ቀን 10 ሰዓት ሲል በዋና ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ ፊሽካ በጀመረዉ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ የተሻለ ብልጫ የነበራቸዉ እና የተወሰኑ ጫናዎችን መፍጠር የቻሉት ባንኮች በ19ነኛዉ ደቂቃ ላይ ሱለይማን ሀሚድ ከቀኝ መስመር በኩል ያሻማዉን ኳስ ባሲሩ ዑመር ወደ ግብ ቢሞክርም የግብ ዘቡ ኳሷን ተቆጣጥሯል ።
ከዚች ተጠቃሽ ሙከራ በኋላ አሁንም የጨዋታዉን የመሐል ሜዳ ብልጫ በመዉሰድ መጫወት የቀጠሉት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በ23ተኛዉ ደቂቃ ላይ በድጋሚ ከቀኝ መስመር ሱለይማን ባሻገረዉ እና ሲሞን ፒተር በቀጥታ ወደ ግብ በሞከረዉ የጭንቅላት ኳስ ድንቅ ሙከራ ማድረግ ችለዉ ነበር ፤ በዚህ ሂደት በቀጠለው ጨዋታ አጋማሹ ሊገባደድ ስድስት ያክል ደቂቃዎች ሲቀሩ አጠቃላይ በእንቅስቃሴ ብልጫ የተወሰደበት ሀዋሳ ከተማ ግብ ማስቆጠር ችሏል።
በዚህም በ39ነኛዉ ደቂቃ ላይ አቤነዘር ዮሐንስ ያቀበለዉን ኳስ ፈጣኑ አጥቂ አሊ ሱለይማን የግል ክህሎቱን ጭምር በመጠቀም ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል። በእንቅስቃሴ ረገድ የተሻሉ ቢሆንም ሳጥን ውስጥ ግን ስል መሆን ያልቻሉት ባንኮች በሀብታሙ ሸዋለም እና ባሲሩ ዑመር ድንቅ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም ግብ ጠባቂዉ ፂዮን መርዕድ ኳሷቹን ተቆጣጥሯል።
- ማሰታውቂያ -
ከዕረፍት መልስ ብልጫቸዉን ያስቀጠሉት ባንኮች በ50ኛዉ ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ አግኝተዋል። በዚህም ከግራ በኩል የተገኘዉን የቅጣት ምት ኳስ ፋዓድ ፈረጃ ሲመታዉ ግብ ጠባቂዉ ፅዮን ኳሱን ሲመልሰዉ ያገኘዉ ሳይመን ፒተር ኳሷን ወደ ግብነት መቀየር ችሏል። አጋማሹ በተጀመረ በአምስት ደቂቃ ውስጥ አቻ መሆን የቻሉት ባንኮች ከደቂቃዎች በኋላ በ65ተኛዉ ደቂቃ ላይ ከመመራት ወደ መሪነት መሸጋገር ችለዋል። በዚህም ፋዓድ ፈረጃ ያቀበለዉን ኳስ ኪቲካ ጀማ ወደ ግብነት ቀይሯል።
ግብ ያስቆጥሩ እንጅ የጨዋታዉ ደቂቃ እየገፋ በሄደ ቁጥር እየተቀዛቀዙ የሄዱት ሀዋሳ ከተማዎች በእንደ እዮብ አለማየሁ እና አሊ ሱለይማንን በመሳሰሉ ተጫዋቾች ጥሩ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም ውጥናቸዉ ሰምሮ የአቻነት ግብ ማግኘት ሳይችሉ ጨዋታዉ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሸናፊነት ተጠናቋል።
በበርካታ ደጋፊዎች ድባብ ታጅቦ በተከናወነው የምሽቱ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ እና ወላይታ ዲቻ አቻ ተለያይተዋል ።
በዋና ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘዉ ፊሽካ ምሽት አንድ ሰዓት ሲል በጀመረዉ እና ተመጣጣኝ የጨዋታ ፉክክር በተመለከትንበት ጨዋታ ወላይታ ዲቻ በቀዳሚነት ሙከራ ማድረግ ችሎ ነበር ፤ በዚህም አብነት ደምሴ ከባየ ገዛኸኝ የተቀበለዉን ኳስ ሳጥን ውስጥ በቀጥታ ወደ ግብ ቢሞክርም ኳሱ በአናት ላይ ወደ ዉጭ ወጥቷል።
በተለይ የጨዋታዉን የእንቅስቃሴ ሚዛን ወደ መስመር በኩል በመዉሰድ እና የተሻለ ብልጫ በመዉሰዱ ሰገድ የተሻሉ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በግራ መስመር በኩል መሐመድ አብዱለጢፍ ያሻማዉን ኳስ ሱራፌል በጭንቅላቱ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ሙከራዉ ግን ዉጤታማ ሳይሆን ቀርቷል።
በ44ተኛዉ ደቂቃ ላይ ባየ ገዛኸኝ ከኋላ ክፍል ከአዛርያ በረዥሙ የተሻገረለትን ኳስ ከተቆጣጠረ በኀላ በቀጥታ ኳሷን ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ኳሷ ለጥቂት በግቡ ቋሚ አጠገብ ወደ ዉጭ ወጥታለች። ከዕረፍት መልስ ጨዋታዉን በጥቂቱም ቢሆንም መቆጣጠር የቻሉት ድሬዳዋ ከተማዎች በ55ተኛዉ ደቂቃ ላይ መሪ መሆን ችለዋል ፤ በዚህም ካርሎስ ዳምጠዉ ላይ የተሰራዉን ጥፋት ተከትሎ የተገኘዉን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ተጫዋቹ ወደ ግብነት መቀየር ችሏል።
ከአበባየሁ ሀጂሶ የተቀበለዉን ኳስ ብዙዓየሁ ሰይፈ የግል ክህሎቱን ተጠቅሞ ተጫዋቾችን አታሎ በማለፍ ድንቅ ግብ በማስቆጠር ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል። የአቻነት ግብ ከተቆጠረ በኋላ በእንቅስቃሴዉ ሁለቱም ክለቦች ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ ዕድሎችን ለመፍጠር እና ግብ ለማስቆጠር ሲያደርጉት የነበረዉ ጥረት ሳይሳካ ቀርቶ መርሐግብሩ አንድ አቻ በሆነ ዉጤት ተጠናቋል።