ክፍል አንድ
በይስሐቅ በላይ
ተጠባቂው የሸገር ደርቢ በኢት.ቡናና በአቡበከር ናስር የበላይነት ተጠናቋል፤ የውጤት ሰሌዳውም ግብ ጠባቂው ማታሲ ጥፋት ሰርቶ በቀይ ካርድ በመውጣቱ በ10 ልጅ ለመጫወት የተገደደው ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ ቡና የ3ለ2 መራራ ሽንፈትን መጎንጨቱን ያሳብቃል፡፡ ሶስት ጎል በማስቆጠር ሀትሪክ የሠራው አቡበከር ናስር በደርቢው ጨዋታ ከሁሉም ከፍ ብሎ ታይቷል፡፡ የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዴተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ በደርቢው ጨዋታ ያንፀባረቀውን ኮከብ ከደስታ ስሜት ውስጥ ሳይወጣ ሀትሪክ ሰሪውን አቡበከር ናስርን የሀትሪክ ጋዜጣ እንግዳ አድርጎ ከዚህ በታች ባለው መልኩ አቅርቦታል፡፡
በደርቢው ጨዋታ ሶስት ጎል በማስቆጠር ሀትሪክ መስራቱ ስለፈጠረበት ስሜት
“በእንደዚህ አይነት የደርቢ ጨዋታ ላይ ሶስት ጎል ማስቆጠር (ሀትሪክ መሥራት) አይደለም ተሰልፎ መጫወት እራሱ ትልቅ እድል ነው፤ ይሄ በራሱ የተለየ የደስታ ስሜት በውስጥህ እንዲፈጠር ያደርጋል፤ ምክንያቱም ትልቅ ስም ያላቸው ክለቦች የሚያደርጉት የሀገሪቱ ትልቁ ደርቢ ነውና፡፡ እንደዚህ አይነት ከፍ ያለ ጨዋታ ያውም የሀገሪቱ ትልቁ ደርቢ ላይ ሶስት ጎል አስቆጥሬ የእግር ኳሱን ሌላኛውን ታሪኬን በማፃፌ ደስታዬን በቃላት ለመግለፅ ይቸግረኛል”
ለቡድን ጓደኞቹ የሰጠው ክሬዲት
“ጎሎቹን ያስቆጠርኩት እኔ በመሆኔ ሁሉም ምስጋናውንና አድናቆቱን ያዥጎደጉዱት ለእኔ ለብቻዬ ነው፤ ከእኔ ይልቅ መመስገንና መደነቅ ያለባቸው የቡድን ጓደኞቼ ናቸው፤ እነሱ ባያግዙኝ፣ ባይረዱኝ ኖሮ እንኳን ሀትሪክ ልሠራ አንድም ጎል አስቆጥሬ አልወጣም ነበርና፤ ሀትሪክ እንድሰራ ምክንያት የሆኑኝን የቡድን ጓደኞቼን ማመስገን እፈልጋለሁ፤ ያለ እናንተ ሀትሪክ መስራት የማይታሰብ ነው ልላቸውም እወዳለሁ፡፡

በተለየ መልኩ መልበሻ ቤት የነበረው ድባብና “ካሳዬ ጋርዲዮላ” እያሉ ስለማወደሳቸው
“ብዙ ጊዜ አሸንፈናል ተደስተናል፤ ማክሰኞ እለት ጊዮርጊስን ስናሸንፍ የነበረው የደስታ ስሜት ግን ከእስከዛሬዎቹ ሁሉ የተለየ ነው፤ ሜዳ ውስጥ፣ ከሜዳ ውጪም በመልበሻ ቤትም በጣም ነው የተደሰትነው የጨፈርነው፤ በተለይ በመልበሻ ቤት የነበረውን የደስታ ስሜትንና ድባቡን ተወው በጣም ልዩ ነበር፤ እንዳለ ስንዘምር ስንጨፍር የነበረው ለካሳዬ ነው፡፡ “ካሳዬ ጋርዲዮላ” እያልን ነበር ስንዘምርለት የነበረው፤ ካሳዬ ከዚህ በላይም ሊዘመርለት ሊጨፈርለት የሚገባው አሰልጣኝ ነው”
ጎል ካስቆጠረ በኋላ ካሳዬ አራጌ ጋር ሄዶ ደስታውን ስለገለፀበት…
“ካሳዬ የተለየ አሰልጣኝ ነው፤ ለቡና ብቻ ሣይሆን ለሀገር የሚጠቅም አሰልጣኝ ነው፤ በእርግጥ እኔ እስከ አሁን እድለኛ ነኝ ብዙ ጥሩ አሰልጣኞችን አይቻለሁ፤ ካሳዬ ግን የተለየ አሰልጣኝ ነው፡፡ ግብ ካስቆጠርኩ በኋላ እሱ ጋ ሄጄ ደስታዬን የገለፅኩት ያለኝን ክብርና ፍቅር ለማሳየት ነው፤ ካሳዬ ሁሉንም ተጨዋች በአንድ አይን ማየቱ የተለየ ያደርገዋል፤ አቡበከር ልሁን 10 ጎል ላግባ ምንም ያላገባ ተጨዋች ይሁን ሁለቱም በካሳዬ አይን ልዩነት የላቸውም፣ ሁለቱም አንድ ናቸው፤ ተጨዋች በጣም ያከብራል፤ እምነቱም ጠንካራ ነው፤ ስታጠፋ ቢያይህም መክሮ ነው የሚመልስህ እንጂ በቅጣት ሊያርምህ አይሞክርም፤ ምክሩ በራሱ ሁለተኛ እንዳታጠፋ ያደርግሃል፤ በአጠቃላይ ስብዕናው የተለየ አሰልጣኝ ነው፤ በዚህ የተነሳም የተሰለፈውም፣ ቤንች የሆነውም፣ ያልተጫወተውም ሁሉም በአንድነት የሚወዱት አሰልጣኝ ነው፤ አንድ አሰልጣኝ እንዳልተመቸህ እያወክ እየደበረህ ለይመሰል አሪፍ ነው ትላለህ… ካሳዬ ግን እንደዛ የምትለው ሳይሆን ከልብህ የምትወደውና የምትናገርለት አሰልጣኝ ነው፡፡”
ካሳዬ ጋር ስላለው ህልም
“በጣም ትልቅ ህልም አለኝ፤ እሱ እያሰለጠነን ሻምፒዮን ብንሆን በጣም ደስ ይለኛል፤ ከካሳዬ ጋር ሻምፒዮን የመሆን እድል ብናገኝ ለእኔ የ100 ድል ያህል ነው የምቆጥረው ይሄ ትልቁ ህልሜ ነው፤ ካሳዬም ይሄን ለማሳካት የሚያስችል ጥሩ ነገር እየሠራ ነው፤ በጣም የሚገርምህ አሁን በተሻለ ደረሻ ላይ መገኘታችንን ሁሉም ወዶታል፤ ግን ካሳዬ የሚፈልገውን ነገር ገና እያሳካ አይደለም፤ ከዚህ የበለጠ ነገር ለቡና ያደርጋል ብዬ ነው የምጠብቀው”

በደርቢው ጨዋታ አምስት ጎሎች ስለመቆጠራቸው
“ብዙ ጊዜ የሁለታችን የደርቢ ጨዋታ ወቀሳ ሲበዛበት ኖሯል፤ ሁሌም 0ለ0 እና በአቻ ውጤት ያለፉክክር መጠናቀቁ ብዙዎች እንደጠበቁት ሣይሆን ቀርቶ ሲበሳጩበት ታይቷል፤ ሚዲያዎችም ደካማው ደርቢ እያሉ የሚተቹት ደጋፊዎች የማይረኩበት አይነት ነበር ብል ይቀለኛል፤ የማክኞው ግን ጥሩ ፉክክር የታየበት ብቻ ሣይሆን አምስት ጎል የተቆጠረበት የደርቢም ጨዋታ ነበር፤ እኛ ስናገባ እነሱ ያገባሉ… ስንደግም ይደግማሉ… ይሄ በራሱ አጓጊ አድርጎት ነበር፤ በእነዚህ አንኳር ምክንያቶች ካለፉት ደርቢዎች ለየት ያለ ነው ብዬ አስባለሁ፤ ከአምስቱ ጎሎች ሶስቱን በማስቆጠሬ ድሉን በተለይ ለእኔ የተለየ አድርጌ እንድወስደው አድርጎኛል”
ኢትዮጵያ ቡና ሁለት ፔናሊቲ አግኝቷል በአቡኪ እይታ ፔናሊቲው ያሰጣል?
“በሚገባ… በሚገባ… ያሰጣል፤ እንኳን እኔን አይደለም የቅዱስ ጊዮርጊስን ተጨዋቾች ራሣቸውን ብትጠይቃቸው “በደንብ ያሰጣል” ብለው ይመልሱልሃል፤ ፔናሊቲውን በተመለከተ ምንም የሚያከራክርና የሚያሻማ ጉዳይ ያለ አይመስለኝም” በጣም ግልፅና ትክክለኛ ነው”
የፍፁም ቅጣት ምት ስለመሳቱ
“የመጀመሪያውን ስላስቆጠርኩ በተመሳሳይ ሁለተኛውንም አስቆጥራለሁ የሚል እምነት ነበረኝ፤ ግን እንዳሰብኩት አልሆነም ሣትኩት ለዚህ ምክንያቱ ግብ ጠባቂው ለአለም ይመሰልኛል፤ ምክንያቱም ነቅቶብኛል፣ በዚህ አጋጣሚ ለአለምን በጣም ነው ማደነቅው የምፈልገው፤ እሱ ባኖብኛል፤ ሀትሪክ ለመስራት መጓጓቴን ለመሳቴ አንደኛው ምክንያት የሆነኝ ይመስለኛል”
አቡበከር የችሎታውን ያህል ፔናሊቲ ቦክስ ውስጥ አወዳደቁን ያውቅበታል ስለመባሉ?
“እኔ እንደውም በተቃራኒው ነው የምወቀሰው… አወዳደቅህን አሳምር እየተባልኩ፤ አወዳደቄን ያለማሳመር ችግር አለብኝ፤ ስጠለፍ ነው የምወድቀው… ሳልጠለፍ ብወድቅ እንኳን ያስታውቅብኛል፤ እንደውም አንደኛው ድክመቴ ፔናሊቲ ቦክስ ውስጥ አወዳደቄን አለማሳመሬ ነው፤ ከዚህ ውጪ ገና ለገና ፔናሊት አሰጣለሁ በሚል ሆነ ብዬ የምወድቅ አይነት ተጨዋች አይደለሁም”

የቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ጠባቂው በቀይ ካርድ መውጣቱ እንዲያሸነፉ ረድቶአቿዋል ስለመባሉ
“ግብ ጠባቂው ቢኖር ቅ/ጊዮርጊሶችን እንደሚጠቅማቸው አያከራክርም፤ መውጣቱ ብቻውን ለእኛ የተለየ ጥቅም ሰጥቶናል ብዬ ግን አላስብም፤ ለእነሱ ግን ጎበዝ በረኛ ስለሆነ ከመውጣቱ ይልቅ መኖሩ በጣም ሊጠቅማቸው ይችላል፤ በተረፈ ግን ባይወጣም እኛ ወደ ሜዳ የገባነው አሸንፈናቸው ለመውጣት ስለነበር በእለቱ ጨዋታ ማሸነፋችን አይቀርም ነበር፤ እንደውም በዕለቱ አስበን የገባነው የክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑ ደጋፊቻቻችን አሸንፈን ገናን በደስታ እንዲያሳልፉ ለማድረግ ነበር፤ ያ ሃሳባችንም ተሳክቶልናል፤ ደጋፊዎቻችንም፣ ተጨዋቾቻችንም አሰልጣኞቻችንም የገናን በዓል በጥሩ የደስታ መንፈስ እንዲያከብሩ ነበር ምኞትችን ተሳክቶልናል፡፡
ወንድሙ ሬድዋን በራሱ ላይ ግብ ስላስቆጠረበት አጋጣሚ
“በእርግጥ ሬድዋን ወንድሜ ነው” ሜዳ ውስጥ ግን ሬድዋንንም ሌሎች ተጨዋቾችንም በአንድ አይን ነው የማየው፤ የቤተሰብነትን ስሜት ሜዳ ውስጥ አላንፀባርቅም፤ ሌሎችን የቡድን ጓደኞቼን በማይበት አይን እኩል ነው እሱንም የማየው፤ ራሳችን ላይ ግብ ሲያስቆጥር ወንድሜ አስቆጠር ሣይሆን ከቡድን አጋሮቼ አንዱ ያስቆጠረ ያህል ነው የተሰማኝ፤ እሱም ራሱ ላይ ግብ ሲያስቆጥር ለወንድሜ ሳይሆን ለቡድኔ ነው ያዘንኩት፣ የደነገጥኩት፤ እግር ኳስ ከስህተት የፀዳ ባለመሆኑ መሳሳት የሚጠበቅ ነው፤ ያንን ስህትት የሚያካክስ ስራ ላለመስራት ወይም ግብ ስለማስቆጠር እንጂ ወንድሜ ነው አይደለም የሚለው ለማሰብ ጊዜው አልነበረኝም፤ እንዳልኩህ የሚቀድመው ቡድናችን ነው፤ በራሳችን ላይ ግብ በመቆጠሩ ከሁላችም በላይ ስህተቱን የሰራው ተጨዋች ነው የሚጎዳው፤ ግብ ለማስቆጠር ስታገል የነበረው ወንድሜ ስለተሳሳተና እሱን ለማስደሰት ሣይሆን ቡድኔ ውጤታማ እንዲሆን ነው፤ የቡድኔ ጉዳይ በዚህ መልኩ ከተሳካ በቀጣይ ተጨዋቹ እረፍት ያገኛል”

ስለ 3ቱ የናስር ልጆች በፕሪሚየር ሊግ
“እኔና ሬድዋን በኢት.ቡና ጅብሪል በሰበታ እየተጫወትን ነው፤ የአንድ ቤተሰብ 3 ተጨዋቾች በፕሪሚየር ሊግ መጫወታችን የቤተሰባችንን ስም በዚህ መልኩ ማስጠራታችን ያስደስታል፤ ለሀገራችንም የበኩላችንን ለማድረግም እንጥራለን፡፡
“ከሶስቱ የናስር ልጆች ማን ይበልጣል በሚል ለቀረበለት ጥያቄ?
“እኔ ከምናገር ሰው አይቶ ቢፈርድ ይሻላል፤ ግን ሠፈር አካባቢ ያለ ወይም በጣም በቅርበት የሚውቀንን ብትጠይቅ ከእኔና ከሬድዋን የበለጠ ጅብሪልን አንደኛ ያደርጉልታል፤ እኔም ጅብሪል ይችላል ባይ ነኝ፤ እናቴንም ብትጠይቃት በተመሳሳይ ጅብሪልን ነው የምታስቀድመው”

ኮከብ ግብ አግቢነትን ስለመምራቱ
“ዘንድሮ በዚህ በኩል እነ ሳላሀዲን፣ ጌታነህ ከበደ የሰሩትን ታሪክ መስራት እንፈልጋለን፤ ከእነሱ ጋር መፎካከሬ ትልቅ ነገር ነው፤ ልክ እንደ እነሱ ይሄን ክብር ማግኘት፣ ሀገሬን ለአፍሪካ ዋንጫ ማሳለፍ ፕሮፌሽናል ሆኜ ስሜን ማስጠራት ምኞቴ ነው፤ አሁን በኮከብ ግብ አግቢነትም ጠንካራ ፉክክር አለ ሙጅቢ ቃሲም ኮከብ ግብ አግቢ ለመባል አሪፍ እድል አለው፤ ከእሱና ከሌሎች ጋር ብርቱ ፉክክር እናደርጋለን፤ ከሁላችንም የተሻለ ክብሩን ያገኛል፤ እኔም ለክብሩ ጥረቴን እቀጥላለሁ፡፡”

ሀትሪክ የሠራበትን ኳስ ስለአለመውሰዱ
“የእኛ ሀገር ነገር ግራ ይገባሀል፤ ሶስት ጎል ያውም በደርቢ ጨዋታ ላይ አስቆጥሬ ለጎልህ ማስታወሻ የሚሆንህን ኳስ ይዘህ መውጣት የማትችልበት ሊግ የእኛ ብቻ ይመስለኛል፤ ሀትሪክ ሠርተህ ሀትሪክ የሠራህበትን የ1 ሺህ ብር ኳስ እንኳን መውሰድ አትችልም ትባላለህ፤ ሀትሪክ ሠርተህ ኳሱን ብትወስድ ፌዴሬሽኑን ያን ያህል የሚጎዳው ነገር አይደለም፤ ለተጨዋቹ ግን ትልቅ ነገር ነው በዚያ ላይ ሀትሪክ የሠራኸው በደርቢ ጨዋታ ሲሆን ታሪካዊነቱ የተለየ ነው፤ ሀትሪክ ሠርቼ ኳሱን መውሰድ ተወውና ኳሱን ይዘህ ለማስታወሻነት እንኳን ፎቶ የመነሳት እድል አታገኝም ሙጂብ ቃሲም ከዚህ በፊት ተናግሮታል
ሀትሪክ ሰርቶ አጥቶታል፤ አሁን ደግሞ እኔም ተመሳሳይ ዕጣ ደርሶኛል፤ በቀጣይ ሀትሪክ የሚሠሩ ተጨዋቾች የእኛ እድል እንዳይደርስባቸው ሊታሰብበት ይገባል፤ አሁን ኳሱን መውሰድ አትችልም ስትባል የምታጣው ኳሱን ብቻ አይደለም ማስታወሻውን ታሪክህን ጭምር ነው፤ እኔ አሁን በታላቁ የሸገር ደርቢ ሀትሪክ ሠርቻለሁ፤ ግን ከወሬ በዘዘለ ወይም ከቪዲዮ ውጪ ሀትሪክ መስራቴን የሚመሰክር አንዳች ነገር የለኝም፡፡ ሀትሪክ የሠራሁባት ኳስ ብትኖረኝ ግን ታሪኬን ትተርካለች፤ ወደፊትም ለቤተሰቦቼ፣ ለወዳጆቼ የሚያስተላልፈው መልዕክት ይኖራል፡፡ በጣም ትንሽ በሆነ ነገር ታሪክህን ስታጣ በጣም ታዝናለህና ይሄ ነገር ይታሰብበት፡፡
ክፍል ሁለትን ለማንበብ ሊንኩን ይጫኑ 👇
አስተያየት ይስጡ