የቀድሞ የእግር ኳስ ተጨዋቾችን
በምናስታውስበት የዛሬው የሀትሪክ ስፖርት
ጋዜጣ የOLDIES BUT GOODIES
ዓምዳችን ላይ ይዘንላችሁ የምንቀርበው
ተጨዋች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ
ውስጥ በክለብ ደረጃ ለብሔራዊ አልኮል፣
ለአግሮ ኢንዱስትሪ፣ ለባንኮች፣ ለኤሌክትሪክ
ለብርሃንና ሰላም ከክለብ ተጨዋችነት
ባሻገር ደግሞ በወጣትና በዋናው ብሔራዊ
ቡድን ውስጥ ኳስን በጥሩ መልኩ
በመጫወት ያሳለፈውንና በብዙዎች ዘንድም
የሚታወቀውን ፀጋዬ ወንድሙ ወይንም
ደግሞ ብዙዎች እንደሚጠሩት ፀጋዬ አግሮን
ነው፤ ይህ የቀድሞ ተጨዋች የእግር ኳስን
ካቆመ በኋላ የአሁን ሰዓት ላይ በተሰማራበት
የአሰልጣኝነት ሙያው ስኬታማ ውጤት
እያስመዘገበ ሲሆን ይህም ጉዞውም በበርካቶች
ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን እያስገኘለትም
ይገኛል፡፡
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ እግር ኳስ
ቡድንን በአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን
ስር ከሚወዳደርበት የታችኛው ዲቪዚዮን
ጀምሮ በማሰልጠንና በዓመት በዓመትም
የሻምፒዮናነትን ውጤት በማምጣት የአሁን
ሰዓት ላይ ክለቡን ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ
ተወዳዳሪነት ያበቃው ይኸው ወጣት አሰልጣኝ
ወደፊት በሙያው ትልቅ ደረጃ ላይ ይደርሳል
ተብሎ እምነት የተጣለበት ሲሆን የቀድሞውን
ይህ ተጨዋችና የአሁኑን አሰልጣኝ ጋዜጠኛ
መሸሻ ወልዴ G.BOYS በአጠቃላይ
የስፖርት ህይወቱ ዙሪያ አናግሮት ምላሾቹን
እንደሚከተለው ሰጥቷል፡፡
-ስለ ውልደቱና እድገቱ፡-
“የእኔ
የትውልድም የእድገትም ስፍራዬ ቃሊቲ
ቼራሊያ አካባቢ ነው፤ አሁንም እዛ ነው
እየኖርኩ ያለሁት”፡፡
-የልጅነት አስተዳደጉን አስመልክቶ፡-
- ማሰታውቂያ -
“የልጅነት አስተዳደጌ እንደ አብዛኛው ታዳጊና
ወጣቶች የእግር ኳስን በመጫወት ሲሆን ከዛ
ውጪም እኔን የሚለየኝ ተጨማሪ ነገርም
አለ፤ ይኸውም ወላጅ አባቴ በመኖሪያችን
ቃሊቲ አካባቢ የራሱ የሆነ የእርሻ ቦታ
ነበረውና እሱን በስራ በማገዝ ጭምር ጊዜዬን
አሳልፍ ነበር፤ ስራም ከጨረስኩ በኋላ
በአካባቢያችን በሚገኘው ሜዳ ላይ የዕድሜ
እኩዮቼንና ጓደኞቼንም በማሰባሰብ ኳስን
እጫወትና ትምህርቴንም እማር ስለነበር
በእዚሁ መልኩ ነው ልጅ ሆኜ ያደግኩት”፡፡
-የእግር ኳስን በመጫወትህ የቤተሰብ
ተፅዕኖ ነበረብህ፡-
“በወላጅ አባቴ በኩል
ከሆነ አዎን! ልጅ እያለው በእርሻው ስራ
እንዳግዘው ስለሚፈልግና እኔም ወደ ስራው
ዘልቄ እንድገባና እንድሰማራም ስለሚፈልግ
ኳስን እንድጫወት አይፈቅድልኝም
ነበር፤ በቤተሰባችን አካባቢ ኳስ ጨዋታ
ውጤት የማያመጣ ስለሚመስላቸው እና
ጊዜያዊ ደስታም ማስገኛ ብቻም አድርገው
ስለሚያስቡት እንዳልጫወት እከለከል
ነበር፤ ሆኖም ግን ያኔ አንድ አንዴ ከስራ
ቦታ ላይ እየጠፋው እና አባቴ ያዘዘኝንም
ስራ አልፎአልፎ ባለመሥራት ኳስንም
የምጫወትበት ጊዜም ነበርና ያ በጣም ትዝ
ይለኛል፤ ወላጅ እናቴ ግን በጊዜው ለቤቱ
ብቸኛው ወንድ ልጅና የመጨረሻውም ልጅ
ስለነበርኩ እኔን ከመውደዷ የተነሳ ብዙ ነገሬን
አባቴ እንዳያውቅ በማድረግና በመደበቅ ጭምር
በጥሩ ሁኔታ ትንከባከበኝም ስለነበር የእሷ
እገዛም ታክሎበት ነው ወደ ኳሱ እንዳዘነብል
ያደረገኝ፤ ወላጅ እናቴ አሁን ላይም የእኔን
በአሰልጣኝነት ሙያው ውጤታማ ሆኜ ስታይና
እዚህም ደረጃ ላይ ከደረስኩ በኋላ “አባትህ
ያኔ ኳስ አትጫወት ብሎ ሲከለክልህ አሁን
እንጀራ ሆነህ አይደል” እያለችም በትዝታ
ወደ ኋላ እየመለሰችኝ ያለበት ሁኔታም ስላለ
ይሄ በጣሙን ያስደስተኛል፤ በነገራችን ላይ
ወላጅ አባቴም ፈጣሪ ነፍሱን ይማረውና ከ7
ዓመት በፊት በሞት ይለየኝ እንጂ በህይወት
በነበረበት ሰዓት በኳሱ ወደ ክለብ ገብቼ እና
ለብሔራዊ ቡድንም ተመርጬ ጥቅምና ዝናን
እያገኘሁ በመጣሁበት ሰዓት እሱም ደስ
ብሎት የእኔን ጨዋታ ከመመልከት ባሻገር
በሞራል ደረጃም የሚያበረታታኝም ጊዜም
ነበርና በእዚሁ አጋጣሚ እናቴንም አባቴንም
ለማመስገን እፈልጋለሁ”፡፡
-የእግር ኳስን በእዛን ወቅት ስትጫወት
የቤተሰቦችህ ድጋፍ አይዞህ እና በርታ
የሚል የሞራልና የቃላት ሙገሳ ብቻ ነበር፡-
“አይደለም፤ ከላይ እንደገለፅኩልህ ቤተሰቦቼ
እርሻ አላቸው ብዬካለው፤ ከእዛ ውጪ ደግሞ
ብዙ ከብቶች እና /ላሞች/ ስለነበሩን ከእነሱ
የሚገኙትን የወተት ተዋፅኦዎችን ኳስ
ተጨዋች እንደመሆኔ መጠንና ብዙ ላብም
በሜዳ ላይ ስለማፈስ ወተቱ ጉልበት ይሆንሃል
በሚል እየሰጡኝና እየጠጣውም በሚገባ
ይንከባከቡኝም ስለነበር ጠንካራ ተጨዋች
ለመሆኔም የእነሱ አስተዋፅኦ ከፍ ያለ ነውና
የአባቴም የእናቴም ውለታ የማይረሳ ነው፤
በእናቴ በኩል በተለይ ከሚታለቡት ላሞቻችን
መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ ልጅ የምትወልደውን
የጊደር ላም ወተት በትኩሱ ሳይፈላ ከፍተኛ
ጉልበት ይሆንሃል ብላ የምትሰጠኝም ጊዜ
ነበርና የእውነትም ወተቱ ጠንካራ ተጨዋች
እንድሆንም ነው ያደረገኝ”፡፡
-የእግር ኳስን ከእናንተ ቤተሰብ ውስጥ
የምትጫወተው አንተ ብቻ ነህ? ስንት
ወንድምና እህትስ አለ?፡- “የቤተሰባችን አባላት
ውስጥ ከእኔ ውጪ ሁለት እህቶች ናቸው
ያሉኝ፤ ብቸኛው ስፖርተኛም ኳስ ተጨዋቹም
እኔ ብቻ ነኝ፤ ከዚህ በፊት የእህቴ ልጅ
የመረብ ኳስ ጨዋታን ትሞክር ነበርና እሷ
አቁማለች”፡፡
–የእግር ኳስን በሰፈር ደረጃ ለማን
ለማን ቡድኖች ተጫወትክ?፡-
“በሰፈር
ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የእግር ኳስን
የተጫወትኩባቸው ክለቦች የመጀመሪያው
ባራካ ወይንም ደግሞ አካባቢያችን ቃሊቲ
ከመባሉ በፊት በጣሊያንኛ አጠራር
ለምንጠራው የኮነናልቤ ቡድን ነው፤ ከእዛ
በኋላም ትንሽ እያደግን ስንመጣ ለቼራሊያ
በ1979 እና ለቆርኪ ቡድኖች 1980 ዓ.ም
ላይ ተጫውቻለው”፡፡
-የእግር ኳስን መጫወት ስትጀምር
ለመጀመሪያ ጊዜ ያደነቅከውና ተምሳሌት
ያደረግከው ተጨዋች፡-
“የቀድሞ የትግል
ፍሬ ተጨዋች የነበረው ንጉሴ አስፋው
ለእኛም የአካባቢ ቡድን ቼራሊያ ተጫውቶ
ነበርና እሱን ነው ልጅ ሆኜ በሰፈር ደረጃ
ስመለከተው አድንቄ ያደግኩት”፡፡
-የእግር ኳስን ትላልቅ በሚባሉ ቡድኖች
ደረጃስ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጫወትከው፡-
“በአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስር
በተመዘገበው የብሔራዊ አልኮል እግር
ኳስ ቡድን ውስጥ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ
የተጫወትኩት፤ እዛም በ1981 ዓ.ም ላይ
የገባሁት የረጅም ጊዜ ምርጫን በወሰደውና
500 የሚደርሱ ተጨዋቾችም ሙከራ
ባደረጉበት ሁኔታ ከእነዛ ውስጥ አራት ሰው
ሲመረጥ አሰልጣኛችን በነበሩት
አቶ አበራ ሀብቴ አማካኝነት
ተመልምዬ ነው ወደ ቡድኑም
የገባሁት፤ በክለቡም ለሁለት
ዓመታት ያህልም ተጨዋትኩና
