በተጠባቂዉ የሮድዋ ደርቢ ሀዋሳ ከተማ ከሲዳማ ቡና ጋር ጨዋታቸውን አንድ አቻ በሆነ ዉጤት አጠናቀዋል።
በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ ቀን 9:00 ሰዓት በዋና ዳኛ ዳንኤል ይታገሱ ፊሽካ በጀመረዉ ጨዋታ እንደጨዋታዉ ተጠባቂነት በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር በሁለቱም ክለቦች በኩል ተደርጓል። በዚህ ሁነት በጀመረዉ ጨዋታ 16ተኛዉ ደቂቃ ላይም ሀይቆቹ ጨዋታዉን መምራት የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። በዚህም አጥቂዉ አሊ ሱለይማን ከኋላ ክፍል የተቀበለውን ኳስ ለታፈሰ ሰለሞን አቀብሎት ተጫዋቹም ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን ቀዳሚ አድርጓል።
ግብ ከተቆጠረባቸዉ በኋላ በቶሎ ሪያክት ለማድረግ መጣር የጀመሩት ሲዳማ ቡናዎች በአጥቂዉ ማይክል ኪፕሩል እና አማካኝነት ካደረጓቸዉ ኢላማቸዉን ያልጠበቁ ሙከራዎች ዉጭ አደጋ ለመፍጠር ሲቸገሩ በተቃራኒው አቤኔዘር አስፉዉ ያደረገዉን ተጠቃሽ ሙከራ ግብ ጠባቂዉ ቻርልስ መልሶበታል።
ከዕረፍት መልስ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተለየ ተሻሽለዉ ወደ ሜዳ የተመለሱት ሲዳማ ቡናዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ ጨና ፈጥረዉ መጫወት የቀጠሉ ሲሆን ፤ ካደረጓቸዉ ሙከራዎች መካከልም በ70ኛዉ ደቂቃ ላይ ብርሀኑ በቀለ ከቅጣት ምት ያሻማዉን ኳስ በዛብህ መለዮ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
- ማሰታውቂያ -
በተቃራኒው ጨዋታዉን በመምራት ላይ የሚገኙት ሀይቆቹ በሁለተኛዉ አጋማሽ በተጋጣሚያቸው ብልጫ ተወስዶባቸዉ የነበረ ሲሆን ይባስኑም በ74ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ አስተናግደዋል። በዚህም ከቀኝ በኩል ከማዕዘን ያሻማዉን ኳስ ደስታ ደሙ በግንባር ገጭቶ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ሁለቱም ክለቦች ከጨዋታዉ ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዘዉ ለመዉጣት ያደረጉት ጥረት ሳይሰምር ቀርቶ ጨዋታዉ 1ለ1 በሆነ ዉጤት ተጠናቋል።
በዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ኢትዮጵያ ቡና ወላይታ ዲቻን 2ለ1 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።
አመሻሽ 12:00 ሰዓት ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ መሪነት በተጀመረዉ ጨዋታ ቡናማዎቹ በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ ሁነዉ በመቅረብ ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ የሚገኙ ዕድሎችንም ለመጠቀም ሲጥሩ ፤ በተቃራኒው ወላይታ ዲቻዎች ደግሞ በአብዛኛው ወደ መስመር ባደላ አጨዋወት ዕድሎችን ለመፍጠር ሲጥሩ ተስተውሏል።
በዚህ ሂደት በጀመረዉ ጨዋታም ምንም እንኳን ሁለቱ ክለቦች አዝናኝ በነበረ የጨዋታ እንቅስቃሴ ጥሩ አጀማመር ያድርጉ እንጅ ሁለቱም ክለቦች ተጠቃሽ ሙከራ ለማድረግ ተቸግረዉ በ38ተኛዉ ደቂቃ ላይ ወላይታ ዲቻዎች ጨዋታዉን መምራት የቻሉበትን ግብ አግኝተዋል። በዚህም የኢትዮጵያ ቡናዉ ተከላካይ ራምኬል የሰራዉን ስህተት ተከትሎ የተገኘዉን ኳስ አበባየዉ ሀጂሶ ለብዙአየሁ አቀብሎት ተጫዋቹም ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ መቆጠር ከአራት ያክል ደቂቃዎች በኋላ በድጋሚ አጥቂዉ ቢኒያም ፍቅሬ ድንቅ ሙከራ አድርጎ ፤ በተቃራኒው በኳስ ቁጥጥሩ የተሻለ የነበረዉ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ተጠቃሽ ኢላማዉን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርግ አጋማሹ ተጠናቋል። ከዕረፍት መልስ የበላይነታቸዉን አጠናክረው የቀጠሉት ቡናማዎቹ በ49ነኛዉ ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ አግኝተዋል። በዚህም አብዱልከሪም ወርቁ ያሻማውን የማዕዘን ኳስ መስፍን ታፈሰ በግንባሩ ወደ ግብነት መቀየር ችሏል።
በ73ተኛዉ ደቂቃ ላይ ናትናኤል ናሲሮን በቀይ ካርድ ምክንያት ከሜዳ ካጡ በኋላ ጨናዉ የበረታባቸዉ ዲቻዎች ይባስኑ በ84 ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ግብ አስተናግደዋል። በዚህም ከቀኝ መስመር በኩል አብዱልከሪም ወርቁ ያሻገረዉን ኳስ መሐመድ ኑር ናስር በግሩም ሁኔታ ወደ ግቅነት ቀይሯል። በቀሪ ደቂቃዎችም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታዉ በኢትዮጵያ ቡና 2ለ1 በሆነ አሸናፊነት ተጠናቋል።