በካፍ ኮንፌደሬሽን ካኘ ኢትዮጵያን ወክሎ በመሳተፍ ላይ የሚገኘው ወላይታ ዲቻ ባለፈው ሳምንት በሜዳው በሀዋሳ አለም አቅፍ ስታዲዬም ዛማሌክን 2ለ1 ማሸነፉ የሚታወስ ሲሆን እሁድ ምሽት 1:00 በካይሮ ኢንተርናሽናል ስታዴም ከዛማሌክ ጋር ላለበት የመልስ ጨዋታ ዛሬ ምሽት 4:20 ወደ ግብፅ ካይሮ ያቀናል፡፡
የጦና ንቦቹ አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሀ ጨዋታውን አስመልክተው ወደ ካይሮ ከማቅናታቸው በፊት ከሀትሪክ ስፖርት ጋር በነበራቸው ቆይታ የተናገሩት
“☞ወደ ካይሮ የምንሄደው የግብፁን ዛማሌክ አሸንፈን ወደ ሌላ ምዕራፍ ለመግባት ነው፡፡ለዚህ ይረዳን ዘንድ ዛሬ ጧት የሜዳችን የመጨረሻ ልምምድ በተሳካ ሁኔታ በሶዶ ስታዲዬም ሰርተናል፡፡
☞ በፕሪሚየር ሊጉ ከወልዲያ ከተማ ጋር በነበረን ጨዋታ ጉዳት ያስተናገዱት ፡ሀይማኖት ወርቁ እና በዛብህ መለዬ ከጉዳታቸው አገግመው ለጨዋታው በሙሉ ጤንነት ዝግጁ ከመሆናቸውም ባሻገር ቡድናችን በጥሩ የአሸናፊነት ስነ ልቦና ላይ እንገኛለን፡፡
☞ተጋጣሚያችን ዛማሌክ በሜዳውና በደጋፊዎቹ ፊት እንደመጫዎቱ የባለፈውን ሳምንት አጨዋወት ይዞ ወደ ሜዳ ይገባሉ ብለን አናስብም፡፡ለዛም ይረዳን ዘንድ በግብፅ ፕሪሚዬር ሊግ ትናንት ዛማሌክ በሜዳው ኢል ራጃን 4ለ1 ያሸነፈበትን ጨዋታ ተመልክቸዋለሁ፡፡በጨዋታው ተጋጣሚያችን ከባለፈው ስብስብ የ3 ተጨዋቾችን ለውጥ በማድረግ የተጫዎተ ሲሆን ዛማሌክን እንዴት ማቆም እንዳለብን ስለምናውቅ በሜዳውም ቢሆን የማናሸንፍበት ምክንያት አይኖርም፡፡
☞በእሁዱ ጨዋታ ከሜዳችን ውጭ ብንጫዎትም ለመከላከል ወደ ሜዳ አንገባም፡፡90 ደቂቃ ተከላክለን ውጤት እናስጠብቃለን ብዬ አላምንም፡፡የኳስ ቁጥጥር የበላይነትትን በመውሰድ ተጋጣሚያችን ጫና ውስጥ የምናስገባበትን አጨዋወት ወደ ሜዳ ይዘን እንገባለን፡፡
- ማሰታውቂያ -
☞ማጥቃት በራሱ መከላከል ነው፡፡መከላከል ግን ማጥቃት አይደለም፡፡በመሆኑም በማጥቃት ውስጥ እየተከላከልን ጎል ለማስቆጠር እንጫዎታለን፡፡
☞ዛማሌክ በጥሩ መነቃቃት ላይ ነው፡፡ በግብፅ ፕሪሚዬር ሊግ በደረጃ ሰንጠረዡ አልሃሊን በመከተል 2ኛ ደረጃ ላይ ሲሆኑ ትናንት ማሸነፋቸው ለእሁዱ ጨዋታ የበለጠ በአሸናፊነት ስነ ልቦና ወደ ሜዳ እንዲገቡ ይረዳቸዋል፡፡
☞እኛም ሃያሉን ዛማሌክ ባሸነፍንበት ማግስት በሊጉ ወልዲያ ከተማን ማሸነፋችን ለጉዟችን ትልቅ የአሸናፊነት ስነ ልቦና የሰነቅንበት ጨዋታ እንደመሆኑ በግብፅ ካይሮ ኢንተርናሺናል ስታዳዬም በጥሩ ውጤት እንደምንደምቅ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
☞ሁሉም ኢትዬጵያዊ ከደቡብ እስከ ሰሜን፡ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ ፡በአራቱም ማዕዘናት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ያላችሁ የማሸነፋችን ብስራት የምትጠባበቁ ሁሉ እሁድ ዛማሌክን በሜዳው አሸንፈን፡የድሉን ችቦ ግብፅ ካይሮ ላይ እንለኩሰዋለን፡፡”