አዳማ ከተማ ደመወዝ ይከፈለን በሚሉ ተጨዋቾች ተወጥሯል

አዳማ ከተማ ደመወዝ ይከፈለን በሚሉ ተጨዋቾች ተወጥሯል

-መረጃዎች ወደ 19 ሚሊዮን ብር ዕዳ እንዳለበት ይጠቁማሉ

 


አዳማ ከተማ ከ1 ወር እስከ 4 ወር ድረስ ያልተከፈለ ደመወዝ ዕዳ እያናጠረበት ቢሆንም አሁንም መፍትሔ አላገኘም ተባለ፡፡ከአዳማ ከተማ ታማኝ ምንጭ በተገኘ መረጃ የነባር ተጨዋቾች የሰኔ ወር ደመወዝ ያልተከፈለ ሲሆን ከአዲሱ የተጨዋቾች የደመወዝ ክፍያ ሕግ በፊት ውል የተዋዋሉ ተጨዋቾች የ2011 የሀምሌና የነሀሴ ወር ደመወዝ አሁንም አልተከፈለንም በሚል ባቀረቡለት ክስ ፌደሬሽኑ ክለቡን ከየትኛውም ዝውውር የማድረግ መብት አግዷል፡፡ በሕጉ የማይገደዱም ቢሆን አስቀድሞ ከ100 ሺ ብር በላይ የሚከፈላቸውና አዲሱ ሕግ የማይመለከታቸውን ተጨዋቾች በአዲሱ ሕግ በ34 ሺ 3 ወር ሙሉ በመክፈል ከውሉ ውጭ ክፍያውን ተግባራዊ በማድረጉ በርካታ ልምድ ያላቸው ተጨዋቾች ክለቡን ለመልቀቅ ተገደዋል፡፡ የክለቡን ቀጣይ ጊዜ ከባድ የሚያደርገው በክለቡ ውስጥ ውል ያደሱ ተጨዋቾች ከሀምሌ ጀምሮ እስከ ጥቅምት የ4 ወር ደመወዝ ፌዴሬሽኑ ውላቸውን ካፀደቀ በኋላ የሚከፈል ቢሆንም የተጣለባቸው የዝውውር እገዳ ሌላ ችግር ውስጥ እንዳይከታቸው ተሰግቷል፡፡

ከአዳማ ውስጥ አዋቂ በተገኘ መረጃ ክለቡ 19 ሚሊዮን ብር እዳ አለብኝ ያለ ሲሆን ወደ 60 ሚሊዮን ብር አካባቢ በጀት ለ2013 ቢፈቀድም ያለብንን 19 ሚሊዮን ብር ከዚሁ ከከፈልን አሁንም ስለማይበቃን ሌላ እዳ ውስጥ መግባታችን አይቀርም ብለው ከሌላ በጀት አውጥታችሁ እዳው ይከፈል እኛ ይህንን በደንብ እናስተዳድረበት የሚል አቋም አዲሱ አመራሮች መያዛቸው ታውቋል፡፡ የበላይ አካል ግን ከተያዘላችሁ በጀት ክፈሉ በሚል ሁለት ፅሁፍ የያዘ አቋም መያዛቸው ታውቋል፡፡

በፌዴሬሽኑ የዕገዳ ጠንካራ አቋም የተያዘባቸው የክለቡ አመራሮች ከፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ጋር በመነጋገር በልዩ ፍቃድ ውል ላደሱት ተጨዋቾች የዘንድሮውን ከፍለው ቡድኑን ወደ ዝግጅት ለማስገባት የጎንዮሽ ሙከራ ቢያደርጉም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ክለቡ ከቀረበበት ክስ አሳዛኝ የተባለው የቀድሞ ተጨዋቹ የአዱልሃኪም ሱልጣን ሁኔታ ነው፡፡ በ2010 ለአዳማ የፈረመው ተጨዋቹ በልምምድ ላይ እያለ የደረሰበት ጉዳትና ክለቡ የወሰደው አቋም አሁን ድረስ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

ተጨዋቹ በጉዳዩ ዙሪያ ለሀትሪክ እንደተናገረው “በልምምድ ላይ እያለሁ ተጎድቻለሁ፡፡ አሁን ድረስ ደመወዝ አልከፈሉኝም፤ ኮሪያ ሆስፒታል እየታከምኩ ሳይሻለኝ ወደ ቡድኑ እንድመለስ ቢያዙኝም ሀኪሙ ጉዳቴን አይቶ እረፍት እንደሰጠኝ ብገልፅም የክለቡ አመራሮች ግን ልምምድ መጀመር አለብህ አለበለዚያ እርምጃ እንወስዳለን ብለው ማስጠንቀቂያ ሰጡኝ፤ ምንም ማድረግ ባለመቻሌ ወደ ልምምድ ተመለስኩ ግን ጉዳቴ እየባሰ ሄደ” ሲል ሁኔታውን ያስረዳል፡፡ “ልምምዴን የምሰራው እያነከስኩ ነበር እየባሰብኝም ሄደ በድጋሚ ደብዳቤ ሲሰጡኝ ለፌዴሬሽኑ ከሰስኩ፡፡ ዲሲፕሊን ኮሚቴ ወሰነልኝ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴም አፀናው እንዲከፍሉ ታዘዙ” የሚለው አብዱልሃኪም “የ16 ወራት ደመወዜን አልከፈሉኝም፡፡ ሲወሰንባቸው ብር የለንም ከእኛ ጋር ያደክ በመሆኑ ክለቡን ማገዝ አለብህ ብለው በየወሩ እንከፍልህ አሉኝ ተስማማሁ፤ ፌዴሬሽን እያወቀ ተፈራርምን ግን አሁን ድረስ የአንድ ወር ደመወዝ እንኳን አልከፈሉኝም፤ አራት ኪሎ የሚገኘው ዳኑ የአጥንት ስፔሻሊስት ጋር የነበረበውን ህክምና በገንዘብ እጦት ሳይቀር አቋርጫለሁ፡፡ ደመወዝ የለኝም መጫወት አልቻልኩም ያደክበት ክለብ ነው በየወሩ እንክፈልህ ቢሉኝም ቃላቸውን አላከበሩም በዚህም በጣም ቅር ብሎኛል” በማለት ያለበትን ሁኔታ ለሀትሪክ አስረድቷል፡፡
የበርካታ ተጨዋቾች ክስ የቀረበበት አዳማ ከተማም ከቀድሞ አሰልጣኙ አሸናፊ በቀለም የደመወዝ ይከፈለኝ ጥያቄ ቀርቦበታል፤ በአሁኑ ሰዓት የሀዲያ ሆሳዕና ዋና አሰልጣኝ የሆኑት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የ2012 የፊርማ ክፍያ ከአዳማ ከተማ ከወሰዱ በኋላ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ የተነሣ ውድድሩ በመቋረጡ እስካሁን ያልወሰዱትን ቀሪውን ደመወዝ እንዲከፈላቸው በዚህ ሳምንት በደብዳቤ መጠየቃቸው ታውቋል፡፡

የክለቡ ዋና አሰልጣኝ አስቻለሁ ኃ/ሚካኤል ለሀትሪክ እንደገለፀው “በተቻለ መጠን አስተዳደራዊ ጉዳዮች በፍጥነት አልቀው ወደ ዝግጅት መግባት አለብኝ እያለኩ ነው፤ እንደተባለው ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ አመራሮቹ ሁኔታውን ለማስተካከልና ችግሮቹን ለመቅረፍ እየጣሩ ነው፡፡ ካምፕ ያለው ነገር ለማስተካከልም እየሰራን ነው” በማለት ተናግሯል፡፡ “አሁንም የተጨዋቾች ውል አልፀደቀም ይሄ ቶሎ መስተካከል አለበት፡፡ አመራሮቹ ከፌዴሬሽኑ ጋር እየተነጋገሩ ነው የኦሮሚያ ክልልም ሶስቱን የክልሉን ክለቦችን ለመርዳት እያሰበ መሆኑ መልካም ጎን ነው በአጭር ጊዜ ተጠቃሎ ቀጣዩ ሣምንት ልምምድ የመግባት እቅድ ይዘናል” በማለት አሰልጣኙ ገልጿል፡፡ ከተጨዋች አብዱልሃኪም ጋር ተያይዞ ከ2010 ጀምሮ ደመወዝ ያልተከፈላቸው ተጨዋቾች መኖራቸውን የተጠየቀው አሰልጣኙ “በአብድልሃኪም ጉዳይ ስህተት ተሰርቷል አሁን ግን ሕጉን ጠብቀው ለመክፈል ተነጋግረዋል፤ ያለውን እዳ ቶሎ ተከፍሎ ወደ መፍትሔው እንደሚገቡ ተስፋ አደርጋለሁ ወደ 32 ልጆችን ይዣለው ልምምዱ በቀጣይ ሳምንት የሚጀመር ከሆነ ጥሩ ውጤት ይመጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤ በፍጥነት የኮቪድ 19 ምርመራው መጀመር አለበት፤ እነኚህ ጉዳዮች በቀጣዩ ቀናቶች መፍትሔ ያገኛሉ ብዬ አስባለው” በማለት አሰልጣኝ አስቻለሁ ኃ/ሚካኤል ለሀትሪክ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ በቀጣይ የቡድኑ አቋም ዙሪያ ትልቅ ፈተና ሊሆንበት ይችላል የተባለው አሰልጣኝ አስቻለሁ ኃ/ሚካኤልን በምክትል አሰልጣኝነት እንዲያግዙ አሰልጣኝ ደጉ ዱባም እንደሁም የቀድሞውን የሻሸመኔ ከተማ አሰልጣኝ አብዲ ቡሊን ሁለተኛ ምክትል አሰልጣኝ አድርጎ ሾሟል፡፡

ከክለቡ ጋር በተያያዘ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ምላሽ ለማግኘት ወደ ክለቡ ፕሬዚዳንት አቶ ገመቹ ጋር ተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ሆነ ቴክስት ብናደርግ ምላሽ ሊሰጡን ባለመቻላቸው የቦርዱኑና የክለቡን ውሣኔና አቋም ማካተት አለመቻላችንን እንገልፃለን፡፡

 

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport