► የቦርድ አባሉ አቶ ሀብታሙ አዱኛ የልቀቁኝ ደብዳቤ
አስገብተዋል..
► በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ መንገድ ላይ
አሰልጣኝ ሃይሉ ነጋሽ /ቲጋና/ ቆሟል
► ቅጥሩ ይፋ ባይሆንም አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ
የክለቡን ተጨዋቾች አግኝቷል
የፋሲል ከነማ ቦርድ ከተሰናባቹ አሰልጣኝ ሃይሉ ነጋሽ
/ቲጋና/ ጋር ያደረገው ድርድር ያለስምምነት ተጠናቋል።
- ማሰታውቂያ -
ትላንት ከቀትር በፊት ሁለት የክለቡ የቦርድ አባላት ከአሰልጣኝ ሃይሉ ጋር የተወያዩ ሲሆን ክለቡ እስከ ሰኔ ያለውን ደመወዝ ሊከፍለው እሱም ከተሰናበተበት ቀን ጀምሮ ያልሰራበትን ቆጥሮ የፊርማ ክፍያውን እንዲመልስ ቦርዱ መወሰኑን ገልጸውለታል። አሰልጣኙም በበኩሉ በራሱ ምክንያት አለመሰናበቱን አሰናባቹ ቦርዱ መሆኑን፣ ውጤት በማጣት ተሰናብቻለሁ ብሎ እንደማያምን ሌሎች የቀረቡለትን የሶስት ክለቦች ጥያቄ ወደጎን ማለቱን በመግለጽ የተሰጠውን የፊርማ ክፍያ ለመመለስ እንደማይችል አቋሙን ግልጽ አድርጎላቸው ሳይስማሙ ቀርተዋል። አመራሮቹ ኦዲት እንደሚደረጉና ክፍተቱ እንደሚያስጠይቃቸው በመግለጽ የፊርማ ክፍያውን ቀሪ ገንዘብ መክፈሉ እንደማይቀር በዚህ ካልተስማማ ወደ ክርክር መግባታቸው እንደማይቀር ጠንከር ባለ መልክ መግለጻቸውን ከታማኝ ምንጭ የተገኘ መረጃ ያስረዳል። አሰልጣኝ ሃይሉም የፊርማ ክፍያውን እንደማይመልስ የስድስት ወር ደመወዙን ግን ከክለቡ እንደሚጠብቅ የማይቀየር አቋሙ መሆኑን በመግለጹ የሁለቱ ወገኖች ስብሰባ ያለ ስምምነት መጠናቀቁ ታውቋል።
አመራርቹ ከአሰልጣኝ ሃይሉ ጋር ያለውን ልዩነት ቋጭተው የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ቅጥርን ይፋ ለማድረግ ቢጥሩም በአሰልጣኝ ሃይሉ ጠንካራ አቋም ሳይሳካ ቀርቷል። የአሰልጣኝ አሸናፊ ቅጥር ይፋ ባይደረግም ግን አሰልጣኝ አሸናፊ ከፋሲል ከነማ ተጨዋቾች ጋር ልምምድ መጀመሩ ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የክለቡ የመሃል አስቻለሁ ታመነ ክለቡን ለመልቀቅ በደብዳቤ ጠይቋል የሚለው መረጃ ውሸት መሆኑ ታውቋል። ከታማኝ ምንጭ በተገኘ መረጃ ተጨዋቹን ጨምሮ የክለቡ አምበሎች ቡድኑን በሚገባ አልረዳችሁም ተብለው አምበልነታቸው ሲነጠቅ አስቻለሁ ካልፈለጋችሁን አልረዳችሁም ካላችሁ መልቀቂያ ስጡንና አሰናብቱን ማለቱ ታውቋል ።ከዚያ ውጪ የወጣው ደብዳቤ አስገብቷል መረጃ ውሸት መሆኑና ተጨዋቹ ውሉን የሚያከብር መሆኑን ማሳወቁን ታማኝ ምንጩ ገልጿል።
የቡድን መሪው ሀብታሙ ዘዋለን የሃላፊነት መልቀቅ ጥያቄ ያልተቀበለው የፋሲል ከነማ ቦርድ ከሌላው የቦርድ አባል የልቀቁኝ ጥያቄ ቀርቦለታል። የቦርድ አባሉ አቶ ሀብታሙ አዱኛ ባለብኝ የስራ መደራረብ ክለቡን ማገልገል ባለመቻሌ ከቦርድ አሰናብቱኝ ሲሉ ደብዳቤ አስገብተዋል።
አቶ ሀብታሙ “ባለብኝ የግል ስራ የፕሮጀክት መብዛትና ተደራራቢ ስራ የተነሳ በበርካታ የቦርድ ስብሰባ ላይ መገኘትና ክለቡን በሚጠበቅብኝ ልክ ማገልገል አለመቻሌ ይታወቃል አሁንም የሚጠበቅብኝን ሃላፊነት በበቂ ሁኔታ እወጣለሁ ብዬ ስለማላምን በቂ ጊዜ አግኝቶ ክለቡን በሚያገለግል ሰው እንድትተኩኝ እጠይቃለሁ። ነገር ግን ከቦርድ ውጪ ሆኜ የከተማዬን ክለብ በሚፈለግብኝ መጠን ለማገዝ ዝግጁ ነኝ ” ሲሉም ጥር 1/2015 ባስገቡት የልቀቁኝ ደብዳቤ ጠይቀዋል።
አጼዎቹ ፋሲል ከነማዎች በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ17ጥብና 2 ግብ በሊጉ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።