በሀያ አራተኛዉ ሳምንት የመጀመሪያ ዕለት ጨዋታ በወንድማማቾች ደርቢ ፋሲል ከነማ እና ባህርዳር ከተማ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።
በተመጣጣኝ የሜዳ ላይ ፉክክር ቀን 9:00 ሰዓት ሲል በጀመረዉ ጨዋታ ባህርዳር ከተማዎች የመጀመሪያ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። በዚህም ከግራ መስር በኩል ፍራኦል መንግስቱ ያሻማትን ኳስ አጥቂዉ ሀብታሙ ካበረደ በኋላ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ግን ለጥቂት ወጥታለች።
በአጠቃላይ በሙከራ ረገድ ቀዝቃዛ በነበረዉ የመጀመሪያዉ አጋማሽ ከዚች የባህርዳር ከተማ ተጠቃሽ ሙከራ በኋላ አፄዎቹ በአጥቂዉ ፍቃዱ አለሙ አማካኝነት ጥሩ የግብ ዕድል መፍጠር ችለዉ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ተጫዋቹ ኳሷን በአግባቡ መጠቀም ባለመቻሉ ምክንያት ጨዋታዉን መምራት የሚችሉበትን ግብ ሳያገኙ ቀርተዋል። በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታ አፄዎቹ በይበልጥ በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ ሁነዉ የተስተዋሉ የነበሩ ቢሆንም ነገር ግን ያን ያህል እምብዛም ተጠቃሽ ሙከራን ሁለቱም ክለቦች ሳያደርጉ አጋማሹ ተጠናቋል።
- ማሰታውቂያ -
በሁለተኛዉ አጋማሽም በተመሳሳይ አፄዎቹ የተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉ ቢሆንም ነገር ግን አሁንም ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ ቡድን ሶስተኛዉ የሜዳ ክፍል ደርሰዉ አደጋዎችን በመፍጠር ረገድ ተዳክመዉ ተመልክተናል። በተቃራኒው ምንም እንኳን በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ብልጫ ይወስድባቸዉ እንጅ አደጋዎችን በመፍጠር ረገድ የተሻሉ የነበሩት የጣና ሞገዶቹ በሀብታሙ ታደሰ እና ተቀይሮ የገባዉ ወንድወሰን ጥሩ ጥሩ አንድ ሁለት ዕድሎችን ቢያገኙም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዉ ጨዋታዉ ያለ ግብ በአቻ ዉጤት ተጠናቋል።
አመሻሽ 12:00 በተደረገዉ ጨዋታ አዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታቸዉን አንድ አቻ በሆነ ዉጤት አጠናቀዋል።
አመሻሽ 12:00 ሰዓት ሲል በዋና ዳኛ ዮናስ ካሳሁን መሪነት በጀመረዉ የአዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ሁለቱም ክለቦች ወሳኟን ሶስት ነጥብ ለማግኘት ከነበራቸዉ ጉጉት አንፃር ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር ብንመለከትበትም ነገር ግን ጨዋታዉ በሙከራ ረገድ ጥሩ ነበር ማለት አይቻልም። በዚህም በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ እምብዛም ሙከራዎችን ባላስመለከተን ጨዋታ በ26ተኛዉ ደቂቃ ላይ ቢኒያም አይተን በአዳማ በኩል ድንቅ ሙከራ ከሳጥን ዉጭ ቢያደርግም ነገር ግን ግብ ጠባቂዉ ዐብዩ ካሳየ ኳሷን ይዟል።
የሜዳዉን የኳስ ብልጫ ለመቆጣጠር ሰመጥሩ የነበሩት ድሬዳዋዎች በ30ኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ በአጥቂዉ ካርሎስ ዳምጠዉ አማካኝነት ድንቅ ሙከራ ቢያደርጉም ነገር ግን ግብ ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ የዳኛዉ ፊሽካ ሲጠበቅ አዳማዎች ግብ ለማስቆጠር ተቃርበዉ ነበር ፤ በዚህም ሱራፌል የግል ብቃቱ ተጠቅሞ ግብ ጠባቂዉን አታሎ ማለፍ ከቻለ በኋላ ኳሷን ወደ ግብ ልኳት የነበረ ቢህንም ነገር ግን ኳሷን መሐመድ አብዱለጢፍ ደርሶ አዉጥቷታል።
ከዕረፍት መልስ በተመሳሳይ እንቅስቃሴ በቀጠለዉ ጨዋታ በ58ተኛዉ ደቂቃ ላይ ድሬዳዋ ከተማዎች ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዉ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ያሬድ ታደሰ ኳሷን መትቷት ግብ ጠባቂዉ ይዟታል። በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታም በ78ተኛዉ ደቂቃ ላይ ቦና አሊ ያቀበለዉን ኳስ ፍቅሩ አለማየሁ ተጫዋቾችን አታሎ በማለፍ ጭምር ኳሷን ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
ብርቱ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለዉ ጨዋታ በ87ተኛዉ ደቂቃ ላይም ብርቱካናማዎቹ ከብዙ ጥረት በኋላ ተሳክቶላቸዉ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። በዚህም ከማዕዘን አሰጋኸኝ ያሻማዉን ኳስ እያሱ ለገሰ በግንባሩ ወደ ግብነት በመቀየር ጨዋታዉ አቻ እንዲጠናቀቅ አስችሏል።