በማስተር ቴክኒሺያን ሀጎስ ደስታ
ተመርጬ የአግሮ ኢንዱስትሪ
ቡድንን በመቀላቀል ከ1983
ዓ.ም እስከ 1985 ዓ.ም ድረስ
ለመጫወት ችያለው”፡፡
-የእግር ኳስን ለመጀመሪያ
ጊዜ ስት ጫወት የተከፈለህ
ደመወዝ፡-
“100 ብር ነበር፤
ይሄንንም ደመወዝ ያገኘሁት
ለመጀመሪያ ክለቤ ብሔራዊ
አልኮል ስጫወት ነው”፡፡
-የመጀመሪያ ደመወዝህ ምን
ላይ ዋለህ?፡-
“መቶ ብሩ ያን ጊዜ
ትልቅ ዋጋ የነበረውና ወቅቱም
የፍቅር ጊዜ ስለነበር ለመጀመሪያ
ጊዜ ደመወዜን ስቀበል ብሩን
ያዋልኩበት ሁኔታ አሁንም ድረስ
በጣም ነው የሚገርመኝ፤ በጊዜው
የመጀመሪያ ደመወዜን ከመቀበሌ
በፊት ብዙ ጊዜ ወደ ልምምድ
ስፍራ ከቃሊቲ በመነሳት ለገሀር
ወደሚገኘው የባቡር ጣቢያው
አውቶብስ ፌርማታ ድረስ ወደ
ትሬሊንግ ስፍራ ለመሄድና
ልምምድም ሰርቶ ወደ ቤት
ለመመለስ በየቀኑ ከእናቴ 60
ሳንቲም በመቀበል 30 ሳንቲሙን
ለመሄጃ 30 ሳንቲሙን ደግሞ
ለመመለሻ እጠቀምም ስለነበር
ያንን የእናቴን ውለታ በማሰብ
ነው የ100 ብሩን እንደተቀበልኩ
50 ብሩን ለእሷ ከሰጠዋት በኋላ
የተቀረውን 50 ብር ደግሞ 1
ጫማና በጊዜው ሊ የሚል የጂንስ ሱሪ ነበርና
እሱን ነበር የገዛሁበት፤ ደመወዛችን ከመቶ
ብር አድጎልን 150 ብር በሆነልን ሰዓት
ደግሞ እንዲሁ ብሩን ለእናቴ ከመስጠት
ባሻገር በጊዜው ቀይ ወጥ በብር ከ50ም
ይሸጥ ነበርና የእኔ ደመወዝተኛ መሆንን
ብዙዎቹ ሰምተውና ደስ ብሏቸውም ስለነበር
ከእነሱ ጋር ምግብ ቤት በመሄድ በጋራ
ብሩን እንመገብበትም ነበርና ያኔ የወርሃዊ
ብሩን ስቀበል በቤተሰባችን በኩልም ልጃችን
ደመወዝተኛ ሆነ በሚል ይነገርልኝም ነበርና
እነዚህ ሁኔታዎች የማይረሱኝ ናቸው”፡፡
-በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ
ለብሔራዊ አልኮልና ለአግሮ ኢንዱስትሪ
ከተጫወትክ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ክለብ የገባክበት ሁኔታ፤ በቡድኑ የነበረክስ
ቆይታ ምን ይመስላል?፡-
“የኢትዮጵያ ንግድ
ባንክ እግር ኳስ ክለብ ውስጥ ኳስ ተጨዋች
ሆኜ የገባሁት የአግሮ ኢንዱስትሪ ቡድን
ውስጥ በነበረኝ የሁለት ዓመታት ቆይታዬ
በሜዳ ላይ ጥሩና አበረታች የሆነ ብቃትን
በማሳየቴ በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ተፈልጌ
ነው፤ እሱም ለቡድኑ ከመለመለኝ በኋላ
በቀጥታ ሄጄ ፊርማዬን ላኖር ችያለው፤ ያኔ
ከአግሮ በመምጣት ወደ ቡድኑ የገባሁትም
የደብረ ዘይት ልጅ ከሆነውና የቡድናችን
ተጨዋች ከነበረው ቶሎሳ ኃይሌም ጋር
ነበርና ወደ ክለቡ ስገባ በጣም ነበር ደስ
ያለኝ፤ የባንክ ቆይታዬን በተመለከተ ጥሩ
ጊዜን ነው በተጫወትኩባቸው ወቅቶች
ያሳለፍኩትና በጣም የምወደው ቡድኔ ነው፤
ያለ ምክንያትም ለ9 ዓመታት ያህል ኳስን
በክለቡ አልተጫወትኩም፤ የአሁን ጊዜ
ተጨዋቾች ብዙ ጊዜ ለሁለት ዓመታት ያህል
ነው በአንድ ቡድን ውስጥ የሚቆዩት እና
እኔ ለእዚያን ያህል አመት ሁሉ መጫወቴ
ደስ ሊለኝም ችሏል፤ የባንክ ቆይታዬ ላይ
ሌላው የማልረሳውና የተደሰትኩበት ነገር
ቢኖር በእኛ ጊዜ ኳሱን ስንጫወት አንተ ላይ
ፕሬዠር ፈጥሮ የሚያጨናንቅህ ነገር እና
አንድም ሰውም የለም ነበርና ብዙዎቻችን
ተጨዋቾች ለ10ም ለ11 ዓመታትም ያህል
በቡድኑ ውስጥ በወወክማ እየኖርንና እንደ
ወንድማማቾችም በመተያየትና በመወያየትም
ቋሚ ሰራተኛ እስከመሆን ጭምር ኳስን
የተጫወትንበትም ጊዜ ስለነበር ይሄ የክለቡ
ምርጥ ትዝታዬና ጥሩ ጊዜዬን ያሳለፍኩበት
ቆይታዬ ነው”፡፡
-በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ በጣም
የተደሰትክበት ቀን፡- “በተጨዋችነት ዘመኔ
ምርጡና መቼም ቢሆን የማልረሳው የደስታዬ
ቀን የባንክ ተጨዋች እያለው ያጋጠመኝን
ነው፤ ያኔ ቡድናችን የ1987ቱን ዋንጫ
አጥቶ ነበርና ለ1988ቱ የውድድር ዘመን
ቡድናችንን እንዲያሰለጥን ኢንስትራክተር
መንግስቱ ወርቁ በክለባችን ተቀጥሮ ነበርና
በእሱ ቡድን ውስጥ እያለውና መጫወትም
በጀመርኩበት ሰዓት እሱ ቡድኑን
በሚፈልገው መንገድ ለመገንባት በማሰቡ
በርካታ ሲኒየር ተጨዋቾችን በክለቡ ውስጥ
አልፈልግም በማለቱና እንዲለቁም በመፈለጉ
እኔም የእዚሁ አካል አንዱ ተጨዋች ሆኜ
የክለባችንን ኮሚቴዎች መልቀቂያ እንዲሰጡኝ
ባናገርኳቸው ሰዓት አንተ ከቡድኑ አትለቅም
በውሰት እንድትሰጥ ትደረጋለህ ብለውኝ ወደ
መብራት ኃይል በውሰት እንድሄድ ከተደረግኩ
በኋላ በመንግስቱ ወርቁ የሚመራው ቡድን
ውጤት እያጣ በመሄዱና እሱም ከክለቡ
ስድስተኛው ወር ላይ እንዲለቅ ከተደረገ በኋላ
በመጨረሻው አጠቃላይ ውጤትም ቡድናችን
መውረዱ ቢረጋገጥም ወዲያው የእግር ኳስ
ፌዴሬሽኑ በአዲስ ፎርማት የክለቦች ቁጥርን
እንጨምር የሚል ውሳኔ ላይ በመድረሱ እኛ
ውጤት ባጣነው ኪቤአድና እኛ ከታችኛው
ዲቪዚዮን ደግሞ የማለፍ እድሉን ባላገኙት
ቡድኖች ኒያላና አቃቂ ብረታ ብረት ቡድኖች
መካከል በአዲስ አበባ ከፍተኛ ሊግ ላይ ገብቶ
ለመጫወት በተደረገው የ4 ቡድኖች ውድድር
ላይ እኛ ኒያላን አሸንፈን ኪቤአድም እኛን
ተከትሎ ወደታችኛው ዲቪዚዮን ሳይወርድ
ቀርቶ ነበርና ያ ቀን በእኔ የተጨዋችነት
ዘመን ክለቤ ያልወረደበት ጊዜ ስለነበር በጣም
ደስ ሊለኝ ችሏል”፡፡
-የባንክ ክለብ በውሰት ሰጥቶህ እንዴት
ነው በድጋሚ ለቡድኑ ልትጫወት የቻልከው?፡
–
“የባንኮች ክለብ ውስጥ በነበረኝ ቆይታ
አሰልጣኛችን ኢንስትራክትር መንግሥቱ
ወርቁ እኔንና ሲኒየር የሆነውን ሌሎች
ተጨዋቾችን አልፈልግም ብሎ በቀነሰበት
ሰዓት እና በተለይ ደግሞ እኔ ለክለቡ ሶስት
ያህል ጨዋታዎችን አድርጌ በአንድ ስታዲየም
በተደረገ ጨዋታ ላይ በረኛውን አልፌ ወደ ግብ
ስመታ እና ኳሷም አግዳሚ
ብረቱን መልሳ ስትመጣ
ሆን ብሎ ነው የሳተው ብሎ
ከቡድኑ ሲቀንሰኝ የክለቡ
ኮሚቴዎች ኧረ ፀጋዬ እንደህ
አይነት ሰው አይደለም
ቢሉትም እኔ አልፈልገውም
ባለ ሰዓት መልቀቂያ
እንዲሰጡኝ ብጠይቅም እነሱ
ለአንተ አንሰጥህም በሚል
በውሰት ወደ መብራት
ኃይል በመንግሥቱ ወርቁ
በሚፋለገው የክለቡ ተጨዋች
ሰይፉ ውብሸት /ፕሮም/ ጋር
ተቀያይረን ወደዚያ ካመራው
በኋላ መንግሥቱ ወርቁ
ቡድናችንን ተረክቦና ውጤት
እያጣ በሄደበት ሰዓት በ6 ወር
ጊዜ ውስጥ ከክለቡ እንዲለቅ
በተደረገበት ጊዜ ነው
እኔም ወደ ባንክ ሰይፈም
ወደ መብራት ሊመለስ
ችሎ የ1988ቱን ቡድን
በድጋሚ ተቀላቅዬ ልጫወት
የቻልኩት፤ በነገራችን ላይ
በኢትዮጵያ የእግር ኳስ
ተጨዋቾች ታሪክ እኔና ሰይፈ
በውሰት ተሰጥተን ተቀያይረን
ስንጫወት የመጀመሪያዎቹም
ነን”፡፡
-በእግር ኳስ
ተጨዋችነት ዘመንህ በጣም
ያዘንከውና ልብህ በሀዘን
የተሰበረበት ቀን፡-
“ያንን ጊዜ
መቼም ቢሆን አልረሳውም፤
በ1987ቱ ጠንካራው እና
አይበገሬው የባንክ ቡድን
ውስጥ እየተጫወትኩና
ቡድኑንም በካፒቴንነት
እየመራው በነበረ ሰዓት ወደ
ሻምፒዮናነቱ እያመራን ስንሄድ ከመድን ጋር
በተደረገው ጨዋታ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ
እንደሆነ የሚታወቀው አልቢትር ኪነ-ጥበቡ
እኔ ምንም ጥፋት ባላጠፋሁበት ሁኔታ ከሜዳ
በቀይ ካርድ እንድወጣ አድርጎኝ ከቅዱስ
ጊዮርጊስ ጋር የነበረው የመጨረሻ ቀን ጨዋታ
ላይ ቡድኔን እንዳልጠቅምና እንዳልሰለፍ ሆን
ብሎ ያደረገበት ሁኔታ በጣም ያሳዘነኝና
ያስቆጨኝ ሆኗል፤ ሌላው የማይረሳኝ የሀዘን
ቀኔ በእዚያው የውድድር ዓመት ላይ ከመድኑ
ጨዋታ በኋላ የነበረው የፍፃሜው ግጥሚያ
እኛ ዋንጫውን ለማንሳት ሁለትና ያን ዕለት
ደግሞ ቀድመን የመሪነት ጎል አስቆጥረን
ስለነበር ሶስት እድል ይዘን ገብተን በቅዱስ
ጊዮርጊሶች 3-1 በመሸነፍ ዋንጫውን ስናጣ
በጣም ነበር የተከፋሁት”፡፡
-በመድኑ ጨዋታ በቀይ ካርድ የወጣሁት
አለአግባብ ነው ስትል ሁኔታውን እስኪ
በደንብ አስረዳን፡-
‘‘አዎን በእዛን እለቱ
የመድን ጨዋታ ኪነጥበቡ እኔን በቀይ
ያስወጣኝ ዓመቱን ሙሉ በጥሩ ብቃት
ላይ እገኝና ሳላቀየርም የተጫወትኩበት
እና ትልቅ ደረጃም ላይ የደረስኩበት ጊዜ
ስለነበር የዋንጫው ቀን እንዳልገባና ቡድኔን
እንዳልጠቅም ነው ከሜዳ ያስወጣኝ፤ ያን
ዕለት እሱ በሚወስናቸው ውሳኔዎች እኛን
እየበደለን ስለነበር እንደ ቡድኑ ካፒቴንነቴ
ለምን በአግባቡ አታጫውተንም ስለው ነው
እረፍ አለኝና ካፒቴን ነኝ እኮ አንተን ማናገር
እችላለው ስል በቀይ ያስወጣኝና ያን በሀዘንነቱ
ነው የምገልፀው”
-በእግር ኳስ ተጨዋችነትን ዘመንህ
የአንተ ምርጡ ጨዋታ፡-
“በባንክ የተጨዋችነት
ቆይታዬ የማክሰኞ ማታ ማታ ጨዋታዎች
በተለይ ደግሞ ከቡና ጋር የምናደርጋቸው
ግጥሚያዎች ሁሌም የሚመቹኝና ምርጦች
ናቸው፤ ቡና በእዛን ጊዜ ፈጣኑን ተጨዋች
ሚሊዮን በጋሻውን፣ ሳምሶን ሽፈራውን /
ጆሮ/፣ ገብረ ኪዳን ነጋሽ ጋምብሬን እና ግብ
ጠባቂውን አብዱ ሳለን /ፊቱሼ/ የመሳሰሉ ጥሩ
የተጨዋቾች ስብስብን ይዞ ስለነበር ከእነሱ
ጋር ያደረግነው ጨዋታ በጣም የሚያምር
ነበር፤ የቡና ደጋፊዎች በጊዜው ግጥሚያው
ስቧቸውም በጨዋታው ለእነሱም ለእኛም
ነበር የሚደግፉት፤ ሆኖም ግን መጨረሻ ላይ
በስዩም አባተ አሰልጣኝነት የሚመራው የእኛ
ቡድን ግጥሚያውን 3ለ1 ሊያሸንፍ ከመቻሉ
ባሻገር በጊዜው የስፖርት ፕሮግራምን በሬዲዬ
ያቀርብ የነበረው ታዋቂው ጋዜጠኛ ደምሴ
ዳምጤም የቡድናችንን ጥሩ ብቃት ተመልክቶ
ይሄን ቡድን ነው ብሔራዊ ቡድን ማድረግ
በሚልም አስተያየት የሰጠበት ወቅትም
ነበርና ቡድናችን ያን ጨዋታ ሊያሸንፍ
በመቻሉ የተለየ የደስታ ስሜት ነበር በውስጤ
ሊፈጠርብኝ የቻለው”፡፡
-በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ የአንተ
ምርጡ አሰልጣኝ፡-
“ማስተር ቴክኒሺያን ሐጎስ ደስታን ነው ፈጣሪ ነፍሳቸውን ይማረውና
በቀዳሚነት የማስቀምጣቸው፤ ጋሽ ሐጎስ
በአሰልጣኝነት ሕይወቱ ብዙ ነገርን ያሟላ ነው፤
የአግሮ ቡድን ውስጥ ልጅ ሆኜ በምጫወትበት
እና በሚያሰለጥኑኝም ሰዓት ችሎታዬን
ተመልክተው የእኔ የወደፊት መድረሻዬን
በመተንበይ ትልቅ ደረጃ ላይ እንደምደርስም
ይነግሩኝ ነበርና ያንን በተግባር ላይ አውዬ
እስከብሄራዊ ቡድን ደረጃ ተጫውቻለው፤ ጋሽ
ሐጎስ በጊዜው እያሰለጠኑን በነበረ ሰዓትም
እኔን ክፍሉ መብራቱንና ዳንኤል ለገሰንም
ያደንቁን ስለነበር ፀጉራችንን እያሻሹም
የሚያበረታቱንም ሁኔታ ነበርና እሳቸውን
ነው የማደንቀው፤ ከእሳቸው ውጭ ሌሎች
የማደንቃቸው አሰልጣኞች የእኔን ችሎታ
በሚገባ የተረዳውን ወርቁ ደልገባን እና
ለተጨዋቾች ከፍተኛ ነፃነት በመስጠትና
በአስተዳደር ችሎታውም የሚደነቀውን
ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻውን ነው”፡፡
-በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ
የአንተ ምርጡ ተጨዋች፡-
“ሲጫወት
ባልደርስበትም፤ ባልመለከተውም ከሰዎች
ስለ ነበረው ችሎታ ከሰማዋቸው ነገሮች
በመነሳት መጀመሪያ ያደነቅኩት ተጨዋች
ቢኖር የኢትዮጵያ ቡናውን አጥቂ ሙሉጌታ
ወልደየስን ነው፤ ሲጫወት ተመልክቼው
ደግሞ በጣም ያደነቅኩት ተጨዋች ኤልያስ
ጁሀርን ነው፤ ኤልያስ በጣም ፈጣን፣ ደፋርና
ጥሩ ክህሎት ያለው ተጨዋች ስለነበር እሱን
ነው በዋናነት የማደንቀው”፡፡
-በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ
ከአጠገብህ ሆኖ ሲጫወት በጣም የተስማማክና
ምቾት የሰጠህ ተጨዋች፡-
“በጣም ተስማምቶኝ
አብሬው የተጫወትኩት ተጨዋች የባንክ ክለብ
ውስጥ በአማካይ ቦታ ላይ ምርጥ ብቃቱን
ያሳይ የነበረው ይሁኔ ታዬ ነው፤ ከይሁኔ ጋር
አብረከው ስትጫወት በእንቅስቃሴ ደረጃ ኳስን
ሳትጨናነቅ እንድትጫወት ስለሚያደርግክና
የጥሩ ክህሎት ባለቤት ስለሆነም እሱን ነው
በዋናነት የማደንቀውም፤ የሚመቸኝም፤
ሌላው የተመቸኝ ተጨዋች ቢኖር በብሔራዊ
ቡድን ውስጥ አንድ ጊዜ አግኝቼው ነበርና
ካሳዬ አራጌ ነው፤ ከሁለቱ ጋር መጫወትም
የተለየ ደስታንም ይሰጣል”፡፡
-በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ
አብረከው ባለመጫወትህ የሚቆጭህ
ተጨዋች፡-
“የብሔራዊ ቡድን ውስጥ ካሳዬ
አራጌን ለአንድ ጊዜ ብቻ ያገኘሁት ስለሆነ
ከእሱ ጋር በክለብ ደረጃ አብሬው ባለመጫወቴ
ይቆጨኛል፤ ካሳዬ በተጨዋችነት ዘመኑ
የተለየ አህምሮን ከኳስ ስኪል ጋር አጣምሮ
የያዘ ተጨዋች ስለሆነ ሁሌም አብሬውና
ደጋግሜም ልጫወት ብዬም የምመኘው
አይነት ተጨዋች ነበር”፡፡
-በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ
የተቃራኒ ቡድን ተጨዋች ሆኖ ያስቸገረህ፡
–
“በጣም ያስቸገረኝ ኤልያስ ጁሀር ነው፤
እሱ ሲያጠቃ በጣም ፈጣን፣ የማይያዝና
የማይጨበጥም ተጨዋች ስለሆነ ብዙ ጊዜም
እያመለጠኝም ያስቸግር ነበርና እሱን ነው
የማነሳው፤ ሌላው አስቸጋሪ ተጨዋች የነበረው
ደግሞ ጌታቸው ካሳ /ቡቡ/ ነው፤ ቡቡ ጥሩ
ችሎታ ቢኖረውም ከእኔ ጋር በምንፋጠጥበት
ሰዓት በጉልበት በጣም እንፈታተን ነበርና
በኋላ ላይ አላሳልፍ ስለው ዳኛ ሳያየው በጥፊ
ሁሉ የመታኝ ጊዜ ነበርና እሱም ያስቸግረኝ
ነበር”፡፡
-ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመጀመሪያ
ጊዜ ሲመረጥ እና ስለተሰማው ስሜት እንዲሁም
ስለመጀመሪያ ጨዋታው፡-
“የኢትዮጵያ
ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ
የተመረጥኩት በወጣት ቡድን ደረጃ በ1986
ዓ.ም ላይ በአሰልጣኝ ስዩም አባተ አማካኝነት
ነው፤ በዓመቱም ይሄ ቡድን እንደ አዲስ እና
እንደ ሁለተኛ ብሔራዊ ቡድንም ተገንብቶ
በአሰልጣኝ ታምሩ ሙሉጌታና ልዑል ሰገድ
በለጠ አማካኝነትም በድጋሚ ልመረጥና
ልጫወት ችያለው፤ በወጣት ቡድን ደረጃውም
ለመጀመሪያ ጊዜ የተጫወትኩት ከዛምቢያ
ጋር በተደረገው ጨዋታ ሲሆን እንደ አዲስ
በተገነባው ቡድን ውስጥ ደግሞ ለመጀመሪያ
ጊዜ ያደረግኩት ጨዋታ ወደ አስመራ
በመሄድ ከኤርትራ ብሔራዊ ቡድን ጋር
ያከናወነውን ነው፤ በዋናው ብሔራዊ ቡድን
ደረጃ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረጥኩት
በአሰልጣኝ ወርቁ ደልገባ አማካኝነት ነው፤
የመጀመሪያዬ ጨዋታም ሆኖ የተመዘገበልኝ
እነ ካሳዬ አራጌንና አንዋር ያሲንን የመሳሰሉ
ድንቅ የአማካይ ስፍራ ተጨዋቾችን በያዘው
የብሔራዊ ቡድን ውስጥ እነ ሆሳም ሀሰንና
