ሀትሪክ ሰሪው በሀትሪክ | በሸገር ደርቢ አንፀባርቆ ያበራው ኮከብ ክፍል ሁለት

ክፍል -2

በይስሐቅ በላይ

በሸገር ደርቢ ሀትሪክ በመስራት የብዙዎች ትኩረትና መነጋገሪያ የሆነው የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር ከሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ጋር ያደረገውን ቃለ-ምልልስ ትናንት(እሁድ)ማቅረባችን ይታወሳል ዛሬ ደግሞ ከትናንት የቀጠለውንና የመጨረሻውን ክፍል ይዘንላችሁ ቀርበናል።አቡበከር ናስር በክፍል ሁለት ቆይታው በደርቢው ጨዋታ ጎል ካስቆጠረ በኃላ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ባሉበት ቦታ ሄዶ ደስታውን የገለፀበትና ቢጫ ካርድ ስላየበት አጋጣሚ፣በደርቢው ጨዋታ የሠራውን ሀትሪክ ማስታወሻነቱ ለኢት.ደጋፊዎች ይሁን ስላለበትና በሌሎች ቀሪ ጉዳዮች ላይ የሚለን ይኖራል ተከታተሉን።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ባሉበት ቦታ ደስታውን የገለፀበት መንገድ ደጋፊዎቹን ስለማስቆጣቱና ቢጫ ካርድ ስላየበት አጋጣሚ

“እኔ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችም ለሁሉም ደጋፊዎች ክብር አለኝ፤ በክለብ ደረጃ ልዩነት ቢኖረንም ሀገር ስንወክል የሚደግፉኝ፣ የሚያበረታቱኝ እነሱ ናቸው፤ ጎል ካገባሁ በኋላ የቀረበኝ እነሱ ያሉበት ቦታ ሆኖ ነገሮች ተገጣጠሙ እንጂ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችን ለመተናኮል ብዬ ያደርኩት ነገር የለም፤ ለእነሱ መጥፎ አስቤ አይደለም አንዳንዴ ደስታ ውስጥ ስትሆን የምታደርገውን አታውቅም፤ ደስታ በድንገት ከውስጥህ ፈንቅሎ የሚመጣ ነው፤ ሆን ብዬ ያደረኩት ነገር እንዳልሆነ እንዲረዱልኝ እፈልጋለሁ”

በደርቢ ጨዋታ ሀትሪክ የሰራበትን ድል ማስታወሻነቱ ለማን?

“ውጤት ሲኖርም ሲጠፋም ሁሌም ከጎናችን ሆነው ለሚያበረታቱን እውነተኛ የክለቡ ደጋፊዎች ትሁንልኝ፤ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሚደረገው ጨዋታ የሀገሪቱ ትልቁ ደርቢ ከመሆኑ አንፃር ሁሉም የተለየ ትኩረት የሚሰጠው ነው፤ እነሱን አሸንፈን የምናገኘው ነጥብ ከሶስት ነጥብም በላይ ነው፤ ስለዚም ይሄን ጣፋጭ ድልና የሀትሪክ ማስታሻነት ክለቡን ከምንም ነገር በላይ አስበልጠው ለሚወዱ ው ደጋፊዎቻችን ትሁንልኝ፡፡”

 

አሁን በሊጉ አናት ላይ መገኘታቸው የ2003ቱን የፕሪሚየር ሊግ ክብር ለመመለስ እየተንደረደሩ እንደሆነ አንድ ማሳያ ይሆን? በሚል ለቀረበለት ጥያቄ?

“ብዙ ጊዜ እንደዚህ አይነት ነገር ተጠይቄያለሁ፤ የሆነች ትንሽ ነገር ስታይ ቡናን ዘንድሮ የሚያቆመው የለም ሻምፒዮን ይሆናል እላለሁ፣ የዘንድሮው ግን ከእስከዛሬው ሁሉ የተለየ ነው፤ ምክንያቱም ነጥብ በጣልንባቸው ጨዋታዎች በሙሉ በልጠን ነው በሀዋሳም፣ ወልቄጤን 2ለ0 ስንመራ ቆይተን አቻ በወጣንበት ጨዋታም በልጠናቸዋል፤ ፋሲልንም አንድ ተጨዋች ወጥቶብን በልጠን ነው ያሸነፍናቸው፤ በአጠቃላይ ውጤት ያጣንባቸውን ጨዋታዎች ስታይ በልጠን ነው… ከዚህ አንፃር ስታየው ዋንጫ ማንሣትን እንድታስብ ያደርግሃል፤ አሰልጣኛችን የሚለንን ሜዳ ላይ የምንተገብር ከሆነ ዋንጫ ላናነሳ የማንችልበት ምንም ምክንያት አይኖርም ብዬ ነው የማምነው፤ ካሳዬ ይዞት የመጣው ነገር አስተሳሰቡ ዋንጫ እናነሳበታለን ብለን ስለምናምን የሚሳካልን ይመሰለኛል፡፡

በመጨረሻ ቀረ የምትለው?

“የክለቤን ተጨዋቾች በጣም አመሰግናለሁ፤ እኔ ሀትሪክ ልስራ እንጂ የመስራቴ ምክንያት እነሱ ናቸው… እነሱ ባይኖሩና ባያግዙኝ ኖሮ እንኳን ሶስት ጎል አንድም ማስቆጠር አልቻልም.. ስለዚህ እነሱን በጣም ማመስገን እወዳለሁ፤ ኮቹንና የኮቺንግ ስታፉን በሙሉ እንዲሁ ማመስገን እፈልጋለሁ፤ ደጋፊው ምስጋና ቢያንስበትም ስኬታማ እየሆንን ያለነው በእነሱ ድጋፍ፣ ሞራል ነው እና እነሱንም በተመሳሳይ አመሰግናለሁ፤ ከውጪ ሆነው ሁሌም የሚያበረታቱኝ፣ ልምዳችውን የሚያካፍሉኝ እነ መስዑድ መሐመድ፣ ኤልያስ ማሞ፣ ኤፍሬም ወንደሰንን በዚህ አጋጣሚ ባመሰግናቸው ደስ ይለኛል ምክንያቱም ያበረታቱኛል፣ ይመክሩኛል፤ ስለዚህ እነሱም ምስጋና ይገባቸዋል፡፡”

ክፍል አንድን ለማንበብ ሊንኩን ይጫኑ 👇

ሀትሪክ ሰሪው በሀትሪክ | በሸገር ደርቢ አንፀባርቆ ያበራው ኮከብ

 

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.