ያሉትን በሙሉ አጫውቶታል፤ አብሮነታችሁ አይለየን፡፡


ሀትሪክ፡-“ቤተ ሰሪ ደም የለውም” የሚለው አባባል ደረሰብህ ልበል…?

አቡኪ፡- …አልገባኝም?…(እንደመገረም እያለ)…

ሀትሪክ፡- …አቡኪ ቤት እየገነባ ነው ብለውኝ…በዚህ ጊዜ ወጪውን እንዴት ቻለው ብዬ ነው አባባሉን ያመጣሁት…?

አቡኪ፡- …ኡ…(በጣም ሳቅ)… እኔ ደግሞ ምን ለማለት ፈልጎ ነው ብዬ ግራ ተጋብቼ ነበር…ወይ ቤት መገንባት…አንተ ታሾፋለህ…ከየት መጥቶ ነው ቤት የምትገነባው…?…(አሁንም ሳቅ)…ለአንገት ማስገቢያ ከሆነች ብዬ ትንሽዬ አክሲዮን የሆነች ነገር ጀምሬ ነበር…እሱም ብሩ አሞላልኝም…ከዚህ ውጪ የገነባሁትም…የምገነባውም ነገር የለም…፡፡

ሀትሪክ፡- …የግለ ህይወትህን እንድትፈትሽ…እንድበረብርስ ትፈቅድልኛለህ…?

አቡኪ፡- …(አሁንም ሳቅ)…የምን የግል ህይወት አመጣህ ደግሞ…?

ሀትሪክ፡- …በእርግጥ በጣም ልጅ እንደሆንክ አውቃለሁ…ግን ታዋቂ ተጨዋች ስለሆንክ ዝናህን ተከትሎ የመጣ የፍቅር ጥያቄ አለ…?…በአጭሩ…አፍቃረሃል…?…ወይም ተፈቅረሃል…?…ብዬ የግል…ጉዳይህን መፈተሽ አምሮኝ ነው…አጠፋሁ…?…

አቡኪ፡- …ሆ…(በጣም ሳቅ)…እስከ አሁን ወፍ የለም…ሙያዬን፣ክለቤን ብቻ…አፍቅሬ ነው ያለሁት…(አሁንም ሳቅ)…

ሀትሪክ፡- …አቡኪ አልዋሽኸኝም…?

አቡኪ፡- …(አሁንም ሣቅ)…አረ በፍፁም…!…አልዋሸኸኝም ያልከው…ምን ሰምተህ ነው…?… (ሳቅ)…በእርግጥ እስከአሀን በዚህ ዙሪያ የጀመርኩት ነገር የለም…ነገር ግን አሁን ሳልጀምረው የምቀር አይመስለኝም…(ያላባራ ሳቅ)….

ሀትሪክ፡- …ማመን አልችልም…ጓደኛ ይዘሃል ማለት ነዋ…?…

አቡኪ፡- …(አሁንም በጣም ሣቅ)…ምነው ሰው አይደለሁም እንዴ…?…ከዚህ በላይ ምንም ስለማላወራህ ባትደክም ደስ ይለኛል…

ሀትሪክ፡- …በል ይመችህ…ባልተለመደ ሁኔታ በኢትዮጵያ ቡና ኮንትራት እያለህ ለአራት አመት የሚቆይ ኮንትራት ፈርመሃል ምን ስሜት ፈጠረብህ…?…

አቡኪ፡- ..በጣም ነው የተደሰትኩት…ኢትዮጵያ ቡና የሀገሪቱ ትልቅ ክለብ ነው…በጣም የሚወደዱ ደጋፊዎች ያለው ክለብም ነው…በዚህ ደረጃ ያለ ክለብ ኮንትራት እያለህም ለተጨማሪ አመታት ፈርም ሲሉህ ለሰከንድም ቢሆን አታመነታም…ሰውም ሳታማክር ከአንድ አንድ ነው የምትፈርመው…እኔም ሚኪም ያደረግነው ይሄንን ነው…፡፡

ሀትሪክ፡- …እንደ እነ አሽናፊ በጋሻው ለረዥም አመታት ማልያውን የመልበስ…ቡና ተጫውተህ እዛው የመጨረስ ሃሣብ…በአንተም በክለቡ ውስጥም አንዳለ ይሄ የረዥም ጊዜ የኮንትራት ስምምነት አያሳብቅም…?…

አቡኪ፡- ለተጨማሪ አመታት በቡና የሚያቆየንን አዲስ የኮንትራት ስምምነት ከመፈረማችን በፊት እነ አሸናፊ በጋሻውን አግኝተናቸው ነበር…እነ አሸናፊ በጋሻውን ስናይ በእኛም ስሜት ውስጥ ከፍተኛ መነሳሳትን ነው የፈጠረው…ለዚህ ታላቅ ክለብ እስከመጨረሻው በመጫወት እኛም ባለ ታሪክ መሆን አለብን የሚል ሃሣብ ነው በውስጣችን የተፈጠረው…አሽናፊ በጋሻው የኢትዮጵያ ቡናንን ማልያ ለብሶ ተጫውቶ ጫማውን የሰቀለው 12 አመታትን በመጫወት ነው…እኔ ደግሞ በኢትዮጵያ ቡና ማልያ ከዚህ በላይ በመጫወት ታሪክ መስራት ነው የምፈልገው…የእነ አሸናፊ ነገር በእኔም በሚኪ ላይም መነሳሳትን ፈጥሮብን ነው…ለተጨማሪ አመታት ለመፈረም ያላመነታነው…፡፡

