በሀያ አራተኛዉ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዕለት ጨዋታ ቀን ዘጠኝ ሰዓት ላይ በተደረገ መርሐግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ መድን ተሸንፏል ።
ከቀናት በፊት አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታን ከአሰልጣኝነት በጊዜያዊነት ማገዱን የገለፀዉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፤ በምትኩ በሾማቸዉ አሰልጣኝ ደረጀ እና ሳምሶን እየተመራ ጨዋታዉን የጀመረ ሲሆን በመርሐግብሩም ከዚህ ቀደሙ ጨዋታ በርከት ያሉ ቅያሪዎችን በማድረግ ወደ ሜዳ የገቡ ቢሆንም በመጀመሪያዎቹ ደቂቃ የሜዳዉ ላይ እንቅስቃሴ እንዲሁም በሙከራ ረገድ ግን የአሰልጣኝ ገ/መድህን ሀይሌዉ ቡድን ኢትዮጵያ መድን ተሽሎ ተስተዉሏል።
በዚህም መድኖች ከመስመር በተሻሙ ኳሷች በተከላካዩ ሚሊዮን ሰለሞን እና አጥቂዉ ብሩክ ሙሉጌታ አማካኝነት የመጀመሪያ ጥሩ ሙከራዎችን ማድረግ ሲችሉ ፤ በተቃራኒው መጠነኛ ብልጫ የተወሰደባቸዉ ፈረሰኞቹም በ33ተኛዉ ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ሄኖክ አዱኛ ያሻማዉን ኳስ ናትናኤል ዘለቀ በግንባሩ በመግጨት ወደ ግብ ቢሞክርም ግብ ጠባቂዉ አቡበከር መልሶበታል።
አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሶስት ያክል ደቂቃዎች ሲቀሩም ኢትዮጵያ መድኖች ለግብ የቀረበ ግሩም ሙከራ ማድረግ ችለዉ ነበር ፤ በዚህም ወገኔ ገዛኸኝ ያሻገረለትን ኳስ አጥቂዉ ብሩክ ወደ ግብ ቢሞክርም ኳሷ ወደ ዉጭ ወጥታለች።
- ማሰታውቂያ -
ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ክለቦች ተመጣጣኝ ፉክክር አድርገዉ በ52ተኛዉ ደቂቃ ላይም ግብ ተቆጥሯል ። በዚህም በግራ መስመር በኩል ተከላካዩ ያሬድ ካሰየ ወደ መሀል ያቀበለዉን ኳስ አጥቂዉ ብሩክ ሙሉጌታ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
ግብ ከተቆጠረባቸዉ በኋላ የአቻነት ጎል ለማግኘት መጣር የጀመሩት ፈረሰኞቹ ከብዙ ደቂቃዎች ጥረት በኋላ በ72ተኛዉ ደቂቃ ላይ ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። በዚሁ ደቂቃም ከቀኝ መስመር ሄኖክ አዱኛ ያሻማዉን ኳስ ግቅ ጠባቂዉ አቡበከር ኑራ ጨርፎ ከመለሰ በኋላ ረመዳን የሱፍ ከግራ ያሻማትን ያችኑ ኳስ ዳግማዊ በጭንቅላቱ ሲገጫት በዕለቱ ድንቅ የነበረዉ አቡበከር ኑራ እንደምንም ጥሮ ኳሷን አዉጥቷታል።
በተጨማሪም በ87ተኛዉ ደቂቃ ላይ ናትናኤል ዘለቀ ብሩክ ሙሉጌታ ላይ የሰራዉን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠዉን የቅጣት ምት ኳስ የግራ ተከላካዩ ያሬድ በሚገርም ብልጠት ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ኳሷን ባህሩ ነጋሽ እንደምንም አዉጥቷል። በጨዋታዉ መጠናቀቂያ በ90+1 ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር በኩል አብዱልከሪም ያሻገረለትን ኳስ ያገኘዉ ጀሮም ፍሊፕ በግንባሩ ቢገጭም ነገር ግን ኳሷ በግቡ አናት ለጥቂት ወደ ዉጭ ወጥታ መርሐግብሩ በኢትዮጵያ መድን 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወልቂጤ ከተማን ማሸነፍ ችሏል።
በፌደራል ዳኛ ሀይማኖት አዳነ በመራዉ የምሽቱ ጨዋታ የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ወስዶ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን በሙከራ ረገድ የተቀዛቀዘ አጀማመር አድርጓል። በተቃራኒው በአብዛኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በራሳቸዉ የሜዳ ክፍል ወደ ኋላ አፈግፍገው በመልሶ ማጥቃት የሚገኙ ዕድሎችን ለመጠቀም የሞከሩት ወልቂጤ ከተማዎች በዚህ ሂደት ቢጀምሩም ነገር ግን ጥረታቸዉ የዘለዉ ለ25 ደቂቃዎች ነበር በዚህም በተጠቀሰዉ ደቂቃ ላይ እንዳለ ዮሐንስ ያሻገረዉን ኳስ የወልቂጤዉ ተከላካይ በአግባቡ ማፅዳት ባለመቻሉ ምክንያት የተገኘዉን ኳስ ሱለይማን ሀሚድ ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
ግብ ከተቆጠረባቸዉ በኋላ በተሻለ መነቃቃት መንቀሳቀስ የጀመሩት ወልቂጤ ከተማዎች በሳምሶን ጥላሁን እና ዳንኤል ደምሱ አማካኝነት ጥሩ የግብ ዕድሎችን ቢፈጥሩም ነገር ግን ወደ ግብ መቀየር ሳይችሉ ቀርተዉ አጋማሹ ተጠናቋል። ከዕረፍት መልስ በቀጠለዉ ጨዋታ በ48ተኛዉ ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጨማሪ ግብ አስቆጥሯል። በዚህም ከግራ መስመር በኩል አዲስ ግደይ ያቀበለዉን ኳስ ፉዓድ ፈረጃ አክርሮ ወደ ግብ በመምታት ግብ አስቆጥሮ የክለቡን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል።
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት ጎሎችን ካስቆጠሩ በኋላ በአብዛኛው የጨዋታውን ቴምፖ በማቀዝቀዝ እና ተጋጣሚያቸው አደጋ እንዳይፈጥርባቸዉ ወደ ራሳቸዉ የግብ ክልል አፈግፍገዉ በመጫወት ሲቀጥሉ ፤ በተቃራኒው በጨዋታዉ እጅጉኑ ደካማ የነበሩት ወልቂጤዎች ከቆሙ ኳሶች እና በመልሶ ማጥቀታት አደጋ ለመፍጠር ሲያደርጉ የነበረዉ ጥረት ተሳክቶላቸው በጨዋታው መገባደጃ በ89ነኛዉ ደቂቃ ላይ ሳምሶን ጥላሁን ከርቀት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታዉ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት ለአንድ አሸናፊነት ተጠናቋል።