መሐመድ አልካስን ከያዘው የግብፅ ብሔራዊ
ቡድን ጋር የተጫወትንበትን እና ጥሩም
ተንቀሳቅሰን 1-1 የተለያየንበት ጨዋታ
ነበርና ያን ግጥሚያ በጣም የማስታውሰውና
የተደሰትኩበት ነው፤ ያኔም ለብሔራዊ ቡድኑ
ስመረጥ የስማችን ዝርዝር የአዲስ አበባ
ስታዲየም ላይ ጨዋታ እየተከናወነ ይጠራ
ነበርና እኔ ከማን አንሼ በሚባለው ስፍራ ላይ
ኳስ እየተመለከትኩ ሳለው ስሜ ሲጠራና
የሚያውቁኝም ሰዎች ወደ እኔ ዞር ብለው
በደስታ ሲጮሁ እኔም በጣም የተደሰትኩበት
አጋጣሚን የማልረሳው ነውና ለብሔራዊ
ቡድን መመረጥ መቻል ያለውን ጥቅም
ያወቅኩትም ያኔ ነው”፡፡
-ፀጋዬ አግሮ ራሱን በ3 በተመረጡ
ቃላቶች ሲገልፅ፡-
“የተጨዋችነት ዘመኑ
ላይ ለአሰልጣኞች ታዛዥና የተሰጠውን ስራ
በአግባቡና በውጤታማነት ጨርሶ የሚሰራ፣
ትሁት፣ ለሰው መልካም ነገሮችን የሚያስብ፣
ለኢትዮጵያ የኳስ እድገትም ወደፊት ደከመኝና
ሰለቸኝ ሳይልም ራሱን በሙያ በማሻሻልና
ታታሪ ሆኖም በመስራት ለውጥን የሚናፍቅ
አይነት ሰው ነው”፡፡
-ከዋናው እና ሙሉ ስምህ ፀጋዬ ወንድሙ
ይልቅ ፀጋዬ አግሮ ተብሎ ስለመጠራቱ፡-
“አዎን፤ ብዙዎች ፀጋዬ አግሮ ብለው ነው
አሁንም ድረስ የሚጠሩኝ፤ በእዚሁ ስምም
ልጠራ የቻልኩት የአግሮ ቡድን ውስጥ
በነበርኩበት ሰዓት ፀጋዬ የሚባል ግብ ጠባቂ
ነበርና ሁለታችንን ለመለየት ሲባል ነው
ለእኔ ፀጋዬ አግሮ የሚለው ስም ተሰጥቶኝ
ልጠራበት የቻልኩት፤ አግሮ በሚለው ስም
ልጠራ መቻሌ ክለቡ አሁን ላይ ባይኖርም
በእኔ አግሮ በሚለው መጠሪያ ስም ሁሌም
እንዲታወስ ስላስቻልኩትና ለእኔ ጥሩ
ቡድኔም ስለነበር ስያሜው በጣም ነው
የሚያስደስተኝ”፡፡
-ስለ ትዳር ሕይወትህ እና ስለ ልጆችህ፡-
“የትዳር ህይወቴ መልካም እና ጥሩ የሚባል
ነው፤ የሰፈሬ ቃሊቲ ልጅ ከሆነችው ባለቤቴ
የሺ ተካ ጋር በመሰረትነውም ትዳር የሶስት
ልጆችን ልናፈራ ችለናል፤ በቆይታችንም
ያፈራናቸው ልጆች የ18 ዓመት ዕድሜ
ያለውንና አሁን በቻይና ዩንቨርስቲ ውስጥ
እየተማረ ያለው ስሞኦን ፀጋዬ የ13 ዓመቱ
ናትናኤል ፀጋዬ እና የ6 ዓመቱ ዮናታን
ፀጋዬ ይባላሉ”፡፡
-ከእግር ኳስ ጋር ስለተለያያበት እና
ጫማውን ስለሰቀለበት ምክንያት፡-
“የእግር
ኳስን ላቆምና ጫማዬን ልሰቅል የቻልኩት
በብሔራዊ ቡድን የተጨዋችነት ዘመኔ ላይ
ከእነ ጳውሎስ ጌታቸው /ማንጎ/ ጋር ተመርጬ
የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድንን በገጠምንበት
ሰዓት አጥቂያቸው ራሺድ ያኪኒን ኳስ
ለማስጣል ከኋላ ታክል በገባሁበት ሰዓት
ጉልበቴ ተናግቶ ነበርና ከእዚያ ጊዜ ጀምሮ
የተለያዩ ህክምናን በሀገር ውስጥ እያደረግኩና
መርፌም እየተወጋው የእግር ኳሱን እስከ
ብርሃንና ሠላም ቡድን ተጨዋችነት ድረስ
ላስኬደው ብችልም በኋላ ላይ ህመሙ
እየባሰብኝ ሲሄድ ኳሱን ለአንዴና ለመጨረሻ
ጊዜ ላቆም ቻልኩ”፡፡
-የእግር ኳስን በማቆም ወደ አሰልጣኝነት
ሙያው ሊመጣ ስለቻለበት ሁኔታ፡-
“የእግር ኳስን እንዳቆምኩ ወደ አሰልጣኝነት
ሙያው ለመምጣት የቻልኩት ለሀገሬ
ስፖርት እንደተጨዋችነቴ ሁሉ አንድ
አስተዋፅኦ ላበርክት በሚል እሳቤ ነው፤ ወደ
አሰልጣኝነቱም ለመጀመሪያ ጊዜ የመጣሁት
በ1996 ዓ.ም ላይ ነው፤ ያኔም በሙያው
ስራዬን የጀመርኩት በቃሊቲ አካባቢ የራሴን
የኳስ ማሰልጠኛ ፕሮጀክትን በመክፈትና
ታዳጊ ወጣቶችንም በሁለት የእድሜ ካታጎሪ
ማለትም ከ10-13 እና ከ14-17 ያላቸውንም
ልጆች በማሰልጠን ነው፤ የኳስ ማሰልጠኛው
የፕሮጀክት ስምም በ1992 ዓ.ም ላይ ትዳር