ሀትሪክ፡- …አህመድ (ሽሪላ)፣ፈቱዲን ጀማል ክለቡን ሊለቁ አንተና ሚኪም ትለቃላችሁ ተብሎ በተለይ በማህበራዊ ትስስር ሚዲያው በስፋት ሲራገብ ነበር…ወሬው ከምን መነሻ ተናፈሰ…?…ነው ወይስ እናንተ የሃሣብ ለውጥ አድርጋችሁ ነው የፈረማችሁት…?…

አቡኪ፡- …የሚገርምህ ነገር ወሬውን ሰምተናል…በፌስ ቡክ ላይም ብዙ ሲባል እንደነበር እንሰማ ነበር… ወሬው ከምን ተነስቶ እንደተወራም አልገባንም…ምክንያቱም በኢት.ቡና የሚያቆይ ኮንትራት እኮ በእጃችን ላይ አለ…ኮንትራት እያለንስ እንዴት እንለቃለን…?…

ሀትሪክ፡- …ከጥቅማጥቅም ጋር በተያያዘ ጥያቄ አቅርባችሁ ምላሽ ባለማግኘታችሁ ምክንያት…ለመልቀቅ እንዳሰባችሁ ነበር በወቅቱ በስፋት ሲናፈስ የነበረው…?

አቡኪ፡- …ከጥቅም ጋር በተያያዘ የጠየቅነው አንድም ነገር የለም…የክለቡ አመራሮች ገበያው ላይ ምን እንዳለ…እኛም ምን እንደሚያስፈልገን…ምን እንደሚገባን እንደማይጠፋቸው ስለምናውቅ…መጠየቅ አልፈለግንም…አልጠየቅንምም….ከጥቅማጥቅም ጋር በተያያዘ ቡናን የምትለቅበት ክለብ ሳይሆን… ጥቅማጥቅምም አጥተህም ቢሆን የምትጫወትበት ክለብ ነው…

ሀትሪክ፡- …በኮንትራት ላይ ኮንትራት ያውም ለ4 አመት በእግር ኳሱ አካባቢ አልተለመደም ይሄ ግርምትን አልፈጠረብህም…?

አቡኪ፡- …በነገራችን ላይ አሰልጣኞችንም ለአራት አመት ነው የፈረመው…እንደተባለው እኔም ሚኪም ኮንትራት እያለን ነው ለተጨማሪ አመታት የፈረምነ…ክለቡ ውስጥ እነ አቶ ገዛኸኝ ያመጡት አዲስ ሃሣብ ያለ ይምስለኛል…ተጨዋቾች ክለቡ ውስጥ ብዙ አመት የሚጫወቱበትና የሚቆዩበት አሠራርን…ይሄ በጣም አሪፍ ሃሣብ ነው…ጥቅማጥቅሙ ከወቅቱ ጋር ተገናዝቦ ከተከበረልህ፣ደሞዝህ ላይ ጊዜውን ያማከለ አሠራር ከተሠራ ተጨዋቹ ከክለብ ወደ ክለብ ምን ያዟዙረዋል ብለህ ነው?…ሃሣቡ ጥሩ ስለሆነ በሌሎች ክለቦችም ቢለመድ ጥሩ ነው ባይ ነኝ…ክለቡ እኛን ስለፈለገን…እኛም ክለቡን ስለፈለግነው ነው ወደዚህ ነገር የመጣነው…ከላይ እንዳልኩህ ኢት.ቡና ትልቅ ክለብ ነው ለ4 አመት ተወውና ለ1ዐ አመትም ፈርም ብትባል ሁለቴ ማሰብን አይጠይቅም…፡፡

ሀትሪክ፡- …በተለይ ለአንተ የክለብ አጋር ብቻ ሳይሆኑ በጣም የቅርብ ጓደኞችህና የክለቡ ቁልፍ ተጫዋቾች የሆኑት ፈቱዲን ጀማልና አህመድ (ሽሪላ) ክለቡን መልቀቃቸውን ስታይ ምን አልክ…?

አቡኪ፡- …ዕውነት ለመናገር በወቅቱ ለማመን ተቸግሬ ነበር…ሁለቱም ተጨዋቾች በክለቡ ጥሩ ጊዜን ያሳለፉ፣ለውጤታማነቱም የነበራቸውም ሚና ከፍተኛ ስለነበር አለመልቀቃቸውን ነበር አጥብቄ ስመኝ የነበረው…እንደ ጓደኛ ከእኔ ጋር በጣም ቅርበት ነበራቸው…ነገር ግን ከቅርበቱም በላይ ለክለቡ እጅግ አስፈላጊው ተጨዋች ስለነበሩ ባይወጡ በጣም ደስ ይለኝ ነበር…ስመኝ የነበረው ይሄንን ነበር… በመጨረሻ ያው ህይወት መቀጠል ስለነበረበት የተሻለ ነው ብለው ያመኑበትን ውሣኔ ወስነው ለቀዋል…በዚህ መልኩ በመለየታቸው እንደቅርብ ጓደኛም እንደ ክለብ አጋርም በጣም ቅር ብሎኛል…ነገር ግን ምርጫውና ውሳኔው የግላቸው በመሆኑ ከማክበር ከመቀበል ውጪ አማራጭ ስለሌለኝ ተቀብየዋለሁ…፡፡

 

ሀትሪክ፡- …የኮሮና ቫይረስ በትንሹ ለሰባት ወር ያህል የስፖርቱን አለም ከእንቅስቃሴ ውጪ አድርጎ ቆይቷል…በየቀኑ በልምምድና በጨዋታ ማሳለፍ የለመደው አቡበከር ይሄንን አስቸጋሪ ጊዜ እንዴት አሳለፈው…?

አቡኪ፡- …ኡ…!…በተለይ ኮሮና ቫይረስ የገባበት የመጀመሪያው አንድ ወር አካባቢ በጣም ከብዶኝ ነበር…የሆነውን ሁሉ አምኜ ለመቀበል ሁሉ ተቸግሬ ነበር…በጣምም ነበር የሚያስጨንቀው…እስቲ አስበው በየቀኑ ልምምድና ጨዋታ በማድረግ ላሳለፈ ሰው በአንዴ ሁሉን ነገር አቁም የሚል አስገዳጅ ነገር ሲመጣ እውነት እንደሆነ እያወክም በአይንህ እያየህም ለመቀበል ትቸገራለህ…ከአዕምሮህ ጋርም ትታገላለህ…በኋላ ላይ ግን የነገሩን ከባድነት እየተረዳን ስንመጣና ጥንቃቄው ላይ ትኩረት ሲሰጥ ትንሽ ቀለል አለልኝ…ካለ ልምምድ መቀመጥ የራሱ የሆነ አደጋን ስለሚያመጣ ህጉን በማይጥስ፣ጥንቃቄን በተከተለ ሁኔታ ልምምድ እንሠራ ነበር…በሂደትም ሠፈራችን ሜዳ ስላለ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ እንጫወት ነበር…እነ መስዑዴም ሰፈር እየመጡ በጥንቃቄ ልምምድ እየሠራን እየተጫወትን ነበር አስቸጋሪውን ጊዜ ያሳለፍኩት…በአጭሩ ከሪትሙ አልወጣሁም…ለብ/ቡድን የተጠራሁት እየሰራሁ ባለበት ሰዓት ስለበር ከብ/ቡድኑ ጋር ዝግጅት ስንጀምር ያልተቸገርኩትም ለዛ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- …በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራውን የብ/ቡድኑን ስብስብ ግልፅልኝ ብልህ እንዴት ነው የምትገልፀው…?

አቡኪ፡- …ስብስቡ በጣም ጥሩ ነው…ከታዳጊ የመጡ፣ከፍተኛ ልምድና የኢንተርናሽናል ተሞክሮ ያላቸው ፕሮፌሽናል ተጨወቹ የተካተቱበት ስብስብ በመሆኑ ምርጥ ስብስብ ነበር…ከሁሉም በላይ ሁላችንም ተጨዋቾች ከ7 ወር ቆይታ በኋላ ወደ መደበኛ ልምምድ የተመለስንበት በመሆኑ ሁላችንም ልምምድም ጨዋታም በጣም ተርበን ነበር የመጣነው…እንደ ሀገር…ህዝብህን ወክለህ የምትጫወትበት ስብስብ ሲሆን ደገሞ ጉጉቱ የበለጠ ነው…ትልቁም ትንሹም እኩል የሚታይበት ስለነበር…መከባበሩም፣ መተሳሰቡም፣ለሀገር አንድ ነገር የመስራት ፍላጎቱ ከፍተኛ ስለነበር የነበረው ስብስብም፣ድባቡም በጣም ደስ ይል ነበር…፡፡

ሀትሪክ፡- …አንተ በአብርም መብራቱም…በውበቱ አባተም…የመሰልጠን እድል አግኝተሃል…ምን አይነት አንድነት ወይም ልዩነት እንዳየህባቸው እውነተኛውን ስሜትህን ንገረኝ እስቲ…?

አቡኪ፡- …(ሣቅ)…ሁለቱም ጥሩዎች ናቸው…የየራሣቸው ጥሩ ነገር ቢኖራቸውም…በአብዛኛው አጨዋወታቸው ተቀራራቢ ነው…ለእኔ ሁለቱም ተመችተውኛል…ሁለቱም ጥሩዎች ናቸው ብዬ ማለፉን ነው የምመርጠው…በጣም የሚገርምህ ነገር ግን ከዚህ ከአሰልጣኝ ጋር በተያያዘ እኔ በጣም እድለኛ ነኝ…እስከአሁን ጥሩ የማይባል አሰልጣኝ አላጋጠመኝም…የገጠሙኝ ሁሉ ጥሩዎች ናቸው…፡፡

ሀትሪክ፡- …ኒጀርን 3ለዐ በሆነ ውጤት ማሸነፋችሁ የተለየ የደስታ ስሜት ነው የፈጠረባችሁ…ግን በሠላም ነው ብለው የሚጠይቁ አሉ መልስ አለህ…?

