በ21ኛው ሳምንት የመጨረሻ እና በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአዳማ ከተማ የመጨረሻ ቆይታ ዕለት በቀዳሚነት የተደረገው እና ስደስት ግቦችን ያስተናገደው የአዲስ አበባ ከተማ እና የሀድያ ሆሳዕና ጨዋታ ሶስት አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል ።
አዲስ አበባ ከተማዎች በ20ኛው ሳምንት ከአዳማ ከተማ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ላይ ከተጠቀሙት የመጀመሪያ አሰላለፍ አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ በመሀመድ አበራ ምትክ አቤል ነጋሽን ሲያሰልፉ በሀድያ ሆሳዕና በኩል ደጌሞ በሳምንቱ ሀዋሳ ከተማን በረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ 11 በተመሳሳይ አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ በፍቅረየሱስ ተክለብርሃን ምትክ እያሱ ታምሩን በማሰለፍ ጨዋታውን መጀመር ችለዋል ።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ገና ከጅምሩ በግቦች የታጀበ ነበር ።
ሮቤል ግርማ ከግራ መስመር በረጅም በተቃራኒ አቅጣጫ የተጋጣሚ ሳጥን አካባቢ ለነበረው እንዳለ ከበደ ያደረሰውን ኳስ እንዳለ ወደ መሀል ለአዶንጎ በሚቀንስበት ጊዜ ፍሬዘር ካሳ በአዶንጎ ላይ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ አዲስ አበባ ከተማዎች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ አዶንጎ በማስቆጠር አዲስ አበባ ከተማን ገና በጊዜ መራ አድርጓል ። ግቡም ጋናዊውን አጥቂ በኮከብ ግብ አግቢነቱ ፉክክር ላይ ከቶጓዊው የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂ እስማኤል ኦሮ ኦጎሮ እኩል 10 ግቦች ላይ እንዲደርስ አስችሎታል ።
ቀድመው በፍፁም ቅጣት ምት ግብ ያስተናገዱት ሀድያ ሆሳዕናዎች ከአራት ደቂቃዎች በኋላ በተመሳሳይ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ አቻ መሆን ችለዋል ። ብርሀኑ በቀለ በቀኝ መስመር ኳስ እየገፋ በሳጥን ውስጥ በገባበት ወቅት በእዮብ በቀታ በተሰራበት ጥፋት ሀድያ ሆሳዕናዎች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ሳምሶን አበበ በ7ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል ።
በሰባት ደቂቃዎች ሁለት ግቦችን ያስመለከተን ጨዋታ 12ኛው ደቂቃ ላይ ሌላ ግብ አስመልክቶናል ።
በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ የአዲስ አበባ ከተማዎች ፈጣን መልሶ ማጥቃት ወደ ሀድያ ሆሳዕና ሳጥን ደርሶ በአዶንጎ የመጨረሻ ኳስ አቀባይነት እና በአቤል ነጋሽ ጨራሽነት የመዲናዋ ክለብ 2 – 1 መምራት ችሏል ።
ሀድያ ሆሳዕናዎች በቁጥር በርከት ብለው በአዲስ አበባ ከተማ የሜዳ ክፍል ላይ በመድረስ በተጋጣሚያቸው ላይ ጫና መፍጠር የቻሉ ሲሆን ከአዲስ አበባ ከተማ በተሻለም የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል ።
በ25ኛው ደቂቃ ላይ የሙሉቀን አዲሱን ኳስ ማግኘት የቻለው ሀብታሙ ታደሰ የአዲስ አበባ ከተማ ተጫዋቾች መዘናጋትን ተጠቅሞ ግብ ጠባቂውንም በማለፍ ጭምር ሀድያ ሆሳዕና ዳግም አቻ እንዲሆን አድርጓል ።
በ34ኛው ደቂቃ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ መልሶ ማጥቃት ዳግም ፍሬ ሲያፈራ አቤል ነጋሽ በፈጣን እንቅስቃሴ ኳሱን እየገፋ ወደ ሳጥኑ ይዞ በመድረስ በግራ እግሩ አከርሮ ወደ ግብ የመታው ኳስ በያሬድ በቀለ መረብ ላይ አርፏል ።
መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃዎች ላይ አቤል ነጋሽ ከቅጣት ምት ሮቤል ግርማ ያሻገረውን ኳስ በግንባር ገጭቶ ማስቆጠር ችሎ የነበረ ቢሆንም ኳሱን ወደ ግብ በሚልክበት ጊዜ እንዳለ ከበደ ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ የነበረ በመሆኑ ገና በመጀመሪያው አጋማሽ ሀት ትሪክ የመስራት ዕድሉ ሳይሳካ ቀርቷል ።
የመጀመሪያው አጋማሽም በአዲስ አበባ ከተማ የ3 – 2 መሪነት ተጠናቀቀ ።
በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ሀድያ ሆሳዕና በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ የአዲስ አበባን የተከላካይ ክፍል አልፈው የግብ ዕድሎችን ለማግኘት የጣሩበት ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ በኩል በመጀመሪያው አጋማሽ እንደተመለከትነው በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ሂደቶች ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ታትረዋል ። የአዲስ አበባ ከተማ የአማካኝ ተከላካይ ቻርለስ ሪባኑ የሀድያ ሆሳዕናን የኳስ ፍሰት በማቋረጥ እና የሚነጠቁ ኳሶች በፍጥነት ወደ ፊት በማድረስ ለአዲስ አበባ ከተማ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ትልቅ ሚና መጫወት ችሏል ።
በአጋማሹ የመጀመሪያ ሙከራ 47ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አርፊቹ ከቅጣት ምት ወደ ግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ ሮቤል ግርማ ገጭቶ ወደ ራሱ ግብ የሄደውን ኳስ ዳንኤል ተሾመ ግብ ከመሆን አድኖታል ።
65ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አርፊቹ ከግራ መስመር ያሻገረው ኳስ በዘሪሁን አንሼቦ በግንባር ተጨርፎ ዳንኤል ተሾመ ጋር የደረሰው ኳስ ግብ ጠባቂው ኳሱን በሚገባ መቆጣጠር ሳይችል ቀርቶ ከእጁ አምልጦት ሊቆጠር የነበረ ቢሆንም እንደምንም ኳሱን ከመስመር ላይ የመለሰው ሲሆን ከሰከንዶች በኋላ ሄኖክ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ወደ ግብ የመታውን ኳስ መቆጣጠር ችሏል ። ነገር ግን ዳንኤል ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት በጨዋታው ላይ የነበረውን ቆይታ ከ65ኛው ደቂቃ ማለፍ ሳይችል በወንድወሰን ገረመው ተቀይሮ ወጥቷል ።በሀድያ ሆሳዕና በኩል ሳምሶን አበበን ቀይሮ የገባው ኤፍሬም ዘካርያስ 79ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ የመታው ኳስ በአስደናቂ ሁኔታ የግቡን አግዳሚ የውስጥ ክፍል ገጭቶ ከመረብ ላይ አርፏል ።
ለሶስተኛ ጊዜ ከመምራት አቻ የሆኑት አዲስ አበባ ከተማዎች ከግቡ በኋላ ሌላ ግብ ለማስቆጠር በአጋማሹ ቀደም ብሎ ከነበራቸው በተሻለ ወደ ፊት አልፈው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል ። መደበኛው የጨዋታ ክፍል ጊዜ በተጨማሪ ደቂቃዎች ላይ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ አጥቂው ሪችሞንድ አዶንጎ በግሩም ሁኔታ በመቀስ ምት ማስቆጠር ቢችልም ረዳት ዳኛው ከጨዋታ ውጪ በሚል ሽረውታል ።
ግቡ ቢፀድቅ ቡድኑን አሸናፊ በግሉም የሊጉ ኮከብ ግብ አግቢነትን መምራት ይችል የነበረው ሪችሞንድ አዶንጎ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ብስጭቱን ሲገልፅ ተስተውሏል ።
ውጤቱን ተከትሎ ሁለቱም ክለቦች ነጥባቸውን በአንድ አንድ ማሳደግ ቢችሉም በደረጃቸው ላይ ለውጥ ማድረግ ያልቻሉ ሲሆን አዲስ አበባ ከተማ 21 ነጥቦችን ሰብስቦ 14ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ሀድያ ሆሳዕና ደግሞ በ29 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል ።
በ22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ( ባህርዳር ) በመጪው ሚያዝያ 29 ( ቅዳሜ ) ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ ሀድያ ሆሳዕና መከላከያን ሲገጥም ከሁለት ቀናት በኋላ ግንቦት 1 ( ሰኞ ) በተመሳሳይ ሰዓት አዲስ አበባ ከተማ ወልቂጤ ከተማን ይገጥማል ።
አስተያየት ይስጡ