በያዝኩበት ጊዜ ተወልዶ በነበረው የመጀመሪያ
ልጄ ስምኦን ስያሜ “ሲማ የእግር ኳስ
ፕሮጀክት ማሰልጠኛ” በሚል ይጠራም ነበርና
በዚህ መልኩ ነው ስልጠናን የጀመርኩት“፡፡
-ወደ አሰልጣኝነት ሙያው ጠልቀህ ከገባህ
በኋላስ ማንን ማንን ቡድኖች አሰለጠንክ፡-
‘‘በአሰልጣኝነት ሙያው ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ
ሳሰለጥን በኃላፊነት የመራዋቸው ክለቦች
በሴቶች ደረጃ የቼራሊያ፣ የምርት ገበያ እና
የመከላከያ የሴቶች ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት
በወንዶች ቡድን ደረጃ የመድን ቡድንን
ከአባይነህ ጋር ረዳት ሆኜ እንደዚሁም ደግሞ
አሁን የማሰለጥነውን የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ
ከተማ ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት ከአዲስ
አበባ አንደኛ ዲቪዚዬን ጀምሮ በኢትዮጵያ
ታሪክ በየዓመቱ ዋንጫን እያነሳ አሁን ቡድኑ
እስከሚገኝበት ከፍተኛ ሊግ ደረጃ ያደረሰም
አሰልጣኝ የለምና በዚህ መልኩ ነው ቡድኖቹን
ያሰለጠንኩት”፡፡
-በአሰልጣኝነት የሙያ ቆይታው
አሰልጥኖ ጥሩ ደረጃ ስላደረሳቸው ተጨዋቾች፡
–
“ብዙ ተጨዋቾች ቢኖሩም የታዳጊ ዕድሜ
ላይ ሳሉ ራሴ ባቋቋምኩት የሲማ ፕሮጀክት
ውስጥ አሰልጥኜያቸው እስከ ፕሪምየር ሊግ
ደረጃ የተጫወቱት ተጨዋቾች አሁን ወደ
ቡና የገባው ዳንሄል ደምሴ፣ ለአዳማ ከነማ
የሚጫወተው ሲሳይ ቶሌ እና ለመድን
ይጫወቱ የነበሩት ወሰኑ ዓሊና ጌትነት
ታፈሰ ናቸው፤ ወሰኑ አሁን ፕሪምየር ሊጉን
ለተቀላቀለው ለባህር ዳር ከነማ እየተጫወተ
ይገኛልና እነዚህን የመሳሰሉ ተጨዋቾችን
ለማፍራት በመቻሌ በጣም ደስ ይለኛል”፡፡
-ወደ ደቡብ አፍሪካ ተጉዞ ስላደረገው
ህክምናና ስላገጠመው ሁኔታ፡-
“አዎን፤
በአንድ ወቅት በድርጅታችን ባንኮች የሙሉ
ወጪ እገዛና ድጋፍ ወደ ደቡብ አፍሪካ
በመሄድ ህክምናዬን አድርጌ ነበር፤ ያኔም
የግራ እግሬን ለመታከምም ነበር የሄድኩት፤
ሆኖም ግን እዛ ከተጓዝኩ በኋላ ለአንዱ እግሬ
ሄጄ ስታከም የቀኝ እግሬም ችግር እንዳለው
በዶክተሮች ተነግሮኝ ሁለቱንም እግሬን ቀዶ
ጥገና አድርጌ የተመለስኩበት ገጠመኝ መቼም
ቢሆን የማልረሰው ነው”፡፡
-የባንኮች ድርጅት ውስጥ የአሁን ሰዓት
ላይ ስለሚሰረው ስራ፡-
‘‘የባንኮች ድርጅት
ውስጥ አሁን ላይ እየሰራው ያለሁት በውጪ
ምንዛሪ ክላርክ ውስጥ ነው የምሰራው”፡፡
-በመጨረሻ….፡-
“የእግር ኳስ
ተጨዋችነት ዘመኔ አንስቶ አሁን ላይ
በአሰልጣኝነት ሙያው እስከዘለቅኩበት
ድረስ ከእኔ ጎን በመሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ
ያበረከቱልኝን አካላቶች በሙሉ ለማመስገን
እፈልጋለው፤ በመጀመሪያ ፈጣሪዬን ቀጥሎ
ቤተሰቦቼንና ከእኔ ጀርባ በመሆን በብዙ
ነገር የምታግዘኝን እና በጣም የምወዳትን
ባለቤቴን እንደዚሁም በቢሮአችን ውስጥ
ያሉት ጓደኞቼን፤ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ
ከተማ አመራሮችንና በቡድኑ ውስጥ ያሉትን
የሙያዬ ጓደኞቼንና ተጨዋቾችን ወደ
አሰልጣኝነት ሙያውም በመጣሁበት ጊዜ
በኮርስ ላይ ያለኝን ተሳትፎ ተመልክቶ ወደፊት
በሙያው ጥሩ ደረጃ ላይ ትደርሳለህ ብሎ
ለእኔም ሆነ ለሌሎቹ ይነግራቸው የነበረውን
ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱን እና
ሌሎችም ስማቸውን ለጊዜው ያልገለፅኳቸውን
ሁሉ ከልብ ለማመስገን እፈልጋለው፡፡”