አቡኪ፡- …እንዴ ምን ማለት ነው…?ወክለን የምንጫወተው ከ11ዐ ሚሊዮን ህዝብ በላይ ነው…በዚያ ላይ ደግሞ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ፉክክር ውስጥ የመለሰን፣ተስፋም እንድንሰንቅ ያደረገ ጨዋታ ስለነበር…በድል መወጣታችን በጣም አስደስቶናል…ከምንም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያዊያንን አንድ አድርጎ በጋራ እንድንደሰትም ያደረገ ውጤት በመሆኑ የተለየ ስሜትን ፈጠሮብናል…የአንድ ቡድን የመጨረሻ ግቡ ወይም አላማው ማሸነፍ ነበር…እሱን ተወጥተናል ብዬ ስለማስብ አስገራሚ የሚሆነው መደሰታችን ሣይሆን ባንደሰት ነበር…(ሣቅ)…

ሀትሪክ፡- ኒጀርን ማሸነፋችሁ ትልቅ ነገር ቢሆንም…3ለዐ ያሸነፉት ደካማውን ኒጀር ነው ብለው የድሉን መጠን በጣም ያሳነሱ ጥቂቶች አይደለም…ይሄስ ምን ስሜት ይፈጥርብሃል…?

አቡኪ፡- …ኒጀርን ደካማ ነው ብለን ደፍረን የምንናገረው ከምን መነሻነት እንደሆነ እኔ ሊገባኝ አልቻለም…ፊፋ በየወሩ በሚያወጣው ደረጃ ላይ እኮ ኒጀር ከእኛ በልጣ ነው የተቀመጠችው…በተሻለ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው እኮ ከእኛ የምትሻልበት ምክንያት ስላለ ይመስለኛል…ከኒጀር ያነሰ ደረጃ ይዘን እንዴት ነው ኒጀርን ደካማ ናት ብለን ደፍረን የምንናገረው፣ውጤቱንም የምናጣጥለው…በዚያ ላይ ኒጀሮች ከሀገራቸው ውጪ የሚጫወቱ ብዙ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾችን የያዘ ቡድን ነው…በዚህ እውነታ ላይ ያለን ቡድን ያውም 3ለዐ ስናሸንፍ ውጤቱን ከማድነቅና እኛንም ከማበረታት ይልቅ…ኒጀሮች ደካማ ስለሆኑ ነው እንጂ የብ/ቡድኑ ጥንካሬ አይደለም ብሎ ማጣጣሉ በእወነት ጥሩ አይደለም… የተጨዋቾችንም ስሜት ይጎዳል፣ሞራልም ይገድላል…ውጤቱን አድንቆ አበረታቶ…የሚታረም፣ የሚስተካከል ነገር ካለ እዛ ላይ መረባረብ ነው እንጂ…እንዳለ የሰውን ልፋት አንስቶ መሬት መጣል ይጠቅማል ብዬ አላስብም…፡፡

ሀትሪክ፡- …አዲስ አበባ ላይ 3ለዐ ካሸነፋችሁና ወደ ፉክክሩ የሚመልስ ውጤት ካገኛችሁ በኃላ ሚያሚ ላይ መሸነፍ አልነበረብንም ብለህስ አልተቆጨህም…?

አቡኪ፡- …በጣም ነው የተቆጨሁት…እውነት ለመናገር መሸነፍ ይገባን ነበር ብዬ አላስብም…ካመከናቸው እድሎች በመነሣት ማሸነፍ ባንችል እንኳን ቢያንስ ነጥብ ተጋርተን መውጣት ነበረብን…ይሄ አለመሆኑ በጣም የሚያስቆጭ ነው…በተለይ እዚህ በሰፊ ውጤት ካሸነፍናቸው በኋላ ቁጭቱ እንደ አዲስ ነው የተቀሰቀሰብን…ግን ምን ታደርግዋለህ…እግር ኳስ ስለሆነ የ9ዐ ደቂቃ ፍርዱን መቀበል ነው…፡፡

ሀትሪክ፡- …ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ የእግር ኳስ ውደድሮች ያለ ተመልካች ነው የሚካሄዱት… አንተ ደግሞ በበርካታ ደጋፊዎች መዝሙርና ድጋፍ ታጅበህ መጫወት ነው የለመድከውና…ያውም ኢንተርናሽናል ጨዋታ ያለ ደጋፊ ማድረግ ስሜቱ እንዴት ነው…?

