“ከፕሪምየር ሊጉ የውድድር ፎርማት በመነሳት ያሉንን ልጆች ሁሉ ልንጠቀም ተዘጋጅተናል” አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው

ወልቂጤ ከተማ የፕሪ-ሲዝን ልምምዱን በባንኮች ሜዳ መስራት ጀምሯል

“ከፕሪምየር ሊጉ የውድድር ፎርማት በመነሳት ያሉንን ልጆች ሁሉ ልንጠቀም ተዘጋጅተናል”
አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው


የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ዓምና የተቀላቀለው ወልቂጤ ከተማ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ተሳትፎው ጥሩ ውጤትን ለማምጣት ያለመ ሲሆን ለዛ የሚረዳውንም የዝግጅት ጊዜ ልምምዱንም ካለፉት አራት ቀናት አንስቶ በአዲስ አበባ ከተማ ላይ በሚገኘው የባንኮች ሜዳ ላይ መስራት ጀምሯል፡፡

ወልቂጤ ከተማ መቀመጫውን በጣም ምቾት ባለው የሆሊዴይ ሆቴል በማድረግ በአሰልጣኙ ደግአረገ ይግዛው በመመራት እየሰራ ባለው የእስካሁኑ የፕሪ-ሲዝን ልምምዱ ነባር እና አዳዲስ ያስፈረማቸውን ተጨዋቾች እንደዚሁም ደግሞ 6 የሚደርሱም ታዳጊ ተጨዋቾችን በመያዝ ልምምዱን አጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን አንዱ ታዳጊ ተጨዋችም የዋናውን ቡድን ስኳድ ሙሉ ለሙሉ ለመቀላቀል የቻለበት ሁኔታ ስላለ የእዚህ ዓመት ላይ በሜዳ ላይ የሚታይበት ሁኔታ እንደሚኖርም እየተገለፀ ይገኛል፡፡

ወልቂጤ ከተማ ለፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው እያደረገ ስላለው ዝግጅት እና በእዚህ ዓመት ላይ ክለቡ ሊያስመዘግብ ስላሰበው ውጤትም የቡድኑን አሰልጣኝ ደግአረገን ጠይቀነው ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቶናል፡፡ “የፕሪ-ሲዝን ዝግጅታችንን እና ልምምዳችንን ቀለል ባሉ እና ተጨዋቾቻችንንም ለጉዳት በማያጋልጥ መልኩ መስራት ጀምረናል፤ በእዚህ የስራ ጅማሬያችንም በኮቪድ ወረርሽኝ ሳቢያ ተጨዋቾቻችን ከበርካታ ወራቶች በኋላ ዳግም ወደ ልምምድ የመጡ ስለሆኑ በአካል ብቃት /ፊትነስ/ ደረጃቸው ላይ የተመለከትኩት ክፍተት ነገር አለና ተጨዋቾቼ በጥሩ አቋም ላይ እንዲገኙ ብዙ መስራት ያለብን ነገር እንዳለ በሚገባ ተረድቻለሁና እዛ ላይ አተኩረን እየሰራን ነው የምንገኘው” ብሏል አሰልጣኝ ደግአረገ በእዚህ ዓመት ቡድናቸው ስለሚያስመዘግበው ውጤትም አክሎ ሲናገር “የእዚህ ዓመት የውድድር ፕሮግራም እስካሁን አልደረሰንም፤ በወሬ ደረጃ እንደሚሰማው ሊጉ በየአራት ቀናት ልዩነት በተመረጡ ሜዳዎች ላይ የሚካሄድበት ሁኔታ ሊኖር ስለሚችል በእዚህ የቶርናመነት ታይት አይነት የውድድር ተሳትፎአችን ጉዳት ሊኖር ይችላል ብለን በማሰብ ዘንድሮ በስኳዳችን የያዝናቸውን ተጨዋቾች ሁሉ አፈራርቀን በመጠቀም ከዓምናው ልምድ ወስደን የተሻለ ቡድን ለመስራት እና በውጤት ደረጃም የሚያኮራንን ስኬት ለማስመዝገብ ዝግጁ ሆነናል”፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website