“ያለፉትን ሁለት አመታት የምናካክስበት አመት 2ዐ12 ይመስለኛል” ጋዲሳ መብራቴ/ቅዱስ ጊዮርጊስ/

 THE BIG INTERVIEW WITH GADISA MEBRATE

“የመቀበል አቅምና የመማር
ፍላጎት እስካለህ ድረስ ቅዱስ
ጊዮርጊስ አስተማሪ ቡድን ነው”
“ሜዳዎቻችን የሠላም ቦታ
ከመሆናቸው የተነሳ ፖሊስ
ባይኖር ሁሉ ደስ ይለኛል”

 

የግራ እግር ምርጥ ተጨዋች ነው ይሉታል አድናቂዎቹ….ኳሷን ሲገፋትና ድሪብል ሲያደርግ ለተመልካች ይማርካል….ትልቅ ትችት የሚቀርብበት መዝናናት
ያበዛል በሚል ነው…እርሱ ግን መዝናናቴ እንደሰው እንጂ አይለይም….ፈረሰኞቹ በመሃል ክፍላቸው እንዲፈነጭ ካደረጉት 3 አመት ቢሞላውም
የሚጠበቅበትን ያህል እየተጫወተ እንዳልሆነ ራሱም አምኗል….2012 ግን የኛ ነው ይላል…..ለሃዋሳ ከተማ 4 አመት. ለኒያላ 2 አመት ከተጫወተ
በኋላ በፈረሰኞቹ ቤት 3ኛ አመቱን ይዟል….የግራ እግር ምርጥ ተጨዋቹ ጋዲሳ መብራቴ ከዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበረው ቆይታ በሸገር ደርቢ ስላስመዘገቡት
ድል፣ ሥለደነቀው የፈረሰኞቹ ባህል፣ በቦታው ኮከብ ስለሆነው ተጨዋች 2012 ዋንጫው የኛ ነው ያለበት፣ መዝናናት ስለማብዛቱ፣ድሬዳዋ ከተማ ላይ
ስላስቆጠራት የቅጣት ምት ግብ፣ስለሚወደው አሰልጣኝ፣ለዋሊያዎቹ ለመጫወት ስላለው ህልም፣ስለስፖርታዊ ጨዋነት፣ስለተገደበው የተጫዋቾች
ደመወዝ፣ ከነደጉ ውጣት በኋላ መሪ ተጨዋቾች የሉም ስለሚባለውና ሌሎች ጉዳዮች ምላሹን ሰጥቷል፡፡

ሀትሪክ፡-የፕሪሚየር ሊጉን ድል ተከትሎ ከረጅም ጊዜ በኋላ መሪነቱን ተረክባችኋል በተመዘገበው ውጤት ላይ ምን አስተያየት አለህ?
ጋዲሳ፡- በጣም ተደስተናል ናፍቆን ስለነበርና ስለተሳካልን ደስ ብሎናል፤ ጥንካሬያችን ነው ቦታውን እንድንይዝ ያደረገን፡፡ ሜዳችን ላይ የተሻለ በመሆን እያሸነፍን ነው፤ 3 ተከታታይ
ጨዋታዎችን አሸንፈን መሪ ሆነናል ይህም ይህ አመት የኛ ነው ብዬ የምንገረውን በጭላንጭል እንዳይ አድርጎናል፡፡ እንደኛ ብዙ ነጥብ የሰበሰበ ክለብ የለም ከእግዚአብሔር ጋር ዋንጫ
እንወስዳለን ብዬ አምናለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ሲዳማ /ቡናን 6ለ2 ረታችሁ… የግቡን ብዛት ጠብቀኸው ነበር?
ጋዲሳ፡- ሲዳማ ቡና ከሌላው አመታት ቀዝቅዝ እንዳለ ይሰማኛል ክፍተቶች ያሉበት ቡድን ነው ጠንክረን ተጫውተን ለማሸነፍ 3 ነጥብ እናገኛለን ከማለት ውጪ ይህን ያህል እናገባለን
ብለን አላሰብንም፡፡ በተመዘገበው ድል ግን በጣም ተደስተናል፡፡


ሀትሪክ፡- የመሪነቱን ጭራ ከያዝን በኋላ ማንም አይረከበንም የሚል አቋም አለህ?
ጋዲሳ፡- አዎ ምንም ስጋት የለብኝም መቐለ ሻምፒዮን ሲሆን የሆነ ሰዓት ላይ መሪ ነበረን ግን ቀሪ ጨዋታ ስለነበራቸውና ማሸነፍ ስለቻሉ ወደ መሪነት ተመልሰዋል፤ አሁንም ነጥቡ
ተቀራራቢ ቢሆንም ቦታውን አንነጠቅም ብዬ አስባለው ደጋፊዎቻችንን እንዳስለመዳችሁን ከጎናችን ሁኑ ማለት እፈለጋለው፡፡
ሀትሪክ፡- በሸገር ደርቢ ኢትዮጵያ ቡና መርታት ምን ስሜት ይፈጥራል?
ጋዲሣ፡- የደርቢ ጨዋታ ሲሆን ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ በተለይ የሁለቱም ክለቦች ለደጋፊዎች በጉጉት የሚጠብቁት ነው….. የደርቢ ጨዋታ ትልቅ ስሜት ይፈጥራልና በዚህ ትልቅ ጨዋታ
ላይ ድል ማድረግ ደግሞ ያስደስታል እኔም ተፎካካሪ የሆነውን ኢትዮጵያ ቡናን በመርታታችን ልዩ ስሜ ተሰምቶኛል፡፡ በሁለት አመት ውሰጥ 3 ጊዜ ተጫውተን ሁለቱን ስናሸንፍ አንዱን አቻ
ወጥተናል ይሄ የበላይነታችን ያስደስታል፡፡
ሀትሪክ፡- ሳምንት በተካሄደው የደርቢ ጨዋታ ላይ ልዩነት ፈጣሪ ተጨዋች ላንተ ማን ነው?
ጋዲሣ፡- ለእኔ ለየት ብለው የታዩኝ ጌታነህ ከበደና ደስታ ደሙ ናቸው፡፡ ሁለቱም በጣም አሪፍ ነበሩ፡፡
ሀትሪክ፡- አሁን ያለው አቋምህ የመጨ ረሻው ጣራ ነካ የሚባለው ነው ወይንስ ገና ጫፍ ጋር አልደረሰም ?

ጋዲሣ፡- ገና 100 ፐርሰንት አቅሜ ላይ አይደለሁም ብዬ ነው የማስበው… ከዚህ በላይ ልዩ በሆነ አቋም ላይ እንደምገኝ አውቃለው….. ገና ወደፊት ነው አቅሜ የሚታየው፡፡
ሀትሪክ፡- አሁን እየጫወትክ ባለው ቦታህ ደስተኛ ነህ…… የሲቲ ካፑና የአሁኑ ስለሚለያይ?
ጋዲሣ፡- በሲቲካፑ ላይ ነበር በፉል ባክ ቦታ ላይ ስጫወት የነበረው… ከዚያ በኋላ ግን በምፈልገውና በምወደው ቦታ ላይ እየተጫወትኩ ነው በዚህም ደስተኛ ነኝ…. ጥሩ ነገር
እንደማደርግም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- በሀዋሳ ከተማ የነበረህ ነፃነት በፈረሰኞቹ ቤት አለ ማለትይቻላል ?
ጋዲሣ፡- በገባሁበት 2 አመታት ላይ ተቸግሬ ነበር ብዙ ጫናዎች ነበሩብኝ….የክለቡን ባህል መልመድ አስቸግሮኝ ነበርና ትንሽ ከብዶኝ ነበር… በ2012 የሶስተኛ አመት ቆይታዬ ግን ተሻሽዬ
የቀረብኩበት አመት ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ሰዎች ባንተ ብቃት ላይ ጥያቄ የላቸውም መጠጥ መዝናናት ግን ያበዛል ይላሉ.. ተቀበልከው?
ጋዲሣ፡- አልስማማም.. በጣም ተጋኗል፡፡ ኖርማል ሰው እንደሚዝናና ካልሆነ በቀር ተለይቼ የምጠጣ መጠጥ የማበዛ ሰው አይደለሁም… ስዝናናም ራሴን አውቀዋለው ራሴን
እስክጥል ድረስ አልጠጣም፡፡ ሰው እንደሚዝናና እኔም እዝናናለው አበቃ፡፡


ሀትሪክ፡- የእግር ኳስ ዲሲፕሊን እንደሚያዝ ዲሲፕሊኑን አክባሪ ነኝ ለማለት ትደፍራለህ?
ጋዲሣ፡- በደንብ እንጂ….. በተለይ በ2ዐ12 ራሴን በብዙ ነገር ለውጪ በመቅረቤ ነው ጥሩ አቋም ላይ የተገኘሁት፡፡ ሰው ሊያወራ ይችላል ትኩረት ውስጥ የምገባ ተጨዋች በመሆኔ
ካልሆነ በቀር የተጋነነ ነገር አላደርግም..ሀዋሳም እያለሁ ተመሳሳይ ነገር ገጥሞኛል ወሬ ማስቆም ባልችልም ከሰው አቅም ባለፈ መልኩ አልተዝናናሁም….
የሚጎዳኝና የሚጠቅመኝን በሙሉ አውቃለው….. በርግጥ ያማረኝን ነገር አደርጋለው በፍፁም ግን የሚጎዳኝ ነገር አያምረኝም፡፡
ሀትሪክ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስና ሃዋሳ ዐለዐ በተለያዩበት ምሽት ስትጠጡም ተይዛችሁ ከደጋፊው ጋር ተጋጫችሁ የሚባል ነገር ሰማሁ እውነት ነው?
ጋዲሣ፡- አዎ ትንሽ አለመግባባት ነበር በውይይት ተፈትቷል ለሚዲያ የሚቀርብ ጉዳይ አልነበረም፡፡/ሳቅ/
ሀትሪክ፡- የዛሬ አመትም ከጊዮርጊስ ደጋፊ ጋር ፀብ ውስጥ ነበራችሁ … እሱስ አሁን ተፈታ?
ጋዲሣ፡- ብዙ የሚጋነን አልነበረም በውስጥ ተነጋግረን ዘግተናል ሚዲያ ጋር መድረስ ያለበትም ጉዳይ አይደለም፡፡
ሀትሪክ፡- አሁንኮ ሚዲያ ጋር ወጥቶ ነው እየጠየኩህ ያለሁት?
ጋዲሣ፡- /ሳቅ/ በቃ ሠላም ነው ተፈቷል….አይበቃም
ሀትሪክ፡- ለቅ/ጊዮርጊስ ስትፈርም በጣም የተገረምከው በምንድነው?
ጋዲሣ፡- በጣም የተገረምኩት በደጋፊው ነው…. ደጋፊው ልዩ በሆነ ስሜት ነው የሚደግፈው እውነተኛ ደጋፊ ያለው እግር ኳስን የሚወድ ደጋፊ ነው ያለን…..ቡድኑን በተመለከተ ሲበዛ
ሽንፈት የሚጠላበት ክለብም ነው… ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ኮከብ ተጨዋች ለጊዮርጊስ ቢፈርምም መቸገሩ አይቀርም ትልቅ ቡድን እንደመሆኑ ውጤት ይጠበቃል…. ማሸነፍ ብቻ ነው
የሚፈለገው…. ይሄ ደግሞ ለማንኛውም ተጨዋች ጥሩ ነው በስነ ልቡና ተዘጋጅቶ እንዲመጣ ነው የሚያደርገው… ማሸነፍን ወደህ መሸነፍን እንድትጠላ ነው የሚያደርግህ….ፍላጎትህ ድል ብቻ
መሆኑ ያስደስታል… መማር ከተቻለና ማወቅ እስከፈለክ ድረስ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት አስተማሪ ነገር አለ፡፡ ራሱን የቻለ ት/ቤት በለው….የመቀበል አቅምና የመማር ፍላጎት እስካለህ ድረስ
ቅዱስ ጊዮርጊስ አስተማሪ ቡድን ነው /ሳቅ/
ሀትሪክ፡- በዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ የተለየ ቡድን ገጥሞሃል?
ጋዲሣ፡- በፍፁም የለም….. ሁሉም ተመሳሳይ ነው ልዩነት የፈጠረ ቡድን የለም ቅዱስ ጊዮርጊስ ገና 5ዐ እና 6ዐ በመቶ አቅሙ ላይ ነው የሚገኘው…..ምርጡ ጊዜ ገና ነው….
የክለቡ ደረጃ ይሄ ነው ብዬ አላምንም ወደፊት ምርጡ ጊዮርጊስ ይታያል፡፡


ሀትሪክ፡- በ6ዐ በመቶ ብቃት 2ኛ ከሆነ 1ዐዐ ፐርሰንት ሲሆን እንደ ሊቨርፑልና ማን.ሲቲ ሊሆን ነው ማለት ነው?
ጋዲሣ፡- /ሳቅ በሳቅ/ እንደዚያ በለው.. ዋንጫ ለማንሣት ቅዱስ ጊዮርጊስ የተሻለ እድል እንዳለው ይሰማኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ስንት አሰልጣኞች አሰልጥነውሃል. የተሻለው አሰልጣኝ ላንተ ማነው?
ጋዲሣ፡- በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ፣ በአሰልጣኝ ከማል አህመድና አሁን ደግሞ በጊዮርጊስ ቤት በነበሩት 3 የውጭ ዜጎች የመሰልጠን ዕድል አግኝቻለው፡፡ በተደጋጋሚ ተናግሬያለው አሰልጣኝ
ውበቱ አባተ ለኔ ልዩ አሰልጣኝ ነው… ውበቱ አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ አሰልጣኞች የማደንቀው ትልቅም ቦታና ክብር የምሰጠው አሰልጣኝ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ተምሣሌት የሆኑህ ተጨዋች አሉ?
ጋዲሣ፡- ሀዋሳ ከተ ማዋ የኳስ ተጨዋቾች መፍለቂያ ናት… በፊትም ነበሩ… አሁንም አሉ ሀዋሳ ከተማ ውስጥ ወጣቶች በብዛት ይገኛሉ ማንን ጥዬ ማንን ልናገር.. እነ ሙሉጌታ
ምህረት፣ ደጉ ደበበ፣ አዳነ ግርማ፣ በኃይሉ ግርማና ሽመልስ በቀለ የመሳሰሉትን አይቼ ነው ያደኩት….ለኔ ብቻ ሣይሆን ለብዙዎች ተምሣሌትም ናቸው፡፡
ሀትሪክ፡- ብሔራዊ ቡድን ላይ ብዙም አትመረጥም ለምን ይመስልሃል?
ጋዲሣ፡- በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ቡድን ውስጥ ተካትቼ ተጫውቻለሁ… ሙሉ ጨዋታ ውስጥ ነበርኩ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ላይ የወዳጅነት ግጥሚያ ላይ ተሰላፊ ነበርኩ፡፡ በርግጥ
በቀቅቱ የቡድኑ አካሄድና ውጤቱ በርግጥ ደስ አይልም ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- ከአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ምርጫ ውጪ እንዴት ሆንክ?
ጋዲሣ፡- በወቅቱ ጥሩ ብቃት ላይ አልነበርኩምና ከምርጫው ተዘልያለው ጊዮርጊስ የገባሁበት አመትም ጥሩ አልነበርኩም….አሁን ግን የተሻለ አቋም በመያዜ ከእግዚአብሄር ጋር
ብሔራዊ ቡድኑን እቀላቀላለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለው፡፡
ሀትሪክ፡- ጊዮርጊስ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ሲጫወት ከኮርና አካባቢ ጋር የቅጣት ምት ተገኘና ቀጥተህ መትተህ አስቆጠርክ.. በርግጥ አስበህ መታኸው?
ጋዲሣ፡- አዎ… በጣም ርግጠኛ ሆኜ ለግቡ ነው የመታሁት… ሀዋሳ እያለው አሰልጣኝ ውበቱ የቅጣት ምት ልምምድ ያሰራኝ ነበር… ለሁለት ቅጣት ምት የማስቆጠር ፉክክር እናደርግ ነበር
አሁን ብዙም የቅጣት ምት አመታት ልምምድ አልሰራም እንጂ አቅሙ አለኝ፡፡ ይህን ፍላጎቴን ውበቱ ስለሚያውቅ ከልምምድ በኋላ 2ዐ እና 3ዐ ደቂቃዎች ቅጣት ምት እለማመድ ነበርና
ውስጤ አለ ያለው ስሜትና አቅም አሁን ጠቅሞኛል፡፡ ያንን ቅጣት ምት ስመጣ ርግጠኛ የሆኩትም ለዚህ ነው… በቀጣይ በተደጋጋሚ ጊዜያት ተመሳሳይና ሌላ ሌላም አይነት ግቦችን ከኔ
ይጠብቁ ከእግዚአብሄር ጋር አሳካዋለው ብዬ ብዬ አስባለው፡፡
ሀትሪክ፡- የስፖርታዊ ጨዋነት መጣስ ለሀገራችን እግር ኳስ ጠንቅ ነው.. ሰሞኑን ደግሞ ደስ የማይሉ ነገሮች እየተሰሙ ነው…. እንዳተጨዋች ምን ትመክራለህ?
ጋዲሣ፡- እግር ኳስ ማለት ሠላም ማለት ነው፡፡ እኔ የማውቀው እግር ኳስ ሀገርን እንደሚያስታርቅ ብቻ ነው… ይህንንም እያየን ነው…. ከፖለቲካ የነፃ ከፀብ የራቀ ሰው የሚዝናናበት
መድረቅክ ነው በፍጹም ስሜታዊ ሊያደርገን አይገባም ሠላማዊ በሆነ መልኩ ችግሮችን መፍታት ይቻላል ሜዳዎቻችን የሠላም ቦታ ከመሆናቸው የተነሳ ፖሊስ ባይኖር ሁሉ ደስ ይለኛል
ሚዲያ ተመልካቹ ሁሉም የኳሱ አካላት በነፃነት ቢያዩ ደስ ይለኛል፡፡ ገና ባላደገ እግር ኪስ ላይ ረብሻ ቢነሣ እድገቱን ማቀጨጭ ስለሚሆን ቢታሰብበት እላለው በመነጋገር ልዩነታችንን መፍታት
አለብን ያ ነው የሚሻለው፡፡
ሀትሪክ፡ ሁሉም ተጨዋች ከ5ዐ ሺህ ብር በላይ አይከፈለው የሚለው ሕግ ለኳሱ ይበጃል- ?
ጋዲሣ፡- አይመስለኝም…ገንዘብ ከውጤት ጋር መያያዝ የለበትም ብዬ ነው የማምነው… ገንዘቡ እንጂ ኳሱ አላደገም የሚባለው ነገር ልክ አይመስለኝም፡፡ አከፋፈሉ ካልተስተካከለ
ለቀጣይ ጊዜያት አደጋ እንዳይፈጥር ስጋት አለኝ፡፡ ኳሱ እንዴት ይደግ በሚለው ላይ መነጋገር ሲኖርብን ገንዘብ መቀነስ ላይ ማተኮሩ አይበጅም ማለት እፈልጋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ጊዮርጊስ ቤት እነ ደጉና አዳነ ከወጡ በኋላ ክለቡ ውስጥ መሪ ጠፋ የሚሉ ወገኖች አሉ…. እውነት ነው?
ጋዲሣ፡- ውጤት ሲጠፋ ነው ብዙ ነገር የሚባለው…. ይሄም ከነዚህ ሃሣቦች አንዱ ነው እንዴት ነው መሪ የሌለው? አመራሩ ይለያይል እንጂ መሪዎቻማ አሉን…እነ ጌታነህ ሳላህዲንስ ምን
ሊባሉ ነው? ምናልባት የነ አዳነና ደጉ አለመኖር የተወሰነ የአመራር ልዩነት ይፈጥራል ቢባል ነው ትክክል የሚሆነው….ተጨዋቾችን ሲናገሩ የሚደመጡ መሪዎችማ በደንብ አሉ፡፡
ሀትሪክ፡- ሁሉም ተጨዋቾች የዳኞችን ውሳኔ በመቃወም ዳኛውን መክበብ ያበዛሉ.. ያዋጣል?
ጋዲሣ፡- ልክ አይደለም፤… የዳኛን ውሳኔ በመቃወምና በመክበብ ለውጥ አይመጣም ግን የዳኞቹም ሁኔታ በደንብ ሊታሰብበት ይገባል እንዳይከበቡ አቋማቸው ሊስተካከል ይገባል
የሚጫወቱትን ቡድኖች ትተው ሕጉን ብቻ ማክበር አለባቸው… ኮሚሽነሩ እዚህ ላይ ትልቅ ኃላፊነት አለበት… ከእግር ኳስ ጋር የተያያዘ ፍትህ የማይሰጡ ዳኞች አሉ.. እነርሱ በትክክል ሊዳኙ
መዘጋጀት አለባቸው…..ሰው ሆኖ የማይሳሳት ባይኖርም ውሳኔያቸውን ዳግም ሊያጤኑት ይገባል…. ይሄ ከሆነ ለውጥ ይኖራል ተጨዋቾችም ብንሆን ዳኞችን መክበብ ተገቢ ነው ብዬ
አላምንም…. ዋናው ግን ዳኞቹ በተቻለ መጠን ሕጉን ብቻ ሊያከብሩ ይገባል፡፡
ሀትሪክ፡- ዴኮ ሲዳማን አንተ ሃዋሳን ትታችሁ ለጊዮርጊስ የፈረማችሁት የተሻለ እድል ለማግኘትና የሊጉን ዋንጫ ለማሳካት ነው…እናንተ ስትገቡ ግን ባለፉት 2 አመታት ዋንጫ
አላገኛችሁም.. ምን ተሰማህ?
ጋዲሣ፡- አንዳንዴ እድለኛ አይደለሁም እንዴ ብዬ አስባለው ግን እንደ አዋቂ በዚህ ተስፋ መቁረጥ የለብኝም ብዬ ደግሞ አምናለሁ…. እድል መቼ እንደም ትመጣ ባይታወቅም የተቻለውን
መስራት ከኛ ይጠበቃል እር ሱን አድርገን መገኘት ብቻ ነው ያለብን… በግሌ ግን ያቺ የእድል አመት ደግሞ 2ዐ12 ይመስለኛል፡፡ለተጨዋቾቹም ሁሌ እናገራለሁ ጥሩ ቡድን አለን በኛ መሃል አሪፍ
ተነሳሽነቱ አለ ዘንድሮ ዋንጫው የኛ ይመስለኛል ብዬ እናገራለሁ ለደጋፊዎቻችንም የምለው ይህንን ነው…. ጊዜው የኛ ነው ጥሩ ስሜት አለን ጥሩ ውጤት ለማምጣት ተዘጋጅተናል ተፋ
ሳትቆርጡ ከጎናችን ሁኑ ማለት እፈልጋለሁ ያለፉትን ሁለት አመታት የምናካክስበት አመት 2ዐ12 ይመስለኛል፡፡
ሀትሪክ፡- የዋንጫ ማጣት ሀትሪክ አይሰራብንም እያልክ ነው?
ጋዲሣ፡- በጭራሽ አይታሰብም….የሊጉ ዋንጫ የኛ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- እስከ 12ኛው ሳምንት ድረስ ልዩ ብቃቱን አሳይቷል የምትለው ተጨዋች ማነው?
ጋዲሣ፡- አለ እንዴ…? አይመስለኝም ….ለየት ብሎ የወጣ ተጨዋች የለም….
ሀትሪክ፡- ለኢትዮጲያና ለኢትዮጲያዊያን ምን ትመኛለህ?

ጋዲሣ፡- ሃገሬን በጣም እወዳለሁ.. ሰላም እንድትሆን እመኛለሁ ሰላም ከሌለ ብዙ ነገሮች ይበላሻሉና ሁሉ ነገር ተረጋግቶ ፖለቲከኞች ልዩነታቸውን አጥብበው አለመግባባቶችን
አስወግደውና አርግበውሰላም በሃገሬ ላይ እንዲሰፍን እመኛለሁ….
ሀትሪክ፡- የጋዲሳ መዝናኛ ምንድነው?
ጋዲሣ፡- ብዙ መዝናኛዎች አሉኝ….የሃገርና የውጪ ፊልሞችን ማየት ደስ ይለኛል….ከካምፕ መውጣት ከደበረኝ ውስጥ ሆኜ የውቺ ፊልሞችን አያለሁ….ከወጣው ደግሞ ሃገርኛ
ፊልሞችን ማየት ደስ ይለኛል…በዚህ ደግሞ ረቡኒን ወድጄዋለው…ከጓደኞቼ ጋርም ሻይ ቡና ማለት ያዝናናኛል፡፡


ሀትሪክ፡- በቦታህ ምርጡ ተጨዋች ማነው?
ጋዲሣ፡- የኢትዮጲያ ቡናው ታፈሰ ሰለሞን ምርጫዬ ነው…….ጨዋታውን ሲመራ ከመስመር እየተነሳ ሲጫወት ያስደስ ተኛል….ምርጡ የመሃል ተጨዋች ነው በቦታዬ ቅድሚያውን
የምሰጠው ለርሱ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ፖለቲካ ትከታተላለህ?
ጋዲሣ፡- ብዙም አይደለሁም ፖለቲካ የመከታተል ልምዱም የለኝም
ሀትሪክ፡- ከውጪ የማን ደጋፊ ነህ?
ጋዲሣ፡- ከእንግሊዝ የማን.ዩናይትድ ከስፔን የሪያል ማድሪድ ደጋፊ ነኝ
ሀትሪክ፡- ብሩኖ ፈርናንዴዝ በመጨረሻ ተሳክቶ ለዩናይትድ ፈርሟል… የምትለው አለ?
ጋዲሣ፡- /ሳቅ በሳቅ/በጣም ደስ ብሎናል…ችግሩን ይቀርፋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ…ወቅታዊ አቋሙ ጥሩ ባይሆንም የሚሻሻል ቡድን እንደሆነ ይሰማኛል፡፡
ሀትሪክ፡- የሊቨርፑል ጉዞ አስደናቂ ነው አይደል?
ጋዲሳ፡- ከዩናይትድ ቀጥዬ የምመለከተው ጨዋታ የሊቨርፑልን ነው…ሲያሸንፉ ደስ ይለኛል ጥሩ ቡድንም ነው
ሀትሪክ፡- ከሃገር ውጪ የመጫወት ዕድል ብታገኝ ምርጫህ የትኛው ክለብ ነው?
ጋዲሣ፡- ሊቨርፑል ነዋ…ለየርገን ክሎፕ ቡድን ባጫወት ደስ ይለኛል …አሰልጣኙ ተጨዋቾችን የሚይዘው እንደ አባት ነው ለርሱ ቡድን ብሰለፍ ደስ ይለኛል
ሀትሪክ፡- ክርስቲያኖ ሮናልዶ ወይስ ሊዮኔል ሜሲ?
ጋዲሣ፡- /ሣቅ/ ያለጥርጥር ሮናልዶን አስቀድማለው፡፡
ሀትሪክ፡- ጋዲሣ አገባ.. እጮኛ አለው… ወይስ?
ጋዲሣ፡- /ሣቅ/ ጥያቄው ይለፈኝ ይለፈኝ /ሳቅ/
ሀትሪክ፡- የምታመሰግነው ካለ እድሉን ልስጥ ?
ጋዲሣ፡- አምላኬ እግዚአብሄር የመጀመሪያ ተመስጋኝ ነው…ከርሱ በመቀጠል በዙሪያዬ ከበው ድጋፍ እያደረጉልኝ ያሉ ሰዎች አሉ… በተለይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት እንዳልቀጥል
ተቃውሞ ሲበዛ ከጎኔ ሆነው የታገሉልኝ ሰዎች አሉ እነርሱን ማመስገን እፈልጋው፡፡ አሁን የደረስኩበት ደረጃ እንድደርስ የረዱኝም ሰዎች አሉ እነሱንም በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ደጋፊቻቻችን
ሁሌም ከጎናችን ናቸው የትም እንሂድ አብረውን ናቸው በዚህም ደስተኛ ነን.. ከዚህ በተሻለ ዘንድሮ ለየት ብለው መቅረብ አለባቸው ተጨዋቾቹ ጋር ያለው ተሳሽነት የሚገርም ነው
ዋንጫውን ለመውሰድ ሁሉም ቋምጧል…. የደጋፊው አብሮነት በጣም ያስፈልገናል ሁሌም አብረውን እንደነበሩ አሁንም በድጋፋቸው በተሻለ መንገድ አብረውን ሊሆኑ ይገባል እላለው፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport