“በዚህ ጦርነት አንድም ሰው መሞት የለበትም ብዬ አምናለሁ” አሚን ነስሩ /መቐለ 70 እንደርታ/

“ቤተሰብ ሲጨነቅ መምጣት ፈለግን እንጂ በመቐለ ስጋት አልነበረብንም”

“በዚህ ጦርነት አንድም ሰው መሞት የለበትም ብዬ አምናለሁ”
አሚን ነስሩ /መቐለ 70 እንደርታ/


ተወልዶ ያደገው ነጋዴው ህብረተሰብ በሚኖርበት ኮልፌ አጠና ተራ ነው…ከዚያ ማህበረሰብ ወጥቶ ግን የበርካታ ኢትዮጵያኖችን ልብ የገዛው እግር ኳስ ልቡን ማርኮት ፊቱን ወደዚህ ሙያ አዙሯል፡፡ በጅማሮው ቤተሰቦቹ ድጋፋቸውን ቢነፍጉትም የማታ ማታ ውጤቱን እያዩ ሲሄዱ ሙሉ ድጋፋቸውን ለግሰውታል፤ በተለይ ከሀገር ውጭ ያለው ታላቅ ወንድሜ ትልቅ ድጋፍ ያደርግልኝ ነበር ሲል ያመሰግናል፡፡ በዚህ ቤተሰብ ውስጥ ሌላ ታሪክ አለ፡፡ እንግዳችን የመቐለ 70 እንደርታ ተጨዋች የሆነው አሚን ነስሩ ኢትዮጵያ ቡናን ሲፋለም ልዩ ስሜት አለው፡፡ ታናሽ ወንድሙ ፉአድ ነስሩ የቡናማዎቹ ማሊያ አጥልቆ ሊፋለመው ወደ ሜዳ ሲገባ ልዩ ስሜት ይፈጥርብኛል ይላል ይሄ የደርቢ ቤተሰብ ቢባል ይቀላል፡፡ አሚን ነስሩ በቡና ቢ ቡድን ውስጥ 3 አመት ከቆየ በኋላ ወደ ሱሉልታ ከተማ አቅንቷል፡፡ በኢትዮጵያ ቡና የሚያውቀው አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ወደ ሱልልታ ከሱሉልታ ደግሞ ወደ ሀዲያ ሆሳዕና ሲጓዝ አሚን ነስሩን አስከትሎ ነበር፡፡ ከሀዲያ ሆሳዕና የጅማ አባጅፋሩ ገ/መድህን ኃይሌ ካምፕን ተቀላቀለ ተራው የገ/መድህን ሲሆን በጅማ በሊግ ዋንጫ ያጠናቀቀውን የውድድር አመት ከጨረሰ በኋላ ወደ መቐለ 70 እንደርታ ሲያቀና አሚን ነስሩን ትቶ መሄድ አልፈለገም በጅማ አባጅፋር በድል ያሸበረቁት ሁለቱ በ2011 በመቐለ 70 እንደርታ እንደገና በፕሪሚየር ሊግ ድል ደመቁ፡፡ በ2005 በቡና ቢ ማሊያ የጀመረው የተጨዋችነት ጅማሮም 9 አመት ሲሞላው በስኬትና በጥሩ ድል ነው ሲል እንግዳችን አሚን ነስሩ ይናገራል፡፡ ከሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበረው ቆይታ ለተነሱለት በርካታ ጥያቄዎች ምላሹን ሰጥቷል፡፡


ሀትሪክ፡- ተወልደህ ያደከው ኮልፌ አጠና ተራ ነው እዚያ ነጋዴ እንጂ ኳስ ተጨዋች ያለ አይመስለኝምና… እንዴት ሆነ?

አሚን፡- /ሳቅ/ እውነት ነው ነጋዴ ነው የሚበዛው፤.. ከእኛ ሠፈር ከፍ ብሎ አንድ ሜዳ አለ.. ክለብ የሚጫወቱ ልጆች ሄደው ሲጫወቱ ከእነርሱ ጋር አብሬ ሄጄ ስጫወት የኳሱ ፍቅር ውስጤ ገብቶ ቀረ እልሀለሁ.. አሁን በዚህ ሙያ ደስተኛ ነኝ በአካባቢችን እነ ፈቱ አብደላ… ኤሊያስ ጫካን የመሳሰሉ ተጨዋቾች መኖራቸውም ኳሱን እንድወድ አድርጎኛል፡፡

ሀትሪክ፡- የአንተ ምርጡ አሰልጣኝ ማነው?

አሚን፡- ስኬታማ ቆይታ የነበረኝ በተለይ ከአሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ ጋር ነው 2 አመቱ የውጤት ነበር፡፡ የደስታ ጊዜም አሳልፌያለሁ.. ለኔ ምርጡ ገ/መድህን ኃይሌ ነው፡፡ ጳውሎስ ጌታቸው ጋርም ጥሩ ጊዜ ነበረኝ በሁለቱ ደስተኛ ነኝ፡፡ በነገራችን ላይ በሀድያ ሆሳዕናም ጥሩ ጊዜ አሳልፌያለሁ፡፡

ሀትሪክ፡-አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ ጨምሮልኛል ብለህ የምታምነው ምንድነው?

አሚን፡- አሰልጣኝ ገ/መድህን ትልቅና ጎበዝ አሰልጣኝ ነው በትክክል መጫወት ያለብኝ እንዴት እንደሆነ ያወኩት በእርሱ ነው፡፡ እስኪመርም ሆነ የመሀል ተከለካይ አድርጎ ያጫወተኝ እርሱ ነው በዚህም ላመሰግነው እፈልጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ከቡና ቢ ውጪ ለዋናው ቡድን አልተሰለፍክም?

አሚን፡-ለኢትዮጵያ ቡና በቢ እና በተስፋ ደረጃ ለ3 አመት ተጫውቻለሁ.. ለዋናው ቡድን በአሰልጣኝ ጰውሎስ ጌታቸው ስር ወደ 2 የሚጠጉ የሲቲ ካፕ ጨዋታዎችን አድርጊያለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- በቦታህ ያንተ ምርጡ ተጨዋች ማነው?

አሚን፡-የምጫወተው 2 ቦታ ነው፡፡ እስኪመርና የመሀል ተከላካይ ሆኜ ተጫውቻለው በመሀል ተከላካይ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አስቸለሁ ታመነ የተሻለ ተጨዋች ይመስለኛል… ከውጪ የሪያል ማድሪዱ ሰርጂዮ ራሞስ ምርጫዬ ነው፡፡ በስኪመር ቦታ በሀገር ውስጥ አብሬው የተጫወትኩትን ይሁን እንዳሻውን እመርጣለሁ፤ በውጪ ደግሞ ፖል ስኮልስ ምርጫዬ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- አሚን ለብሔራዊ ቡድን የመጫወት እድል አግኝቷል?

አሚን፡- በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ጊዜ ለኦሎምፒክ ቡድን ጠርቶኝ ነበር፡፡ በፊት ቡና ቢ እያለሁ ፓስፖርቴን ሳወጣ እድሜ ጨምሬ ነበርና አሠልጣኙ ጠርቶኝ ፓስፖርቴን ልኬለት ሲመለከተው ይሄማ መስተካከል አይችልም እድሜው አልፏል ብሎ ቀረሁ፡፡ አሁንም ግን ሀገሬን የማገልገል ህልሙ አለኝ የፈጣሪ ፍቃድ ታክሎበት እንደሚሳካ ተስፋ አደርጋለሁ ለብሔራዊ ቡድኑ ለመጫወት ደርሻለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከተወሰኑ የመቐለ 70 እንደርታ ተጨዋቾች ጋር ከመቐለ ተነስታችሁ በአፋር ሰመራ በኩል አዲስ አበባ የገባችሁትና ኳስ መጫወት ተቸግራችሁ ነበር እንዴ?

አሚን፡- እስክንመጣ ድረስ ልምምድ አላቋረጥንም ሰኞ ማታ ልንነሳ ጠዋት ላይ ልምምድ ሰርተናልኮ እንደሚወራውማ አይደለም፡፡ የደረሰብን ችግር የለም ሰልክ ስለሌለና መገናኘት ስላልቻልን ቤተሰብ ሲጨነቅ መምጣት ፈለግን እንጂ ስጋት አልነበረንም እየተዘጋጀን ነበር ምንም የተስተጓጎለ ነገር የለም ይሄ ነው እውነቱ… ቤተሰብ ሲጨነቅ መምጣት ፈለግን እንጂ በመቐለ ስጋት አልነበረብንም አሁንም ስልክ አይሰራም ምንም አይነት ግንኙነት የለንም፡፡

ሀትሪክ፡- በሻምፒዮንስ ሊግ የመካፈል እድሉ አለ እንዴ? አንካፈል ይሆን ብለህ አልሰጋህም?

አሚን፡- የሆነ ፌስቡክ ላይ ያየሁት ነገር ነበር ለካፍ ደብዳቤ ተልኮ አዲስ አበባ ያሉት ይጫወቱ ተብሎ ተጠይቋል ይሳካ አይሳካ ባላውቅም ይሄ ተስፋ ያለው ይመስለኛል… አዲስ አበባ ያለነው ከአማኑኤል ገ/ሚካኤል ጋር 12 ነን ከተፈቀደ ጥሩ ይመስለኛል ሁሉም በየራሱ ከልምምድ ስላልተስተጓጎለ መጫወት እንችላለን ብለን ስለምናሳብ ባይሳካ ቅር ያሰኛል ግን አገራዊ ችግር በመሆኑ ምን ማድረግ ይቻላል አምናም ተሳትፈን ነበር የዛን አመት ቁጭት ለማስተካከል አስበን የነበረ ቢሆንም ያው በሀገር የመጣ በመሆኑ መቀበል የግድ ይላል፡፡ በዚያ ላይ ግን ሊግ ካምፓኒው ምን አስቦ እንደነበር ባናውቅም አንካፈልም ማለቱ ይገርማል… ያ ሁሉ አልፎ አሁን ይሄ ችግር መከሰቱ ግን ቅር ያሰኛል ብንሳተፍ ግን አሪፍ እድል መሆኑ ይሰማኛል፡፡ /ከዚህ ቃለ ምልልስ በኋላ ግን ሲሞከር የነበረው ሙከራ ከሽፎ ካፍ ከ14 ተጨዋች በታች አልቀበልም በማለቱና ለጨዋታው ዝግጁ የሆኑት ተጨዋቾች 11 ብቻ በመሆናቸው የመቐለ 7ዐ እንደርታ በሻምፒዮንስ ሊግ እንደማይሳተፍ ተረጋግጧል፡፡/

ሀትሪክ፡- ፕሪሚየር ሊጉ ሊጀመር 17 ቀን ይቀረዋል (ቃለ ምልልሱ የተደረገው ረቡዕ ጠዋት ነው) ያለመጫወት ስጋት የለብህም?

አሚን፡- በእርግጥ በቡድንና በግል የሚሰራው ይለያያል ያም ሆኖ በግል እየሰራን እንጠብቃለን ልጆቹም እየሰሩ ይቆያሉ ብዬ አምናለሁ ወደፊት የሚሆነውን አብረን እናያለን፤ ውድድሩ ላይ እንሳተፋለን ብዬ ተስፋ አደርጋሁ፡፡

ሀትሪክ፡-ከተጨዋቾቹ ጋር የመገናኘት እድል አልተፈጠረም በተለይ አዲስ አበባ ከመጣህ በኋላ?

አሚን፡-ምንም አይነት ግንኙነት የለንም ስልክም አይሰራም ስልክ ካልሰራ ደግሞ በምን መረጃ ትለዋወጣለህ? ስልክ ቢኖርማ ተደዋውለንም ይመጡ ነበር፡፡

ሀትሪክ፡- ከአመራሮቹስ ጋር ግንኙነት ነበራችሁ?

አሚን፡-አዎ ቅርብ ጊዜ ድረስ ይመጡና ያዩን ነበር በሻምፒዮንስ ሊግ እንደምንሳተፍ አይነት ነገር ነበር ይናገሩ የነበሩት… እንደዚህም ይከራል ተብሎ አልተጠበቀም ስምምነት ይፈጠራል የሚል ተስፋ ነበራቸው በኋላ ግን ሳይቻል ቀርቷል፡፡

ሀትሪክ፡- ኳሱ ውስጥ ዘርና ፖለቲካ መግባቱ መድረኩን አላበላሸውም?

አሚን፡- ሲጀመር ኳስና ፖለቲካ አይገናኝም፤ ከእግር ኳስ ፍልስፍና ጋርም ይቃረናል፡፡ ሁለቱ ፅንፍ ያሉ ነገሮች መገናኘትም አልነበረባቸውም በሀገራችን እግር ኳስ አምና ይሻል ነበር ደጋፊውም የክለብ አመራሮችም ተነጋግረው ጥሩ ስሜት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ያው ኮቪዱ ነው ያቆመው አምና ዘረኝነቱ ጠፍቶ ነበር ማለት ይቻላል፤ ባህርዳር ስንሄድ የሞቀ አቀባበል ነበረን፡፡ ፋሲል መቐለ መጥቶ መቐለ 70 እንደርታን አሸንፎ በሠላም ሄዷል ይሄ ትልቅ ለውጥ እንደነበር ያሳያል፡፡

ሀትሪክ፡-ዘንድሮ ግን በዝግ በመካሄዱ የረብሻ ስጋት የለም…?

አሚን፡- አዎ፤… ስጋት የለውም /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- እንደውም ስጋት የሚሆነው በዝግ ሲሆን ተጨዋቾቹ እርስ በርስ ስትሰዳደቡ እንዳይሰማ ነው አይደል?

አሚን፡-/ሳቅ በሳቅ/ እሱ ነው ስጋቱ? /ሳቅ በሳቅ/ ያኮ ያስፈራል.. የዘረኝነት ስጋት አለመኖሩ ጥሩ ቢሆንም ያለተመልካች መጫወትን የመሰለ ደባሪ ነገር ልንጋፈጠው ነውኮ መቐለ ያን ሁሉ ደጋፊ መሃል ተጫውተን አሁን ያለደጋፊ ነው ሲባል ይከብዳል፡፡

ሀትሪክ፡-በዲ ኤስ.ቲ.ቪ ከታየ ግን አሪፍ እድል ነው አይደል?

አሚን፡-አዎ ምርጥ እድል ነው በርታቶ ለሚጫወት ተጫዋች መልካም እድል ነው ከሀገር ወጥቶ ለመጫወትም ሰፊ እድል ይፈጥራል ይሄ ይመቻል ዳኛውም ሆነ ተጨዋቾቹ ስህተታቸውን እንዲቀንሱ ያደርጋል ብዬ አምናለሁ ከሜዳ ውጪ እና በሜዳ የሚባል ነገር የለም፡፡

ሀትሪክ፡- ከ50 ሺ ብር በላይ የሊጉ ተጨዋቾች ክፍያ መብለጥ የለበትም መባሉን እንዴት አየኸው?

አሚን፡-ደስ አይልም ቋሚ ቤንች እያልክ ስትሄድ ለውጡ አይለይም አሰራሩ ቢስተካከል ደስ ይለኛል ለኳሱ ለውጥና እድገት አይጠቅምም፡፡

ሀትሪክ፡- ከ2014 ጀምሮ ሁሉም በአቅሙና በደረጃው ይከፈለው የድርድሩ ሂደት የግል ነው በሚል ደንቡ እንዲሻር ተወስኗል?

አሚን፡-ይሄ ደስ የሚል ዜና ነው.. በራስህ አቅምና የመደራደር ብልጠት የሚወሰን መሆኑ ደስ ይላል፡፡ አከፋፈሉን ክለቦችና ተጨዋቹ ራሱ በተለያየ መንገድ ስለሚያስተካክሉት ጥሩ ይመስለኛል

ሀትሪክ፡-50ሺ፣ 75ሺ 100ሺ ብር… የየትኛው የደመወዝ ክፍያ ይመጥንኛል ትላለህ?

አሚን፡-/ሳቅ/ የ50ሺው ነኛ /ሳቅ/ ያው 34 ሺ የሚደርሰው ስብስብ ውስጥ ነኝ /ሳቅ/

ሀትሪክ፡-ለኢትዮጵያ ቡና የሚጫወተው ፉአድ ነስሩ ወንድምህ ነው?

አሚን፡-ታናሽ ወንድሜ ፉአድ ጎበዝ ተጨዋች ነው፡፡ ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን አምበልም ነበር ቤታችን ደርቢ ሆኖልሃል….

ሀትሪክ፡- መቐለ 70 እንደርታና ኢትዮጵያ ቡና ሲጫወቱ ቤተሰባችሁ ጋር የነበረው ስሜት ምን ይመስል ነበር?

አሚን፡- /ሳቅ/ ከባድ ስሜት ነው… ቤተሰብ የሚፈልገው በአቻ ውጤት እንዲጠናቀቅ ነው ለይተው የሚደግፉት ቡድን አይኖርም አምና 1ለ1 ነው የተለያየነው… ደስተኛም ነበሩ /ሳቅ/

ሀትሪክ፡-ከሀገር ውጪ አሚን የማን ደጋፊ ነው?

አሚን፡- የማን.ዩናይትድ ደጋፊ ነኝ

ሀትሪክ፡-ማን.ዩናይትድ እንደስሙ ነው ማለት ይቻላል?

አሚን፡- አይደለም ከፈርጊ በኋላኮ ወርዷል ያ አስፈሪነቱ የለም ጥሩ አይደለም ደግፈን ደግፈን እንቢ ሲለንኮ ወጣልን ዝም ብዬ ውስጤ ስላለ ኳስ አያለሁ እንጂ ብዙም አይደለሁም፡፡

ሀትሪክ፡-ገና በጥቂት አመት ትማረራለህ.. የሊቨርፑል ደጋፊዎች 30 አመት የአርሰናል ደግሞ ወደ 16 አመት ሞላቸው ደጋፊዎቹ ግን አልተማረሩም…አንተ ታዲያ ምነው?

አሚን፡- /ሳቅ በሳቅ/ አሁንኮ 7 አመት አካባቢ ሞላን፡፡ እኛኮ አልለመድነውም ለዚያ ነው የመረረን፡፡

ሀትሪክ፡-ያው ትለምደዋለህ?

አሚን፡-/ሳቅ/ አሁንማ ለመድነው /ሳቅ/

ሀትሪክ፡-መዝናኛህ ምንድነው?

አሚን፡-ፊልም ማየት ደስ ይለኛል ግን አብዛኛውን ጊዜ መቐለም ሆነ አዲስ አበባ ቤት ውስጥ ነው የማሳልፈው፡፡

ሀትሪክ፡- የኮቪድ 19 መነሻ ቀን ጀምሮ ለ7 ወራት እግር ኳስ አልነበረምና እንዴት አለፈልህ?

አሚን፡- በርግጥ ከባድ ጊዜ ነበር… የሚያስፈራና የሚያሰጋ ጊዜ ነው ያሳለፍነው..በእርግጥም አታግሎናል.. ከዚያ ውጪ ያንን ክፉ ጊዜ ከወንድሜ ጋር ልምምድ እየሰራሁ አሳልፌያለሁ 35 ሜዳ እየሄድን ፉትሳል እንሰራ ነበር፡፡

ሀትሪክ፡-የኮትዲቯሩ ዲዲየር ድሮግባ በአገሪቱ ቴሌቪዥን ጥሪ አድርጎ ጦርነት ላይ የነበሩት የመንግሥትና የተቃዋሚዎች ወታደሮች ጦርነቱን በተኩስ ማቆም ስምምነት እንዲፈቱ አድርጓል፡፡ ይህን ማድረግ የሚችል እግር ኳስ ተጨዋች አለን ብለህ ታምናለህ?

አሚን፡- አይታሰብም.. የሚኖርም አይመስለኝም ህዝቡም በዚህ ደረጃ የሚወደው አለ ብዬ አልገምትም፡፡
ነገር ግን ከዚያም በላይ ተፅዕኖ ያላቸው ሰዎችም ሞክረውኮ አልተሳካላቸውም ጦርነቱን ማስቆም አልቻሉም፡፡

ሀትሪክ፡-በእግር ኳስና በአትሌቲክስ ዝና ማማ ላይ ወጥተው በዚህ መሰል ችግር ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ሰዎች የሉንም…. ይሄ ቅር አያሳኝም?

አሚን፡-ሁኔታው እንደየሀገሩና እንደ ህዝቦቹ ይወሰናል የሚቀበልህና የማይቀበልህ ሊኖር ይችላል… የፖለቲካውም ሁኔታ ከባድ በመሆኑ ሂደቱን አስቸጋሪ ያደርገዋል በዚያ ላይ ስፖርትና ፖለቲካ አይገናኙም፡፡

ሀትሪክ፡-ለሁለቱም ወገኖች የምትለው ነገር አለ?

አሚን፡- ጦርነት የሚፈልግ ማንም የለም ሁሉ ነገር ሰላም ቢሆን የሚጠላ አለ ብዬ አላምንምና ሁሉም ወገን ሠላሙን መፈለግ አለበት አንድም ሰው መሞት የለበትም ብዬም አምናለሁ፡፡
ሀትሪክ፡-አገባህ አሉኝ… ትዳር እንዴት ይዞሃል?
አሚን፡-በቅርቡ ነው ያገባሁት.. ወደ 10 ወር ይሆነኛል ባለቤቴ ሀያት ኑረዲን ትባላለች

ሀትሪክ፡-ታዲያ በ7 ወር የኮቪድ የጫና ጊዜ ላይ እኔ ምርጥ የሃኒሙን ጊዜ ላይ ነኝ አትለኝም?

አሚን፡- /ሳቅ በሳቅ/ እውነት ነው አልደበረኝም ጥሩ ጊዜ ነበረን ከባለቤቴ ጋርም ጥሩ የቅርበት ጊዜ ነበረን ልምምድ ሳቆም ቀላ ወፈር ብዬ ተስማምቶኝ ነበር/ ሳቅ/

ሀትሪክ፡-ጨረስኩ… የምታመሰግነው ካለ?

አሚን፡- የምወዳቸውን ቤተሰቦቼን፣ ባለቤቴን ሀያት ኑረዲንን፣ ጓደኞቼን፣ አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌና አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸውን እንዲሁም ያሰለጠኑኝን አሰልጣኞች፣ የመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊዎችንና በእኔ ነገር ላይ ድጋፍ ያደረጉትን በሙሉ አመሰግናለሁ፡፡

ስለ አባይ
ኢትዮጵያዊ ነኝኮ በአባይ ካልተደሰትኩ በምን ልደሰት? የግድቡ የመጀመሪያ ደረጃ ውሃ ሙሌት ዜናኮ ልዩ ስሜት ይፈጥራል በዚህም ደስተኛ ነኝ የሀገር ህልውና መሰረት በመሆኑና እዚህ ደረጃ በመድረሱ ደስ ብሎኛል በአባይ ግድብ የማይደሰት አለ ብዬ አላምንም፡፡ በ8100A ተሳታፊ ነኝ ት/ቤት ሆኜ ሳይቀር ቦንድ ገዝቻለሁ የበኩሌን አስተዋፅኦ አድርጌያለሁ ለወደፊቱም አደርጋለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡

ስለ ኮሮና
ለዚህ የጦርነት ዜና ትኩረት ስንሰጥ ኮቪድ 19 ላይ የተዘናጋን ይመስለኛል በሽታው ግን አልጠፋም አለ መዘናጋት የለብንም አለም ላይ በድጋሚ ማገርሸቱ እየተገለፀ ነውና የባሰ እንዳይሰፋ መጠንቀቅ አለብን አብዛኛው ሰው ሌላ ለተጨማሪ በሽታ ያለባቸውን ብቻ ነው የሚገለው እያለ መዘናጋት ውስጥ ገብቷል ልክ ግን አይደለም የማስታውሳቸው ወጣቶችም አልቀዋልና መዘናጋት የለብንም የጤና ባለሙያዎች ምክር ልንሰማ ይገባል እላለሁ፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport