“በእግር ኳሱ ጥያቄው ምን መስራት ትችላለህ?… ሳይሆን ማንን ታውቃለህ?…
ምን ትለቃለህ? መሆኑን ሀገሬን በሙያዬ እንዳላገለግል አድርጎኛል”

የትውልድ ቦታው፡-
ለእግር ኳስ
ተጨዋችነቴ ብዙ አስተዋፅኦ ያደረገው ከአዲስ
አበባ ስታዲየም በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው
አዲሱ ቄራ ነው ተወልጄ ያደኩት፡፡ ብዙ
ያልተነገረላቸውን ተጫዋቾችን አሰልጣኞችን
ያፈራ የባንኮቹን ደፋር አጥቂ ካሳ አባዬን
የመሳሰሉ ልጆችን ያፈራው አዲሱ ቄራ ነው
ተወልጄ ያደኩት፡፡
ስንት ክለቦች የሳምሶን አየለን
የስልጠና በረከት ቀምሰዋል? የት…?
የት…? አሰልጥነሃል…? የተለያዩ ክለቦችን
በማሰልጠን አሳልፌያለሁ፤ የሰራሁባቸውን
ክለቦች ከመዘርዘሬ በፊት አንድ ነገር ባስቀድም
ደስ ይለኛል፡፡ እኔ ወደ ስልጠናው አለም
የመጣሁት በድንገትና በአቋራጭ አይደለም፤
በትምህርትም፣ በልምድም፣ በስልጠና
እውቀትም ራሴን በበቂ ሁኔታ አስታጥቄ
ነው የመጣሁት፡፡ በተለይ በተጫዋችነት
ዘመኔ በበርካታ አልጣኞች ሰልጥኜ በማለፌ
ካገኘሁት የስልጠና እውቀት በተጨማሪ
የተለያዩ የስልጠና ኮርሶችን በመውሰድ
ራሴን በእውቀት ለማስታጠቅ ሞክሬያለሁ፡፡
በኮርስ ደረጃ የአንደኛ ደረጃ፣ የሁለተኛ ደረጃ
በማለት የተለያዩ ማሻሻያ ኮርሶችን ከመውሰዴ
በተጨማሪ ከሲ ላይሰንስ ጀምሮ እስከ ኤ
ላይሰንስ ድረስ ወስጃለሁ። የሰራሁባቸውን
ክለቦች በተመለከተ ደግሞ ከታዳጊ ወጣቶች
ጀምሮ የተለያዩ የብሔራዊ ሊግ ክለቦችን
በዋና አሰልጣኝነትና ከሌሎች አሰልጣኞች ጋር
በፕሪሚየር ሊግ በረዳትነት ከመስራቴ ውጪ
በሐረር ቢራና በዳሽን ቢራ በዋና አሰልጣኝነት
በመስራት የበኩሌን አስተዋፅኦ ለማድረግ
ሞክሬያለሁ፤ በዚህም ደስተኛ ነኝ፡፡
በተለይ በፕሪሚየር ሊግ በማሰልጠን
የሚጠቀስ ሥራ ሠርቷል ስለመባሉ፡-
ፕሪሚየር ሊግ የሀገራችን ትልቁ ውድድር
ነው፤ ስም ያላቸው ክለቦች፤ አሰልጣኞችና
ተጨዋቾች ያሉበት የሀገሪቱ ትልቁ የሊግ
ውድድር ላይ መስራት ትልቅ አቅም፣
እውቀትና ልምድን አጣምሮ መያዝን
ይፈልጋል፡፡ እኔ ደግሞ ከላይ እንደገለፅኩልህ
ወደ አሠልጣኝነት ስመጣ በስርዓት ስለሆነና
እውቀትና ልምዴን ደረጃ በደረጃ አሻሽዬ
ስለመጣሁ የተሰጠኝን የዋና አሰልጣኝነት
ሥራ ለመስራት ብዙም ሳልቸገር በሜዳ
ላይም ከሜዳ ውጪም ባሉት ሥራዎች ላይ
ኃላፊነቴን በአግባቡ ስወጣ ነበር፡፡
በዋና አሰልጣኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ
ስለሰራበት የፕሪሚየር ሊግ ክለበ ስለነበረው
ሐረር ቢራ፡-
የሐረር ቢራ እግር ኳስ ቡድን
የምስራቁ የሀገራችን ክፍል ብቸኛው ተወካይ
ነበር፤ በወቅቱ ክለቡን በአገራችን አንጋፋ
የተባሉ አሰልጣኞች አሰልጥነውት ያለፉ፤
የተለያዩ ምርጥ ተጨዋቾችን ለሀገራችን
እግር ኳስ ያፈራ ክለብም ነበር፡፡ በዚህ
ክለብ ውስጥ መጀመሪያ የመጣሁት በረዳት
አሰልጣኝነት ነው፤በረዳት አሰልጣኝነት አንድ
አመት እንደሰራሁ የክለቡ አመራሮች ያለኝን
አቅምና እውቀት ተረድተው ዋና አሰልጣኝ
ሆኜ እንድሰራ ኃላፊነት ሰጡኝ፤ በዚህን
ጊዜ ነባርና ወጣት ተጫዋቾችን በአንድነት
በማቀናጀት በመጀመሪያ የዋና አልጣኝነት
ኃላፊነቴ ሠራተኛውን የስፖርት ቤተሰቡን
በተለይ የክለቡን ደጋፊዎች የሚያስደስት
ቡድን መገንባቴን የሚያረጋግጥ ምላሽ በተለያየ
መንገድ ገለፁልኝ፡፡ በተለይ በፕሪሚየር ሊጉ
ቡድኑ በሚያሳየው የጨዋታ እንቅስቃሴ
የሚዲያውንም፣ የስፖርት ቤተሰቡን ይሁንታ
በማግኘቱ “የውድድሩ ክስተት” የሚል
ድንቅ ስምም እስከማግኘት ደርሶ እንደነበር
አስታውሳለሁ፡፡ ይህ ግን ብዙም አልቀጠለም፡
፡ ክለቡ ባለበት ጥንካሬ እንዳይቀጥል የተለያዩ
ውስጣዊና ውጪዊ መሰናክሎች ገጠሙት፤
በተለይ በዚህ ወቅት ክለቡን በባለቤትነት
የሚያስተዳድረው ድርጅት የሐረር ቢራ
ፋብሪካ መሸጡ ክለቡ በክለብነት እንዳይቀጥል
ህልውናውን አደጋ ላይ ጥሎታል፡፡ ሐረር
ቢራ በዚህ መልኩ ወደ ታሪክነት ቢቀየርም
በክለቡ የአሰልጣኝነት ዘመኔ ስለአለኝ
የማሰልጠንና ቡድን የመገንባት አቅም ጉልበት
የሆነኝ አቅሜን ለስፖርት ቤተሰቡ አቅሜን
በመጠኑም ቢሆን እንዳሳይ ለስፖርት ቤተሰቡ
በተለይ ለክለቡ ደጋፊዎች ጥሩ ትዝታን
በውስጣቸው እንዲቀር ያደረገ ቡድን እንደነበር
አስታውሳለሁ፡፡
ሌላውን የፕሪሚየር ሊግ ክለብ ዳሽን
ቢራን ስለማሰልጠኑና ስለነበረው ቆይታ፡- ስለ
ዳሽን ቢራ ካነሳን ከሐረር ቢራ ቀጥሎ ጥሩ
የሥራና የውጤት ጊዜን ያሳለፉኩበት ክለብ
ነበር ማለት እችላለሁ፤ ዳሽን ቢራ በወቅቱ
ክልሉን የሚወክል የፕሪሚየር ሊግ ቡድን
ባለመኖሩ በአካባቢው ሰዎች ኃይለኛ ቁጭት
በተፈጠረበት ወቅት የመጣ ነው፤ ይህ ክለብ
ከፍተኛ በጀት በመመደብ የሀገሪቱን እግር
ኳስ ለመታደግም አስቦ የተቋቋመ ነበር፡
፡ ከወጣቶች በተጨማሪ ከፍተኛ ስምና ዝና
ባላቸው ተጨዋቾች ቡድኑ በመዋቀሩ በአጭር
ጊዜ የምስረታ እድሜው ከፍተኛ ትኩረትን
ማግኘት የቻለም ቡድን ነበር፤
እኔ ወደ ቡድኑ በአሰልጣኝነት
ስመጣ ከ80 በመቶ በላይ
የቡድኑ ተጨዋቾች ቀሪ የውል
ዘመን ስለነበራቸው እነሱ ላይ
የተወሰኑ ወጣት ተጨዋቾችን
በማካተት ጠንካራና ተፎካካሪ
ቡድን ለመስራት ሞክሬያለሁ፡
፡ በአጭሩ በክለቡ የነበረኝ
ቆይታ ባላሰብኩት ሁኔታ
ቢያጥርም ዳሽንን በማሰልጠን
ባሳለፍኩት…….. ወራት
በፕሪሚየር ሊጉ ጠንካራ፣
ተፎካካሪና ተመልካቹን
የሚያረካ ቡድን በመገንባት
በጣም ጥሩ የሚባል ጊዜን
አሳልፌያለሁ፡፡
ከዳሽን ጋር የነበረው
ቆይታ ጥሩ ከነበረ ከክለቡ
ጋር በድንገት ለምን ተለያየ፡-
አሁንም እደግመዋለሁ ከዳሽኖች
ጋር ጥሩ ቆይታ ነበረኝ፤ጥሩና
ተፎካካሪ ቡድን ነበረኝ፡፡
በውጤት ደረጃም ብትወስደው
የውጤት ደሃ የሚባል ቡድን
አልነበረም፡፡ በአንደኛው ዙር
የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር
በምስረታም በሊጉ ታሪክም
ከእኛ የተሻለ ስም ያላቸው
ክለቦችን በልጠን በ6ኛ ደረጃ
ነበር ያጠናቀቅነው፡፡ በቡድኑ
በነበረኝ የአሰልጣኝነት ቆይታ
የእኔ ዝቅተኛው የውጤት
ደረጃ ዝቅተኛው 8ኛ ደረጃ
ነበር፡፡ ከውስጥም ከውጪም
የሚጎትቱት ባይኖሩ ኖሮ
ቡድኑ ከነበረው ስብስብና አቅም
አንፃር ከዚህ የተሻለም ውጤት
ማስመዝገብ የሚችልበት አቅም
ነበረው፤ ግን አልሆነም፡፡ በሜዳ
ላይ የቡደኑ እንቅስቃሴ ጥሩ
ሆኖ ከሜዳ ውጪ ከቅርብም
ከሩቅም በቡድኑ ላይ ድብቅ
ፍላጎቶች ስለነበሩ በረዥም የጥፋት እጃቸው
የሜዳውን ሥራ በጥንካሬ እንዳይቀጥል
ይረብሹት ነበር፡፡ እነዚህ የጥፋት እጆች ዳሽን
ብዙ ርቀት በስኬት እንዳይጓዝ በህልውና
እንዳይቆይ እንቅፋት ፈጥረውበታል፡፡ በዳሽን
ብዙ ህልም ነበረኝ፤ ነገር ግን ያልኩህ እጆች
ሁሉንም ነገር በአጭር አስቀርተውታል፡፡
ዳሽን ቢራን ያወረደው ማነው? ስሙ
ከዳሽን ቢራ መውረድ ጋር ተያይዞ መነሳቱን
በተመለከተ፡-ትክክለኛ ምላሽን የሚሻ ጥያቄ
ነው ያነሳኸው፤ ብዙዎች ይሄንን ጉዳይ
በተመለከተ ውዥንብር ውስጥ ሲገቡ ነው
የምሰማው፤ እውነታው ግን ዳሽን ቢራ በእኔ
የአሰልጣኝነት ዘመን አልወረደም፡፡ ከላይም
ለመግለፅ እንደሞከርኩት በአንደኛው ዙር
ቡድኑ ስድስተኛ ሆኖ ነው የጨረሰው፤
ከክለቡ ጋር እስከተለያየሁበት ጊዜ ድረስ
የእኔ ዝቅተኛው ውጤት 8ኛ ደረጃ ነው፤
ቡድኑ የወረደው እኔ ከክለቡ ጋር ተለያይቼ
ሌሎች አሰልጣኞች ከተረከቡት በኋላ ነው፡፡
ዳሽንን 8ተኛ አድርጌ ከክለቡ ጋር በመለያየቴ
ሚዲያው የስፖርት ቤተሰቡም ተገርሞ ያወራ
ይጠይቁኝ ነበር፡፡ ውጤቱ እስከመለያየት
የሚያደርስ አይደለም ብለው የሞገቱም ነበሩ፡፡
አንዳንድ የግል ፍላጎትና ሴይጣናዊ አስተሳሰብ
ያላቸው አካላት በሙያዬ ሀገሬን እንዳላገለግል
የዳሽንን መውረድ ከእኔ ጋር እያያዙ ክለብ
እንኳን እንዳላሰለጥን ዘመቻ የጀመሩብኝ ክፉ
ሰዎች ያስወሩት ወሬ ነው ፡፡ ክለቦችም ከእኔ
ጋር በብዙ ነገር ስምምነት ላይ ደርሰው
ይሄን ልብ ወለድ ወሬን ምክንያት አድርገው
እድሉን ሲነጥቁኝ አስተውዬ አዝኛለሁ፡፡ ዛሬ
ላይ ግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመግለፅ
እፈልጋለሁኝ፤ ዳሽን የወረደው በእኔ
የአሰልጣኝነት ዘመን አይደለም፤ እኔ ከክለቡ
ጋር ተለያይቼ ሌሎች አሰልጣኞች ተተክተው
እንደወረደ ሁሉም ሊያውቀው ይገባል፡፡
በአሰልጣኝነት በቆይህባቸው ክለቦች
ውስጥ የነበረህ የስራ ግንኙነት ምን
ይመስላል፦ በዚህ በኩል ችግር የለብኝም፤
ምክንያቱም መጀመሪያ መነሻ የማደርገው
ስራዬንና ሥራዬን ብቻ ነው፡፡ በሥራ ላይ
አለመግባባቶች ቢፈጠሩ እንኳን በውይይትና
በመነጋገር ሥራውን ማዕከል ባደረገ መልኩ
የመፍታት ባህል አለኝ፤ ከዚህ ውጪ እኔ
ምንም የጀርባ ችግር የሌለብኝ ሰው ስለሆንኩ
ሥራዬን በነፃነትና በጥሩ መግባባት ነው
የምሰራው፡፡ ለዚህም ይመስለኛል በሥራ
ካገኘሃቸው አንዳንድ ሰዎች ጋር እስከአሁንም
ድረስ የቤተሰብ ያህል የተቀራረብነው፡፡
ባንኮች በረዳትነት፣ ሐረር ቢራንና
ዳሽን ቢራን በዋና አሰልጣኝነት በማሰልጠን
ብታሳልፍም አሁን ያለ ክለብ ተቀምጠሃል
የዚህ ምክንያቱ ምንድነው፡-
ለእኔ ብቻ ሣይሆን ለብዙዎች እልፈታ ያለ እንቆቅልሽ
የሆነ ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳኸው፤ እኔ
እንግዲህ ወደ አሰልጣኝነት ስመጣ እንዴት
እንደመጣሁ የወሰድኳቸው ኮርሶች፣ የሥራ
ልምምዴ፣ ተግባብቶ በመስራት በኩል
ያለኝ ግንኙነትና እንዴት ደረጃ በደረጃ
በሥራና በሥራ ብቻ እንደመጣሁ ከላይ
ገልጬልሃለሁ፡፡ ነገር ግን እኛ ሀገር በተለይ
የእግር ኳስ አሰልጣኝነት ቅጥር ላይ ጥያቄው
“ምን አለህ…?… ምን መስራት ትችላለህ…?”
ሣይሆን ጥያቄው“ …ማንን ታውቃለህ…?
ምንስ ትለቃለህ…?” ከሆነ ሰነባብቷል፤ ይሄን
መስመር የተከተሉ ቡድን አወረዱ ውጤት
አጡ በየዓመቱ ላለመውረድ ተጫወቱ ሳይባሉ
ከክለብ ወደ ክለብ እየተገለባበጡ የማይሞቱ
የፊልም አክተር ሆነው እያየናቸው ነው፡፡
እኔ ደግሞ በዚህን አይነት ወጣ ባለ መስመር
አሰልጣኝ የሚቀጥሩትን አላውቃቸውም፤
ላውቃቸውም አልፈልግም፡፡ ምናልባት በዚህ
የተጣመመ መስመር ውስጥ አለማለፌ
መስራት በምችልበት፣ እውቀትና ልምድም
በታጠኩበት፣ የሚንተከተክ የመስራት ፍላጎት
ባለኝ በዚህ ሰዓት ያለስራ እንድቀመጥ
አድርጎኛል፡፡ አንዳንዶች አንተም ለምን
እንደ ጊዜው ሆነህ ክለብ አትይዝም?
መስራት እኮ ትችላለህ፤ ብለው እስከመውቀስ
የደረሱ አጋጥመውኛል፡፡ ምናልባት በዚያ
የተንጋደደ መንገድ ሄጄ ኪሴን ልሞላ፣
ቤትና መኪና ልገዛ እችላለሁ፤ ህሊናዬ
ግን ሁሌም ሲወቅሰኝ ስለሚኖር
ያንን ማድረግ አልፈልኩም፡፡
ይሄን አለማድረጌ ጎድቶኛል፤ ያለ
ሥራ እንድቀመጥም አድርጎኛል፡
፡ ከህሊና ወቀሳ ነፃ በመሆኔ ግን
ሐዘኔን ቀንሶታል፡፡ የሀገር እግር
ኳስን እየጎዳሁ የግል ኪሴን
መሙላት አለመፈለጌ፣ የወቅቱን
መሞዳሞድ አለመቻሌ ከስልጠናው
አርቆ እንዳስቀመጠኝ አልክድም፡፡
ደግሞም በዚህ መስመር ከማለፍ
መጎዳትን እመርጣለሁ፡፡ በዚህ
የተሳሳተ መስመር የተጓዙ ጥቂቶች
ኪሳቸውን ከማደለባቸው ውጪ
እግር ኳሱ የት እንዳለ እያየነው
ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ በጣም
እየተስፋፋ መጥቶ አንድ አሰልጣኝ
እየሠራ ባለው ነገር አቅሙንና
እውቀቱን በሚያዳብር ተፎካካሪ
ሆኖ ከመምጣት ይልቅ በዚህ
ባልተለመደ መልኩ በጊዜያዊነት
ቅጥር ላይ ብቻ በማተኮር
ሙያተኛውም ያለው አቅም ላይ
እንዳይሠራና እንዳያተኩር ችግር
እየሆነ ነው፡፡ ይህ አካሄድ ከዚህ
ውጪ ላለን ሙያተኞች ፈተና
እየሆነብን ነው፤ በነገራችን ላይ
ከላይ በገለፅኳቸው ችግሮች ውስጥ
ገብተው የማይንቦጫረቁ፣ ከግል
ኪሣቸው ይልቅ የሀገርን እግር
ኳስ የሚያስቀድሙ፣ የተሰጣቸውን
ኃላፊነት ጠብቀው የሚሄዱ፣
የማይሞዳሞዱና በህሊናቸው
የሚሠሩ ጥቂት አሰልጣኞች፣
ክለቦች፣ አመራሮች መኖራቸው
መጥቀስ እፈልጋለሁ፡፡
ብዙውን ጊዜ ስሙ ከተለያዩ
ክለቦች ጋር በዋና አሰልጣኝነት
ተያይዞ ስለመነሳቱና ጫፍ ደርሶ
በመጨረሻ ለሌላ አሰልጣኝ
ስለመስጠቱ፡- ይሄ እውነት
ነው፤ባለፉት ጊዜያት ስሜ ከተለያዩ
ክለቦች ጋር ተያይዞ ይነሣና
ለአሰልጣኝነት እታጭና ብዙ ርቀት ከሄድኩ
ከተነጋገርኩ በኋላ በመጨረሻ ምክንያቱን
በማላውቀውና በማያሳምነኝ መልኩ ሌሎች
አሰልጣኞች ሲቀጠሩ ያጋጥመኛል፡፡ በተይ
ከአንዳንድ ክለቦች ጋር 95 በመቶ ወደ
ክለቡ ለመግባት ተቃርቤ መስፈርቱን በሙሉ
አሟልቼ ሚዲያዎች ሁሉ እርግጠኛ ሆነው
ዘግበው በተለመደው ያልታወቀ ድራማ
በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ ተደርጌያለሁ፡፡
የፕሪሚየር ሊግ ልምድ የለውም እንዳልባል
ከአንድም ሁለት ክለብ በማስልጠን ልማዱ
አለኘ፤ ስልጠና አልወሰደም እንዳልባል
እስከ ኤ ላይሰንስ ደርሻለሁ፤ ልምድን
ከእውቀት ጋር አጣምሬ ለምን መጨረሻ ላይ
እንደምወድቅ አይገባኝም፡፡ ብዙዎች ይሄን
የሚያዩ “አንተ ያልገባህ ነገር አለ ይሉኛል”
ምን እንዳልገባኝ ግን ደፍረው አይነግሩኝም፡፡
ደግሞ እኮ የሚገርመው አለመቀጠሬን አምኜ
እንዳቀበል ከእኔ በልጦ የሚቀጠረው ሰው
ከእኔ የተሻለ አለመሆኑ ነው፤ “የሚባለው
ሲስተም ወይም ኔትርክ ውስጥ ስላልገባህ
ነው” ብለው የሚወቅሱኝ ብዙዎች ናቸው፡፡
በአጭሩ አንድን ክለብ ለመያዝ በዚህ ዘመን
መስፈርቱ ምን እንደሆነ ለማወቅ በጣም
ተቸግሬያለሁ፡፡
ከዚህ አንፃር በርካታ አሰልጣኞች የዚህ
ችግር ሰለባ እንዳይሆኑ ምን መደረግ አለበት
ትላለህ፡- የሀገራችን እግር ኳስ በአሁኑ ጊዜ
ከፍተኛ መነቃቃት ላይ ነው፤ እግር ኳሱ
ከፍተኛ የገንዘብ ቁጥርም እየፈሰሰበት ነው፤
መንግሥት ለስፖርቱ እድገት በመቆርቆር
ያለ ስስት ከፍትኛ በጀት እየመደበበት ነው፡
፡ ከዚህም አልፎ የተለያዩ ስታዲየሞች
በተለይ በክልል እየተገነቡ ነው፡፡ ከመጠነኛ
ግጭቶች ችግሮች ውጪ የደጋፊው የአደጋገፍ
ስርዓት ይደግ የሚያስብል ነው፡፡ ሚዲያውም
በአብዛኛው ሠፊ ጊዜ ለእግር ኳሱ በመስዋት
መረጃና ግንዛቤን የሚያስጨብጡ ሥራዎች
እየተሰሩ ነው፡፡ ይሄ እንደመልካም የሚወሰድ
ቢሆንም በእግር ኳሱ በኩል እድገት ከመታየት
ይልቅ እየወረደና እየተዳከመ መሄዱ ደግሞ
ያሳስባል፡፡ ከማሳሰብ አልፎም ወደ አደገኛ
ሁኔታ እየገባ ነው ማለትም ይቻላል፡፡
ለዚህ ደግሞ ብዙ ምክንያቶችን መደርደር
ቢቻልም ትልቁ የእግር ኳሱ ካንሰር ግን
ጥቂቶች ኔትወርክ ዘርግተው በመሞዳሞድ
ከክለብ ክለብ መገለበጣቸውና እግር ኳሱን
ጎድተው ኪሳቸውን ማደለባቸው ነው፡፡ ክለቦች
የአሰልጣኝ አቀጣጠራቸው፣ አሰልጣኞች
የተጫዋች አመላመላቸው መስመሩን በሣተ
መልኩ መሆኑን የሚያሳብቁ ነገሮች በስፋት
ይታያሉ፡፡ ለእኔ ከእግር ኳሱ ይልቅ ግለሰቦች
አድገዋል፤ ተጠቅመዋል፡፡ በደካማው እግር
ኳስ ላይ ይሄ ችግር መጨመሩ በጣም
ያስፈራኛል፤ ከሌሎች የእግር ኳሱ ችግሮቻችን
ባልተናነሰ ለዚህም አደገኛ መስመር መድሃኒት
ልንሰጠው ይገባል፡፡ ይሄን ካላደረግን የከፋ
ነገር መምጣቱ አይቀሬ ነው የሚሆነው፡፡
እግር ኳስ ወደተሻለ መንገድ እንዲመጣ
ምን ምን ይካተት፡-
እግር ኳሱ በእውቀት
በሥርዓት መመራት አለበት ይሄ እነጋገርር
ከአባባል በዘለለ መልኩ ነው መሰራት
ያለበት፡፡ ሙያተኛው በተለይ አሰልጣኞች
በእውቀትና በአቅሙ በሠራው ሥራ
ተመዝኖ ከቡድንተኝነት ከመጠቃቀም በፀዳ
መልኩ የሚሰራበት ስርዓት ነው መፈጠር
ያለበት፤ የእስካአሁኑ አካሄድ ምናልባት
ግለሰቦችን ጠቅሟል ካላልን በስተቀርለእግር ኳሱ የፈየደው ነገር የለም፡፡ የክለቦች
አደረጃጀትም አለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ
መልኩ በተጠያቂነት መንፈስ በሙያተኞች
እንዲመራ፣ ተተኪዎች ላይ የመስራት ቢህል
እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ተተኪዎች
ላይ መስራት ሲባል በአነማን? እንዴት
ይሠራ? የሚለው በደንብ ተፈትሾ ይሠራየሚለው መለየት እንዳለበት መዘንጋት
የለበትም፡፡ ሚዲያውም ቢሆን አሁን በያዘው
መልኩ ነገር ግን ከወገንተኝነት በፀዳ ሀገርን
ማዕከል ባደረገ መልኩ ቢሠራ መልካም ነው፡
፡ ደጋፊውንም በሌለ እግር ኳስ የሚሻኮት
ሣይሆን የወረደውን እግር ኳስ በማሳደጉ
በኩል የላቀ ተሳትፎ ያለው የሰለጠነ ደጋፊ
ቢሆን እግር ኳሳችን ተጠቃሚ ነው፡፡
የአንድ ክለብ ማልያን ስለለበሰበት
የመጀመሪያ ክለቡ፡- እግር ኳስን በትልቅ
ክለብ ደረጃ ተጫውቼ ያቆምኩት በእርሻ
ሰብልና በእርሻ ሰብል ብቻ ነው፡፡ በኢትዮጵያ
ፕሪሚየር ሊግ በጥንካሬውም ሆነ በስብስቡ
የገዘፈ ስም የነበረው የእርሻ ሰብል ማልያን
ለ13 አመታት ለብሼ ተጫውቻለሁ፡፡ እግር
ኳስን ያቆምኩት ከእርሻ ሰብል ወርቃማው
ማልያ ውጪ የሌላ ክለብ ማልያን ሳልለብስ
ነው፤ በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
የእርሻ ሰብልን ስብስብ በተመለከተ፡-
እውነት ለመናገር በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ
አንፀባራቂና በእግር ኳሱ ላይ እንደፈርጥ
የሚቆጠሩ ተጫዋቾችን ያካተተ ቡድን ነበር
እርሻ ሰብል፡፡ የድንቅ ችሎታ ባለቤት የሆኑ
ከክለብ አልፈው ለሀገር የማይዘነጋ አስተዋፅኦ
ያደረጉ ተጨዋቾች ተጫውተው ያለፉበት
ክለብ ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ እኔን ጨምሮ እነ
መንግሠቱ ሁሴን፣ አፈወርቅ (ካቻ)፣ ፍላጎት
ደምሴ፣ ኃይሌ ካሴ፣ ርዕሶምና ቢተው አብሬን
የመሳሰሉ ተጫዋቾች አብረውኝ የተጫወቱበት
ኃይለኛ ስብስብ ነበር፡፡ የእርሻ ሰብል ቡድን
በድንቅ ጨዋታ ብቻ ሣይሆን ስም ላላቸውና
ኃያላን ለሚባሉ ቡድኖችም ትልቅ ፈተና የሆነ
ቡድንም ነበር፡፡
ከእርሻ ሰብል ጋር ስላሳካቸው ድሎች፡-
ከእርሻ ሰብል ጋር ካገኘሃቸው ስኬቶች
ውስጥ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፈን የኢትዮጵያ
የጥሎ ማለፉ ሻምፒዮን የሆንበት ባይሳካም
ሀገር የመወከል እድል ያገኘንበት በዋናነነት
የሚጠቀስ ሲሆን ከዚህ ውጪ የአዲስ አበባ
ዋንጫ አሸናፊ የሆንበትም ይጠቀሣል፡፡
በተለይ በኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ሻምፒዮና
ከአንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተገናኝተን
90 ደቂቃ 0ለ0 ጨርሰን በጭማሪ 30 ደቂቃም
የመጀመሪያ 15 ደቂቃ 0ለ0 ሆነን ሁለተኛ 15
ደቂቃ ተጠናቆ ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ልንገባ
ስንል ሰይፈ የሚባል የቡድናችን ተጫዋች
ከርቀት መትቶ የግብ ጠባቂውን የደሳለኝ
እጅን ጥሳ በገባች ግብ በማሸነፍ ሻምፒዮን
የሆንበት አጋጣሚ አይረሣም፡፡ ጎሉን
ያስቆጠረው ሰይፈ በነጋታው ለንባብ በበቃው
አንድ ጋዜጣ ላይ “ጎሉን ያስቆጠርከው ክሮስ
ለማድረግ ስትል ነው?” በሚል ተጠይቆ
“አስቤ” ነው ብሎ በመመለሱ በርካታ
የጊዮርጊስ ደጋፊዎች በመሸነፋቸውና በንግግሩ
ተበሳጭተው በሌላ ጨዋታ ሊያጫውቱን
አልቻሉም፤ በየጨዋታው በጣም ይቃወሙን
ነበር፡፡ የደጋፊው ተቋውሞ በጣም እየጠነከረ
በመምጣቱ ከረሜላና አበባ በትነን ተጫዋቹም
ሜዳውን ዞሮ ይቅርታ ጠይቆ ነው ነገሩ
የበረደው፡፡ ያ አጋጣሚ ሻምፒዮን የሆንበትና
ሀገር የመወከል እድል ያገኘንበት አጋጣሚ በ
መሆኑ ሁሌም ሳስታውሰው ነው የምኖረው፡፡
ቅ/ጊዮርጊስን አሸንፈው ሻምፒዮን
በመሆናቸው ሀገር ወክለው ወደ ታንዛኒያ
ለመሄድ ሙሉ ሱፍ ተስፍቶላቸው ከውድድሩ
ስለመቅረታቸው፡- ይሄ አጋጣሚ በጣም
የሚያሳዝን ነው፤ እንዳልከው ቅ/ጊዮርጊስን
አሸንፈን ሻምፒዮን በመሆናችንና ሀገር
በመወከላችን ለሁላችንም የቡድኑ ተጨዋቾች
ሙሉ ሱፍ ተሰፍቶልን ለጉዞ እየተዘጋጀን
ባለንበት ሰዓት ምክንያቱን ባለወቅንበት
ሁኔታ ከጉዞ የቀረንበት አጋጣሚ ተፈጥሮ
ሁሉም የቡድናችን ተጨዋቾች በጣም አዝነን
ነበር፡፡ ሙሉ ሱፍ ተሰፍቶልን፣ ፓስፖርት
ወጥቶልን፣ ትኬት ሁሉ ተዘጋጅቶ፣
የምድብ ድልድሉ ሁሉ ወጥቶ ሀገር ወክለን
በአውሮፕላን ከዛሬ ነገ ሄድን ስንል ዛሬም
ድረስ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ውድድሩ
ተሰርዟል ተብለን ቀርተናል፡፡ ውድድሩ
በመሰረዙ ብንቆጭም ግን በግርግር ሙሉ
ሱፍ አግኝተናል፤ ሙሉ ሱፍ ያኔ ውድ ነበራ፡፡
አስራት በዲሲፕሊን የሚያስችግሩትን
ወይም ልምምድ ላይ ደካማ እንቅስቃሴ
የሚሳየቱን”አንተማ ታንዛንያ አትሄድም” ብሎ
ማስፈራሪያ ስለማድረጉ፡-
(በጣም ሣቅ)ማነው
የነገረህ… የሚገርምህ ሁሉም ታንዛንያ
ለመሄድ በጣም ጓጉቶ ነበር፤ አሰልጣኛችን
አስራት ኃይሌ ደግሞ ይሄንን ጠንቅቆ ያውቅ
ስለነበር ተጫዋቾቹን ለማነሣሳትና ጠንክረው
እንዲሰሩ ዲሲፒሊን እንዲያከብሩ ለማድረግ
አንድ ጥፋት ሲያጠፉ ወይም ከልምምድ
ሲቀሩ “…አንተማ በቃ አለቀልህ… ታንዛኒያ
አትሄድም፤ …የአንተ ጉዳይማ አልቋል…
ከታንዛኒያው ጉዞ ተሰርዘሃል…” እያለ
ሁሉም ጠንክሮ እንዲሠራ ያደርግ ነበር፡፡
እኛ ተጫዋቾችም ይሄ ነገር ለምዶብን አንድ
ተጫዋች ካረፈደ “…አንተማ አለቀልህ… በቃ
ታንዛኒያን በካርታ እንጂ በአይንህ አታያትም”
እያልን እንቀላለድ ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ
ታንዛኒያ ህልም ሆና ቀረች፡፡
ለብ/ቡድን የመመረጥ እድልስ አግኝቶ
ይሆን፡-
ለኢትዮጵያ ብ/ቡድን በተደጋጋሚ
የመመረጥ እድልን አግኝቻለሁ፤ በተለይ
ሁለት ብ/ቡድን በነበረበት በአሰልጣኝ አስራት
ኃይሌና አስፋው አስመሮም አሰልጣኝ
በነበሩበት ጊዜ ተመርጫለሁ፡፡ ከብ/ቡድንም
ውጪ አሰልጣኝ ሰለሞን ቸሩ በነበረበት ጊዜ
ለአዲስ አበባ ምርጥ ቡድንም የመመረጥ
እድል ነበረኝ፡፡ የያኔው የአዲስ አበባ ምርጥ
ብ/ቡድን በለው፤ ለብ/ቡድን እንደመመረጥ
ነበር የሚያስደስተም፡፡
የጨዋታ ዘመንህ ምርጥ አሰልጣኝ፡-
እንደየችሎታቸው በጣም የማደንቃቸውና
የማከብራቸው አሰልጣኝ አሉ፤ አሰልጣኝ
አስራት ኃይሌ፣ ኢንስትራክተር ካሳሁን ተካና
ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው የየራሳቸው
ትልልቅ ኳሊቲዎች አሏቸው፡፡
የጨዋታ ዘመንህ ምርጥ ተጫዋች፦
አብሮኝ የተጫወተው የራሱ የሆነ የተለየ
ተአምራዊ ጥበብ ያለው አፈርወቅ (ካቻ)
የእኔ የጨዋታ ዘመኔ ምርጡ ተጨዋች ነው፡
፡ ከአፍወርቅ ሌላ አሁን ፉል ባክ እየተባለ
በሚጠራው ቦታ ተመላላሽ መስመር ላይ
ፎርሜሽኑ ሳይታወቅ ጎልቶ የታየውና ትልቅ
አቅም ለነበረው የባንኮቹ ሸዋረጋ ደስታም
የተለየ አድናቆት አለኝ፡፡ ሸዋ ሲስተሙ
ሳይታወቅ ቦታውን ማስተር ያደረገ ለሲስተሙ
