የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ መጋቢት 30 2016 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ(ዎች)ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
በሳምንቱ መርሃ ግብር በተደረጉ ጨዋታዎች ስድስት በመሸናነፍ ቀሪ ሁለቱ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ 19 ጎሎች በ17 ተጫዋቾች ተቆጥረዋል። 28 ቢጫ ካርድ ለተጫዋቾችና ቡድን አመራሮች ሲሰጥ ሁለት ቀይ ካርድ ተመዝግቧል።
በሳምንቱ በስድስት ተጫዋቾች ላይ የዲሲፕሊን ውሳኔ ተላልፏል። ጋቶች ፓኖም(ፋሲል ከነማ)፣ አብዱልባሲጥ ከማል(ሃዋሳ ከተማ)፣ ዳዊት ማሞ(መቻል) እና በረከት ወልዴ(ቅዱስ ጊዮርጊስ) በሳምንቱ ጨዋታ አምስተኛ የጨዋታ ቢጫ ካርድ በመመልከታቸው ለፈፀሙት ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 1500 /አንድ ሺ አምስት መቶ/ እንዲከፍሉ ፤ ናትናኤል ናሴሮ(ወላይታ ድቻ) በሁለተኛ ቢጫ ካርድ በቀይ ካርድ ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ ለፈፀመው ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገድ እንዲሁም ታዬ ጋሻው(አዳማ ከተማ) የተጋጣሚን ተጫዋች በመማታት በቀይ ካርድ ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ ለፈፀመው ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 4 ጨዋታ እንዲታገድና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 3000 /ሶስት ሺ/ እንዲከፍል ተወስኗል።
በሳምንቱ መርሃ ግብር የአዳማ ከተማ ተጫዋች የሆኑት ፍቅሩ አለማየሁ፣ ዮሴፍ ታረቀኝ፣ አህመድ ረሽድ እና ታዬ ጋሻው በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ክለቡ የገንዘብ ቅጣት ብር 5000 /አምስት ሺ/ እንዲከፍል ተወስኗል፡፡