*….አምስት ክለቦች ፌዴሬሽኑ ላይ ክስ መስርተዋል…
*…. ለክልል ሻምፒዮና በ13ቱ ክለቦች ውጤት ላይ
ይመሰረታል ተብሏል።
*…. ፉሪ ክ/ከተማ የደረጃ ሰንጠረዡን እየመራ ነው…
- ማሰታውቂያ -
የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር የአዲስ አበባ ከፍተኛ ከፍተኛ ዲቪዚዮን የ2016 ሻምፒዮና ተጠናኮሮ
እንደቀጠለ ነው።
በ13 ክለቦች መሃል እየተካሄደ ባለው ሻምፒዮና ፉሪ ክፍለ ከተማ በ11 ጨዋታ 31 ነጥብ ይዞ ውድድሩን እየመራ ሲሆን ድሮጋና አራዳ ክፍለ ከተማ በ26 እና 22 ነጥቦች ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። ኤልቴክስ፣ የኛ አዲስ ከቴ ፣ ፎርቹኔትና ፍቅር በአንድነት ከ4-7 ያለውን ስፍራ ሲይዙ ከ8-13 ያለውን የደረጃ ሰንጠረዥ ሽሮሜዳ ፣ ቃኘው፣ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ፣ ዳለቲ ፣ ቫርኔሮና አቦል ዩናይትድ በመያዝ ውድድራቸውን እያካሄዱ ይገኛሉ።
13ቱ ክለቦች እያደረጉት የነበረው ውድድር ቅሬታ በነበራቸውና መብታችን ተነካ ባሉት 5 ክለቦች ክስ በመደበኛ ፍ/ቤት ታግዶ የነበረ ሲሆን የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ደረጄ አረጋ ባቀረቡት ይግባኝና በሰጡት ምላሽ እግዱ ተነስቶ ውድድሮቹ መቀጠላቸው ታውቋል። ቅሬታ ያላቸው አምስቱ ክለቦች ኒው ሆፕ፣ ገርጂ ፌሰን ፣
መድኃኒዓለም፣ ጨርቆስና ቃሊቲ 08 ማዞሪያ መሆናቸው ታውቋል።
13ቱም ክለቦች የመመዝገቢያ 60ሺህ ብር ከፍለው እየተወዳደሩ ሲሆን አምስቱ ግን አቅም የለንም በማለት 30 ሺህ ብር ከፍለው ወደ ውድድር እንመለስ ማለታቸው ቅሬታ ፈጥሯል። የፌዴሬሽኑ የጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አበበ ድረስ ከስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አቋም በተለየ የአምስቱን ክለቦቼ ጥያቄ ተቀብለው ለከፈሉት ክፍያው ደረሰኝ መቁረጣቸው አምስቱ ክለቦች ለምስክርነት ማቅረባቸው ታውቋል።
የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊዎች ልዩነቱን ለማጥበብ የፌዴሬሽኑን አመራሮችና 18ቱን ክለቦች ጠርተው አነጋግረዋል። አምስቱ ክለቦች ከ13ቱ ክለቦች ጋር ለመወዳደር ካልቻሉ ብቻቸውን ውድድር ለማካሄድ ጥያቄ ያቀረቡ ቢሆንም 13ቱ ክለቦችና ፌዴሬሽኑ ተቃውሞ በማሰማታቸው ሳይሳካ ቀርቷል። በውድድሩ ከ1-4ኛ ደረጃ ይዘው የሚያጠናቅቁት ኮለቦች የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በሚያዘጋጀው የክልል ሻምፒዮና አዲስ አበባን ወክለው የሚወዳደሩ ሲሆን ይህን ውክልና 13ቱ ክለቦች በሚያመጡት ውጤት መሰረት የሚከናወን መሆኑን ፌዴሬሽኑ አሳውቋል።
የከተማ አስተዳደሩ የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ ከውይይቱ በኋላ በሰጡት መመሪያ መሰረት ውድድሩ እንዲቀጥልና ካሁን በኋላ በምንም ምክንያት ውድድሩ መቋረጥ እንደሌለበት ችግሮችም በውይይት ብቻ እንዲፈቱ አሳስበዋል።
እስካሁን ስብሰባው ባይካሄድም አምስቱ ክለቦች፣ ከ13ቱ ክለቦች ደግሞ ሶስቱ ተወክለው ፌዴሬሽኑ ባለበት በቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ዳዊት ትርፉ ሰብሳቢነት በችግሩ ዙሪያ ውይይት እንዲደረግ ቢወሰንም እስካሁን ውይይቱ አለመደረጉን ከክለቦቹ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።