የተፈጠረ ብቻ ሣይሆን ሲስተሙ ለራሱ
ተብሎ የተዘጋጀ ነበር የሚመስለው፡፡ በዚህ
ምክንያት ለእሱ የተለየ አድናቆት አለኝ፡፡

አብሮት ባለመጫወቴ የሚቆጨውው፡-
ካሳዬ አራጌ፣ ካሳዬ በአዕምሮው የሚጫወት
ኳስ ጨዋታን የሚያቀል ተጫዋች በመሆኑ
በወሬ ከምሰማው በዘለለ አብሬው ተጫውቼ
ባይ በጣም ደስ ይለኝ ነበር፡፡
በጨዋታ ዘመንህ በጣም የሚያስቸግርህ
ተጫዋች፡–
እኔ ከምነሳበት መስመር አንፃር
በተለይ በግራ መስመር ላይ አላንቀሳቅስ እያለ
ሲያስቸግረኝ የነበረው ተጫዋች ለመብራት
ኃይል በወቅቱ ሲጫወት የነበረው ፋሲል
(ጭንቅሎ) የተባለው ተጫዋች ነው፡፡ ፋሲል
ጉልበትና አለው፣ ታክሉም በጣም ከባድና
አስፈሪ ስለነበር ለአጥቂዎች በጣም አስቸጋሪ
የነበረ ተጫዋች ነው፡፡
በጨዋታ ዘመንህ በጣም የተከፋህበትና
ልብህ ያዘነበት ቀን፡-
በ1990 ዓ.ም ፕሪሜየር
ሊጉ እንደ አዲስ ሲቋቋም ፌዴሬሽኑ ከተራ
ቁጥር እስከ ተራ ቁጥር ድረስ ያላችሁት
በአንደኛ ዲቪዚዮን ከተራ ቁጥር በታች
ያላችሁት ደግሞ ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን
ወርዳችሃል የሚል ድንገተኛ ውሳኔ
ያሳተላለፈበትና እርሻ ሰብል በዚህ ውሳኔ ወደ
2ኛው ሊግ የወረደበት ጊዜ በእግር ኳስ በጣም
ያዘንኩበትና አምርሬ ያለቀስኩበት አጋጣሚ
ነበር፡፡ ምክንያቱም እርሻ ሰብል አቅም ያለው
ምርጥ ምርጥ የሚባሉ ተጨዋቾችን የየዘ
ቡድን ሆኖ በዚህ ውሳኔ መውረዱ ከልብ ነበር
ያሳዘነኝ::
በጨዋታ ዘመንህ በጣም የተደሰትክበት
ቀን፡-
ብዙ ደስታዎችን አጣጥሜያለሁ፤ ከላይ
እንዳልኩህ እርሻ ሰብል በዚያ መንገድ ወርዶ
በዓመቱ ወዲያውኑ ወደ ከፍተኛ ዲቪዚዮን
ተመልሶ ማየቴ በጨዋታ ዘመኔ ትልቁን ቦታ
የሚይዝ ደስታ ያገኘሁበት ቀን ነው፡፡ ከዚህ
ውጪ ቅ/ጊዮርጊስን አሸንፈን የኢትዮጵያ
ሻምፒዮን የሆንበትና ባይሳካም ሀገር
ለመወከል የበቃንበት እድል ያገኘንበትን ቀን
ሌላው በእግር ኳስ የተደሰትኩበት አጋጣሚ
ነው፡፡
ከሀገር ውጪ የሚያደንቀው አሰልጣኝ፡-
ጋርዲዮላ
ከሀገር ውጭ የሚያደንቀው ተጨዋች፡-
ሜሲ
ከሀገር ውጪ የሚደግፈው ብ/ቡድን፡-
በፍልስፍናቸው፣ ቡድን ላይ መሰረት
ባደረገ አጨዋወቱ የስፔንን ብ/ቡድን ከሌሎች
አስበልጣለሁ፡፡
በመጨረሻ፡-
የኢትዮጵያ እግር ኳስ
ባሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል፡፡ በተለይ
ሙያቸውን አክብረው የሚሰሩ ወጣ ባለ
መስመር ውስጥ ከመጓዝ ይልቅ ትክክለኛውን
መስመር የመረጡ አሰልጣኞች በብልጣብልጥና
በጥቅመኛ ኮሜቴዎች እየተገፉ ሀገራቸውን
እንዳያገለግሉ እየተፈረደባቸው ነው፡
፡ ይሄ ጉዳይ አንድ ቦታ ሊቆም ይገባዋል፡
፡ ፌዴሬሽኑም፣ የአሰልጣኞች ማህበርም፣
ሚዲያውም፣ የስፖርት ቤተሰቡም አምርረው
ሊዋጉትና አንድ ቦታ ሊያቆሙት ይገባል ባይ
ነኝ፡፡ ከዚህ በተረፈ በመጨረሻ ሳልናገር ማለፍ
የማልፈልገው በሙያዬ ሀገሬን ከማገልገል
ወደ ኋላ እንዳልል ሰው ሰራሽ ፈተናዎች
ቢበዙም ለተስፋ መቁረጥ እጅ እንዳልሰጥ
ውስጤን በመረዳት ድጋፍ ለምታደርግልኝ
ባለቤቴ እና ልጆቼ እንዲሁም ከጎኔ በመቆም
ተስፋ የሆናችሁኝን ሁሉ በዚህ አጋጣሚ
ሳላመሰግን አላልፍም፡፡
አስተያየት ይስጡ