👉…የፊታችን ቅዳሜ የቡድን ስብስቡን በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ለደጋፊው ያስተዋውቃል…
👉… ቤተሰባዊ ሩጫው መስከረም 29 ይካሄዳል…
ኢትዮጵያ ቡና በ2015 የሚያደርገውን እያንዳንዱን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 30 ጨዋታዎችን በስፖንሰርሺፕ ለማጀብ ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።
ክለቡና የደጋፊ ማህበሩ ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ፊት ፊት ባለው አምባሳደር ሞል በጋራ በሰጡት መግለጫ እያንዳንዱን የሊግ ጨዋታ በስፖንሰርሺፕ ለማጀብ ለተለያዩ ተቋማት ጥያቄ አቅርበው ጥሩ ምላሽም እንዳገኙ ገልጸዋል። ክለቡን ለማጠናከር የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም እንደሚኖር የገለጹት አመራሮቹ የክለቡን ብራንድ ከፍ ለማድረግ በጋራ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።
ክለቡ በመጪው ቅዳሜ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ከጠዋቱ 3 እስከ 5 ሰአት ድረስ ተጨዋቾቹን ከደጋፊው ጋር እንደሚያስተዋውቅና እንደ መደበኛ ጨዋታ ደጋፊው የስታዲየም ትኬት እየቆረጠ በመግባት የገቢ ማሰባሰቡን እንዲያግዙ ተጠይቋል። ክለቡ እንደገለጸው ሙሉ የአሰልጣኞች ስብስቡን ከነሀሴ 1 በኋላ እንደሚያሳውቅና ከመጪው እሁድ ጀምሮ ለ2015 ዝግጅት ቡድኑ ወደ ሀዋሳ እንደሚያቀና አስታውቋል ።
የኢትዮጵያ ቡና ቤተሰባዊ ሩጫ መስከረም 29 እንደሚከናወንና እስከ 50ሺህ ደጋፊ ይወጣል ብለው አንደሚያምኑ የተናገሩት አመራሮቹ የማሊያው ዋጋ 500ብር እንደሆነ ገልጸው ምዝገባና ሽያጩ ከነሀሴ 1-30 በቡና ባንክ ብቻ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
ክለቡ እንደገለጸው አምባሳደር ሞል ላይ ከሀ እስከ ፐ ጋር በጋራ በተከፈተው የሽያጭ ሱቅ የክለቡን ብራንድ ለፈቀደበት ከቀን ሽያጭ 20 በመቶ እንደሚያገኝና በአጠቃላይ የአመት ትርፍ ደግሞ ሁለቱ ተቋማት በመነጋገር ክለቡ ተጨማሪ ክፍያ እንዲያገኝ መስማማታቸውን የክለቡ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ቡና በዘንድሮው የውድድር አመት ግጥሚያዎቹ ከተካሄዱባቸው ሀዋሳ ከተማ፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ አዳማ ከተማና ባህርዳር ከተማ በአዳማ ከተማ በነበረው ቆይታ ከፍተኛ ገቢ ማግኘቱን ይፋ አድርጓል።
አስተያየት ይስጡ