በውድድር ዓመቱ ስምንት ግቦችን ካስቆጠሩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። ትውልድና ዕድገቱ የእግር ኳስ ተጫዋቾች መፍለቂያ ከሆነችው አርባምንጭ ከተማ ነው። አምና በለገጣፎ ለገዳዲ መጥፎ የውድድር ዘመን በግሉ ጥሩ ጊዜን ያሳለፈው ይህ ተጫዋች በዚህ ዓመት ቅዱስ ጊዮርጊስን ተቀላቅሎ አመርቂ የመጀመሪያ አመትን በማሳለፍ ላይ ይገኛል።
አማኑኤል ኤርቦ!!!
በፈረሰኞቹ 12 ቁጥር መለያን ለብሶ እስካሁን 8 ግቦችን በማስቆጠር ከአቤል ያለው እኩል የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች ነው። ተጫዋቹ ከእግርኳስ ህይወቱ ጅማሮ አሁን እስከደረሰበት ያለውን ጉዞ በተመለከተ ከሀትሪክ ስፖርት ድህረገጽ ባልደረባ ሀብታሙ ምትኩ ጋር ቆይታ አድርጓል።
አማኑኤል በተለይም ቅዱስ ጊዮርጊስን ለመቀላቀል እንዲወስን ስላደረገው አንድ የስልክ ጥሪ ያለው አለ። ስለ ውድድር ዓመቱ የሻምፒዮንነት ጉዞ የዋንጫ ማረፊያውን በርግጠኝነት ይናገራል። በብዙ ችግሮች ውስጥ እያለፈ ነገር ግን ሜዳ ላይ ጥንካሬውን ያስለቀጠለው የቅዱስ ጊዮርጊስ ሚስጥርም ይናገራል። የሳምንቱ መጨረሻ ተጠባቂ የመቻልና ቅዱስ ጊዮርጊስ ፍልሚያም ምንም እንኳን “ያዘነበት አጋጣሚ ቢፈጠርም” ግምቱን አስቀሞጧል።
- ማሰታውቂያ -
መልካም ንባብ!!!
ሀትሪክ :- የእግርኳስ አጀማመርክ ምን ይመስላል?
አማኑኤል :- እግርኳስን ደደቢት ፕሮጀክት በ2003 አካባቢ በመቀላቀል ነበር የጀመርኩት ያው ከዛ ቀደም ብሎ ሰፈር ውስጥ በመጫወት ነበር። በታዳጊ ከ13 አመት በታች። ከዛ በመቀጠል ፋይቭ የሚባል ፕሮጀክት አለ እዛው አርባምንጭ ፤ ከደደቢት ቀጥሎ አሪፍ የሚባለው ፕሮጀክት ነው እዛ ገባሁ። እስከ 2010 ድረስም በዛው ነበር ያሳለፍኩት።
በ2010 ላይ ወደ አዲስ አበባ መጥቼ ነበር ለሙከራ ግን ትምህርትም ስለነበር በዛ በዛ ምክንያት ሳይሳካልኝ ቀረ። በ2011 ግን ኢትዮጵያ ቡና ተስፋ ቡድን የመግባት ዕድል አገኘሁ። ያንን አመትም በኢትዮጵያ ቡና ቤት አሳለፍኩ። በዛን ጊዜ ወደ ዋናው ቡድን የመግባት ዕድሎችም ነበሩ። በወቅቱ ወደ ዋናው ቡድን ያደጉ ልጆች ነበሩ ከነሱጋር የመስራት ነገሮች ነበረን ከዋናው ቡድን ጋር ማለት ነው።
ከዛን በኋላ ሊጉ አልቆ በነበረበት ጊዜ ትመጣላችሁ ብለውን ወደ አርባምንጭ ተመለስን። ግን ብንጠብቅ ብንጠብቅ ሳንጠራ ቀረን። ስለዚህ ቀጣዩን አመት 2012 እዛው አርባምንጭ ጎፋ ባራንቼ የሚባል ቡድንን ተቀላቀልኩ። ያ አመት እንደምታስታውሰው የኮቪድ የተቀሰቀሰበት ጊዜ ነበር።
ጥሩ ላይ ነበርን ወደ ከፍተኛ ሊግ ለማደግ ጥሩ ውጤት እያስመዘገብን ነበር። ግን በኮቪድ ምክንያት ተቋረጠ።
በቀጣይ አመትም በዛው በአርባምንጭ ቆየሁ ።በዛ አመትም ወደ ከፍተኛ ሊግ ለመግባት የመጨረሻ ስምንት ቡድኖች ለሚያደርጉት ውድድር አዳማ ከተማ ነበርን። በዛ ውድድር ግን ወደቅን።
የአሁኑ የሸገር ከተማ የቀድሞው የለገጣፎ ለገዳዲ አሰልጣኝ ጥላሁን አይቶኝ 2014 በከፍተኛ ሊጉ ለገጣፎ ለገዳዲን ተቀላቀልኩ።
ያው በ2015 ቡድኑን ወደ ፕሪሚየር ሊግ አሳደግን በአመቱ በጣፎ አሳለፍኩ በ2016 ደግሞ በቅዱስ ጊዮርጊስ እገኛለሁ።
ሀትሪክ :- የአርባምንጭ የደደቢት ፕሮጀክት በርካታ ተጫዋቾች አፍርቷል አይደል?
አማኑኤል :- አዎ በርካታ ብቃት ያላቸው ልጆች ወተዋል። እኛ በነበርንበት ጊዜ ትምህርት የጨረሱ ነበሩ እነሱ በወቅቱ ወደ ክለብ የመግባት ዕድልን አገኙ ያው እኛ ተማሪ ስለነበርን ዕድሜያችንም ትንሽ ስለነበር እዛው ለመቆየት ተገደደን።
ሀትሪክ :-አምና በለገጣፎ ለገዳዲ የነበረክ ቆይታ ምን ይመስል ነበር?
አማኑኤል :-አሪፍ ነበር ከፍተኛ ሊግ ዋንጫ በልተህ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ስትገባ በጣም ደስ የሚል ስሜት አለው።
ሀትሪክ :-የቤተሰብ ድጋፍ ምን ይመስል ነበር በእግርኳሱ እንድትቀጥል ይፈልጉ ነበር ?
አማኑኤል :- አዎ በጣም። አባቴ በጣም ኳስ ይወዳል።የአርባምንጭ ተወላጅ ስትሆን ለእግርኳስ ያለህ ፍቅር የተለየ ነው። እኔም እዚህ እንድደርስ አባቴም ሆነ የአካባቢዬ ማህበረሰብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቶልኛል።
ሀትሪክ :-አባትህ ጨዋታዎችህን ያያሉ ማለት ነው?
አማኑኤል :-አዎ ስራም ቢሆን ወደ ቤት ሄዶ ያያል። ባይመቸው እንኳን የሆነ ካፌ ምናምን አካባቢ ቁጭ ብሎ ያያል እንጂ የኔ ጨዋታ አያመልጠውም። ከጨዋታ በኋላም ይደውልልኛል ካሸነፍን ወድያው ካልሆነ ደግሞ ስሜቱን ስለሚያውቀው በማግስቱ ደውሎ ያበረታታኛል።
ሀትሪክ :-ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጣህበት መንገድ ምን ይመስል ነበር?
አማኑኤል :-ክረምት ላይ በርካታ ክለቦች አናግረውኝ ነበር። በተለይም ሀዋሳ ከተማና ኢትዮጵያ መድኅን ገፍተው መጥተው ነበር። እንደውም ኢትዮጵያ መድኅን አሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ በግልም አዋርቶኝ ነበር። እኔም ወደ መድኅን ለመግባት ተስማምቼ በሚቀጥለው ቀን ለመፈረም በተዘጋጀሁበት ጊዜ ወደ 11 ሰዓት አካባቢ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ደወለልኝ።
ከኔ ጋር ብትሰራ ደስ ይለኛል የሚል ጥያቄ አቀረበልኝ። ከዛ እኔም አላንገራገርኩም ጊዮርጊስ መጫወት ህልሜ ስለሆነ እድለኛ ነኝ ብዬም አስባለሁ በዚህ ዕድሜዬ ላይ ጊዮርጊስ በመጫወቴ።
ማንም ኢትዮጵያዊ ተጫዋች ጊዮርጊስ መጫወት ይፈልጋል። ትልቅ ቡድን ሻምፒዮና የሚሆን ቡድንም ነው። የተሻለ ነገር ሰርተህ የተሻለ ደረጃ መድረስ የምትችልበት ስለሆነ ዘሪሁን ጥያቄውን እንዳቀረብልኝ አላንገራገርኩም በነጋታው ፊርማዬን አኖርኩኝ።
ሀትሪክ :-ስለዚህ ለኢትዮጵያ መድኅን ለመፈረም ሙሉ ለሙሉ ተስማምተህ ነበር?
አማኑኤል :-አዎ። ከኢትዮጵያ መድኅን እና ከሀዋሳ ከተማ ጋር ብዙ ንግግሮች ነበሩ በቀጣዩ ቀን ፊርማዬን ለማኖር ስልክ ነበር የምጠብቀው። ዘሪሁን ሲደውልልኝ ግን ሀሳቤን ቀይሬ ለጊዮርጊስ ፈርሜያለሁ።
ሀትሪክ :-ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተቀላቀልክ በኋላስ እንዴት አገኘከው ? ነገሮች ቀድሞ እንደነበረህ ግምት ነበሩ?
አማኑኤል :-ጊዮርጊስ በጣም የሚለይ ቡድን ነው። ፍቅራቸውና አንድነታቸው ደስ ይላል። እኔም ብዙም አልከበደኝም ። አዲስ ቡድን ስትገባ ለመላመድ ትንሽ ጊዜ ይወስዳል ግን እኔ ቶሎ ነበር የተላመድኩት የነባር ተጫዋቾች አቀባበላቸውም በጣም ደስ ይላል። ነባሮቹ ለወጣት ተጫዋቾች ያላቸው አቀባበል አስደሳች ነው። በአጠቃላይ እኔም አልከበደኝም በአጭር ጊዜ ነው የተላመድኳቸው።
ሀትሪክ :-የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ መለያን በርካታ ታላላቅ ተጫዋቾች ለብሰውት ተጫውተዋል። ይህን ማልያ መልበስ እንዴት ይገለፃል?
አማኑኤል :-የጊዮርጊስ ማልያ ከባድ ነው። በርካታ ትልቅ ስም ያላቸው ተጫዋቾች ለብሰውት ተጫውተዋል። ለመልበስ እድለኛ መሆን አለብህ።
ሀትሪክ :-ከነጥብ መጣሎች በኋላ ያለው የመልበሻ ክፍል ስሜት ምን ይመስላል?
አማኑኤል :-በጣም ይከብዳል።አይደለም ሽንፈት አቻ በጊዮርጊስ ቤት አይታሰብም። ጊዮርጊስ ሁሌም ሻምፒዮን ሁሌም የዋንጫ ቡድን ስለሆነ አቻ ሽንፈት ነው ለኛ። ጊዮርጊስ ቤት አቻ ሽንፈት ነው።
ሀትሪክ :-በውድድር አመቱ ስምንት ግቦችን አስቆጥረህ በኮከብ ግብ አስቆጣሪዎች ተርታ ትገኛለህ? በዓመቱ መጨረሻ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆኜ አጠናቅቃለሁ ብለህ ታስባለህ?
አማኑኤል :-አዎ። እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኜ አጠናቅቃለሁ ብዬ ነው የምሰራው ።ከክለቤ ጋርም ዋንጫ የማንሳት ህልም አለኝ።
ሀትሪክ :-የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መቻል ተፎካካሪነት እንዴት ተመለከትከው? የዋንጫ ፉክክሩ በሶስታችሁ ክለቦች መካከል ብቻ ወይንስ?
አማኑኤል :-ሁለቱም ቡድኖች አሪፍ ናቸው። ያው ሊጉ ገና ነው ሻምፒዮንም ወራጅም ያኔ ነው የሚለየው።ሻምፒዮን ለመሆን እያንዳንዱ ጨዋታ ወሳኝነት አለው። ፉክክሩ ዘንድሮ የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ።
ሀትሪክ :-የድሬዳዋ ስታድየምን እንዴት አገኘከው?
አማኑኤል :-ሜዳው የኢትዮጵያን እግርኳስ ገፅታ የቀየረ ሜዳ ነው። በጣም ምቹ ነው። ከሌሎች ሜዳዎች በብዙ ነገር እጅግ በጣም የተሻለ ነው። እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን እንዲህ አይነት ሜዳ አግኝተናል ሊጉ በዲኤስቲቪም ስለሚተላለፍ ለሀገርም ጠቀሜታው የጎላ ነው ብዬ አስባለሁ።
ሀትሪክ :-ቅዱስ ጊዮርጊስ በውጫዊ ችግሮች ውስጥ ስለመሆኑ የሚሰሙ ነገሮች አሉ። ቡድኑ ግን አሁንም በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ አለ። ሚስጥሩ ምን ይሆን?
አማኑኤል :-አዎ የሚወራው ነገር እንዳለ ሆኖ እኛ ስራችንን ነው የምንሰራው። ከላይ ያሉት ስራቸውን ይሰራሉ። አሰልጣኞች ጋር ያለው ነገር በጣም ደስ ይላል። እኛንም በተገቢው እየደገፉን ነው ያሉት እኛም በፍላጎት ነው እየሰራን ያለነው፤ ምንም እንከን የለም።እኛ ጋር ያለው ነገር ደስ ይላል። እኛ ሻምፒዮን ለመሆን ነው የምንጫወተው ስለዚህ ትኩረታችንን ሜዳ ላይ አድርገን አመቱን በስኬት ለማጠናቀቅ ነው የምንሰራው።
ሀትሪክ :-ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመቱን በሻምፒዮንነት ያጠናቅቃል?
አማኑኤል :-አዎ በእርግጠኝነት ሻምፒዮን እንሆናለን።
ሀትሪክ :-በአንድ የስልክ ጥሪ ሀሳብህን ስላስቀየረህ አሰልጣኝ ዘሪሁን ምን ትላለህ?
አማኑኤል :-አሰልጣኝ ዘሪሁን ትልቅ አሰልጣኝ ነው። ለኔ በጊዮርጊስ ቤት ጥሩ መሆን ትልቁን ድርሻ የሚወስደው እርሱ ነው። ለኔ ክብር አለው እኔም በጣም ነው የማከብረው።
ሀትሪክ :-ከቤተሰብ ሌላ እግርኳስ ተጫዋች አለ?
አማኑኤል :-አይ የለም።
ሀትሪክ :-እህት ወንድም አለህ?
አማኑኤል :-ሁለት ወንድም ሁለት እህት አለኝ። እኔ አራተኛ ልጅ ነኝ።
ሀትሪክ :-አባትህ ኳስ ይወዳሉ ብለኸኝ ነበር? የማን ደጋፊ ናቸው?
አማኑኤል :-ከሀገር ውስጥ እኔ ያለሁበትን ክለብ ነው የሚደግፈው። ከውጪ ደግሞ የሊቨርፑል ነው።
ሀትሪክ :-አንተስ?
አማኑኤል :-እኔም የሊቨርፑል ደጋፊ ነኝ።
ሀትሪክ :-አርአያክ ማነው?
አማኑኤል :-አርአያዬ ብዬ የምወስደው ጌታነህ ከበደን ነው። አርአያዬ አድርጌ የተነሳሁት እሱን ነው። ያው ሌሎችም አሉ እነ ሳልሀዲን ሰይድ ፣ አዳነ ግርማን የመሳሰሉ እነሱን እያየሁ ነው ያደኩት። ከውጪ ደግም የክርስትያኖ ሮናልዶ አድናቂ ነኝ።
ሀትሪክ :-በፕሪሚየር ሊግ አልያም በከፍተኛ ሊግ የፈተነክ ተከላካይ ማነው?
አማኑኤል :-እስካሁን የተፈነኝ ተከላካይ ማንም የለም።
ሀትሪክ :-ከቡድናችሁ ስብስብ በባህሪው የተለየ አሪፍ የምትለው አንድ ተጫዋች ?
አማኑኤል :-ናትናኤል ዘለቀ።
ሀትሪክ :-ታታሪው ተጫዋች ?
አማኑኤል :-ሁሉም የኛ ቡድን ተጫዋቾች ጥራት ያላቸው ናቸው። በስራ እና በወኔ ካልከኝ ግን ሔኖክ አዱኛ።
ሀትሪክ :-የደጋፊዎችን አቀባበል እንዴት አገኘኸው?
አማኑኤል :-ለጊዮርጊስ ደጋፊ ቃል የለኝም። በሚገርም አቀባበል ነው የተቀበሉኝ። ያልተጠበኩትን አቀባበል ነው ጊዮርጊስ ቤት ያገኘሁት። አምና በነበረኝ እንቅስቃሴ አይተው የተሻለ ነገር ያደርግልናል ብለው አስበው በጣም ነው የተቀበሉኝ። በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እወዳለሁ።
ሀትሪክ :-ከአማኑኤል በዚህ ማልያ ምን ይጠብቁ?
አማኑኤል :-ብዙ ነገር መስራት ይጠበቅብኛል በግሌ ከእግዚአብሔር ጋር ትልቅ ነገር ሰርቼ አሳያቸዋለሁ ብዬ አስባለሁ ።
ሀትሪክ :-የወደፊት እቅድህ ምንድነው ?
አማኑኤል :-ረጅም አመት በተጫዋችነት መቆየት እፈልጋለሁ ። ለብሔራዊ ቡድን ብዙ መስራት እፈልጋለሁ።
ሀትሪክ :-ከጨዋታ ውጪ ያለ ጊዜህን እንዴት ነው የምትታሳልፈው?
አማኑኤል :-በብዛት ከጓደኞቼ ጋር ነው የማሳልፈው ጨዋታዎች እናያለን። በተጨማሪም ፕሌይስቴሽን በመጫወት አሳልፋለሁ።
ሀትሪክ :-በቅርቡ የትውልድ ከተማህ ልጅ የሆነው አለልኝ አዘነ በአሳዛኝና አስደንጋጭ ሁኔታ ህይወቱ አልፏል። የአለልኝን ህልፈት እንዴት ነበር የሰማኸው?
አማኑኤል :-አስደንጋጭ ነበር። ለሊት ላይ ነበረ የሰማሁት ፋሲል ገ/ሚካኤል ነበር ደውሎልኝ እውነት ነው እንዴ ብሎ የጠየቀኝ። እሱም አላመነም ነበር። እኔም ግራ ገባኝ ደንግጬ ነበር ። ወድያው ወንድሜ ጋር ነበር የደወልኩት ወንድሜ እዛው አካበቢ የአለልኝ ሰፈር ነው የሚኖረው ።እሱ ጋር ስደውል ለቅሶ ነው የሰማሁት ንግግሩን አልሰማሁም። አመንኩኝ በዛን ሰአት ።በወቅቱ ራሴን መቆጣጠር በጣም ከብዶኝ ነበር።
ሀትሪክ :-ከአለልኝ ጋር የነበራችሁ መቀራረብ ምን ያህል ነው?
አማኑኤል :-እንተዋወቃለን ። ያው እሱ ከኔ አንድ ደረጃ ከፍ ይላል። ሰፈር ውስጥ የካፕ ውድድሮች ላይ እንጫወታለን ። ጊዮርጊስ ስፈርምም በብዙ ነገር አውርቶኛል። ካለው ልምድ አንፃር ያለውን ስሜት ነግሮኝ ነበር። በጣም ብዙ ነገር ሲመክረኝ ነበር። ከመፈረሜ በፊት በስልክ ብዙ አውርተን ነበር። ብቻ ያለው ስሜት ከባድ ነው። እግዚአብሔር ለነፍሱ ምህረቱን ያውረድለት።
ሀትሪክ :-የቀጣዩ ጨዋታ ዝግጅት ምን ይመስላል? ከመቻል ጋር?
አማኑኤል :-ከሽንፈት ነው የምናገኛቸው። እኛ ጋር ደግሞ ከሽንፈት ቶሎ ማገገም አለበህ። ከዚህ ቀደም ያለንም ልምድ ያ ነው። ጠንክረን ቀርበን መቻልን ረተን ወደ መሪነት እንመለሳለን ብዬ አስባለሁ። በሚያሳዝን ሁኔታ በአምስት ቢጫ ይህ ጨዋታ ያልፈኛል። የአዳማውን ጨዋታ ተጠንቅቄ ነበር ግን ቢጫ ያየሁበት አጋጣሚ ተፈጠረ።
ሀትሪክ :-የጨዋታ ግምትህን ንገረኝ እስኪ?
አማኑኤል :-2 – 0 እናሸንፋለን ።
ሀትሪክ :-ምስጋና ለማን ማቅረብ ትፈልጋለህ?
አማኑኤል :-ቤተሰቦቼን ፤ ያሰለጠኑኝ አሰልጣኞቼን ጓደኞቼን እንዲሁም የትውልድ አካባቢዬ ነዋሪዎች አርባምንጭ ሲቄላ 02 በጣም አመሰግናለሁ ። በተለይም እንደ አሰልጣኝም ፣ ወንድምም ጓደኛም የነበረው ፋሪስ ንጉሴን ማመስገን እፈልጋለሁ እዚህ ደረጃ ለመድረሴ የርሱ አስተዋጽኦ ትልቅ ነበር።