ቅ/ጊዮርጊስን በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ከሰበታ ከተማ ክለብ በመምጣት የተቀላቀለው ቡልቻ ሹራ ለአዲሱ ቡድኑ ፊርማውን በማኖሩ የተሰማውን ደስታ ገልፆ በፈረሰኞቹ ቤት ቆይታው አዲስ ታሪክ ለማፃፍ እንዳለመም ከሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል።
የእግር ኳስ ጨዋታ ዘመን ቆይታውን በአዳማ ከተማ ተተኪ ቡድን ጀምሮ ወደ ዋናው ቡድን በማደግና ወደ ሰበታ ከተማ ክለብ ከተዘዋወረ በኋላም ስኬታማ በሚባል አቋም ላይ የሚገኘው ይኸው ተጨዋች የውል ጊዜውን ከነበረበት ክለብ ጋር ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ስላደረገው ዝውውር፣ በአዲሱ ቡድኑ ስለሚጠብቀው የውድድር ዘመን ጉዞና ስላለፉት ጊዜያት የኳስ ቆይታዎቹ ጥያቄዎችን አንስተንለት የሰጠንን ምላሽ በሚከተለው መልኩ ጀባ ብለናችኋል፤ ተከታተሉን።
ሀትሪክ፦ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ መዘዋወርህን ሰማን፤ ቡድኑ እንዴት የቅድሚያ ምርጫህ ሆነህ?
ቡልቻ፦ ቅ/ጊዮርጊስን የተቀላቀልኩት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት ትላልቅ ቡድኖች ውስጥ አንዱ በመሆኑና ማንኛውም እግር ኳስ ተጨዋች ደግሞ ወደዚህ ክለብ መጥቶ መጫወትንና ድልንም መጎናፀፍ ስለሚፈልግ እኔም ይህን የህይወቴን ትልቁን ስኬቴንና እልሜን ለማሳካት ስልም ነው ወደ ቡድኑ በማምራት ፊርማዬን ለማኖር የቻልኩት።
ሀትሪክ፦ ከቅ/ጊዮርጊስ ውጪ አንተን ለመውሰድ ጥያቄ ያቀረበልህ ክለብ አለ?
- ማሰታውቂያ -
ቡልቻ፦ አዎን፤ ከሁሉም በፊት ቅድሚያ የጠየቀኝ ሌላኛው የሀገሪቱ ትልቅ ቡድን ኢትዮጵያ ቡና ነበር፤ ከእነሱም ጋር ተነጋግረናል። ያም ሆኖ ግን ሁለታችን ባደረግነው ድርድር ልንስማማ ስላልቻልን አሁን የፈረምኩበት ቡድንም እኔን ይፈልገኝ ስለነበር ከእነሱ ጋር ተስማማውና ፊርማዬን ላኖር ቻልኩ።
ሀትሪክ፦ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ መዘዋወርህ እውን ሆኗል፤ ከዚህ ቡድን ጋር በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ዋንጫን የምታነሳ ይመስልሃል?
ቡልቻ፦ አዎን፤ ያለዚያማ ለምን መጣው! ይሄ ክለብ እኮ የሀገሪቱ ትልቅ ቡድን ነው። ድልን አሁን አሁን አጣ እንጂ በየዓመቱ የለመደ ነው። ስለዚህም ወደዚህ ቡድን ሳመራ በሻምፒዮናነት አዲስ ታሪክን ለማስፃፍም ስለሆነ ይሄን እንደማሳካውም እርግጠኛ ነኝ።
ሀትሪክ፦ ቅ/ጊዮርጊስ የሻምፒዮናነት እልሙን ማሳካት ካቆመ አሁን አራተኛ ዓመቱን እያስቆጠረ ነው፤ ወደለመደው ድል በፍጥነት ይመለሳል እያልክ ነው?
