በሀያ አንደኛዉ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሶስተኛ ዕለት የመጀመሪያ ጨዋታ በወራጅ ቀጠናዉ ዞን ላይ የሚገኙት ወልቂጤ ከተማ እና ሻሸመኔ ከተማ ጨዋታቸውን ያለ ገብ በአቻ ዉጤት አጠናቀዋል ።
በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ መሪነት ቀን 10:00 ሰዓት ሲል በጀመረዉ እና ከወራጅ ቀጠናዉ ዞን ለመሸሽ ወሳኝ በነበረዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከጨዋታዉ መባቻ አንስቶ ደካማ የሚባል እንቅስቃሴ የተመለከትንበት ሲሆን ፤ እንቅስቃሴዉም የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ለማስመልከት 22 ደቂቃዎችን ያስጠበቀ ሲሆን ፤ በተጠቀሰው ደቂቃም ወልቂጤ ከተማዎች ከቀኝ መስመር በኩል ከተገኘ ቅጣት ምት በጋዲሳ መብራቴ አማካኝነት ድንቅ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገዋል።
ከዚች ሙከራ በቀር በአጋማሹ ይህ ነዉ የሚባል ተጠቃሽ አደገኛ ሙከራን ማስመልከት ያልቻሉት ሁለቱም ክቦች እጅጉኑ ቀዝቃዛ የነበረዉን የመጀመሪያ አጋማሽ ያለ ግብ በአቻ ዉጤት አገባደዉ ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍሉ ያመሩ ሲሆን ፤ ከዕረፍት መልስም እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ጨዋታዉ በቀዝቃዛ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የቀጠለ ሲሆን ከነበሩ አንድ ሁለት ተጠቃሽ ሙከራዎች መካከልም በ56ተኛዉ ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር በኩል ጋዲሳ መብራቴ ለሳምሶን ጥላሁን ድንቅ ኳስ አቀብሎት ተጫዋቹ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂዉ ኬን ሰይዲ ኳሷን ግብ ከመሆን እንደምንም አምክኗል።
- ማሰታውቂያ -
የጨዋታዉ ደቂቃዎች እየገፉ በሄዱ ቁጥሩ ይበልጥኑ እየተቀዛቀዘ በቀጠለዉ ጨዋታ ሻሸመኔ ከተማዎች በስንታየሁ መንግሥቱ አማካኝነት አንድ ሁለት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን አድርገዉ ፤ በተመሳሳይ ክትፎዎቹም በተመስገን አማካኝነት ድንቅ ሙከራ ቢያደርጉም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታዉ 0ለ0 በሆነ አቻ ዉጤት ተጠናቋል።
በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን ከመመራት ተነስቶ መቻልን 2ለ1 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።
በሁለት ፅንፍ በኩል በሚገኙት ክለቦች መካከል ምሽት አንድ ሰዓት ሲል በጀመረዉ ጨዋታ ገና በመባቻዉ መቻል ግብ አስቆጥረዋል ። በዚህም ዮዳሄ ዳዊት ከግራ መስመር በኩል ያሻገረዉን ኳስ ምንይሉ ወንድሙ ሲጨርፈዉ ያገኘወለ ሽመልስ በቀለ ወደ ጎልነት ቀይሮ ክለቡን ገና በ1ኛዉ ደቂቃ መሪ አድርጓል።
ገና በጨዋታዉ መጀመሪያ ደቂቃ ላይ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ለማግኘት በቶሎ መንቀሳቀስ የቻሉት መድኖች ዉጥናቸዉ ሰምሮ በ10ኛዉ ደቂቃ ላይ አቻ መሆን ችለዋል ። በዚህም በመልሶ ማጥቃት የተገኘዉን ኳስ ጄሮም ፍሊፕ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ ግብ ጠባቂዉ ኳሷን ሲመለስ በቅርበት ያገኛት አብዱልከሪም መሐመድ ግብ አስቆጥሮ ክለቡን አቻ አድርጓል።
ጨዋታዉ ገና በጊዜ ሁለት ጎሎች ከተቆጠሩበት በኋላ በመጠኑ እየተቀዛቀዘ ሂዶ ግማሽ ሰዓታ ያክል ሲያስቆጥር ሁለቱም ክቦች የተጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠርም በብዙ ሲቸገሩ ተስተውሏል። ሁለቱም በኳስ ቁጥጥሩ የበላይ ለመሆን ከሚያደርጉት ፉክክር ባሻገር በአጋማሹ መገባደጃ ወቅት መቻል በከንዓን ማርክነህ አማካኝነት ድንቅ ሙከራ አድርገዉ ነበር ፤ በዚህም ተጫዋቹ ከዮሐንስ መንግስቱ የተቀበለውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ቢልክም ኳሷ ለጥቂት ወጥታለች። ከዚያ ውጭ አቤል ነጋሽም ድንቅ የሚባል ሙከራ ማድረግ ችሎ የነበረ ሲሆን ፤ መድኖችም በወገኔ ገዛኸኝ አማካኝነት ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለዉ ነበር ።
ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ክለቦች የሜዳዉን የመሐል ክፍል ላይ ብልጫ ለመዉሰድ ከሚደረግ ፉክክር በዘለለ ያን ያህል ተጠቃሽ ሙከራዎች ሳይደረጉበት ሁለተኛዉ አጋማሽም ዘለግ ላለ ጊዜ ቀጥሏል ። በዚህ ሂደት በቀጠለዉ የምሽቱ መርሐግብርም በ75ተኛዉ ደቂቃ ላይ መድኖች ግብ ለቆጠርባቸዉ ከጫፍ ደርሰዉ በተከላካዩ ሚሊዮን ሰለሞን ጥረት የመቻሎች ሙከራ ከሽፏል።
በጨዋታዉ መገባደጃ ወቅት ከንዓን ማርክነህ በሚሊዮን ሰለሞን ጥፋት ተሰርቶበታል በሚል እና ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በላይ ታደሰ ባልሰጡት ፍፁም ቅጣት ምት ከነበረዉ አከራካሪ ሁነት በኋላ መደበኛዉ ዘጠና ደቂቃ ተገባዶ በተጨመረዉ ሰባት ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ መድን በአብዱልከሪም መሐመድ አማካኝነት ሁለተኛ ግብ አስቆጥረዉ ጨዋታዉ በኢትዮጵያ መድን 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።