በሀያ አራተኛዉ ሳምንት የሊጉ መርሐግብር የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታ ሀድያ ሻሸመኔ ከተማን 3ለ1 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።
ቀን ዘጠኝ ሰዓት ሲል በጀመረዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በሙከራ ረገድ ቀዳሚ የነበሩተ ሻሸመኔ ከተማዎች በ9ነኛዉ እና በ10ኛዉ ደቂቃ ጥሩ ሙከራዎችን አድርገዋል። በዚህም ሁዛፍ አሊ ከእዮብ ገ/ማርያም የተቀበለዉን ኳስ ከሳጥን ዉጭ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ በግቡ የግራ ቋሚ አጠገብ ለጥቂት ስትወጣ ፤ በተጨማሪም ተከላካዩ ገዛኸኝ ደሳለኝ የቅጣት ምት በተሻማ ኳስም ድንቅ ሙከራን አድርጓል።
በሙከረ ረገድ ብልጫ የተወሰደባቸዉ ሀድያዎች ከቀኝ መስመር በኩል እዮብ ገ/ማርያም ድንቅ ኳስ ለቻላቸዉ አቀብሎት ተጫዋቹም በደካማ ዉሳኔ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ግብ ጠባቂዉ ኳሷን ወደ ውጭ አውጥቷል። በዚህ ሂደት በጀመረዉ ጨዋታ በ19ነኛዉ ደቂቃ ላይ ጎል ተቆጥሯል። በዚህም ተመስገን ብርሀኑ ከመሐል ሜዳ ጀምሮ ያገኛትን ኳስ ግብ ጠባቂዉን አቤልን እና ቻላቸዉን ጭምር አልፎ ጎል በማስቆጠር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
አጋማሹ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረዉም ከግራ መስመር በኩል ዳዋ ሁቴሳ ከኋላ የተሻገረለትን ኳስ ከተቆጣጠረ በኀላ ለተመስገን ብርሀኑ አቀብሎት ተጫዋቹም ኳሷን ወደ ግብነት በመቀየር የክለቡን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ከድርጎ አጋማሹ ተገባዷል።
- ማሰታውቂያ -
ከዕረፍት መልስ የተጫዋች ቅያሪ ካደረጉ በኋላ በይበልጥ ረዣዥም ኳሶችን ተጠቅመዉ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲጥሩ የተስተዋሉት ሻሸመኔ ከተማዎች በ55ተኛዉ ደቂቃ ላይ ከማዕዘን በተሻማ ኳስ ተከላካዩ ገዛኸኝ ግብ አስቆጥሮ ክለቡን ወደ ጨዋታዉ መልሷል። ከግቧ መቆጠር በኋላ በተመስገን ብርሀኑ አማካኝነት ሙከራ ማድረግ የቻሉት ሀድያዎች በ74ተኛዉ ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ዮሐንስ ከሳንጥኑ ዉጭ ከርቀት የቀኝ ጠርዝ ድንቅ የግብ ሙከራ ማድረግ ችሎ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ኳሷ በግቡ ቋሚ አጠገብ ለጥቂት ወደ ዉጭ ወጥታለች።
በጥሩ መነቃቃት እየቀጠለ በነበረዉ ጨዋታም በ84ተኛዉ ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት የተሻማዉን ኳስ የሻሸመኔ ከተማ ተከላካዮች በሚገባ ማፅዳት ባለመቻላቸው ምክንያት በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘዉ ደስታ ዋሚሾ ኳሷን ወደ ግብነት በመቀየር የሻሸመኔ ከተማዎችን የማንሰራራት ተስፋ አደብዝዞ ጨዋታዉ በሀድያ ሆሳዕና 3ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር መቻል በሽመልስ በቀለ ሁለት ጎሎች ታግዞ ሀምበሪቾ ዱራሜን ማሸነፍ ችሏል።
በዋና ዳኛ ተካልኝ ለማ ፊሽካ 12:00 ሰዓት ሲል በጀመረዉ ጨዋታ መቻሎች ገና በመባቻዉ በ2ተኛዉ ደቂቃ ላይ በሽመልስ በቀለ አማካኝነት ድንቅ ሙከራ ማድረግ ችለዉ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ግን ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥታለች። ገና በጊዜ ሙከራ በማድረግ ጨዋታዉን የጀመሩት እና በእንቅስቃሴ ረገድም የተሻሉ የነበሩት መቻሎች በ30ኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበዉ ነበር በዚህም ከግራ መስመር በኩል በረከት ደስታ ያሻገረዉን ኳስ ያገኘዉ ሽመልስ በቀለ ወደ ግብ ቢሞክርም የግብ ዘቡ ኳሷን ይዞበታል።
በድጋሚ ከሶስት ደቂቃዎች በኋላም ሽመልስ በቀለ ድንቅ የግብ ዕድል አግኝቶ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን በዉሳኔ አሰጣጥ ችግር ጭምር ኳሷን ሳይጠቀምባት ወደ ዉጭ ወጥታለች። በተቃራኒው በአብዛኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ በመከላከል ያሳለፉት እና ከቆሙ ኳሶችም ዕድሎችን ለመፍጠር ሲጥሩ የነበሩት ሀምበሪቾዎች በአጋማሹ አንድም ተጠቃሽ ሙከራ ሳያደርጉ ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት በኋላም የማጥቃት ሀይላቸዉን አጠናክረዉ የቀጠሉት መቻሎች በ53ተኛዉ እና በ60ኛዉ ደቂቃ ላይ በተከታታይ ግብ ማስቆጠር ችሏል። በዚህም በመጀመሪያው ደቂቃ ከወደ ግራ በኩል የተገኘዉን የቅጣት ምት ኳስ ወደ ግብነት በቀጥታ መቀየር ሲችል ፤ ከደቂቃዎች በኋላም ከበረከት ደስታ የተቀበለዉን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ የክለቡን መሪነት ዘደ ሁለት ለዜሮ ከፍ ማድረግ ችሏል።
ግብ ካስቆጠሩ በኋላ በይበልጥ ጨዋታዉን የተቆጣጠሩት መቻሎች በምንይሉ ወንድሙ እና ሽመልስ በቀለ አማካኝነት ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር ተቃርበዉ እንዲሁም በ80ኛዉ ደቂቃ ላይ ዳዊት ማሞ ከርቀት ድንቅ ሙከራ አድርጎ የግቡ ቋሚ መልሶበት ጨዋታዉ በመቻል 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።