****በየአመቱ 6 ሚሊዮን በወር 500ሺህ ብር…..
****የዛሬ አራት አመት በተጠና ጥናት ሊጉ 2.2 ቢሊዮን ወጪ ነበረው አሁን ደግሞ በጣም ጨምሯል..
“አክሲዮን ማህበሩ ከክለቦች በላይ አይደለም አዲሱ ውል ከቡና ባንክ ጋር ያለንን ውል የሚነካ ከሆነ በፍጹም አንቀበልም”
“በቤትኪንግ ምክንያት ማግኘት ያለብንን ጥቅም አጥተናል … አሁን ግን በፍጹም አንፈቅድም”
- ማሰታውቂያ -
አቶ ገዛኧኝ ወልዴ
የኢትዮጵያ ቡና ዋና ስራአስኪያጅ
“በእኛ በኩል ማግኘት ያለብንን አግኝተናል ብለን ባናምንም አላኮረፍንም አሁን ግን የምንካካስበት ጊዜ ነው”
“ያልተተገበረ ውል ስላለ ጥለን አንሄድም ከነገ ጀምሮ ግን ጥቅማችንን ማግኘት እንጀምራለን ”
አቶ አብርሃም ተ/ማሪያም
የቤቲካ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ
ኢትዮጵያ ቡና ከ8 ሀገራት ጋር የስፖርት የውርርድ ስራዎችን እየሰራ ካለው ቤቲካ ኢትዮጵያ ጋር የነበራቸውን ውል ለተጨማሪ ሶስት አመታት አራዝሟል።
ዛሬ ጠዋት በኢንተርሌግዠሪ ሆቴል በተካሄደው የፊርማ ስነስርዓት ላይ የኢትዮጵያ ቡናው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኧኝ ወልዴ እንደተናገሩት ” ከቤቲካ ጋር የባለፉት ሁለት አመት ሂደቶችን ገምግመናል። ከሊጉ ጋር ውል የገባው ቤትኪንግ ስለነበር የቤቲካ መብት በተወሰነ መልኩ ተገድቦ ቆይቷል። የቀጥታ ስርጭት ላይ የቤቲካ አርማን ማስተላለፍ አንችልም ነበር አሁን ግን ህግና ስርአቱን ተከትለን ለማስተዋወቅ ተዘጋጅተናል ከቤቲካ ጋር ቁጭ ብለን ከተነጋገርን በኋላ ውሉን እንደገና ለቀጣዮቹቹ 3 አመታት አድሰነዋል አሁን የተገደበ ነገር ሳይኖር ቤቲካ ማግኘት ያሉበት መብቱ ሁሉ ይከበራል ባለፉት አመታት በቤትኪንግ ምክንያት ማግኘት ያለብንን ጥቅም አጥተናል … አሁን ግን ይህ እንዲሆን አንፈቅድም” ሲሉ ገልጸዋል።
አቶ ገዛኧኝ እንደገለጹት ” ከቤቲካ ጋር ከጥቅምት 2016 ጀምሮ እስከ ጥቅምት 2018 ድረስ ውላችንን አድሰናል ነገር ግን ከክፍያው ጋር ተያይዞ በየአመቱ እንነጋገራለን
ባለፉት ሁለት አመታት እንደነበረው በአመት 6ሚሊየን ብር ይከፍሉናል ከሁለቱ አመት የሚለየው ግን በአሁኑ ውል በየወሩ 500ሺ የሚከፈለን መሆኑ ነው ክለቡ የሚያስመዘግበው ውጤትና በየጊዜው ያለውን የዋጋ ግሽበት ላይ ለመነጋገር በየአመቱ መጨረሻ ባለው ጉዳይ ላይ እንወያያለን”ሲሉ አስረድተዋል። ፕሪሚየር ሊጉ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከተስማማ እናንተ ቡና ባንክ ጋር ካላችሁ ውል አንጻር እንዴት ለማስኬድ አስባችኋል..? የተባሉት አቶ ገዛኧኝ አጽንኦት ሰጥተው እንደተናገሩት
“ሼር ካምፓኒው 16 ክለቦች ቆርሰው የሰጡትን መብት ነው እየተገበረ ያለው … ሁሉም ክለቦች መብት አላቸው ክለባችን ማግኘት ያለበት ጥቅም በሊግ ኩባንያው እንዲቀር አንፈቅድም… በቤትኪንግ ምክንያት ማግኘት ያለብንን አጥተናል አሁን ግን አንፈቅድም። የኛን ጥቅም ባልነካ መልኩ ኩባንያው መወያየት መፈራረም ይቻላል ..የስፖንሰሮቻችንን ፍላጎትና ጥቅማቸውን ማክበር አለብን የትኛው ስፖንሰር የክለባችንን ጥቅም ካላስከበረ አንቀበልም “ሲሉ መልሰዋል።
የሊጉ የፊይናንስ ስርዓትና የክለቦች ደመወዝ መክፈል አለመቻል የሚፈጥረው አደጋ ዙሪያ የተጠየቁት አቶ ገዛኧኝ ” የሀገሪቱ ሊግ ከፋይናንስ ስርዓቱ ጋር ተያይዞ ስርዓተ አልበኝነት የነገሰበት ነው የዛሬ አራት አመት በተጠና ጥናት ሊጉ 2.2 ቢሊዮን ወጪ ነበረው። አሁን ደግሞ ከዚህም ይጨምራል በመንግስት የሚደጎሙት ክለቦች የገንዘብ ችግር ያን ያህል ላይጎዳቸው ይችላል ከስፖንሰር ሰብስበው ለሚንቀሳቀሱ ክለቦች ግን አደጋ ነው በርግጥ በኛ በኩል የፋይናንስ ችግር ውስጥ ሆነን የደመወዝ ክፍያ ጥያቄ አልተነሳንም ነገር ቀጣይ አመታቶች ያሰጉናል እንደ ክለባችን ቦርድ ውሳኔ ከቀጣዩ አመት ጀምሮ በወጣት ተጨዋቾች ላይ እንሰራለን
ዘንድሮ ከ11 ቋሚ ተጨዋቾች አምስቱ ከቢ ያደጉ ናቸው እነሱም የ4 አመት ውል ያላቸው ናቸው። ሊጉ ብዙ የገንዘብ ኔቴወርክ ሰንሰለትም አለው እንዲቀጥል ከተፈለገ መንግስት ዞር ብሎ ሊያየው ይገባል” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። ከራይድ ጋር ስላለው ግንኙነት የተጠየቁት አቶ ገዛኧኝ “ከራይድ ጋር በገባነው ውል መሠረት ማግኘት ያለብን 100 ፐርሰንት ክፍያን ወስደናል ያም ሆኖ ያለው ውሉ በመጠናቀቁ ተለያይተናል” ሲሉ ተናግረዋል።
የቤቲካ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አቶ አብርሃም
ተ/ማሪያም በበኩላቸው ህዝባዊ መሠረት ያለው ክለብ ጋር ውላችንን በማደሳችን ክብር ይሰማናል ቤቲካ ከተለያዩ ማህበራዊ ስራና መዝናኛው ላይ እየሰራ ነው በአሁኑ ስምምነትም ደስ ብሎናል….አምና ወደ 15 የውርርድ ተቋማት ሂሳባቸው ታግዶ ነበር እዚያ ችግር ውስጥ ሆነንም እንኳን ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያለንን ውል ስናክብር ቆይተናል በእኛ በኩል ባለፉት ሁለት አመታት ማግኘት ያለብንን አግኝተናል ብለን ባናምንም አላኮረፍንም አሁን ግን የምንካካስበት ጊዜ ነው በእስካሁኑ ውል ያልተተገበረ ነበር ብለንም ጥለን አንሄድም ከነገ ጀምሮ ግን ጥቅማችንን ማግኘት እንደምንጀምር ተስፋ አደርጋለሁ ኢትዮጵያ ቡና ያለው ግንኙነት ቤተሰባዊ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ቡናና የቤቲካ ኢትዮጵያ የውል ዕደሳውን በቤቲካ በኩል ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ አብርሃም
ተ/ማሪያምና የኢትዮጵያ ቡና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኧኝ ወልዴ በፊርማቸው አጽድቀውታል።