በ21ኛዉ ሳምንት ሁለተኛ ዕለት ጨዋታ ፋሲል ከነማ ከሀምበሪቾ ዱራሜ ጋር ሁለት አቻ ተለያይተዋል።
ቀን 10:00 ሰዓት ሲል በዋና ዳኛ ባህሩ ተካ ፊሽካ በጀመረዉ እና ቀዝቃዛ በሚባል የጨዋታ እንቅሰቃሴ በጀመረዉ ጨዋታ ባሳለፍነዉ ሳምንት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ5ለ1 ሽንፈት ደርሶባቸዉ የነበሩት ሀምበሪቾዎች ገና በ11ኛዉ ደቂቃ ላይ ጨዋታዉን መምራት ጀምረዋል። በዚህም አብዱልሰላም ይሴፍ ከግራ መስመር በኩል ወደ ዉስጥ ገብቶ ያሻማዉን ኳስ የፋሲሉ ግብ ጠባቂ ሚካኤል ሳማኪ ራሱ ግብ ላይ አስቆጥሮ ሀምበሪቾዎች ገና በመባቻዉ ጨዋታዉን መምራት ጀምረዋል።
ግብ ከተቆጠረባቸዉ በኃላ የጨዋታዉን የበላይነት በመዉሰድ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ተጭነዉ መጫወት የቀጠሉት አፄዎቹ በቃልኪዳን ዘላለም እና ሌሎችም ተጫዋቾች ዕድሎችን ከፈጠሩ በኋላ በ28ተኛዉ ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። በዚህም ከቀኝ በኩል ዮናታን ፍስሀ ያሻገረዉን ኳስ ያገኘዉ ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ በቀጥታ ወደ ግብነት መቀየር ችሏል። ከሁለቱ ግቦች እና አልፎ አልፎ በሁለቱም በኩል ከሚደረጉ ኢላማቸዉን ያልጠበቁ ሙከራዎች ዉጭ ይህ ነዉ የሚባል ዕድል መፍጠር ያልቻሉት ሁለቱ ክለቦች አጋማሹን አንድ አቻ አገባደዋል።
- ማሰታውቂያ -
በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ጨዋታዉ ለመመለስ በቶሎ መንቀሳቀስ የጀመሩት ሀምበሪቾዎች በ51ኛዉ ደቂቃ ላይ ዳግም ጨዋታውን መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አግኝተዋል ፤ በዚህም በዕለቱ ድንቅ የነበረዉ አብዱልሰላም የሱፍ ከሚካኤል ሳማኪ ተጭኖ የቀማዉን ኳስ ወደ ግብነት በመቀየር ድንቅ ስራ ሰርቷል።
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታ በ77ተኛዉ ደቂቃ ላይ የፋሲል ከነማዉ ተከላካይ ሀቢብ መሐመድ በረከት ወንድሙ ላይ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወገድ ፤ ከደቂቃዎች በኃላም በድጋሚ ጫናቸዉ የበረታዉ ሀምበሪቾዎች በበረከት ወንድሙ አማካኝነት ድንቅ ሙከራ አድርገዉ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ለጥቂት ወደ ዉጭ ወጥታለች ። በዚህ ሂደት ቀጥሎ መደበኛ ዘጠና ደቂቃዉን በፈጀዉ ጨዋታ ላይም በ90+2 ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባዉ ሸምሰዲን መሐመድ ከርቀት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ አፄዎቹ ውድ የሆነ አንድ ነጥብ እንዲያገኙ አስችሏል።
በባህርዳር ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ መካከል የተደረገዉ የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ በአቻ ዉጤት ተጠናቋል ።
በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ መሪነት ምሽት 1:00 ሰዓት ሲል በጀመረዉ እና ድንቅ ፉክክር ባስመለከተዉ የምሽቱ ጨዋታ ገና ከመባቻዉ አንስቶ ሁለቱም ክለቦች የጨዋታዉን የበላይነት ለመቆጣጠር ሲጥሩ የነበረ ሲሆን በ5ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግን ባህርዳር ከተማ ድንቅ ሙከራ አድርገዋል። በዚህም አማካዩ ያብስራ ተስፋየ ከኋላ ክፍል የተላከለትን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም የግቡ ቋሚ ግን ኳሷን መልሶበታል።
በ29ነኛዉ ደቂቃ ላይ ተከላካዩ ፍራኦል መንግስቱ ከቀኝ መስመር በኩል ያሻማዉን ኳስ ሌላኛዉ ተከላካይ ፍሬዘር ካሳ ሞክሮ ወደ ዉጭ ሲወጣ ያንኑ ኳስም ማዕዘን ሆኖ ቸርነት ጉግሳ የማዕዘን ኳሱን ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል። ግብ ከተቆጠረባቸዉ በኋላ የአቻነት ግብ ፍለጋ የቀጠሉት ፈረሸኞቹ ሞሰስ ኦዶ ከማዕዘን ቢኒያም በላይ ያሻማውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ያሬድ እና መሳይ ኳሷን ተረባርበዉ እንደምንም አውጥተዋል።
በተደጋጋሚ የፈረሰኞቹን የግብ ክልል ሲፈትሹ የነበሩት የጣና ሞገዶቹ በፍሬዘር ካሳ አማካኝነት ከግራ መስመር በኩል ከቆመ ኳስ የተሻገረዉን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክረዉ ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል ። ከዕረፍት መልስ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ሁለቱም ቡድኖች ቀይረዉ ወደ ሜዳ በማስገባት የጨዋታውን የበላይነት ለመዉሰድ ሲጥሩ የተስተዋለ ሲሆን ፤ ባህርዳር ከተማዎች በይበልጥ ወደ ራሳቸዉ የግብ ክልል አፈግፍገው በጥብቅ መከላከል እና በመልሶ ማጥቃት በቸርነት በኩል ባመዘነ እንቅስቃሴ ለመጫወት ሲጥሩ ፤ በተቃራኒው ፈረሰኞቹ ግን ወደ ጨዋታዉ የሚመልሳቸዉን የአቻነት ግብ ለማግኘት ሲጥሩ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውሏል።
በ75ተኛዉ ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ በድጋሚ ከግራ መስመር ሳጥን ውስጥ ከገባ በኋላ በቀጥታ ወደ ግብ ድንቅ ሙከራ አድርጎ የነበረ ቢሆንም ኳሷ በግቡ ቋሚ አጠገብ ለጥቂት ወጥታለች።
በ89ነኛዉ ደቀቃ ዳግማዊ አርአያ ፍሬዘር ካሳን አታሎ ያገኘዉን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ሲሞክር ግብ ጠባቂዉ ሲመለስ የተገኘዉን ኳስ በቅርበት የነበረዉ ታምራት እያሱ ሞከሮ የነበረ ቢሆንም ተከላካዮች ተረባርበዉ አፅድተዋል። በ94ተኛዉ ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር በኩል ተከላካዩ አማኑኤል ተርፉ ያሻማውን ኳስ ሳጥን ውስጥ ያገኘዉ አማኑኤል ኤረቦ በጭንቅላቱ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን አቻ አድርጎ ፤ መርሐግብሩም አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ዉጤት ፍፃሜዉን አጊኝቷል።