አቡኪ፡- …እግር ኳስን ያለ ደጋፊ ማሰብ በጣም ከባድ ነው…የእግር ኳስ ውበቱም ሁሉም ነገሩ ደጋፊው እንደሆነ በተግባር ያወቅነው አሁን በቦዶ ሜዳ ስንጫወት ነው…በተለይ ለእንደ እኔ አይነት በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ መጫወትን ለለመደ ተጨዋች ሁኔታውን በቀላሉ ለመላመድ ይቸግረዋል…ወደ ራስህ ተመልሰህ እውነታውን መቀበል ካልቻልክ የእውነት ኢንተርናሽናል ጨዋታ አልመስል ሁሉ ሊልህ ይችላል…ሀገርህን ወክለህ ስትጫወት ደጋፊው ከሌለ ብዙ ነገርም ይጎድልብሃል…ደጋፊው የሀገሩን ባንዲራ ይዞ ሲጨፍር፣እየዘመረ ሲያበረታታህ፣የቡና…የጊዮርጊስ ሣይል ሁሉም ለአንተም ለሀገርህም የሚዘምርበት አጋጣሚውን ስታጣ የሆነ አንድ ነገር የጎደለህ ያህል እንዲሰማህ ያደርጋል…ከታሪክህ ላይም የሆነ ነገር ያጎድላል…ግን ነገሮች ሁሉ ግድ መሆናቸውን ስታውቅ፣እግር ኳሱ አዲስና ያልተለመደ ባህል ውስጥ መውደቁን ስትረዳ ያለውን ነገር አምነህ መቀበልና በዛው መስመር ማለፍ እንዳለብህ ስታውቅ መራራም ቢሆን ሳትወድ በግድ ትቀበለዋለህ…፡፡

ሀትሪክ፡- …አዲሱ የውድድር አመት ታህሳስ 3 ቀን ይጀመራል…ፕሪሚየር ሊጉን ያለ ደጋፊዎቻችሁ ማድረግስ አያስፈራም…?

አቡኪ፡- …ሌላው ከባዱ ነገር የሆነብኝ ይሄ ነው…በተለይ አዲሱን የውድድር ዘመን ሳስብ ካለ እነዛ የሚወደዱ፣የውደድሮች ድምቀት ከሆኑት ደጋፊዎቻችን ውጪ እንዴት ነው የምንጫወተው…?…ብዬ ከወዲሁ ሳስብ በጣም ይጨንቀኛል፣ያስፈራኛል…እኔን ጨምሮ ብዙ ተጨዋቾች ወደ ኢት ቡና የመጣታችን የክለለቡን ማልያ ለመልበስ የምንጓጓት ምስጢር ከክለቡ ትልቅነትና ታሪክ በተጨማሪ በዚህ ምርጥ ደጋፊ ታጅቦ መጫወትን በመፈለጋችን ጭምር ነው…የኢት.ቡና ደጋፊ…የተለየ ደጋፊ ነው…ሲደግፍህ፣ሲያበረታታህ፣ለክለቡ ሲዘምር ስታይ ውስጥህን ይነዝርሃል…ይሄ ምርጥ ደጋፊ በሌለበት እንደምንጫወት ሳስብ ገና ይረብሸኛል…ከወዲሁ በጣም እያስጨነቀኝ፣እያስፈራኝም ያለው ይሄ ነው…የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ በውስጥህ የሚፈጥረው ሙቀት የሚጀምረው እኮ ሜዳ ውስጥ ብቻ አይደለም…ገና ከካምፕ ተነስተን ወደ ስታዲየም ስናመራ ጀምሮ በየመንገዱ ማልያውን ለብሶ የሚሰጠን ድጋፍና ፍቅር ፍፁም የተለየ ነው…የሆነ የተለየ ኃላፊነትም ይጭንብሃል…የሚገርምህ ነገር…

ሀትሪክ፡- …ቀጥል…?

አቡኪ፡- …የሚገርምህ ነገር…አሁን እንኳን የወዳጅነት ጨዋታ ስናደርግ…ደጋፊው በብዛት መጥቶ የነጥብ ጨዋታ ያህል ነው የሚደግፈን…ልክ እንደ ነጥብ ጨዋታ ማልያውን ይዞ የሚጨፍር የሚያበረታታ ደጋፊ ነው…በወዳጅነት ጨዋታ ላይ ያየሁት፣የሚነግረኝ ነገር ራሱ እኛን እንደናፈቁ… እኛም እነሱን እንደናፈቅናቸው ነው…ሁለታችንም በከፍተኛ ናፍቆት ውስጥ ነን…አላህ ይሄን በሽታ አጥፍቶ ወይም የሆነ ነገር ተፈጥሮ የምንገናኝበት አጋጣሚ ቢፈጠር በጣም ነበር የምደሰተው…ከዚህ ውጪ ግን ያለ ኢት.ቡና ደጋፊ ጨዋታን ማድረግ ለእኔ ከወዲሁ ከባድ ሆኖብኛል…፡፡

ሀትሪክ፡- …ወደ ብ/ቡድኑ ልመልስህ ነው ቀጣይ ጨዋታችሁ ከማዳጋስካር ጋር ነው…ስለ ጨዋታው ምን ታስባለህ…?

አቡኪ፡- …የማዳጋስካርን ጨዋታ ጨምሮ ቀሪዎቹ ሶስቱም ጨዋታዎች ለእኛ በጣም ወሳኞች ናቸው… ያሰብነውን ለማሳካት ከማሸነፍ ውጪ ሌላ አማራጭ አለ ብዪ አላስብም….ቀድመህ ተናገርክ ካልከኝ በስተቀር ማዳጋስካርን በሜዳችን እንደምናሸንፍ…ማሸነፍም ግዴታችን እንደሆነ ነው የማስበው…እነሱን አሸንፈን ነው ወደ ኮትዲሾዋር መሄድ ያለብን…ማዳጋስካሮችን ቀላሎች አድርጎ ማሰብ አደጋ አለው…ከዚህ አንፃር በጣም ትኩረት ሰጥተን በጥንቃቄ መዘጋጀትና መጫወት አለብን…ማዳጋስካሮች በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፉት ከሁለት አመት በፊት ነው…ከዚያ በኋላ እየተለወጡ መጥተዋል…ከኮትዲቭዋር ጋርም ነጥብ ተጋርተዋል…አሁንም ምድቡን በእኩል ነጥብ እየመሩ በመሆኑ ቀላል ግምት የሚሰጣቸው አይደለም…በአጭሩ ቀሪ ሶስት ጨዋታዎቻችን “Do or Die” የመኖርና የመሞት ያህል ዋጋ ያላቸው ናቸው፡፡

