የአዲስ አበባ ከተማ እግርኳስ ፌዴሬሽንና “ዋናው” ሀገር በቀል ትጥቅ አምራች ኩባንያ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ተፈራረሙ።
በሁለቱ ተቋማት መሃል የተካሄደው ስምምነት የ3.4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚያደርግ ስምምነት ሲሆን ስምምነቱ ለሶስት ዓመት የሚጸና በየአመቱ የሚታደስ ይሆናል ተብሏል።
በኔክሰስ ሆቴል በተካሄደ የፊርማ ስነስርዓት ላይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ደረጄ አረጋ እንደተናገሩት
“በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ17 አመት በታች ውድድርን ዋናው ካፕ ተብሎ ይጠራል የሰፈር ለሰፈር ውድድርንም ዋናው ትጥቅ አምራች ኩባንያ ስፖንሰር እንደያደርገው ተስማምተናል። በስምምነቱ መሰረት የዋናው የስፖርት ትጥቅ መሸጫ ሱቆችም ከዛሬ ጀምሮ በበርካታ የአዲስ አበባ ከተማ ቦታዎች ይከፈታል” ሲሉ ተናግረዋል።
- ማሰታውቂያ -
እንደ አቶ ደረጄ አገላለጽ ” የጃንሜዳ ካፕ የውድድር መጠርያ ወደ አዲስ አበባ ካፕ እንዲለወጥ አድርገናል የከተማው እግርኳስ ፌዴሬሽን ከ10 እና 13 አመት ሴትና ወንድ እግርኳስ ሰልጣኞች እውቅ በሆኑና በአንደኛ በሁለተኛ በሲ ላይሰንስ በሰለጠኑ አሰልጣኞች የሚሰለጥኑ ይሆናል። ሰፈር ለሰፈር በምናደርገው ከሜዳና ከሜዳ ውጪ እግርኳሳዊ ውድድርን ለማስኬድ በንጽጽር ጥሩ የተባለ ሜዳ አለን በአስራ አንዱም ክፍለ ከተማ ያሉ የማዘውተሪያ ሜዳዎችን ለውድድሩ መርጠን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን” ሲሉ አስረድተዋል።
ይሄኛው ስምምነት ከሌላው ሀገር በቀል ትጥቅ አምራች ተቋም ጎፈሬ ጋር ጋር ካላችሁ ስምምነት ጋር አይጋጭም ወይ? የተባሉት አቶ ደረጄ “እግርኳሱ ላይ ካለው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ ሁለቱም አንድ ላይ ቢሆኑም አይበቁንም ከዋናው ጋር ያለን ስምምነት ከማንም ጋር የሚጋጭ አይደለም በዓመት ስምንት ውድድር ስናካሂድ “ዋናው” የወሰደው ሁለቱን ብቻ ነው.. ካሉን ውድድሮች አንጻር ከጎፈሬ ውጪም ለሌላም የሚበቃ ነው ለማንኛውም ከተቋማቱ ጋር ከገባነው ህጋዊ ውል ጋር ተያይዞ የሚጋጭ ነገር የለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። የዋናው ትጥቅ ኩባንያ ባለቤትና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሃ/ስላሴ ገ/ክርስቶስ በበኩላቸው ” የገበያ ችግር የለብንም ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ፋሲል ከነማና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አብረውን ይሰራሉ ያበረታቱናል እገሌ ከሚባል ተቋማት ውጪ ሌላ አንቀበልም አይሉም በዚህም ደስተኛ ነን እግርኳሱ ሰፊ ኢንዱስትሪ ነው ገቢ እስካገኘን ስራው እስከጠቀመንና እስካመንበት ድረስ ማንም ይስራው ገበያውን አንተወውም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ስለ ኩባንያቸው የዘረዘሩት አቶ ሃ/ስላሴ “ልብሶቻችን ተወዳጅና ለህብረሰቡ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ ናቸው
የስፖርት ልብስ ዕጥረት የማህበረሰባችን ችግር በመሆኑ በመጠነኛ ዋጋ ጥራቱን የጠበቀ ትጥቅ ለገበያ ለማቅረብ ወስነን ገብተንበታል። የኛ አልባሳት በፕሪሚየር ሊግና በአፍሪካ እየተለበሰ ነው ሩዋንዳ ሱቅ አለን በምስራቅ አፍሪካም ትጥቆቻችን ይፈለጋሉ ስራውን ስንሰራ ሁሉንም ነገር የማንገልጸው የንግድ ምስጢር ስለሆነ ነው ስለ ስራችን መግለጫ ስንሰጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ምርቶቻችን ግን ታዋቂና የውጪ ምንዛሬ እያስገኙ ናቸው። በውሉ መሠረት ማህበራዊ ግዴታችንን ስንወጣ በተመሳሳይ ገበያ ይኖረናል እንሸጣለን በዚህም ደስተኛ ነን” ሲሉ አብራርተዋል።
የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሸንን እንዴት መረጣችሁ..?
የተባሉት አቶ ሃ/ስላሴ “የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽንን የመረጥነው በማርኬቲንግ ስትራቴጂ ትልቁ ገበያ ያለን አዲስ አበባ በመሆኑ ነው ሌላው ምርጫችን የሆነው ከአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን የቀረበልን ፕሮጀክት ከእኛ ጋር በመጣጣሙና በመስማማታችን ነው” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ አበባ ዳኞች ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ የፊታችን ጥቅምት 20/2015 በጃንሜዳ ይካሄዳል። ቀድሞ የነበረው ማህበር ባለፉት ስድስት አመታት ፍቃዱን ባለማደሱና ተግባራዊ እንቅስቃሴ አድርጎ የከተማውን ዳኞች መብት ባለማስከበሩ የዳኞቹ ተቃውሞ መበርከቱ ለእሁዱ ስብሰባ ጥሪ ምክንያት ሆኗል። በዋናነት የቀድሞዎቹ ዳኞች አሰፋ ደቦጭ፣ ዳዊት አሳምነውና ኢብራሂም አጋዥ በአመራርነት ያሉበት ማህበሩ ውሉን ባለማደሱ ጉባኤው ማህበሩን እንደገና የማጠናከርና ህጋዊ የማድረግ ስራውን ለመስራት ቀጠሮ መያዙ ታውቋል።
የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን በበላይነት በሚያስተባብረው የጃንሜዳው ጉባኤ በበርካታ የከተማው ዳኞች በጉጉት የሚጠበቅ ሆኗል።