በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ሁለተኛ ጨዋታ በአርባምንጭ ከተማ እና በኢትዮጵያ መድኅን መካከል ተደርጎ አዝናኝ የመጀመሪያ እና የመጨረሻ ደቂቃዎች እና ሰባት ግቦች ተቆጥረውበት በኢትዮጵያ መድኅን አሸናፊነት ተጠናቋል ።
በመጀመሪያው ሳምንት ጨዋታ በወልቂጤ ከተማ ሽንፈት ያስተናገዱት አርባምንጭ ከተማዎች በጨዋታ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ስድስት ለውጦችን በማድረግ አካሉ አትሞ ፤ በርናንድ ኦቼንጌ ፤ ወርቅይታደስ አበበ ፤ መሪሁን መስቀሌ ፤ ሱራፌል ዳንኤልን እና አሸናፊ ተገኝን በማሰለፍ አሸናፊ ፊዳ ፤ ሙና በቀለ ፤ መላኩ ኤልያስ ፤ ቡታቃ ሸመና ፤ አቡበከር ሻሚል እና አህመድ ሁሴንን ያሳረፉ ሲሆን በኢትዮጵያ መድኅን በኩል ደግሞ በሳምንቱ በቅዱስ ጊዮርጊስ በሰፊ ውጤት በተረቱበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ አስራ አንድ ሁለት ለውጦችን በማድረግ አሚር ሙደሺርን እና ያሬድ ዳርዛን በቴዎድሮስ በቀለ እና ኪቲካ ጀማ ተክተው ገብተዋል ።
የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም ተጋጣሚዎች በኩል ክፍት የነበረ እና ኳሶች ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ክልሎች የደረሱበት ነበር ። በዚህም በመጀመሪያ 23 ደቂቃዎች ውስጥ አራት ግቦች ተስተናግደውበታል ።
- ማሰታውቂያ -
የመጀመሪያው ግብ በ5ኛው ደቂቃ ላይ የተቆጠረ ሲሆን ግብ አስቆጣሪዎቹ ደግሞ አዞዎቹ ነበሩ ። ሙና በቀለ ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ እዮብ በቀታ ከጨረፈው በኋላ አሸናፊ ፊዳ አግኝቶ ከመረብ አሳርፏል ።
ከግቡ በኋላ በአሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ የሚመሩት ኢትዮጵያ መድኅኖች የተሻለ በመንቀሳቀስ ከዘጠኝ ደቂቃዎች በኋላ የአቻነቱን ግብ አስቆጥረዋል ። በጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን የደረሰውን ኳስ ብሩክ ሙሉጌታ በሁለተኛ ሙከራ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል ።
የኢትዮጵያ መድኅን ጫና ቀጥሎ ከስደስት ደቂቃዎች በኋላ መሪ መሆን የሚችሉበትን ዕድል አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል ። በአጋጣሚው ከርቀት ከቆመ ኳስ የተሻገረን ኳስ ሀብታሙ ሸዋለም በግንባር ገጭቶ ለብሩክ ሙሉጌታ ያቀበውን ኳስ ብሩክ ከግቡ በቅርብ ሆኖ በግንባር ገጭቶ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል ። ነገር ግን ከዚህ ሙከራ የሰከንዶች ቆይታ በኋላ ኢትዮጵያ መድኅን መሪ ሆኗል ።
በጥሩ ቅብብል ወደ ሳጥን የደረሰውን ኳስ ኪቲካ ጀማ ከብሩክ ሙሉጌታ ተቀብሎ በግሩም ሁኔታ ከመረብ አሳርፎታል ።
ኢትዮጵያ መድኅኖች ከመመራት ወደ መምራት ቢሸጋገሩም ከ64 ሰከንዶች በኋላ ዳግም ወደ አቻ የተመሱበትን ግብ አስተናግደዋል ። ለአዞዎቹ ግቡን ያስቆጠረው ተመስገን ደረሰ ሲሆን በአስደናቂ የመቀስ ምት ኳሱን በአቡበከር ኑሪ መረብ ላይ አሳርፎታል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች በአንፃራዊነት ቀዝቀዝ ብሎ የቀጠለው ጨዋታ ሌላ ግብ ሳይቆጠርበት ወደ እረፍት አምርቷል ።
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አርባምንጭ ከተማዎች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር መጫወት የቻሉ ሲሆን ቀድመው ሶስተኛውን ግብ ለማስቆጠር የኢትዮጵያ መድኅንን የኋላ መስመር ደጋግመው አንኳክተዋል ። ነገር ግን ለደቂቃዎች ይህ ነው ሊባል የሚችል ጠንካራ የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም ነበር ።
በአጋማሹ የመጀመሪያው የግብ ዕድል 74ኛው ደቂቃ ላይ አዞዎቹ በተመስገን ደረሰ አማካኝነት ቢያገኙም ሙከራው ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል ።
ጨዋታው 78ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ተመስገን ደረሰ ዳግም በግሩም ሁኔታ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል ። አሸናፊ ተገኝ ከቀኝ መስመር ወደ ግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ ተመስገን ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ደግሞ ሶስተኛውን ግብ አስቆጥሯል ።
ከአንድ ደቂቃ በኋላ አሸናፊ ኤሊያስ ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑሪን አልፎ አስቆጠረው ተብሎ የተጠበቀውን ኳስ ቴዎድሮስ በቀለ ደርሶ አድኖታል ።
ጨዋታው ወደ መገባደጃ ደቂቃዎች ሲደርስ ኢትዮጵያ መድኅኖች አከታትለው ሁለት ግቦችን አስቆጥረዋል ።
ከቆመ ኳስ በረጅም የተሻማን ኳስ ከኪቲካ ጀማ በግንባር ተገጭቶ የደረሰው አስጨናቂ ፀጋዬ የጨዋታውን ውጤት ወደ ሶስት አቻ የቀየረ ግብ አስቆጥሯል ። በዚህ ያልቆሙት መድኅኖች በሰከንዶች ልዩነት የአርባ ምንጭ ተከላካዮች ክፍተትን ተጠቅመው በእዮብ ገብረማርያም አማካኝነት የማሸነፊያ ግብ አግኝተዋል ።
በመጨረሻም ጨዋታው በኢትዮጵያ መድኅን የ4 ለ 3 አሸናፊነት ፍፃሜወን አግኝቷል ።
በሶስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ጥቅምት 2 (ረቡዕ) 10:00 ላይ አርባምንጭ ከተማ ከመቻል ሲጫወት ከሁለት ቀናት በኋላ ጥቅምት 4 (አርብ) 7:00 ላይ ኢትዮጵያ መድኅን ከለገጣፎ ለገዳዲ ይጫወታሉ ።