የከፍተኛ ሊግ የምድብ ድልድል ፌዴሬሽኑና ክለቦችን አጋጭቷል

የከፍተኛ ሊግ የምድብ ድልድል በክለቦችና በፌዴሬሽኑ መሀል ውዝግብ የፈጠረ ሆኗል፡፡

የፌዴሬሽኑ የከፍተኛ ሊግ ውድድር አዘጋጅ ኮሚቴ ከወራት በፊት በተሰጠው ማንዴት የከፍተኛ ሊግ ክለቦችን በ3 ምድብ ደልድሎ በማዘጋጀት ለክለቦች ባቀረበበት ሰዓት ከፍተኛ ክርክር ተነስቷል፡፡ በምድብ 2 የነበረው የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ ወደ ምድብ አንድ እንዲዞር ሲደረግ በዚህ ምድብ የነበረው አቃቂ ቃሊቲን ወደ ምድብ 2 እንዲቀየር የተደረገበት ውሣኔ የክለቡን ተወካይ አበሳጭቶ ፕሮግራሙን ረግጦ እንዲወጣ አድርጎታል፡፡
ውድድሩ ከተዟዙሮ ይልቅ በአንድ ከተማ ውስጥ እንዲሆን መደረጉ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በመሆኑ ቅሬታ ባይቀርብበትም መከላከያና አቃቂ ቃሊቲ ምድብ እንዲቀያየሩ የተደረገበት የከፍተኛ ሊግ የውሣኔ ሃሣብ ቁጣ ቀስቅሷል፡፡

በተለይ በ2012 በአንድ ምድብ ተደልድሎ ከነቀምት ከተማ ጋር ፍልሚያ የገጠመውና በደረጃ ሳይቀር ተመርቶ የነበረው መከላከያን እነ ኢትዮ-ኤሌክትሪክና ደደቢት ወዳሉበት ምድብ እንዲገባ መደረጉ ክለቡን ከመጥቀም ውጪ ሌላ ምንን ምክንያት አይኖረውም በሚል ቅሬታ ቀርቦበታል፡፡

የከፍተኛ ሊግ አዘጋጅ ኮሚቴ 6 አባላት ያሉት ሲሆን ዋና ሰብሳቢውና የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ አሊሚራህ መሀመድ ግን “የተለየ ምንም አጀንዳ የለውም” ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ “በተሰጠን ማንዴት መሰረት ስራዎችን ሰርተናል ማንንም የመጥቀምም ሆነ የመጉዳት አላማ የለንም ከፋይናንስ ጥንካሬ አንፃር መከላከያ የተሻለ በመሆኑ ወደ ምድብ አንድ እንዲገባ አድርገናል ከዚህ በተጨማሪ በወቅቱ ከነበሩ 29 ክለቦች መሀል 23ቱ በድምፅ ብልጫ ምድቦቹ ባለበት እንዲቀጥል ወስነው የምንወቀስበት ምክንያት ሊኖር አይገባም” ሲሉ ይከራከራሉ፤ ቅሬታ አቅራቢዎቹ አቃቂ ቃሊቲ ከፍተኛ ወጪ በነበረበት የአምናው ውድድር ላይ ተካፍሎ ምንም የፋይናንስ ጥያቄ ሳያቀርብ ዛሬ ወጪው በሚቀንስበት መርሃ ግብር ለእርሱ የፋይናንስ ክፍተት አስበን ነው መባሉ ተቀባይነት የለውም የክለቡ ተወካይም ቅሬታውና ተቃውሞውን ያሰማበትን መንገድ ስናይ የፌዴሬሽኑ የምድብ ድልድል ሌላ አላማ አለው ብለን እንድንጠይቅ አድርጎናል የሚል አስተያየት ይሰጣሉ፡፡

በከፍተኛ ሊግ የነበረው ክርክር እግር ኳሳዊ እውቀት አላቸው ወይ የሚያስብልም ሆኗል፡፡ የእግር ኳስ ቋንቋ ምን እንደሆነ ተረድተው ይሆን የሚያስብል አመራሮችም የታዩበት ሆኗል… ለምን በቋንቋችን ደንቡ አይፃፍም፣ ጅማ የፀጥታ ችግር ስጋት አለና ወደዚያ አንጓዝም የሚሉ አስተያየቶች ግርምትን የጫሩ ሆነዋል፡፡
በጁፒተር ሆቴል በወጣው የምድብ ድልድል መሠረት በምድብ አንድ የሚገኙ 12 ክለቦች በባቱ ስታዲየም፣ በምድብ 2 የሚገኙትም 12 ክለቦች በሀዋሳ ስታዲየም እንዲሁም በምድብ 3 የሚገኙ 12 ክለቦችም በጅማ ስታዲየም ጨዋታቸውን እንዲያደርጉ ተወስኗል፡፡ የከፍተኛ ሊግ አመታዊ ውድድር የፊታችን ታህሳስ 10/2013 ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport