8 ሰአት ላይ የተጀመረው የመዲናዋ ክለብ የአዲስ አበባ ከተማ እና የጅማ አባጅፋር ጨዋታ በጅማ አባጅፋር 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል ።
የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ያን ያህል ሳቢ ያልነበረ ተደጋጋሚ ጥፋቶች የታዩበት እንዲሁም የግብ ሙከራዎች በብዛት ያልታዩበት የነበረ ቢሆንም 44ኛ ደቂቃ ላይ መሐመድኑር ናስር ግብ አስቆጥሮ ጅማ አባጅፋሮች እየመሩ ወደ እረፍት አምርተዋል ።

በሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ክለቦች በኩል ቅያሪዎች የተደረጉ ሲሆን ሁለቱም ክለቦች ተመጣጣኝ ለማለት የሚያስችል ጨዋታ አድርገዋል ።
አዲስ አበባ ከተማም ሆነ ጅማ አባ ጅፋር በተደጋጋሚ ወደ ግብ ለመድረስ ቢሞክሩም 65ኛው ደቂቃ ላይ የጅማ አባጅፋሩ 8 ቁጥር መሀመድ አወል ከርቀት አክርሮ መቶ የግቡ አግዳሚ ከመለሰበት ኳስ ውጪ ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ አልነበረም ።
በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ቡድን ተጭኖ በመጫወት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርግም ምንም ግብ ሳያስቆጥር ጨዋታው በጅማ አባጅፋር 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል ። የጨዋታውን ብቸኛ ግብ ያስቆጠረው መሐመድኑር ናስር የጨዋታው ኮከብ በመባል የዋንጫ እና የ12,000 ብር ተሸላሚ ሆኗል ።

በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በካሳዬ አራጌ የሚመራው ኢትዮጵያ ቡናን በዮሀንስ ሳህሌ ከሚመራው መከላከያ ያገናኘ ነበር ።
ጨዋታውንም መከላከያ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል ። ኢትዮጵያ ቡና በቋሚ አሰላለፍ በርካታ ታዳጊ ተጨዋቾች ይዞ የገባ ሲሆን በመከላከያ በኩልም አዳዲስ እና ወጣት ተጨዋቾችን ያስመለከተ ጨዋታ ነበር ።
በጨዋታው የኢትዮጵያ ቡና ቡድን በተደጋጋሚ ኳስን ከግብ ጠባቂ ጀምረው መስርተው በመውጣት ለመጫወት ሲሞክሩ የነበረ ሲሆን በተጋጣሚ ሜዳ ሲገቡ ግን ኳሶች በቀላሉ ይበላሹባቸው ነበር ። ይህም ሆኖ በአንዳንድ አጋጣሚዎች በአጥቂ መስመር ተጨዋቾቻቸው የግብ ሙከራዎችን ለማድረግ ጥረት አድርገዋል ።

በመከላከያ በኩል ኳስን መስርቶ የሚጫወተውን የኢትዮጵያ ቡናን የኳስ ፍሰት በማቋረጥ እና መልሶ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ ጥሩ የሚባሉ የግብ ሙከራዎችን አድርገዋል ። የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽም ያለምንም ግብ 0 ለ 0 ተጠናቀቀ ። በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሬ መከላከያ ሁለት ተጨዋቾችን ቀይረው ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን የሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታ እንደመጀመሪያ አጋማሽ ቡናማዎቹ ኳስን መስርተው ሲጫወቱ ተስተውሏል ። እስከ 62ኛ ደቂቃ ያለምንም ግብ የቀጠለው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ቢንያም በላይ ባስቆጠረው ግብ መከላከያ 1 ለ 0 መሪ መሆን ቻለ ። ቡናማዎቹ ከግቧ መቆጠር በኋላ ግብ ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት ፍሬ ሊያፈራላቸው አልቻለም ይባሱንም መከላከያ በተደጋጋሚ በመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ነበር ።

የተጫዋች ቅያሪ ለማድረግ 75ኛ ደቂቃ ድርስ የጠበቁት ኢትዮጵያ ቡናዎች በተጠቀሰው ደቂቃ 3 ቅያሪዎችን በማድረግ በአንፃራዊነት የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ ግብ ለማስቆጠር ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቀርቶ የዳኛው የጨዋታ ፍፃሜ ማብሰሪያ ፊሽካ ተሰማ ።
የጨዋታው ኮከብነትም በጨዋታው ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረው ቢንያም በላይ ማሸነፍ የቻለ ሲሆን የዋንጫ እና የ12,000 ብር ተሸላሚም መሆን ችሏል ። ቢንያም በላይ በመጀመሪያው ዙር መከላከያ ከ አዲስ አበባ ከተማ ባደረጉት ጨዋታም የጨዋታው ኮከብ ተብሎ እንደተመረጠ ይታወሳል ።

በዛሬ ውጤቶች መሰረትም ያደረጓቸውን ሁለቱንም የምድብ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻሉት ጅማ አባጅፋር እና መከላከያ በእኩል 6 ነጥብ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፋቸውን ያረጋገጡ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና እና አዲስ አበባ ከተማ ከምድብ መውደቃቸውን ያረጋገጡ ክለቦች ሆነዋል ። የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታዎች በመጪው ቅዳሜ የሚደረጉ ይሆናል ።
አስተያየት ይስጡ