“ዘንድሮ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ዋንጫ መውሰድ ቀላል ነው፣ ከዋንጫው ይልቅ ያለ መውረድ ፉክክሩ ከባድ ይሆናል” ሙሉአለም መስፍን (ዴኮ)

በዮሴፍ ከፈለኝ 

ሀትሪክ፡- በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ለ7 ወራት እግር ኳሱ ቆሞ ነበር.. እንዴት አለፍከው?

ሙላለም፡- ከባድ ጊዜ ነው ያሳለፍነው.. በሀገርም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ከባድ ጊዜ ታልፏል፡፡ ከምትወደው ስራ ተገልለህ ከማህበራዊ ስራ ቆመህ መገኘት ከባድ ነው፡፡ በግሌ ቤት ውስጥ ልምምድ በመስራት መፅሀፍትን በማንበብ አሳልፌያለሁ.. እንደተፈራው ሳይሆን እግዚአብሔር ደርሶልን የነበረው ስጋት በዛ ደረጃ ጉዳት አለማድረሱ ደስ ብሎኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ውድድሩ መመለሱና ልምምድ መጀመራችሁስ ምን ስሜት ፈጠረብህ?

ሙላለም፡-ቃላት አጥቻለሁ… ውድድር መመለሱ በጣም አስደስቶኛል ከራኩበት ስራና ጓደኞቼ ጋር መገኘት ደስታን ፈጥሮልኛል፡፡ ኳስ ጨዋታው ብቻ ሣይሆን ከጓደኞቼ ጋር እንደ ቡድን ተገናኝተን የምናሳልፈው ጊዜና ጨዋታ ይናፍቃልና በመመለሱ ተደስቻለሁ… ትልቅ መነሳሳት ፈጥሮልን ከናፈቅነው ኳስ ጋር በመገናኘታችን በጣም ደስታ ተሰምቶኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ለ2013 የውድድር ዘመን የቅዱስ ጊዮርጊስ የቡድን ግንባታ ምን ይመስላል?

ሙላለም፡- ጊዮርጊስ የኮቪዱ መቋረጥን ጨምሮ ባለፉት 3 አመታት በታሪኩ ባልገጠመው መልኩ ከዋንጫ መራቁ በውስጣችን ትልቅ መነሳሳት የፈጠረበትና ቆርጠን የተነሳንበት ጊዜ ነው… ትልቅ ሲቪ ያላቸው አሰልጣኞች ከመቅጠር አንስቶ በሀገር ደረጃ ያሉትን ምርጦችን በማስፈረም ነባሮችን በማቆየት በቁርጠኝነት ልምምዳችንን ስንሰራ ሰንብተናል፡፡ ቡድኑ ከየትኛውም ጊዜ በላይ በስኳድም ሆነ በስነልቦና ተጠናክሮ ይገኛል፡፡ ካለፈው ጊዜ የተሻለውን ጊዮርጊስ እናያለን ብዬ አስባለው፡፡

ሀትሪክ፡- አዲስ ስለፈረሙትና ስለተሰናበቱት ተጨዋቾች የምትለው ነገር አለ?

ሙላለም፡- ስለነርሱ ብዙ ባላወራ ደስ ይለኛል ያስገባሁትም ሆነ ያስወጣሁት እኔ አይደለሁም (ሣቅ)

ሀትሪክ፡- ስለገቡት ተጨዋቾች ጥንካሬና አቅም መናገር አልችልም እያልክ ነው?

ሙላለም፡- /ሳቅ/ የመጡትማ ሀገሪቱ ላይ ያሉ ጎል አስቆጣሪ ናቸው፡፡ አሁን የፈረመው አማኑኤል፣ ጌታነህ ከበደ.. አቤል ያለው፣ አዲስ ግደይ፣ ከነአን ማርክነህ በሙሉ በልዩ ብቃት ላይ ያሉ ናቸው እዚህ ቡድን ውስጥ ለመግባት በነበርክበት ቡድን ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆነህ ካልተገኘህ አትመጣም ተፅዕኖ ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን ደግሞ ዲሲፕሊንም ወሳኝ ነው፡፡ አዲስ ፈራሚዎቹ ሁለቱንም ያሟሉ በመሆናቸው ቡድናችን በጣም ተጠናክሯል ብዬ አምናለሁ ስለወጡት ተጨዋቾ ምንም ባልልህ እመርጣለሁ /ሳቅ በሳቅ/

ሀትሪክ፡- ውድድሩ ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ይባላል ገንዘብ ማምጣትም ሊጀመር ነው ዴኮ እዚህ ላይ ምን ይላል?

ሙላለም፡- በዚህ ረገድ ሊግ ካምፓኒው በጣም ሊመሰገን ይገባል፡፡ ለሀገሪቱ እግር ኳስ ትልቅ እገዛ እያደረጉ እንዳለ ይሰማኛል፡፡ እግር ኳሱ በፌዴሬሽኑ ረጅም ጊዜ በተመራበት ወቅትን እንኳን እንደዚህ አይነት ሃሣቦች ሲታሰቡ ሰምተን አናውቅምና ካምፓኒውን አመሰግናለው፡፡ ሌላው ቢቀር ሌሎች ውሣኔዎችው ሲወስን ሚዛናዊ ሆኖ በመሆኑ ለውጡ ደስ ይላል፡፡ ሊጉ ትኩረት እንዲያገኝ ያደረገበት መንገድም የሚያስመሰግነው ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ለተጨዋቾች ትልቅ መነሳሳት ይፈጥራል፡፡

ሀትሪክ፡- በዲ.ኤስ.ቲቪ ሊተላለፍ መሆኑ የሚፈጥረው በጎ ገፅታስ ምን ይመስላል?

ሙላለም፡- ይሄ የሊግ ካምፓኒው ትልቅ ስራ ነው በመላው አለም ያሉ ተመልካቾች ሊያዩት ነው፡፡ የሌሎች ሀገራት የክለብ አመራሮች የሚፈልጓቸው ተጨዋቾችን የማየት እድል ሊኖር ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ለኛ ትልቅ መነሳሳትን ይፈጥራልና ተደስቻለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ምን ታልማለህ?

ሙላለም፡- 3 አመት ዋንጫ አጥተናል የዚህ መጥፎ ታሪክ አካል መሆኔን ለመሻር የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ በቁጭት ተነሳስተናል ሁሉም ውስጥ ቁጭት ስላለ ዘንድሮ ሻምፒዮን ለመሆን የሚከብደን አይመስለኝም፡፡ ከክልል ክልል ስንሄድ ዳኛ ላይ የነበረው ጫና ቀርቷል፡፡ ቡድን ላይ ተጨዋች ደጋፊ ላይ የሚኖረው ጫና አለመኖሩ ብዙ ነገሮችን ያቀላልና ሻምፒዮን ሆነን እንጨርሳለን፡፡ ዘንድሮ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ዋንጫ መውሰድ ቀላል ነው፣ ከዋንጫው ይልቅ ያለ መውረድ ፉክክሩ ከባድ ይሆናል፡፡ በግል ደግሞ በተደጋጋሚ የኮከብ ተጨዋች ምርጫ ላይ ስሜ ሲጠራ ቆይቷል፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ኮከብ ተጨዋች ለመሆን አልማለሁ፡፡ ከዚያ ባለፈ ምክንያቱን በማላውቅበት መንገድ ከብሔራዊ ቡድን ውጪ ነኝና ተመልሼ ብሔራዊ ቡድኑን ማገልገል እፈልጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ለብሔራዊ ቡድኑ አለመመረጥህ ቆጭቶሃል..? ለዋሊያዎቹ የሚመጥን አቋም አለኝ ብለህ ታምናለህ?

ሙላለም፡- ለብሔራዊ ቡድኑ የሚመጥን ብቃት አለኝ በዚህ ርግጠኛ ነኝ አንዳንዴ ግን አቅምህ የተጠበቀውን ያህል ላይሆን ይችላል፡፡ በዓለም እግር ኳስ ላይም የሚከሰት ነው በኔ ግምት ለብሔራዊ ቡድን ያልተመረጥኩት አቋሜ ወርዶ ነው ብዬ አላምንም… አሰልጣኙ የፈለገውን መምረጥ መብቱ ነው… ይህን አከብራለሁ… በእኔ በኩል ግን በተቻለ አቅም ላይ ተገኝቼ ወደ ቡድኑ መመለስ እፈልጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናል የምትለው ክለብ ማነው?

ሙላለም፡- ሁሉም ገና እየዘጋጀ በመሆኑ ይሄ ነው ተፎካካሪ ማለት ይከብዳል በተለምዶ መቐለ 7ዐ እንደርታና ፋሲል ከነማ ነበሩ… መቐለ አሁን በተፈጠረው አገራዊ ችግር በውድድሩ ላይ ባለመኖሩ ፋሲል ከነማ እንደተለመደው ይፎካከራል ብዬ አስባለው… ከዚያ ውጪ ቻሌንጅ ያደርገናል የምለው ቡድን የለም፡፡

ሀትሪክ፡- ሶስቱ የትግራይ ክልል ክለቦች ከሊጉ መውጣታቸው ውድድሩ ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል ማለት ይቻላል?
ሙላለም፡- ብዙም ተፅዕኖ ያመጣል ብዬ አላስብም… በርግጥ ቢኖሩ መልካም ነው… አለመኖራቸው ግን ያን ያህል የሚያጎለው ነገር ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡

ሀትሪክ፡ -ከ13 የሊጉ ክለቦች 3 ወራጅ መሆኑ ፉክክሩን ከባድ አያደርገውም?

ሙላለም፡- … ይሄ ጥያቄ የለውም 3 ወራጅ መሆኑ ከባድ ነው ሁሉም ቡድን የግድ መጠንቀቅ አለበት፡፡

ሀትሪክ፡- ከቅዱስ ጊዮርጊስ በዘንድሮ የውድድር አመት ጎልቶ ይወጣል ብለህ የምታስብው ማነው?

ሙላለም፡- አቤል ያለው ጎልቶ የሚወጣ ይመስለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ጨዋታው በዝግ መካሄዱና ከደጋፊዎቻችሁ ጋር አለመገናኘታችሁ ምን አይነት ስሜት ፈጠረብህ?

ሙላለም፡- ምንም ማድረግ አንችልም አለመኖራቸው ቡድኑ ላይ የሚያጎድለው ነገር ይኖራል ደጋፊዎቻችን ከ12…13…14 ተጨዋቾችም በላይ ናቸውና አለመኖራቸው የሚፈጥረው ክፍተት አለ ቢሆንም ግን ውስጣችን ያለው ቁጭት የተፋፋመና ደጋፊውን ለመካስም የምንፋለም በመሆኑ እጅ አንሰጥም በሌላ በኩልም ሁሉም በዲ.ኤስ.ቲቪ በቀጥታ ስለሚያይ አብሮን እንዳለ እንዲሰማን ያደርጋል፡፡ መንግሥትም ሁኔታውን አይቶ ለተወሰነ ደጋፊዎች የሚፈቅድ በመሆኑ በተወሰነ መልኩ የነርሱን ድጋፍ እናገኛለን ብዬ አምናለሁ፡፡ ደጋፊዎቻችን ግን ሁሌ ከኛ ጋር በመሆናቸው አንከፋም… ክልል ላይ ሄደን በስልክ ላይቭ የሚከታተሉ ደጋፊዎች ናቸው ያሉንና ሁሌም ከጎናችን እንዳሉ አድርገን ነው የምንፋለመው፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport