የ ቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ ጅማሮ እና ቁጥሮች !

 

የቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ በመጀመሪያው ሳምንት አስራ ሁለት ክለቦች ተሳትፎ አድርገው አስራ ሰባት ጎሎችን ለመመልከት ችለናል ።

ይህም ከባለፈው አስራ ስድስት የኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ባደረጉት የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ ጋር ሲነፃፀር በአራት ከፍ ብሎ ታይቷል ። አስራ ሰባት ጎሎች ተቆጥረው ሲያልፉ አዳማ ከተማ አራት ግቦችን በማስቆጠር ቀዳሚው ክለብ ሆኗል ። ከዚህ በተጨማሪም መቆጠር ከቻሉት አስራ ሰባት ጎሎች መካከል አምስቱ ብቻ በመጀመሪያ አጋማሽ ተቆጥረዋል ።

በዚህ ሳምንት አንድ ብሎ በጀመረው የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ አንድ የቀይ ካርድ ሲመዘዝ የጅማ አባ ጅፋሩ ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑሪ ቀይ ካርዱን የተመለከተ ተጫዋች ነው ።

በባለፈው የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ሳምንት ላይ ሁለት ቀይ ካርዶች ሲመዘዙ አዲስ ተስፋዬ እንዲሁም ዘሪሁን አንሼቦ መመልከታቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ሲሆን ዘንድሮ በአንድ ዝቅ ብሏል ።

በመጀመሪያው ሳምንት የ ቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ አራት ፍፁም ቅጣት ምቶች ሲሰጡ የሰበታ ከተማው ተስፈኛ ግብ ጠባቂ የበረከት ሳሙኤልን ሙከራ ማዳን የቻለ ብቸኛው ግብ ጠባቂ ሲሆን ሌሎች ሶስት የተገኙ የፍፁም ቅጣት ምቶች በ ታፈሰ ሰርካ ፣ አቡበከር ናስር እንዲሁም ዳዊት ተፈራ ወደ ግብነት መቀየር ችለዋል ። የሰበታ ግብ ጠባቂ ፋሲል ገ/ሚካኤልን ጨምሮ የድሬድዋው ፍሬው ጌታሁን እንዲሁም ሚኬል ሳማኪ በሳምንቱ ግብ ያላስተናገዱ ብቸኞቹ ግብ ጠባቂዎች ናቸው ።

የባለፈው የውድድር ዓመት የኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ ኮከብ ግብ አግቢነት ሲመራ የቆየው ሙጂብ ቃሲም የዘንድሮውን የውድድር ዓመት አንድ ብሎ ግብ ሲያስቆጥር አቡበከር ናስር ፣ ፍፁም አለሙ ፣ ታፈሰ ሰርካ እንዲሁም አብዲሳ ጀማል በሳምንቱ ሁለት ጎሎችን ማስቆጠር የቻሉ ተጫዋቾች ናቸው ። በባለፈው የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ሳምንት አስራ አንድ ተጫዋቾች በመጀመሪያው ሳምንት የግብ አግቢነት ደረጃ ሰንጠረዥ ላይ መቀመጥ ሲችሉ የጣና ሞገዶቹ የፊት መስመር ተጫዋች ባዬ ገዛኸኝ ብቸኛው በዘንድሮው የውድድር ዓመት በዝርዝሩ ውስጥ መካተት የቻለ ተጫዋች ሆኗል ።

በዚህ ሳምንት ከተመዘገቡ አዲስ ሁነቶች መካከል በርካታ የውጭ ሀገራት ተጫዋቾችን የያዘው የ ቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ አንድም የውጭ ሀገር ተጫዋች ግብ ማስቆጠር ሳይችል ቀርቶ ሲያል በባለፈው የውድድር ዓመት በዚህ ረገድ ዲዴዬ ሌብሪ ግብ በማስቆጠር ብቸኛው ተጫዋች መሆን ችሎ ነበር ።

በዝውውር መስኮቱ ወደ ሌላ ክለብ ከተዘዋወሩ ተጫዋቾች መካከል በሳምንቱ ከተቆጠሩ አስራ ሰባት ግቦች መካከል አምስት ተጫዋቾች ዘጠኙን ማስቆጠር ችለዋል ።

በዚህ ሳምንት በዘንድሮው የውድድር ዓመት ሙጂብ ቃሲም የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ግብ ፣ አቡበከር ኑሪ የመጀመሪያውን ቀይ ካርድ ፣ አቡበከር ናስር የመጀመሪያው ፍፁም ቅጣት ምት በማስቆጠር የመጀመሪያዎቹ መሆን ችለዋል ።

የ ቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግን ከበርካታ ከዋክብሮቹ ጋር መለያየቱ እና ከ ገንዘብ ጋር በተያየዘ ከፍተኛ ጥያቄ ሲነሳባቸው የቆዩት አዳማ ከተማዎች ሊጉን እየመሩ ይገኛሉ ።

Hatricksport website Editor

Twitter

kidus Yoftahe

Hatricksport website Editor