ሊግ ካምፓኒ ስለ ሶስቱ የትግራይ ክልል ክለቦች መረጃ የለኝም አለ

ሊግ ካምፓኒ ስለ ሶስቱ የትግራይ ክልል ክለቦች መረጃ የለኝም አለ

መረጃዎች ከወልዋሎ አዲግራት ውጪ ስሁል ሽረና መቐለ 70 እንደርታ እንደሚካፈሉ ያሳያሉ


የትግራይ ክለቦች ከሆኑት መሀል የወልዋሎ አዲግራት የመካፈል እድል አጠራጣሪ ቢሆንም መቐለ 70 እንደርታና የስሁል ሽረ ተሳትፎ የተረጋገጠ መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

የፊታችን ቅዳሜ በሚጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2013 መርሃ ግብር ላይ የ3ቱ የትግራይ ክለቦች መቐለ 70 እንደርታ፣ ስሁል ሽረና ወልዋሎ አዲግራት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው የሚገልፀው የፕሪሚየር ሊጉ ሊግ ካምፓኒ ከክለቦቹ የመሳተፍና ያለመሳተፍ ማረጋገጫ እንዳላኘ በመግለፅ የሚጀመርበት ቀን ታህሳስ 3/2013 እንደማይቀየር ነገር ግን የክለቦቹ የመጨረሻ ውሣኔ እስከ ፊታችን ማክሰኞ እንደሚታወቅ ለሀትሪክ አስረድቷል፡፡

ሀትሪክ ከታማኝ ምንጯ ባገኘችው መረጃ ግን አሰልጣኙ ሲሳይ አብርሃምና 16 ተጨዋቾች አዲስ አበባ የሚገኙለት ስሁል ሽረ መካፈሉ እንደተረጋገጠና የመቐለ 70 እንደርታ የመሳተፍ እድል ሰፊ መሆኑን እስከ ማክሰኞ ድረስም ተጨማሪ ተጨዋቾችና አሰልጣኙ ገ/መድህን ኃይሌ ይመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የደረሰን መረጃ ያስረዳል፡፡

የወልዋሎ አዲግራት ቡድን ጋር ምንም አይነት የመረጃ ልውውጥ ማድረግ እንዳልተቻለና የመሳተፍ እድሉም የጠበበ መሆኑ የሀትሪክ ምንጭ አስረድቷል፡፡
የሁለቱ ክለቦች የመሳተፍ ነገር የሰፋ ቢሆንም የወልዋሎ አዲግራት 25 ተጨዋቾችና ወደ 4 የሚጠጉ የአሠልጣኝ ስታፍ አባላትና ከጀርባቸው ያሉት ቤተሰቦች እድል አስጊ ሆኗል፡፡ በተለይ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የክለቡ ተጨዋች ለሀትሪክ እንደገለፀው “ቼክ ተሰጥቶኝ ሄጄ ላወጣ ስል ምንም ገንዘብ የለውም ተባልኩ፤ ግራ ገብቶኛል ቤተሰብ አለኝ መኖር እፈለጋለሁ ከክለቡ ሰዎች ጋር ምንም መገናኘት አልቻልኩም፤ ፌዴሬሽኑ መላ ሊያበጅልን ይገባል” ሲል ተናግሯል፡፡ ውል ያላቸው ተጨዋቾች ሆነው ቼክ ተሰጥቷቸው ገንዘብ የለውም አካውንቱ ባዶ ነው የተባሉትም ይሁኑ ውላቸው ፌዴሬሽን የፀደቀ ተጨዋቾች ወይ ከገንዘቡ አሊያም ወደ ሌላ ክለብ መጓዝ አለመቻላቸው አጣብቂኝ ውስጥ ከቷቸዋል፡፡

በዚህ የክለቦቹ ጉዳይ ከሀትሪክ ጥያቄ የቀረበላቸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በበኩላቸው “ጉዳዩን እየተከታተልነው ነው በኛ በኩል አስቀድመን በስራ አስፈፃሚ ደረጃ ተወያይተንበታል እስኪ የውድድሩ ቀን ይቀረብና ያለውን ሁኔታ አይተን ውሣኔ እንሰጣለን በሚል በቀጠሮ ይዘነዋል በኛ በኩል ተገቢ ያልነውን ውሣኔ ለመወሰን በስራ አስፈፃሚ ደረጃ ተዘጋጅተናል” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport