ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለ4
ዓመታት በፕሬዚዳንትነት እንድትመራ ተመረጠች

በይስሀቅ በላይ


በእርግጥ ዜናው ለብዙዎች አደናጋሪ ወይም እንግዳ
ሊሆን ይችላል…ምክንያቱም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤውን፣የፕሬዝዳንትና
የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች ምርጫ የሚያደርገው ገና የፊታችን ሰኞ ነውና፡፡

ከዚህ አንፃር ዜናዉ ከፈረሱ ጋሪውን ያስቀደመ ቢመስልም ጠቅላላ ጉብኤውና ምርጫው የፊታችን ሰኞ የሚከናወን
ቢሆንም ጉባኤው ተካሄዶ ሲጠናቀቅ ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ለመጪዎቹ አራት አመታት ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነትእንድትመራ ተመረጠች ከሚል ዜና ውጪ እንደማያሰማን እርግጠኛ ሆኖ
መናገር ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት የአሁኑ የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል
ፕሬዚዳንት ጀግናዋ አትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉና ከደቡብ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በእጩነት ተወክለው የነበሩት
አቶ ተፈራ ሞላ ቀርበው የነበረ ቢሆንም የደቡቡ ተወካይ አቶ ተፈራ ህዳር 25 ቀን በፃፉት ደብዳቤ ራሣቸውን
ከፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ፉክክር ውጪ ማድረጋቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡

በዚህመ መሠረት በአሁኑ ሰዓት ቀድሞዋ ባለ ታሪክ ውጤታማዋ አትሌት ደራርቱ ቱሉ ብቸኛዋ የፕሬዝዳንታዊ ፉክክር እጩ ሆና
ለምርጫ የምትቀርብ በመሆኑ ቀጣይዋ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ሆኖ እንደምትመረጥ ተረጋግጧል፡፡ ላለፉት አራት አመታት ፌዴሬሽኑን በተቀደሚ ምክትል ፕሬዚዳንትነት እንድትመራ ከተመረጠች በኋላ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ በግል ምልክያቱ ራሱን
ከፕሬዚዳንትነት ካነሣበት ቀን ጀምር ቦታውን ሸፍና ስትሠራ የነበረችው የቀድሞዋ አትሌት ደራርቱ ቱሉ ሰኞ
በሚካሄደው ምርጫ ሙሉ ፕሬዚዳንት ሆና በመመረጥ ፌዴሬሽኑን
እንደምትመራ ከወዲሁ ታውቋል፡፡

የ1992 የባርሴሎና፣የ2000 የሲዲኒ ኦሎምፒክ የ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ፣የ2004 የአቴንስ ኦሎምፒክ የ10 ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳልያ አሸናፊና የመጀመሪያዋ ጥቁር አፍሪካዊት ሴት
የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ በመሆን የራስዋንም የሀገርዋንም ስም በወርቅ ቀለም ለማፃፍ የበቃችው
ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ለመጪዎቹ 4 አመታት ስኬታማውን የአትሌቲክስ መንደር በበላይነት ትመራለች።

አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ የፊታችን ሰኞ ጠቅላላ ጉባኤውን ሲያደርግ ፌዴሬሽኑን በስራ አስፈፃሚነትነት የሚያገለግሉ ሰዎችን ምርጫም የሚያደርግ እንደሆነ ከተያዘው መርሃ ግብር ለመረዳት
ተችሏል፡፡ 

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.