ሀትሪክ፡- …ብ/ቡዱኑ ከ31 አመት በኋላ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ጊዜ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ተመልሷል፤ ይሄ ከተሳካ ከስምንት አመት በኋላስ በእነ አቡኪ ዘመን ወደ ካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ የሚመለስ ይመስልሀል…?

አቡኪ፡- …ከመነሻው ወደ ውድድሩ የገባነው ይሄን ታሪክ ለመድገም ነው…እኔም እንደ አንድ ተጨዋች የሀገሬን ብ/ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ በማሳለፍ ታሪክ የመስራት ትልቅ ህልምና ጉጉት አለኝ…የእንደዚህ አይነት ትልቅ ታሪክ አካል ብሆን ደስ ይለኛል…በእርግጥ ሁሉም ጨዋታዎች ከባድ ናቸው…እነሱም የማለፍ እድላቸው ሰፊ ነው…እኛም የማለፍ እድል በእጃችን ነው ያለው…ጠንክረን ከሰራን ለካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ በማለፍ ሌላ አዲስ ታሪክ እናፅፋለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ…፡፡

 

ሀትሪክ፡- …ብዙዎቹ የብ/ቡድኑ ተጨዋች ለአንተ የተለየ አድናቆት አላቸው…በተለይ ጌታነህ ከበደና አማኑኤል ገ/ሚካኤል በብቃትህ ዙሪያ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፤በእነሱ መሞገስህ ምን ስሜት ይሰጥሃል?

አቡኪ፡- …የተለየ ደስታና ክብር ነው የሚሰማኝ…በኢትዮጵያ እግር ኳስ ደማቅ አሻራ ባላቸው ተጨዋቾች በአደባባይ መሞገስ ከደስታ በዘለለም የበለጠ እንድሰራ ነው የሚያደርገኝ፣የሚያነሳሳኝም… ሌላው ሳልናገር ማለፍ የማልፈልገው ነገር ጌታነህ ከበደን ከመሰለና ከአማኑኤል ገ/ሚካኤል ጋር በአንድነት በአጥቂ መስመር ላይ መጫወቴ እድለኝነቴን ነው የሚያሳየው…ራሴንም እንደ እድለኛ ነው የምቆጥረው…ጌታነህ ከበደ በሀገሪቱ እግር ኳስ የደመቀ ታሪክ ያለው…ከሀገር ውጪም የተጫወተ፣ በፕሪሚየር ሊጉም ሪከርድ ያለው ተጨዋች ነው…አማኑኤልም ወጥቶ መጫወት የሚያስችል አቅም ያለው…በፕሪሚየር ሊጉም ቡድኑን ሻምፒዮን ከማድረግ ጀምሮ ድንቅ ብቃቱን ያሳየ ተጨዋች በመሆኑ በዚህ ደረጀ ካሉ ተጨዋቹ ጋር አብሬ መጫወቴና መሞገሴ አስደስቶኛል…ለበለጠ ነገር እንድነሳሳም አድርጎኛል…በዚህ አጋጣሚ ሁለቱንም አመሰግናለሁ…ስለ ጌታነህ ከበደ ካነሰህ…

ሀትሪክ፡- …ስለ ጌታነህ…ምን…?

አቡኪ፡- …ስለ ጌታነህ ከበደ ካነሣህ አንድ ነገር ብናገር ደስ ይለኛል…በብ/ቡድን ቆይታዬ ጌታነህ ከበደን ከጠበኩትና ከገመትኩት በላይ ሆኖ ያገኘሁት ተጫዋች ነው…ጌታነህ ከበደን የማውቀው በሜዳ ውስጥ ብቻ ነበር….በነበረን ቆይታ በተለይ ከሜዳ ውጪ ባለው ህይወቱ ጌታነህ ከበደ በጣም የተረጋጋ፣ ልምዱን፣ችሎታውንና ስኬቱን የሚያካፍል አዳዲስ ተጨዋቾችን የሚያበረታታ የሚመክር ሰው ሆኖ ማግኘቴ ያልጠበኩት ነገርም ሆኖብኛል…ከአንድ ሲኒዬርና ስኬታማ ተጨዋች የሚጠበቅበትን ነገር ነው ያየሁበት…የሚገርምህ ከመደበኛው ልምምድ ውጪም በግሉ ወጥቶ ትሬይኒንግ ሲሰራ ታየዋለህ… እውነት ለመናገር በዚህ ደረጃ ስላልጠበኩት ነው መሰለኝ በጣም ተገርሜበታለሁ…ሜዳ ውሰጥም በጣም ይመክረኝ…ከእኔ ብዙ አትራቅ ይለኝ ነበር…በየክለባችን ከነበረው የመፎካከርና የመሸናነፍ ስሜት፣በርቀት ከማውቀው አንፃር የተለየ ሆኖብኝ ጌታነህን በጣም ወድጄዋለሁ…በእርግጥ ሁሉም የሚወደዱ ቢሆኑም የጌታነህ ነገር ግን ተለይቶብኛል…፡፡

ሀትሪክ፡- …ከዚህ በፊት የብሔራዊ ቡድን ማሊያን የመልበስና ሀገርህን የመወከል ትልቅ ጉጉት እንዳለህ ያጫወትከኝን አስታውሳለሁ…አሁን ያን ህልምህን አሳክተሃል…ከዚህ በኋላስ ምን ይቀርሃል…?

አቡኪ፡- …በእርግጥ የ11ዐ ሚሊዮን ህዝብን ወክሎ የመጫወት ትልቅ ህልም ነበረኝ…ያ ህልሜ በአላህ ፈቃድ ተሳክቶልኛል…ግን ይሄ የህልሜ መጨረሻ አይደለም…አሁንም ማለሜን ቀጥያለሁ…ደግሞም ለሀገሬ ገና መጫወት ጀመርኩ እንጂ አልጨረስኩም…ለሀገሬ ብዙ መስራት የምፈልጋቸው ነገሮች አሉ…በተለይ ሩቅ ሆኖ እያስቸገረን ያለውን የአፍሪካ ዋንጫ በየሁለት አመቱ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን የማሳካት ትልቅ ህልም ነው ያለኝ…ህዝቡ ኳስ ወዳድ ነው…የመውደዱን ያህል፣ለእኛ የሚከፍለውን መስዋዕትነት ያህል ግን ተከሷል ማለት ይከብደኛል…ከዚህ አንፃር በድላችን ተደስቶ ማየት እፈልጋለሁ…ከአህጉሪቱ ምርጥ ብ/ቡድኖች ውስጥ አንዱ ሆኖ ማየትና ህዝቡን ማኩራትም ነው ምኞቴ…በተደጋጋሚ ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፋችን ሌሎች ታዳጊዎችንም ያነሳሳል…ይሄንና ሌሎች በሀገር ደረጃ ትልልቅ ስኬቶችን አልማለሁ…ለዚህ ደግሞ የሁላችንም ርብርቦሽ ያስፈልጋል…ተሸንፈን ተወው በሠፊ ውጤትም አሸንፈን ደካማ ብለን የምናጣጥለው ከሆነ የምንፈልገውን ለማሳካት ይቸግረናል…እኛን ተጨዋቾችንም በጣም ነው የሚያወርደን…በአጠቃላይ በእኔ የጨዋታ ዘመን የሀገሬን ስም የሚያስነሳ ታሪክ የማፃፍ ህልሙ አለኝ፡፡

ሀትሪክ፡- …እስቲ ወደ ክለብህ ኢት.ቡና እንምጣ…ለአዲሱ የውድድር ዘመን እያደረጋችሁት ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል…?

አቡኪ፡- …ጥሩ ዝግጅት እያደረግን ነው…አሰልጣኞችን ለውድድሩ የሚመጥአ ነገር እያሠራን ነው… እንደምታወቀው ረዥም ጊዜ ከብ/ቡድኑ ጋር ቆይቼ ነው የተቀላቀልኩት…ስቀላቀልም የከበደኝ ነገር የለም…የምናውቀውን ነገር ነው አየሠራን ያለነው…አብረህ ስትቆይ…አብረ አየሠራህ ስትመጣ ይበልጥ እየተዋወቅ ትሄዳለህ…ኮቹ ከአንተ ምን እንደሚፈልግ…አንተም ምን እንደምትፈልግ እየተረዳህ ስለምትሄድ ዝግጅቱን የበለጠ ጥሩ ያደርገዋልና…በአጠቃላይ ግን ጥሩ የሚባል ዝግጅት እያደረግን ነው…፡፡

ሀትሪክ፡- …ይሄን ቃለ-ምልልስ እስከሰራንበት ማክሰኞ ድረስ አራት የወዳጅነት ጨዋታ አድርጋችሁ አራቱም ላይ አግብተሃል…አቡኪ ይበልጥ ጨምሯል ማለት ነው…?

አቡኪ፡- …(ሳቅ)…ይሄንን እኔ መመስከር አልችልም…ለክለቤ ከዚህ በላይ መሆን እንዳለብኝም ነው የማስበው…ራሴን ከፍ ማድረግ እፈልጋለሁ…የወዳጅነት ጨዋታው ራሳችንን ለመፈተሽ በጣም ያግዘናል… ድክመትና ጥንካሬያችንን ከዋናው ውድድር በፊት እናማርበታለን…ዕውነት ለመናገር ቡድናችንን ብታዩት በጣም ጥሩ ነው…ያለው ነገርም በጣም ደስ ይላል…፡፡

 

ሀትሪክ፡ …የካሳዬ አራጌን ስራ መስክርልኝ ብልህስ…?

አቡኪ፡- …ጥሩ እየሠራ ነው…አጨዋወቱ ስኬት ያመጣልናል ብሎ አስቦ ነው እየሠራን ያለው… የአንድ አሠልጣኝ ትልቁ ነገሩ ተጨዋቾቹን ለውጤት ይረዳኛል ብሎ ባስበው ነገር መቅረፅ ነው…ካሳዬም እያደረገ ያለው ይሄንን ነው…ቀጣይነት ያለው ቡድን እየሠራ መሆኑን ነው የታዘብኩት…፡፡

ሀትሪክ፡- …በአዲሱ የውደድር ዘመን ከኢት.ቡና ጋር ምን አስበሃል…?…ዋንጫ…?…ብልህ…መልስህ አዎን ነው…?

አቡኪ፡- …(ሣቅ)..ትልቁ ግባችን ዋንጫ ማንሣት…ሻምፒዮን መሆን ነው…አምና በሁለተኛው ዙር የመጣንበት መንገድ አለ በዚያ መቀጠል ነው የምንፈልገው…አሰልጣኙ የሚፈልገውን ነገር ተጨዋቾቹ እየተረዱት መጥተዋል…ይሄ መረዳታችን ነው ወደ ውጤት የሚወስደን…ከዚህ አንፃር የምንጫወተው ለተሳትፎ ብቻ ሣይሆን ለሻምፒዮናነት…ደጋፊዎቻችንን በጨዋታም በውጤትም ለማስደስት ነው…፡፡

ሀትሪክ፡- …የግል ክብርስ አያጓጓህም…?…ማሳካት የምትፈልገው ነገር…?

አቡኪ፡- …ከየግል ክብሬ ይልቅ የክለቤ ክብርና ስኬት ነው የሚበልጥብኝ…ከግል ክብሬ ይልቅ ክለቤ መጀመሪያ ውጤት እንዲያመጣ፣ሻምፒዮን ሲሆን ነው ማየት የምፈልገው…ቲሙ ሻምፒዮን ሣይሆን በግሌ ብዙ ክብሮችን ባገኝ ደስታዬ ሙሉ አይሆንም…ቲሙ ውጤታማ ሆኖ እኔም የግል ክብሮችን ብጎናፀፍ የበለጠ ነው የምደሰተው…የምመርጠውም ይሄንን ነው…?

ሀትሪክ፡- …በቃ…?

አቡኪ፡- …አዎን…በቃ…!ከዚህ ውጪ ግን…ትልቅ ክለብ ውስጥ እንደመጫወቴ ዘንድሮ የሀገሪቱ የኮከብ ግብ አግቢነትን ክብር ለራሴም ለክለቤም በማፃፍ ከቀደሙት ኮከቦች ተርታ ታሪኬን ማፃፍ እፈልጋለሁ…፡፡

ሀትሪክ፡- …የዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ በዲ.ኤስ.ቲ.ቪ በመላው አለም ይተላለፋል…ይሄ አጋጠሚስ ምን ስሜት ፈጠረብህ…?

አቡኪ፡- …ለእግር ኳሳችንም፣ለእኛ ለተጨዋቾችም ጥሩ አጋጣሚን ነው ይዞልን የሚመጣው…እግር ኳሳችንንም፣የተጫዋቾቻችንን አቅምም ለአለም ገበያ አቅርቦ የሚያሳይ ወርቃማ እድል ነው…እኔ እንኳን ባይሳካልኝ ሌሎች የሀገሬ ልጆች የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት እድል እንዲያገኙ ጥሩ አቋራጭ መንገድ ስለሚሆነን…ጨዋታውን በዲ.ኤስ.ቲቪ መተላለፉ ትልቅ ጥቅም ይዞ ነው የሚመጣው…ከላይ ያለውን ትልቅ ነገር ሁላችንም ታሳቢ አድርገን ስለምንጫወት የፉክክሩ መጠን፣የግል ብቃትም ከፍ ይላል…በዚህ ደግም ብ/ቡድኑንም ተጠቃሚ ያደርገዋል የሚል እምነት ነው ያለኝ…፡፡

ሀትሪክ፡- …አመሰግኜህ ከመለያየቴ በፊት…በአንድ ወቅት ፕሮፌሽናል ተጨዋች የመሆን ህልም እንዳለህ ነግረህኝ ነበር…እሱስ ምን ደረሰ…?…የሚለውን የመጨረሻ ጥያቄዬ ላድርገው…?

አቡኪ፡- …በእርግጥ አምና እድሉን አግኝቼ ባልሆነ ምክንያት ሳልገፋበት ቀርቻለሁ…አሁን ለጊዜው በዚህ ዙሪያ የጀመርኩት ነገር ባይኖርም ፕሮፌሽናል የመሆን ህልሜ አሁንሜ ግን አሁንም አብሮኝ አለ…ህልሜን አሳክቼ የራሴንም የሀገሬንም ስም የማስጠራት ትልቅ ጉጉት አለኝ…ሽመልስ በቀለም ባለፈው ሲናገር…“የሀገራችን ተጨዋቾች ወጥተው መጫወት የሚችሉበት አቅሙ አላቸው” ብሏልና… እኔም ተስፋ አልቆርጥም…ህልሜን እውን ለማድረግም እጥራለሁ…፡፡


photo © Hatricksport archives

©natanim pictuers

©kalusha picters

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.