የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን በ2015 መርሃግብር አጀማመርና በከተማው እግርኳሳዊ ጉዞ ዙሪያ ምክክር አደረገ።
ዛሬ ጠዋት በሆቴል ዲሊዮፖል በተካሄደው የምከክር መድረክ ላይ እንደተገለጸው “ፌዴሬሽኑ ዕውቀታችን ለእግርኳሳችን” በሚል መሪ ቃል የከተማውን እግርኳስ ለማነቃቃትና ለማጠናከር ይረዳል ያለውን ሀሳብ አቅርቦ ጉባኤተኛው በሰፊው ተወያይተውበታል። አዲስ አበባ ከተማ እንደ መዲናነቱ በእግርኳሱ አላደገም፣ አመራሮቹ ኳሱን በቦታው ተገኝተው እንዲከታተሉ፣ ታዳጊ ላይ በደንብ እንዲሰራ፣ ለሴቶች ትኩረት እንዲሰጥ፣ በክለቦች መሃል ያለው የደረጃ ልዩነት ከግምት ገብቶ ውድድሩ ቢጀመር፣ የሜዳ ዕጥረት፣ባለሙያ የማብዛት፣ የዳኞች ጥራት ላይ ጥንቃቄ ቢደረግ፣ የውድድር ምልመላው ጥራት ከግምት ቢገባና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ሀሳቦች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ደረጄ አረጋ በበኩላቸው በሰጡት ምላሽ ” 2014 ፌዴሬሽኑ መጠነ ሰፊ ችግር ነበረበት በፋይናንስም ሆነ በሰው ሃይል ብቁ ያልሆነ እንደነበረና የተፈጠረው ችግር በጋራ የምንቀበለው ይሆናል በ2015 ከተማው ብቃት ያለው ፌዴሬሽን እንዲሆን የምንችለውን እናደርጋለን ውድድሩን ለመጀመር ሀምሌ 2014 ላቀረብነው የላይሰንስ ዕደሳ ጥሪ ስንቶች ናችሁ የመለሳችሁት..? ዕደሳው ካልሰራ ውድድሩስ እንዴት ይጀመራል..? ከሜዳና ከዕድሜ ተገቢነት ጋር ተያይዞ ለውድድሩ የጋራ ሃላፊነት አለብን የምንፈራራ ሳይሆን የምንደማመጥ ወገኖች መሆን አለብን ከፋይናንስ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ችግር የጋራ ሆኗል በተቻለ መጠን ለማስተካከል ልንሰራ ይገባል እንደ ሜዳ ውድድሩ በየክለቦቹ ሜዳ የሚካሄድ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
- ማሰታውቂያ -
” ፌዴሬሽኑ በየትኛውም የመንግስት ተቋም የፋይናንስ ድጋፍ ተደርጎለት አያውቅም ተደርጓል የሚለው ሀሳብ ስህተት ነው እንደፌዴሬሽን እየተሰራ አይደለም ፌዴሬሽኑ ጭራሽ የለም ብዬ ስራ አስፈጻሚው ላይ ጣቴን ስጠቁም ስለነበር ዛሬ ቦታውን ይዤ የላችሁም ብባል ብተች ለመቀበል አልቸገርም 2015 እንደምንም የፋይናንስ ችግሩን ለመቅረፍ በጋራ እንሰራለን በ2016 ግን በፋይናንስ የማይቸገር ክለቦችን ማየት እንፈልጋለን” ያሉት አቶ ደረጄ ” አዲስ አበባ ላይ የነበረው የፋይናንስ ችግር ማሳያ ከተማውን ወክሎ የተጓዘው ክለብ መተኛ ሆቴል አጥቶ በር በሌለው ሆቴል ውስጥ መተኛቱን የመሠለ ስሜት የሚጎዳ ድርጊት የለም በአጠቃላይ ፌዴሬሽኑ የተቸገረውን ችግር ለማስወገድ ጥቂት ጊዜ ያስፈልገናል በእርግጠኝነት ችግሮቻችንን በጋራ እንፈታለን” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ፌዴሬሽኑ አጽንኦት ሰጥቶ እንደገለጸው የአመቱ ውድድርን ለማስጀመር ያለው የላይሰንስ ዕደሳ የመጨረሻ ቀነ ገደብ ከጥቅምት 20/2015 እንደማያልፍ አስታውቋል።