“ለሻምፒዮናነት የሚጫወት ቡድን አለን” ዮናስ ገረመው /መቐለ 70 እንደርታ/

መቐለ 70 እንደርታ በእዚህ ዓመት ላለበት የፕሪምየር ሊጉ ተሳትፎው እና የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታው የፕሪ-ሲዝን ዝግጅቱን ካለፉት ሶስት ሳምንታት አንስቶ በቀን ሁለት ጊዜ በመስራት እየተለማመደ ሲሆን በእዚህ የውድድር ጉዞውም የሊጉን ዋንጫ ዳግም ለማንሳት እና በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ደረጃም አበረታች ውጤትን ለማስመዝገብ እቅድ መያዙን የቡድኑ የአማካይ ስፍራ ተጨዋች ዮናስ ገረመው /ሀላባ/ ከሀትሪክ ስፖርት ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሹን ሰጥቷል፡፡

መቐለ 70 እንደርታ የእዚህ ዓመት የውድድር ተሳትፎውን በጥሩ ውጤት ለማጠናቀቅ ዝግጅቱን አጧጡፎ በቀጠለበት የአሁን ሰዓት ክለቡን ለማጠናከር የተለያዩ አዳዲስ ተጨዋቾችን ከተለያዩ ቡድኖች ያስመጣ እና ከባህር ማዶም በረኛ እና ተከላካይ ለማስመጣት እንደተዘጋጀ እየተነገረ ሲሆን የእነዚህ ተጨዋቾች ውህደትም ቡድኑን ተጠቃሚ ሊያደርገው እንደሚችልም አስተያየቶች እየተሰጡበት ይገኛል፡፡

የመቐለ 70 እንደርታን የእዚህ ዓመት የውድድር ተሳትፎን በተመለከተ እና ሌሎችንም ጥያቄዎች አንስተን ከቡድኑ ተጨዋች ዮናስ ገረመው ጋር አጠር ያለ ቆይታን ያደረግን ሲሆን ምልልሱም በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፡፡

ሀትሪክ፡- በፕሪምየር ሊጉ የዘንድሮ ተሳትፎህ አሁንም ለመቐለ 70 እንደርታ ለመጫወት ውልህን ማራዘምህ ይታወሳል፤ ቡድኑ ተመችቶሃል?

ዮናስ፡- በጣም ነው የተመቸኝ፤ ለዛም ነው ውሌን ያራዘምኩት፤ መቐለ ጥሩ ጊዜን ያሳለፍኩበት የሊጉ ቡድኔ ነው፤ ጠንካራ ቡድን አለን፤ ከዛ ውጪም እኛን የሚወዱን እና የሚያበረታቱን ምርጥ ደጋፊዎችም አሉን፤ ውጤት እንድናመጣ ከጎናችን ሆነው ይደግፉናል፤ አሁን ራሱ በኮቪድ ጊዜ የዝግጅት ጊዜ ልምምዳችንንም በመከታተል እያበረታቱን ይገኛልና በቡድኑ መቆየቴን ወድጅዋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- የመቐለ 70 እንደርታ የፕሪ-ሲዝን ዝግጅት አጀማመሩ ምን ይመስላል?

ዮናስ፡- እስካሁን ወደ አራት ሳምንት ለሚጠጋ ጊዜ ነው በቀን ሁለቴ ጠዋት እና ከሰዓት በጂም ደረጃ እና ወደሜዳ በመውጣት እየተለማመድን የሚገኘው፤ አሰልጣኛችን እያሰራን ያለው ልምምድም እኛን እና ክለቡን በውጤት ደረጃም በሚጠቅም መልኩም ነውና ይሄ የዘንድሮ ዝግጅታችን ሁላችንንም እያስደሰተን ይገኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ወደ ዘንድሮ ዝግጅት የገባችሁት በኮቪድ ወረርሽኝ የተነሳ ከበርካታ ወራቶች በኋላ ነው፤ ልምምዳችሁን ስትጀምሩ የተለየ ነገር አጋጥሞአል?

ዮናስ፡- አዎን፤ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ከፍተኛ ስጋት ሆኖ በቀጠለው የኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ከኳሱ ለወራቶች ርቀን ወደ ዝግጅት ስንገባ ያጋጠመኝ ነገር በጣም ከባድ ነው፤ በእዛን እረፍት ወቅት በግል እንሰራ የነበረው ልምምድ አሁን ላይ በጋራ እንደምንሰራው አይነት ጠንካራ እና ራሳችንን በሚለውጠን ደረጃም ላይ አልነበረምና ያን በዝግጅታችን ወቅት ለማስተዋል ችያለው፤ ስለዚህም ከክለቤ መቐለ 70 እንደርታ የቡድን አጋር ተጨዋቾቻችን ጋር አሁን እየሰራን የሚገኘው የዝግጅት ጊዜ ልምምዳችን በጣም ጥሩ ስለሆነ በራሴ ላይ በተለይ ደግሞ በአካል ብቃቱ ላይ ከፍተኛ ለውጥን እየተመለከትኩበት ነው የሚገኘው፡፡

ሀትሪክ፡- መቐለ 70 እንደርታ በዘንድሮ ቡድኑ ምርጥ ስብስብን ይዟል?

ዮናስ፡- አዎን፤ ማለት ይቻላል፤ ይሄን ለማለት የቻልኩትም ቡድናችን ባለፈው አመት ይዟቸው የነበሩትን ጠቃሚ ተጨዋቾቹን ውል ሊያራዝም ስለቻለ እና ከዛ ውጪም ደግሞ ቡድኑን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ተጨዋቾችንም ከተለያዩ ቡድኖች ስላስመጣም ነው፡፡

ሀትሪክ፡- በመቐለ 70 እንደርታ በሚኖርህ ቆይታ ዘንድሮ ምንን ለማሳካት አልመሃል?

ዮናስ፡- የመጀመሪያው እና ዋናው እቅዴ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ከክለቡ ጋር በማንሳት 3ኛውን የሊግ ዋንጫዬን በተጨዋችነት ዘመኔ ማግኘት መቻል ነው፤ ኳስን እስካሁን ስጫወት ከጅማ አባጅፋር እና ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ይህን ዋንጫ ለማግኘት ችያለሁ፤ ዘንድሮም ክለባችን ለሻምፒዮናነት የሚጫወት ቡድን ስላለሁ 3ኛውን ዋንጫ ከክለቡ ጋር አሳካለሁም ብያለሁ፤ ሌላው በእዚህ ዓመት ከክለቡ ጋር ላሳካው የምፈልገው ነገር ቡድናችን በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ደረጃ የሚጫወትበት ተሳትፎ ስላለው ከቡድኑ ጋር አበረታች የሚባል ውጤትን ማግኘት መቻል ነው፡፡

ሀትሪክ፡- በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመንህ የሚቆጭህ ነገር አለ?

ዮናስ፡- አዎን ይኖራል፤ በአብዛኛው ጊዜዬ ደስተኛ ሆኜ ባሳልፍም ለብሔራዊ ቡድን ተመርጬ አለመጫወቴ ግን ሁሌም ይቆጨኛል፤ ስለዚህም ይህን ቁጭቴን ለመወጣት በቀጣይ ጊዜ የሊጉ ጨዋታዎች ላይ በጣም ጥሩ ሆኜ በመቅረብ ለብሔራዊ ቡድን ለመመረጥ እና ለመጫወት ጥረትን አደርጋለሁኝ፡፡

ሀትሪክ፡- ጨረስኩ ማለት የምትፈልገው ነገር ካለ?

ዮናስ፡- መቐለ 70 እንደርታ ካለፉት ሁለት እና ሶስት ዓመታት ወዲህ ለዋንጫ እንጂ ለደረጃ የሚጫወት ቡድን ባለመሆኑ ሁሌም ተፈሪ ቡድን እንዲሆን አድርጎታል፤ ይሄ መሆን መቻሉም እኔን እንደ አንድ ተጨዋች በጣም እያስደሰተኝ ይገኛል፤ ከዛ ውጪ ማለት የምፈልገው ነገር ክለባችን ዘንድሮ በሚያደርገው የኢንተርናሽናል የውድድር መድረክ ላይ ቡድናችን ጥሩ ውጤት አምጥቶ እኔም የምመኘውን በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ደረጃ ወደ ውጪ መጫወት ፍላጎቴን እንዳሳካ ነውና ያ ዕድል እንዲገጥመኝ እፈልጋለው፤ ሌላው መጥቀስ የምፈልገው ፈጣሪ ከክፉው የኮቪድ ወረርሽኝ እንዲጠብቅን ነው፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website