ቡልቻ፦ አዎን፤ በእርግጥ አንድ ቡድን ሻምፒዮና ለመሆን ሁሌም ነገሮች አልጋ በአልጋ ይሆኑለታል ማለት አይደለም። በኳስ ውስጥ ዋንጫም ዝም ብሎም አይመጣም። ብዙ ቻሌንጆች ይጠብቁሃል። እነዛን ልትቋቋም የምትችለውና ወደ ውጤታማነትም ልትመጣ የምትችለው ለዛ የሚረዳ ጥንካሬ ሲኖርህ ነውና ያን አስቤም ነው አዲሱ ቡድኔ ባለፉት ዓመታት ዋንጫን ከማጣቱ ጋር በተያያዘ የቁጭት ስሜት ውስጥ ስለሚገኝና ያንንም በመንተራስ ክለቡ ለጥሩ ውጤት ያበቁኛል ብሎ ያሳባቸውን ተጨዋቾች ስላስፈረመና ከነባር የቡድኑ ተጨዋቾች መካከልም ሊጠቅሙ የሚችሉ ልጆችን በስኳዱ ውስጥ ስላስቀረ ቶሎ ወደሚታወቅበት ስኬታማነቱ ይመለሳል ለማለት የወደድኩት።
ሀትሪክ፦ ቅ/ጊዮርጊስን በተቃራኒ ሆነህ ነበር የምትገጥመው፤ አሁን ግን የቡድኑ ተጨዋች ሆነህ ሌሎቹን ልትፋለም ነው፤ በዚህ ዙሪያ ምን አልክ?
ቡልቻ፦ ትልቅ ቡድን ሁሌም ትልቅ ነው። እኔም በዝውውር መስኮቱ የተዘዋወርኩበትንና ብዙ ተጨዋቾችም ያላገኙትን የታላቁን ክለብ ቅ/ጊዮርጊስን መለያ በማጥለቅ በተቃራኒ ሌሎች ቡድኖችን ለመግጠም ያልቻሉበትን እድል ለማግኘት እየተዘጋጀው መሆኔ እያስደሰተኝ ነው። በዚሁ ቡድን ቆይታዬ ጥሩ ነገሮች እንደሚገጥሙኝም አስባለው።
ሀትሪክ፦ ለቅ/ጊዮርጊስ ስትፈርም ቡድኑ ሁሌም በስብስቡ ከሚይዛቸው ተጨዋቾች ጋር በተያያዘ በቋሚነት ከመሰለፍና አለመሰለፍ ጋርም የሚታሰብ ነገር አለ፤ በዛ ዙሪያ ቡልቻ ምን ይላል?
ቡልቻ፦ የእግር ኳስን ስትጫወት እኮ ሁሌም ይሄን አስበህ ነው ከክለብ ወደ ክለብ ዝውውርን የምታደርገው። መሰለፍ አለ፤ መቀመጥም ያጋጥማል። ያ የሚወሰነው ደግሞ በአንተ ብቃት ላይ ተንተርሶ ነው። ስለዚህም ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ሳመራም ቡድኑ ከሚይዛቸው ጠንካራ ተጨዋቾች አንፃር በቦታዬ ለመሰለፍ ከፍተኛ ፉክክር እንደሚገጥመኝ አውቃለው። ላለመቀመጥ ስልና ያን ሰብሮ በቋሚነት ለመጫወት ስልሞ ጠንካራ መሆን አለብኝና በዛ መልኩም እየተዘጋጀው ነው።
ሀትሪክ፦ ለቅ/ጊዮርጊስ በፈረምክበት ሰዓት ስለ ቡድኑ ምን ያህል ነገሮችን አወቅህ? ከየትኞቹ ከፍተኛ አመራሮች ጋርስ ተገናኘህና በአንድአንድ ነገሮች ላይ ተወያየህ….?
ቡልቻ፦ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ሳመራ በመጀመሪያ ደረጃ እኔም ስለ ቡድኑ ታላቅነትና ስኬታማነት የማውቀው ነገር ነበርና ስለ ቡድኑ ያለኝ ግንዛቤ ጥሩ ነበር። ከእነሱ አመራሮች ጋር ደግሞ በተለይ ከክለቡ የቦርድ ሊቀመንበርና ፕሬዝዳንት ከሆኑት ከአቶ አብነት ገብረመስቀል ጋር ተገናኝቼ ከእሳቸው አንደበት ስለ ቡድኑ የስኬታማነት ጉዞና ቅ/ጊዮርጊስ ማለት ለእሳቸውና ለብዙዋኑ የቡድኑ ደጋፊ ምን ማለት እንደሆነ ስረዳ እነሱ ምን ያህል ለክለቡ ተቆርቋሪዎች እና ሟቾች እንደሆኑ ያስመለከተኝም ነገር አለና ከእዛ በመነሳት ነው ለቡድኑ መጫወት ለእኔ ክብርም ጭምር እንደሆነ በመረዳት ክለቡንም ለሻምፒዮንነት ለማብቃት እንድችል የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች መጀመር እያጓጓኝ የሚገኘውና ወደዚህ ቡድን በማምራቴ በጣም ነው ደስ ያለኝ።
ሀትሪክ፦ የቅ/ጊዮርጊስን ካምፕ በዝግጅት ጊዜ ስትቀላቀል ቶሎ የምትላመድ ይመስልሃል?
ቡልቻ፦ እርግጠኛ ሆኜ የምነግርህ አዎን በፍጥነት ነው የምላመደው፤ አዳማን ለቅቄ ወደ ሰበታ ሳመራ ቶሎ ነበር ቡድኑን የተላመድኩት። ያስቸገረኝ ምንም ነገርም የለም። ኳስ ተጨዋች ስትሆን ደግሞ ሁሌም ስለ ኳስም ነው የምታስበውና የምትግባባው የቅ/ጊዮርጊስን ካምፕ ስቀላቀልም በፍጥነት ቡድኑን እንደምላመደው አውቃለሁ።
ሀትሪክ፦ ባሳለፍከው የኳስ ህይወት ደስተኛ ነህ?
ቡልቻ፦ በጣም።
ሀትሪክ፦ ምርጡ ቆይታህ የት ሳለህ ነው?
ቡልቻ፦ በአዳማ ነዋ! በዚሁ ቡድን የነበረኝ የኳስ ቆይታ በጣም ምርጥ ነበር። የህይወቴንም የመስመር ጅማሬ ያገኘሁበትም ነው ከዛ ውጪም ብዙ ሰዎች ሊያውቁኝ የቻሉበት ሁኔታም ተፈጥሮልኛልና አዳማን ከራሴ በማለየው መልኩ ጥሩ ጊዜን ስላሳለፍኩበት በዚህ ቡድን ሁሌም ደስተኛ ነኝ።
ሀትሪክ፦ በአዳማ ከተማ ቆይታህ አንዴ ተከፋህ ልበል?
ቡልቻ፦ አዎን፤ እሱንማ መቼም አልረሳሁም። አዳማ እኔን ለዛሬ እውቅና ያበቃኝ ክለብ ነው። አሳድጎም ጥሩ ነገርን እንዳገኝም አድርጎኛል። ይሄ ሆኖ ሳለ ግን በዚህ ቡድን ቆይታዬ የሊጉን ዋንጫ አለማንሳቴ ይቆጨኛል። በተለይ በ2010 ይህን ዋንጫ ለማንሳት ተቃርበን ነበር። ያም ሆኖ ግን በአንድ አንድ ጥቃቅን ችግሮች ምክንያት ድሉን አጣንና ያ ሁሌም ያስከፋኛል።
ሀትሪክ፦ በሰበታ ከተማ የነበረህ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ቆይታህ ምን ይመስል ነበር? ቡድናችሁ ስላስመዘገበው ውጤትስ ምን የምትለን ነገር አለ?
ቡልቻ፦ በቡድኑ የነበረኝ ቆይታ ጥሩ ነበር። ይህ ክለብ አገራችን ውስጥ ካሉ ትላልቅ አሰልጣኞች መካከል አንዱን የያዘና በስኳዳችን የሚገኙት ተጨዋቾችም ጥሩ ክህሎትን የያዙ ስለነበሩ በውጤት ደረጃ ጥሩ እየመጣን ነበር። ቢሆንም ግን የፋይናንስ ችግር ጎዳን እንጂ በመጨረሻ ላይ ካስመዘገብነው ጥሩ ከሚባለው የ5ኛ ደረጃ ውጤትም በተሻለ ደረጃ ላይም መቀመጥ እንችል ነበር።
ሀትሪክ፦ በእግር ኳስ ችሎታህ ባለህ ብቃትና ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ከመዘዋወርህ አኳያ ራስህን የሀገሪቱ ምርጥ ከሚባሉት ተጨዋቾች መካከል አንዱ ነኝ ብለህ ታስባለህ?
ቡልቻ፦ በእግር ኳስ ባሳለፍኩት የህይወት ቆይታዬ ጥሩ ተጨዋች እንደሆንኩ አስባለው። ለዛም በአዳማ ከተማና በሰበታ ከተማ ቡድኖች ውስጥ የነበሩኝ ችሎታዬም ምስክሮች ናቸውና እነዛ አይረሱኝም። ያም ሆኖ ግን ጥሩ ተጨዋች ብሆንም የሀገሪቱ ምርጥ ነኝ ብዬ ግን አስቤ አላውቅም። እኔ ወደ ምርጥ ተጨዋችነቱ ለመምጣት እየተንደረደርኩኝ ያለው ተጨዋች ነኝ። ገና ያላወጣሁት እምቅ ችሎታና አቅሙም ስላለኝ ይሄን በአዲሱ ቡድኔ ቅ/ጊዮርጊስ ውስጥ የማሳየው ነው የሚሆነው።
ሀትሪክ፦ በአዳማ ከተማ በነበረህ የተጨዋችነት ቆይታ ጎሎችን ታስቆጥር ነበር፤ ወደ ሰበታ ስታመራ ግን በዚህ ረገድ ተቀዛቅዘሃል። አሁን ደግሞ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ በማምራትህ ጎሎች ይጠበቁብሃልና እነዚህን ስለማሳካት ምን የምትለው ነገር አለ?
ቡልቻ፦ ጎሎችን ስለ ማስቆጠር ከእኔ የሚጠበቅ ስለሆነ ሁሌም ነው ይህን ለማሳካት የማስበው። ጎል ለማግባት ደግሞ የቡድንህ የአጨዋወትህ ዘይቤና አጠገብህ የሚገኙት ልጆችም ወሳኞች ናቸውና አንዳንዴ ከዛ በመነሳት ጥሩ ብጫወትም ጎልን የማላስቆጥርበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ያም ቢሆን ግን ለአንድ ተጨዋች ትልቁ ነገር ሜዳ ሲገባ ምን ነገርን ሰርቶ ወጣ የሚለው ነገር ሊታይ ይገባል። ጎልን በተደጋጋሚ ባያስቆጥር እንኳን ጎልን ለሚያገባና ለሚያስገድደው ተጨዋች ኳስን ሊያቀብል ይገባል። እኔም ይህንን እና ፔናሊቲም ማሰጠት የሚያስችል ብቃቱ አለኝና በዚህም ውስጥ ነው በኳስ ህይወቴ እየተጓዝኩ የምገኘው።
ከዛ ውጪ በአጨዋወቴም ብዙ ጊዜ በግል ስሜታዊ ሆኜ ጎሎችን ለማስቆጠር ከመጣር ይልቅም ቡድኔን በማስቀደም ለአጋር ጓደኞቼ የተመቻቹ ኳሶችን የማቀብልበት ሁኔታም አለና ነገሮችን እኔ የማስኬዳቸውም በዚሁ መልኩ ነው። ወደ ቅ/ጊዮርጊስ በተዘዋወርኩበት የአሁኑ ወቅትም ከእኔ ምን እንደሚጠበቅ የማውቅ ተጨዋች ስለሆንኩኝ ወደ ጎል አስቆጣሪነቴ መመለሴ የማይቀርም ነው።
ሀትሪክ፦ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ፍፃሜ እንዳገኘ ያለውን የእረፍት ጊዜ በምን መልኩ እያሳለፍክ ነው?
ቡልቻ፦ ውድድሩ እንደተጠናቀቀ ከባለቤቴና ከልጄ ጋር ነው በኳሱ ምክንያት ለረጅም ጊዜ ተለያይተን ነበርና በጣም ስለናፈቁኝ በቀጥታ ወደ እነሱ በማምራት የእረፍት ጊዜዬን ለአንድ ወር ያህል ያሳለፍኩት። ከዛ በተጨማሪም ከውድድር ከመምጣቴ አኳያም ለ15 ቀናት ያህል ሪከቨር /በቂ እረፍት አደረግኩና/አሁን በግሌ ወደ ዝግጅት እስክንገባ ድረስ ለአዲሱ የውድድር ዘመን የሚያዘጋጀኝን ልምምድን እየሰራው ነው የሚገኘው።

ሀትሪክ፦ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በዲ.ኤስ ቲቪ በመተላለፉ፣ ፋሲል ከነማና የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር የውድድር ዘመኑ ሻምፒዮና በመሆናቸው ዙሪያ ምን አልክ?
ቡልቻ፦ ቤትኪንግ ወደ አገራችን መጥቶ ሊጋችን በዲ. ኤስ ቲቪ ለመተላለፍ መቻሉ ተጨዋቾቻችን በቀጥታው ስርጭት ከሚቀረፀው ጨዋታ የእንቅስቃሴያቸውን ቪዲዮን ማግኘት ስለሚችሉና ያላቸውን አቅምና ችሎታንም በደንብ ስለሚያውቁበት ከዛ ውጪም ክለቦቻችንም በምን ደረጃና ሁኔታም ላይ እንዳሉ ራሳቸውን ስለሚያዩበት የአገራችንን እግር ኳስ ከዛ በመነሳት አንድ ደረጃ ወደ ላይ ከፍ ያደርገዋልና ይሄ ሊሆን መቻሉ አስደስቶኛል።
ይህን ካልኩ ፋሲል ከነማ የሊጉን ዋንጫ ስላነሳበት ሁኔታ ደግሞ ቡድኑ ትልቅ ክለብ ከመሆኑ ባሻገር ለፍቶና ጥሮ ነውና ውጤታማ የሆነውና ሻምፒዮናነቱ ይገባዋል። አቡበከርን በተመለከተ ደግሞ በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ላይ ሁሉ ለክለቡ ውጤታማነት ከእሱ የሚጠበቁና አንዳንዶቹም አስገራሚ የሆኑ ነገሮችን አስመልክቶናልና ለእሱም የጣምራ የኮከብነት ሽልማቶቹ የሚገባው ሆኖም ነው ላገኘው የቻልኩት።
ሀትሪክ፦ የአቡበከርን በዛ ደረጃ መሸለምን ስታውቅ ለቀጣዩ ጊዜ እኔስ አላልክም?
ቡልቻ፦ እሱንማ ታስባለህ። ለዛም ብዙ ጠንክሮ መስራትም ያስፈልጋልና በጊዜው ሁሉም ነገር ይሆናል።
ሀትሪክ፦ በወደፊት የኳስ ተጨዋችነት ህይወትህ የአንተ ዋንኛ ምኞቶችህ ምንድን ናቸው?
ቡልቻ፦ እንደ ብዙዋኑ ተጨዋቾች የመጀመሪያው ምኞቴ አሁን ላይ ለትልቅ ክለብ ፈርሜያለሁና ከዚህ በፊት በሌላ ቡድን ያላገኘሁትን የሊግ ዋንጫ ማንሳት እፈልጋለውና ያን ቡድናችን በክፍተቶቹ ላይ እያስፈረማቸው ካሉት ተጨዋቾች አኳያና ጥሩ ቡድንን ለመገንባትም ከመፈለጉ የተነሳ ይሄ የሚሳካልን ይመስለኛል። ሌላው የእኔ ምኞት ለብሄራዊ ቡድን ተመርጦ በመጫወት ሀገርን በስኬታማነት ማገልገል መቻልና ከሀገር ወጥቶ መጫወትም ነውና ይሄ እልሜም ከፈጣሪ እርዳታ ጋር የሚሳካ ይመስለኛል።
ሀትሪክ፦ ባለቤትህ ከአንተ የኳስ ህይወት ጀርባ ያላት አስተዋፅኦ በምን ሁኔታ ይገለፃል? ስለ እሷም የተወሰነ ነገር ብትለን?
ቡልቻ፦ ባለቤቴ እየሩሳሌም ስዩም ትባላለች። ኤምራኬል ቡልቻ የተባለች የአንድ ዓመት ከአንድ ወር ህፃን ልጅም አለን። በኳስ ተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ እሷ ባለቤቴ ለእኔ ያደረገችው ነገር በገንዘብ ተተምኖ አያልቅም። እስካሁን ለመጣሁበት መንገድ እሷ ዋናው ሰው ናት። ለህይወቴ አስፈላጊም ሰው ነችና ለምታደርግልኝ እገዛና እንክብካቤዋ ከልቤ ነው ላመሰግናት የምፈልገው።
ሀትሪክ፦ አንድ ነገር ብለህ ብናጠቃልል?
ቡልቻ፦ ከላይ ብዙዎቹን ነገሮች ተናግሬያለው ያን ካልኩ እስካሁን በኳሱ ለመጣሁበት መንገድ ከጎኔ ሆነው ለረዱኝ ቅድሚያውን ፈጣሪ ይውሰድና ለእሱ፣ ለቤተሰቦቼ እንደዚሁም ለባለቤቴና ሌሎች ብዙ ሰውች አሉና እነሱ ይመስገኑልኝ።


