ዋልያዎቹ በምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታ ሽንፈት አስተናግደዋል

ምሽት 1 ሰዓት ላይ በካሜሩን እና ቡርኪናፋሶ ጨዋታ ጅማሮውን ያደረገው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያን እና ኬፕ ቨርዴን አገናኝቶ 45+1 ላይ በተቆጠረ ግብ ሰማያዊ አሳነባሪዎቹ ሶሰት ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል ።

በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ኳስን ከኋላ መስርቶ ለመጫወት የሞከረው የኢትዮጵያ ብሄራዊ በቀላሉ ከራሱ የሜዳ ክልል ለመውጣት ተቸግሮ ነበር ። ይባስ ብሎም ገና በ8ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ባየህ ጁልዮ ታቫሬው ላይ በሰራው ጥፋት የጨዋታው የመሀል ዳኛ የማስጠንቀቂያ የቢጫ ካርድ አሳይተውት የነበረ ቢሆንም በድጋሚ ጥፋቱን በቫር ከተመለከቱ በኋላ ተጫዋቹ በቀጥታ የቀይ ካርድ ከሜዳ አሰናበተውታል ። ይህም ቀጣዮቹን ደቂቃዎች ለዋልያዎቹ ከባድ አድርጎት ነበር ።

በቀይ ካርዱ ምክንያት አሰልጣኝ ውበቱ መሱድ መሀመድን በማስወጣት ምኞት ደበበን ያስገቡ ሲሆን በተወሰነ መልኩ መደናገጥ የታየባቸው ዋልያዎቹ ወደ ፊት ኳሱን ይዘው ለመሄድ የሚያደርጓቸው ጥረቶች እምብዛም ነበሩ ። በኬፕ ቨርዴ በኩል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ላይ ጫና በማድረግ ኳሱን እንደፈለገው እንዳይጫወት በማድረግ ረገድ በአመዛኙ የተሳካላቸው ነበሩ ።

በጨዋታው የመጀመሪያው አስደንጋጭ ሙከራ 27ኛ ደቃቃ ላይ ነበር የተደረገው ። ከቀኝ መስመር ላይ ጋሪ ሮድሪጌዝ ወደ ግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ ምኞት ደበበ ለማውጣት ሲሞክር ተጨርፎ ግብ ከመሆን ያዳነው ግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆ ነበር ። ከዚህ ሙከራ በኋላም በተወሰኑ አጋጣሚዎች ከዚህ መስመር ወደ ግብ በሚላኩ አደገኛ ኳሶች ሰማያዊ አሳነባሪዎቹ የግብ ዕድል ለመፍጠር ጥረቶችን አድርገው ነበር ።

በዋልያዎቹ በኩል 42ኛው ደቂቃ ላይ በረጅም ወደ ግብ ክልል የተሻገረውን ኳስ የኬፕቨርዴው ተከላካይ ፒኮ ለግብ ጠባቂው በደረቱ ለማቀበል ሲሞክር አቡበከር ናስር ፈጥኖ በመሮጥ ኳሱን ለማግኘት ያደረገው ጥረት በማርስዮ ዳ ሮሳ ከሽፎበታል ።

የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ ላይ ነበር የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ግብ ያስተናገደው ። ከግራ መስመር በአየር ላይ ወደ ግብ ክልል የተሻገረውን ኳስ የዋልያዎቹ ተከላካዮች ወቷል ብለው በተዘናጉበት ጊዜ ጋሪ ሮድሪጌዝ ደርሶበት ወደ ግብ የላከው ኳስ በጁልዮ ታቫሬዝ አማካኝነት ግብ ሆኗል ።

በሁለተኛው አጋማሽ ዋልያዎቹ ከመጀመሪያው በተሻለ ለመንቀሳቀስ የሞከሩ ሲሆን የተለያዩ ቅያሪዎችንም በማድረግ ግብ ለማግኘት ጥረቶች አድርገዋል ። በተለይም በአጋማሹ ጅማሮ በፈጣን ወደፊት ለማለፍ ፍላጎቶች ይስተዋሉ ነበር ። ሆኖም አሁንም ቢሆን ከራሱ የሜዳ ክልል ለመውጣት የተቸገረው የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድን በሚነጠቁ ኳሶችን በቶሎ ወደ ተጋጣሚ ክልል በማድረስ የማጥቀታል ዕድልን ለመፍጠር ቢሞክርም የሚገኙ ኳሶች በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ኬፕቨርዴ የግብ ክልል ማድረስ አለመቻል እና በአየር የሚላኩ ኳሶች የሰማያዊ አሳነባሪዎቹ ሲሳይ መሆኑ ያሰቡትን እንዳያሳኩ አግዷቸዋል ።

የማጥቃት እንቅስቃሴውን ጥሩ ለማድረግ በሁለት የተለያዩ ቅያሪዎችም ጌታነህ ከበደ ፤ አማኑኤል ገብረሚካኤል ፤ አቡበከር ናስር እና ሱራፌል ዳኛቸው ወተው ፍፁም አለሙ ፤ ፍሬው ሰለሞን ፤ ሙጂብ ቃሲም እና በዛብህ መለዮ ወደ ጨዋታው መግባት ችለዋል ። ምንም እነኳን የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን መውሰድ ቢቻሉም አብዛኞቹ ቅብብሎች በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የሜዳ ክልል መሆን እና ወደ ኋላ የሚመለሱ ጥቅም አልባ ኳሶች ወደ ፊት የሚደረገውን እንቅሰቃሴ ደካማ እንዲሆን አስችለውታል ።

በኬፕቨርዴ በኩል 48ኛ እና 69ኛ ደቂቃ ላይ በኬኒ ሮቻ አማካኝነት ወደ ግብ የተሞከሩት ጠንካራ ኳሶች በተክለማርያም ሻንቆ ተመልሰዋል ። በመስመሮች ሲያደርጓቸው የነበሩት የማጥቃት አማራጮችም በተደጋጋሚ በዋልያዎቹ የተከላካይ ክፍል ሲከሽፍባቸው ተመልክተናል ። ጨዋታውም ሌላግብ ሳያስተናግድ በኬፕቨርዴ 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቀቀ ።

ውጤቱን ተከትሎም ምድቡን ካሜሩን ስትመራ ኬፕቨርዴ ቡርኪናፋሶ እና ኢትዮጵያ በቅደም ተከተል እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል ። የምድቡ ቀጣይ ጨዋታዎች በመጪው ሀሙስ የሚደረጉ ሲሆን ምሽት 1 ሰዓት ላይ ካሜሩን ከኢትዮጵያ እንዲሁም ምሽት 4 ሰዓት ላይ ቡርኪናፋሶ ከ ኬፕቨርዴ በኦሎምቤ ስታድየም የሚጫወቱ ይሆናል ።

Writer at Hatricksport

Facebook

Habtamu Mitku

Writer at Hatricksport

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *