► ተገቢነት የሌለውን ተጨዋች የያዘ ሚዲያ ይታገዳል….
► ለአሸናፊው 100ሺህ ብር ሽልማት ተዘጋጅቷል..
► ዋናው ትጥቅ አምራች ኩባንያ ለ24 ሚዲያዎች ማሊያዎችን ስፖንሰር አድርጓል
ባለፉት 11 አመታት ያለምንም መቋረጥ ሲካሄድ የቆየው “አዝናኙ ሲዝናና” የሚዲያ ካፕ
የፊታችን ቅዳሜ ለ12ኛ ጊዜ ይካሄዳል።
የውድድሩ 52 ጨዋታዎች አማካይ ስፍራና
ለተመልካች በሚመቸው በትንሿ ስታዲየም
የሚካሄዱ ሲሆን አዲስ የተቀላቀሉትን ሀገሬ ቲቪ፣ ኢሳት ፣ ፊደል ፖስትና ኤን ቢሲን ጨምሮ 24 ሚዲያዎች በስድስት ምድብ ተደልድለው የሚጫወቱ መሆኑ ታውቋል።
ውድድሩ ካለፉት 11 አመታት በተሻለ መልኩ እያደገ የመጣ ሲሆን ዋናው አገር በቀል ትጥቅ አምራች ኩባንያ ዋጋው 12 ሺህ ብር የሚያወጡ ማሊያዎችን ለ24 ቡድኖች በነጻ መስጠቱ፣ ለአሸናፊዎቹ ሚዲያዎች እስከ 100 ሺህ ብር በሽልማት መልክ መዘጋጀቱ፣ ዋንጫ ላነሳ ሚዲያ 25 ሺህ ብርና የ10ሺህ ብር ዋንጫ ከወርቅ ሜዳሊያ ጋር ለሁለተኛው ሚዲያ 15 ሺህ ብርና የብር ሜዳሊያ ሶስተኛ ለወጣው ደግሞ 10ሺህ ብርና የነሀስ ሜዳሊያ እንደሚሰጥ የውድድሩ አዘጋጅ የዮ ስፖርት ኤቨንት ኦርጋናይዚንግ ዋና ስራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ አንዷለም አስፋው ተናግሯል።በውድድሩ 52 ጨዋታዎች ላይ የጨዋታ ኮከብ ተብለው ለሚመረጡ ኮከቦች ከዋናው ትጥቅ አምራች ኩባንያ የተዘጋጀ ብራንድ ማሊያ በሽልማት መልክ እንደሚበረከትላቸው አዘጋጆቹ አስረድተዋል። በምሽት ፕሮግራሙ ላይ እንደተገለጸው በውድድሩ ግማሽ ፍጻሜ የደረሱ አራት ሚዲያዎች በመጪው ግንቦት ቢጂ አይ ኢትዮጵያ 100ኛ አመት ክብረ በአል ላይ ተጋባዥ ተወዳዳሪ እንደሚሆኑም አስረድተዋል።
- ማሰታውቂያ -
ትላንት በሳፋየር አዲስ ሆቴል በተካሄደው የዕጣ ማውጣት ስነስርዓት ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ዕጣውን ያወጡትና ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ደረጄ አረጋ፣ የዋናው ትጥቅ አምራች አገር በቀል ተቋም ፕሬዝዳንት አቶ ሀብተስላሴ ገ/ክርስቶስ እንዲሁም የቅዱስ ጊዮርጊስ ከ20 አመት በታች ቡድን አሰልጣኝና የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ አሸናፊው አሰልጣኝ ሳምሶን ሙሉጌታ ናቸው።
አቶ ደረጄ አረጋ በዕለቱ እንደተናገሩት ” የስፖርቱ ዋነኛ ተጠቃሽ የሆኑት ሚዲያዎች ባሉበት መድረክ ላይ እንድናገር እድሉን ስላገኘሁ አመሰግናለሁ የስፖርት ጋዜጠኞች ከዘገባዎቻችሁ መለስ እንዲህ አብራችሁ የምትገናኙበት መድረክ በመሆኑ ደስ ይላል ውድድሩ ለከተማው እግርኳስ ትልቅ ውበት ነው የከተማው ምልክትም በመሆኑ ደስታ ይሰማኛል ፌዴሬሽናችንም ለውድድሩ ሙሉ ድጋፉን እንደሚያደርግ አረጋግጣለሁ”ሲሉ ተናግረዋል። የዋናው ትጥቅ አምራች ኩባንያ ባለቤት አቶ ሀብተስላሴ ገ/ክርስቶስ በበኩላቸው ” ድርጅታችን ሀብቴ ጋርመንት በ”ዋናው” ብራንዱ ባለፉት 10 አመታት በኢንዱስትሪው ላይ አስተዋጽኦ ሲያደርግ ቆይቷል። ተለያዩ መድረክ ላይም የስፖርት አጋርነቱን አሳይቷል የዚህ ውድድር አካል በመሆናችንም ደስ ብሎናል ውድድሩም ባለፉት 11 አመታት ያለመቋረጥ መቀጠሉ አዘጋጆቹ ዲሲፕሊን እንዳላቸው ያሳያል ድርጅታችን ባለፉት አመታት በርካታ ማህበራዊ ግልጋሎት ሲሰጥ ቆይቷል አንዱም አላማችን ይሄ ነው ይህም አላማ ከናንተ ጋር እንድንሰራ አድርጎናል ሚዲያ ካፑ 12 ኛ አመቱ ላይ እንደደረሰ ሁሉ 30 50 አመት እያለ እንደሚቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ እኛም ከጎናችሁ ነን” ሲሉ ተናግረዋል። የውድድሩ አዘጋጅ የሆነው ” የዮ የስፖርት ኤቨንት ኦርጋናይዚንግ ዋና ስራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ አንዷለም አስፋው ድጋፍ ያደረጉትን ባለድርሻና ስፖንሰር አድራጊዎችን ሚዲያዎቹን አመስግኗል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚህ 12ኛው የአዝናኙ ሲዝናና የሚዲያ ካፕ ኢቢሲ የማይካፈል ሲሆን “በ11ኛ ሻምፒዮና ላይ ጨዋታዎች ላይ በተፈጠረ አለመግባባት ልዩነት ቢፈጠርም ልዩነቱን ለማስወገድ ተደጋጋሚ ሙከራ መደረጉን ካጠፋንም ይቅርታ ለመጠየቅ ዝግጁ መሆናችንንም ብንገልጽም ሽማግሌዎች ቢላኩም በኢቢሲ በኩል ፍቃደኛነት ባለመኖሩ በዘንድሮ ውድድር ላይ ባለመገኘታቸው ተከፍተናል” ሲል ጋዜጠኛ አንዷለም አስፋው ተናግሯል። ” በኛ በኩል የመረረ ቅሬታ የለንም ነገር ግን ስድብ ትችት ባጠፉት ተጨዋቾች ላይ ሳይሆን ተቋሙ ላይ መሆኑ ትልቅ ቅሬታ ፈጥሮብናል ያጠፉትን መቅጣት ዲሲፕሊን ርምጃ መውሰድ ሲቻል የተቋም ችግር አድርጎን ኢቢሲን ወደመሳደብ ሲመጣ ራሳችንን ከውድድሩ ማግለል ምርጫችን ሆኗል” ሲል የኢቢሲ ባልደረባ ተናግሯል። በዚህ ውድድር ላይ የተሟላ ስብስብ የለንም በሚል ፋና ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ከተሳትፎ ውጪ ሆኗል።
በዘንድሮ ውድድር ላይ ተገቢነት የሌለው ተጨዋች የያዘ ሚዲያ ከውድድሩ እንደሚታገድና ተገቢነት የሌለው ተጨዋች ይዞ በመገኘት ላይ ድርድር እንደማይኖር አዘጋጅ ክፍሉ አስታውቋል።