በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ጨዋታ 3 ወንድማማቾችን በአንድ ጨዋታ ያገናኘው የወላይታ ድቻና ፋሲል ከነማ ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡
እንደወትሮው ሁሉ በርካታ ሺ የወላይታ ድቻ ደጋፊ እንዲሁም በግምት ከ200 በላይ ተጓዥ የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች በሶዶ ሁለገብ ስታዲየም የተከታተሉት የ7ኛ ሳምንት ጨዋታ 9:05 ደቂቃ የጀመረ ሲሆን፣ ድቻዎች እንደሁልጊዜው ሁሉ ኳስ ተቆጣጥሮ ማጥቃት ላይ መሰረት ያደረገ በሚመስል መልኩ ባዬ ገዛኸኝ፣ ዳንኤል ዳዊትንና ቸርነት ጉግሳን ከፊት መስመር በማሰለፍ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት ያደረጉ ሲሆን ፋሲል ከነማዎች በአንፃሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪያቸው የሆነውን ሙጂብ ቃሲም ለብቻው እንዲያጠቃ ወደፊት ለቀውት በመልሶ ማጥቃት ረዣዥም ኳሶችን ወደ ተጋጣሚያቸው በመጣል አደጋ ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። ዳንኤል ዳዊት ጨዋታው በተጀመረ በ4ኛው ደቂቃ ከርቀት መቶ ወደ ውጭ የወጣበት፣ ከማዕዘን ምት የተመለሰ ኳስ ደጉ ደበበ በግምባሩ ገጭቶ አገባ ሲባል ወደ ሗላ የተጨረፈበት፣ ቸርነት ጉግሳ በ39ኛው ደቂቃ በክንፍ ኳስ ገፍቶ በመግባት አክርሮ መቶ ግብ ጠባቂው የመለሰበትና እራሱ ቸርነት ጉግሳ ሳጥን ውስጥ እየገፋ ገብቶ ያባከናቸው 2ኳሶች በወላይታ ድቻ በኩል በመጀመሪያው 45 የተደረጉ ሙከራዎች ሲሆኑ፣ ሙጂብ ቃሲም በ9ኛው እና በ39ኛው ደቂቃ ካደረጋቸው ሁለት ሙከራዎች በቀር ፋሲል ከነማዎች የጥንቃቄ አጨዋወትን መርጠው የመጀመሪያው አጋማሽ ግብ ሳያስተናግድ ብዙም ተመልካቹን ሳያዝናና 0-0 አቻ ተጠናቋል፡፡
- ማሰታውቂያ -
10:08 ሲል በጀመረው በሁለተኛው 45 ወላይታ ድቻዎች ወደ ግብ በመድረስ የተሻሉ የነበሩ ሲሆን፣ በጉዳት ብዙም ክለቡን እያገለገለ የማይገኘው በዛሬው ጨዋታ ተቀይሮ እስኪወጣ ድረስ የጦና ንቦቹ የአማካይ ብልጫ እንዲወስዱ ያስቻለው በረከት ወልዴ ከዕረፍት መልስ ፍፁም ቅጣት ምት ውስጥ በመግባት በመሬት አክርሮ መቶ ግብ ጠባቂው የያዘበትና እራሱ በረከት ወልዴ ኳስ እየገፋ ሲሄድ ተጠልፎ ባዬ ገዛኸኝ በግሩም ሁኔታ በቅጣት ምት ግብ በማስቆጠር ባለሜዳዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
ድቻዎች ግብ ካስቆጠሩ በኋላም ተጭነው ቢጫወቱም አደገኛ የነበረው የፋሲል ከነማ የክንፍ አጨዋወት ባለሜዳዎቹን ጫና ውስጥ መክተት ችሎም ነበር። 90ኛው ደቂቃ ላይ የወላይታ ድቻው እዮብ አለማየሁ በእጁ ነክቶ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ሙጂብ ቃሲም ወደ ግብነት ቀይሮት እንግዳዎቹ ጣፋጭ አንድ ነጥብ እንዲወስዱ አስችሏል፡፡
3ቱ የጉግሳ ልጆች ማለትም ሺመክት ጉግሳ፣ አንተነህ ጉግሳና ቸርነት ጉግሳ ለሁለተኛ ጊዜ በተቃራኒ የተጫወቱ ሲሆን፣ 1-1 በተጠናቀቀው ጨዋታ ተጓዦች የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች በውጤቱ ሲደሰቱ በአንፃሩ የድቻ ደጋፊዎች በትካዜ ከሜዳ ሲወጡ ተስተውሏል። ውጤቱንም ተከትሎ ወላይታ ድቻ ከወራጅ ቀጠናው መውጣት ተስኖት በ6ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ፋሲል ከነማ በአንፃሩ አቻ በመውጣቱ የሊጉ መሪ መሆን የሚችልበትን እድል አምክኖ በ12ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
ሊጉን ወልዋሎ አ.ዩ. በ14 ነጥቦች ሲመራ መቐለ 70 እ. እና ፋሲል ከተማ በቅደም ተከተል በ13 እና በ12 ነጥቦች 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። የኮከብ ግብ አግቢነቱን ደግሞ የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲም በ7 ግቦች ቀዳሚ ሲሆን የባህርዳር ከነማው ፍፁም ዓለሙ በ6 እንዲሁም የመቐለ 70 እ. አማኑኤል ገ/ሚካኤል በ5ግቦች ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።