ትዉልድ እድገቱን በድሬዳዋ ከተማ በማድረግ እግር ኳስን በሰፈር እየተጫወተ ጀምሮ ከታይገር እግር ኳስ ክለብ አንስቶ እስከ ሀገራችን ትልቁ የዉድድር እርከን በሆነዉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እንዲሁም እስከ አዉሮፓ ድረስ መጫወት ከቻለዉ እና በርካታ የግልም የቡድንም ስኬቶችን ካሳካዉ በአሁን ጊዜ ለቅዱስ ጊዮርጊስ በመጫወት ላይ ከሚገኘዉ ቢኒያም በላይ ጋር ሀትሪክ ስፖርት ድህረገጽ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚከተለዉን ቃለ መጠየቅ አድርጋለች።
ሀትሪክ :- በመጀመሪያ ራስህን ለሀትሪክ ቤተሰቦች አስተዋውቅልን ?
ቢኒ :- ቢኒያም በላይ እባላለሁ።
ሀትሪክ :- ትዉልድ እድገትህ የት ነዉ ? ለቤተሰብህስ ስንተኛ ልጅ ነህ ?
- ማሰታውቂያ -
ቢኒ :- ተወልጄ ያደኩት ድሬዳዋ ጎሮ በተባለ አከባቢ ሲሆን ለቤተሰቤ ሁለተኛ ልኝ ነኝ። ሁለት እህቶች ያሉኝ ሲሆን ታላቄ ማህሌት በላይ የምትባል ሲሆን ታናሼ ደግሞ ቤቴልሄም በላይ ትባላለች።
ሀትሪክ :- እግር ኳስን የጀመርክበትን አጋጣሚ አጫዉተን ?
ቢኒ :- እግር ኳስን የጀመርኩት ሰፈር ዉስጥ ከጓደኞቼ ጋር እና በትምህርት ቤት ሲሆን እንደ ቡድን የተጫወትኩት ደግሞ ታይገር የሚባል ቡድን ዉስጥ ነዉ።
ሀትሪክ :- ከታይገር በመቀጠልስ የት ተጫወትክ ?
ቢኒ :- ከታይገር በመቀጠል ለጎሮ ዋሊያ ለ5 ዓመት በአሰልጣኝ እዮብ ተዋበ ስር እየሰለጠንኩ እየተጫወኩ አድጊያለሁ።
ሀትሪክ :- ከጎሮ ዋሊያ በመቀጠል ወዴት ወዴት አመራህ ?
ቢኒ :- ከጎሮ ዋሊያ በመቀጠል ከትምህርት ቤት ዉድድር ላይ ተመርጬ ወደ አካዳሚ ባመራም በሰዉነቴ ምክንያት ሳልገባ ቀረሁ። ከእዛ ትቼ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሄጄ ብሞክርም ሳይሳካልኝ ቀርቶ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አምርቼ ለB ቡድን የተጫወትኩ ሲሆን በአንድ አመት ዉስጥ ወደ ተስፋዉ ቡድን አደኩኝ።
ተስፋዉ ላይ እየተጫወትኩ በወቅቱ በአሰልጣኝ ዩሀንስ ሳህሌ በሚመራዉ በዋናዉ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጥሪ የተደረገልኝ ሲሆን ከእዛ መልስ ንግድ ባንክ ወደ ዋናው ቡድን አደኩኝ።
ሀትሪክ :- ንግድ ባንክ ዋናዉ ቡድን ካደክ በኋላስ ?
ቢኒ :- 2009 በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋናዉ ቡድን ከተጫወትኩ በኋላ 2010 ወደ አልቤኒያ በማምራት እስከ 2011 ግማሽ ድረስ በቆየሁ በኋላ ወደ ሲዉዲን በማምራት እስከ 2013 ግማሽ ድረስ ከተጫወትኩ በኋላ ወደ ሀገር ቤት በመመለስ ግማሽ የዉድድር ዓመቱን ለሲዳማ ቡና የተጫወትኩ ሲሆን ከእሱ በመቀጠል 2014 ላይ ወደ መቻል ያመራሁ ሲሆን ከእዛ በመቀጠል አሁን ወደምገኘዉ ቅዱስ ጊዮርጊስ መጥቻለሁ።
ሀትሪክ :- በጠቀስክልን ክለቦች ዉስጥ የነበረህን ቆይታ አጫዉተን ?
ቢኒ :– በክለቦቹ ዉስጥ በነበርኩበት ወቅት ጥሩ ጊዜያትን አሳልፌያለሁ። በተለያ 2010 እና 2011 ምርጥ ጊዜ ከሀገር ቤት ዉጪ ማሳለፍ የቻልኩ ሲሆን ሀገር ቤት ተመልሼ ለሲዳማ ቡና በተጫወትኩ ጊዜ ክለቡን ከቡድን አጋሮቼ ጋር ከመዉረድ ታድገናል። እሱም ጥሩ ጊዜዬ ነበር ከመቻል ጋርም አሪፍ ጊዜ አሳልፌያለሁ።
ሀትሪክ :- ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጣህበትን አጋጣሚ አጫዉተን ?
ቢኒ :- ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት በጣም ብዙ ጊዜ የመምጣቱ እድሎች የነበሩኝ ቢሆንሜ እንደ አጋጣሚ ሆኖ አልተሳኩም ነበር። አስቀድሜ እንደነገርኩህ አልተሳካም እንጂ በልጅነቴም ሞክሬ ነበር። የነበርኩበትን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ለቅቄ ወደ ዉጪ ሀገር በሄድኩበት ወቅት ከጊዮርጊስ ጥሪ ተደርጎልኝ የነበረ ቢሆንም ዉጪ ፈርሜ ስለነበር በእዛ ጊዜም ሳይሳካ ቀረ። በስተመጨረሻ ግን የእግዚአብሔር ፍቃድ ሆኖ 2014 መጨረሻው ላይ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ መጥቻለሁ።
ሀትሪክ :- በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት እያሳለፍክ ስለምትገኘዉ ቆይታህ አጫዉተን ?
ቢኒ :- በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት እያሳለፍኩ የምገኘዉ ቆይታ በጣም አስደሳች ነዉ። በመጣዉበት ዓመት ከቡድን አጋሮቼ ጋር በመሆን የሊጉን ዋንጫ ያሳከንበት እና በግሌ የዉድድሩ ኮከብ ተጨዋች ተብዬ የተመረጥኩበት ጊዜም ነዉ።
ሀትሪክ :- በግልህ እና እንደ ቡድን አሳክቻለሁ ስለምትለዉ ስኬቶች አጫዉተን ?
ቢኒ :- በግሌ ብዙ ስኬቶችን አሳክቻለሁ። ዉጪ በነበርኩበት ወቅት በርካታ ጨዋታዎች ላይ የጨዋታዎቹ ኮከብ ተብዬ መመረጥን ችያለሁ።በአዉሮፓ መድረኮችም መጫወት ችያለሁ። እንዲሁም ወደ ሀገር ቤት ከመጣሁ በኋላም የዉድድሩ ኮከብ ተጫዋች ተብዬ ተመርጫለሁ። ቢሆንም ግን ለእኔ ከግል ስኬት ይልቅ የቡድን ስኬት ይበልጥብኛል እንደ ቡድን በአልቤኒያ በነበርኩበት ወቅት ሶስት ዋንጫ ያነሳሁበት ወቅት ጣፋጩ የዉድድር ጊዜዬ ነበር እንዲሁም በሀገር ቤት ከጊዮርጊስ ጋር ያነሳሁት ዋንጫ ስኬቴ ነዉ።
ሀትሪክ :- በአንድ ወቅት “ይሄን ማለያ ለብሰህ ሁለተኛ የሚባል ነገር የለም” ብለህ ተናግረህ በእዛዉ አመት ሻምፒዮን ሆናችሁ ነበርና ስለ እሱ ወቅት አጫዉተን ?
ቢኒ :- እዉነት ነዉ የቅዱስ ጊዮርጊስን ማለያ ለብሶ ሁለተኛ መዉጣት አይቻልም። ይሄንን እዉነት የሚያደርገዉ ደግሞ እኔ የቅዱስ ጊዮርጊስን ማለያ ከመልበሴ በፊት ብዙ ተጫዋቾች የቅዱስ ጊዮርጊስን ማለያ ለብሰዉ ቡድኑን ሻምፒን ማድረግ የቻሉ ልጆች አሉ። እንዲሁም ክለቡም ለበርካታ ጊዜያት ሻምፒን በመሆን ለ31 ጊዜ ዋንጫ ማንሳት ችሏል። ገና ለቅዱስ ጊዮርጊስ ስትፈርም የሚነገርህ ነገር ክለቡን ሻምፒዮን አድርገህ ማስቀጠል አለብህ ተብሎ ነዉ የሚነገርህ። ለዚህ ነዉ የጊዮርጊስን ማለያ ተለብሶ ሁለተኛ መዉጣት አይቻልም የምለዉ።
ሀትሪክ :- በእስከዛሬዉ የእግር ኳስ ህይወትህ የሚያስደስት እና የሚያስከፋ ግዜን አሳልፌበታለሁ ብለህ የምታስበዉን አጋጣሚ አስታዉሰን ?
ቢኒ :- እዉነት ለመናገር እግዚአብሔር የፈቀደዉ ብቻ ነዉ የሚሆነዉ። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በነበርኩበት ወቅት የወረድንበት ጊዜ በጣም ያዘንኩበት ወቀት ነዉ። እንዲሁም በብሄራዊ ቡድን በዩሀንስ ሳህሌ ጊዜ ለሴካፋ እየተጫወትን ለዋንጫ ለማለፍ ተጫዉተን የወደቅንበት ጊዜ ያስቆጨኛል።
የተደሰትኩበት ወቅት ደግሞ አልቤኒያ በነበርኩበት ጊዜ የካፕ ፣ የሱፐር ካፕ እና የሊጉን ዋንጫ አንድ ላይ ሶስት ዋንጫ ያነሳሁበት ጊዜ ሲሆን እንዲሁም በሲዉዲን ጣፋጭ የሚባሉ ጊዜያትን ያሳለፍኩ ሲሆን ሲዳማ ቡናን ከመጣሁ በኋላም ክለቡን ከመዉረድ የታደግንበት ጊዜም አስደሳች ነበር።
ሀትሪክ :- እዚህ ለመድረስህ ትልቁን አሻራ ያሳረፈዉ ማነዉ ?
ቢኒ :- እዚህ ለመድረሴ ትልቁን አሻራ ያሳረፈዉ እግዚአብሔር ነዉ። በመቀጠል ቤተሰቦቼ ፣ ባለቤቴ ፣ ያሰለጠኑኝ አሰልጣኞቼ ፣ አብሬያቸዉ የተጫወትኳቸዉ የቡድን አጋሮቼ ትልቁን አሻራ አሳርፈዋል።
ሀትሪክ :- ለእግር ኳስ ህይወቴ አርአያዬ ነዉ የምትለዉ ተጫዋች ማን ነዉ ?
ቢኒ :- እኔ እግር ኳስን የማየዉ በሜዳም ከሜዳም ዉጪ ባለዉ ነገር ነዉ። እንደ ኳስ ተጫዋች አራአያዬ ናቸዉ የምላቸዉ ብዙ ሲሆኑ ከእነዛም ዉስጥ የመጀመሪያውን መስመር የሚዪዙት ምንተስኖት አዳነ ፣ አዳነ ግርማ እና ሽመልስ በቀለ ናቸዉ።
ሀትሪክ :- የብሄራዊ ቡድን ግልጋሎትህ ምን ይመስላል ? ለወደፊቱስ ምን ታስባለህ ?
ቢኒ :- የብሄራዊ ቡድን ግልጋሎቴ ገና ይቀረኛል ብዬ ነዉ ማስበዉ። ምክንያቱም ለብሄራዊ ቡድኑ ብዙ ላደርግ እፈልጋለሁ። በክለብ ዉስጥ ያሳየዉትን አቅም በብሄራዊ ቡድኑ መድገም እፈልጋለሁ።
ሀትሪክ :- ከሀገር ዉስጥ እና ከሀገር ዉጪ የምታደንቃቸዉ ተጫዋቾች እነማን ናቸዉ?
ቢኒ :- ከሀገር ዉስጥ እግር ኳስ ተጫዉቼ አልጨረስኩም የማደንቃቸዉን ተጫዋቾች ወደፊት እመርጣለሁ። ከሀገር ዉጪ ግን የሜሲ አድናቂ ነኝ።
ሀትሪክ :- ስለ ቤተሰብህ አጫዉተን ?
ቢኒ :- በቤተሰቦቼ በባለቤቴ ፣ በልጆቼ በጣም ደስተኛ ነኝ። ስለ እነሱ ተናግሬ አልጨርስም። የእነሱን ፍቅር መግለጽ ከባድ ነዉ እንዲሁ ወዳቸዋለሁ።
ሀትሪክ :- ትርፍ ጊዜህን የት ነዉ የምታሳልፈዉ ?
ቢኒ :- ትርፍ ጊዜዬን የማሳልፈዉ ከባለቤቴ ፣ ከልጆቼ ፣ ከቤተሰቤ እና ከወንድሜ እዮብ ጋር ነዉ።
ሀትሪክ :- የወደፊት እቅድህ ምንድነዉ ?
ቢኒ :- የወደፊት እቅዴ እግዚአብሔር ቢወድ እና ቢፈቅድ ከዚህ የተሻለዉን በእያንዳንዱ ጨዋታ ላይ ተፅእኖ የሚያሳድረዉን ቢኒያምን ማሳየት ነዉ። ለእሱም ጠንክሬ እሰራለሁ እንግዲህ የእግዚአብሔር እርዳታ ከእኔ ጋር ይሁን።
ሀትርክ :- ቢኒ ተጫዋች ባይሆን ኖሮ ምን ይሆን ነበር ?
ቢኒ :- በትምህርቴ ጠንካራ ነኝ ብዬ አስባለሁና በእሱ የምገፋ ይመስለኛል። ያ ባይሳካ ደግሞ ብዙ ወንድሞቼ ቤተክርስቲያን አሉኝና እዛ የማገለግል ይመስለኛል።
ሀትሪክ :- በስተመጨረሻም ማመስገን የምትፈልጋቸዉ አካላት ካሉ እድሉን ልስጥህ ?
ቢኒ :- በመጀመሪያ የእናታችን የቅድስት ድንግል ማሪያም ልጅ የሆነዉን ኢየሱስ ክርስቶስን ማመስገን እፈልጋለሁ።
ምስጋና ሲመጣ የሚረሱ አካላት ቢኖሩም እዚህ ትልቅ ደረጃ ላይ እንድደርስ ቢኒያም በላይን ትልቅ ቦታ ላይ ልናየዉ ይገባል በማለት በጉልበትም ፣ በሀሳብም አብራቹኝ የነበራቹትን በሙሉ በፈጣሪ ስም ማመስገን እፈልጋለሁ።
በመቀጠል ደግሞ ባለቤቴን ፣ ልጆቼን ፣ ወንድሜን እዮብ አስፋዉን ፣ ቤተሰቦቼን ፣ በእግር ኳስ ህይወቴ አሻራ ያሳረፉ አሰልጣኞችን እዮብ ተዋበን ፣ ታደሰን ፣ ፍስሀን ፣ ጣሰዉን ፣ ሲሳይን ፣ ፀጋዬን እንዲሁም የቅዱስ ጊዮርጊስ አጠቃላይ ኮቺንግ ስታፍ ዘሪሁንን ፣ ደረጀን ፣ አዲሴን ፣ ዉብሸትን ፣ አዳነን በተለየ መንገድ ደግሞ ጆ ሀኪም ፊከርትን ፣ ዩሀንሳ ሳህሌን እና የቡድን አጋሮቼን እንዲሁም የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችን አመሰግናለሁ።
ሀትሪክ :- ስለነበረን ቆይታ በሀትሪክ ስፖርት ድህረ-ገፅ ቤተሰቦች ስም አመሰግናለሁ።
ቢኒ :- እኔም እንግዳችሁ አድርጋችሁ ስላቀረባችሁኝ አመሰግናለሁ።