“የኢትዮጵያ ግብ ጠባቂዎችን ለማጎበዝ የውጪዎቹን በረኞች መከልከል መፍትሔ ነው ብዬ አላምን” አቶ ሽፈራው ተ/ሃይማኖት (የመቐለ 7ዐ እንደርታ ዋና ስራ አስኪያጅ)

ከ2013 ጀምሮ ማንኛውም የኢትዮጵያ ክለብ የውጪ ሀገር በረኞችን መጠቀም አይችልም የሚል ሕግ እንዳወጣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለየክለቦቹ በላከው ደብዳቤ አስታውቋል፡፡ ይህን ተከትሎ ወደ መቐለ 7ዐ እንደርታ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሽፈራው የደወለው ባልደረባችን ዮሴፍ ከፈለኝ ስለወጣው አዲሱ ሕግ ክለቡ ከአልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ ጋር ሊለያይ ነው መባሉ ዙሪያና ሌሎች ጉዳዮች ተወያይተዋል፡፡
ሀትሪክ፡- መቐለ እንዴት ናት?
ሽፈራው፡- ምንም አትልም ይሄ አለም አቀፍ ችግር ኮሮና ቫይረስ ግን ሁሉንም ነገር ወደፊት ጉዞ እንዳይሄድ ማድረጉ ትንሽ ቅር ያሰኛል፡፡
ሀትሪክ፡- አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ ጋር ተለያያችሁ እንዴ?
ሽፈራው፡- ለምን ጠየቅከኝ … ምን ሰምተህ ነው?
ሀትሪክ፡- ውሉ በማለቁ ቀጣይ ማረፊያ ክለቡ በቅርቡ ይታወቃልየሚል ነገር ሰምቼ ነው?
ሽፈራው፡- /ሳቅ በሳቅ/ በራሱ አቧራ ማስነሳት የሚፈልግ ወገን ካልሆነ በስተቀር የምናውቀው ከኛ ጋር መሆኑን ነው፤ በመርህ ደረጃ ተስማምተን ተጨዋቾችን እየመለመለ እንደሆነ ነው የማውቀው፡፡ በኛ እምነት ቀጣዮቹ 3 አመታት አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ ከኛ ጋር ይሆናል ብለን እናምናለን፤ የማውቀው ይህንን ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ በአፍሪካ መድረክ ተወካይ ማጣቷ አሁንም በሊጉ ኮሚቴ ፀንቷል ምን ማለት ይቻላል?
ሽፈራው፡- ሊግ ካምፓኒው የሀገሪቱን ኳስ የማሳደግ እንጂ ሌላ ኃላፊነት የለውም ያለውን እድል ተጠቅመን በአፍሪካ ደረጃ መካፈላችን መቀጠል አለበት ብይ ነው የማስበው፡፡ ለጠቅላለ ጉባኤ የተመራ በመሆኑ ክለቦች ይወያዩበታልና ሁሉን ነገር ያኔ እናያዋለን፡፡ አንዳንድ የሕግ ክፍተቶችን አስተካክለው ለቀጣይ አመታት ችግር እንዳይፈጠር የሚያደርግ ስራ ሰርተዋል፡፡ ጥሩ ነው ሊበረታታ ይገባል፡፡ እዚህ ላይ መናገር ያለብን ነገር የኔ ክርክር ምንጭ እንደ ስፖርት ሰው ይጠቅማል ብዬ የማስበው ይሄንን ነው፡፡ የትም ላንደርስ ተሳትፈን አልተሳተፍን ለውጥ የለውም ለምኑ ነው ክርክሩ የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ አሁን ይሄን መነጋገር የለብንም፡፡ እየተሸነፍን እያሸነፍን ዛሬ ላይ የደረስነው ስለተሳተፍን ይመስለኛል፡፡ ባንሳተፍ አሁን ደርሰናል የምንለው ቦታ ለመድረሳችንስ እርግጠኛ መሆን እንችላለን? ጊዜማ ለውጥ ያመጣል፡፡ ኳሱ አማተር ነው ቢባልም የእድገት ለውጥ አለው ሊጉ በካምፓኒ ደረጃ ተዋቅሯል ይሄም ለውጥ መከበርና መጠበቅ አለበት፡፡
ሀትሪክ፡- ፌዴሬሽን ከ2ዐ13 ጀምሮ የውጪ በረኛ አንቀበልም የሚል ትዕዛዝ ማስተላለፉ ይታወቃልና ይስማሙበታል?
ሽፈራው፡- በፍፁም አልስማማም…. በእርግጥ ለኢትዮጵያዊያን ብቻ የተፈቀደ ለውጥ ሀገር ዜጋ የማይቻል ፖሊስ መከላከያ ደህንነት የሚሰኙ ቦታዎች ከሀገር ሉዓላዊነት አንፃር ለውጭ ዜጋ አይፈቀድም፡፡ ከዚያ ውጪ ግን ችግር የለውምና ከውጪ ተጨዋቾች ይመጣሉ የኛዎቹም ወደ ውጪ ይሄዳሉ ይሄ የተለመደ አሰራር እኛ ሀገር ሲቀር ያበሳጫል የኢትዮጵያ በረኞችን ለማጠናከር መፍትሔው የውጪዎቹን በረኞች በመከልከል ነው ብዬ አላምንም፡፡ የውጪ በረኛ መጠቀም ከጀመርንኮ 5 ወይም 6 አመት አልሞላውም፡፡ ጊዮርጊስ ብቻ ያመጣል ሌሎቻችን በሀገር ውስጥ በረኛ እንጠቀማለን፤ ይሄ ሁኔታ የበረኞቻችን ስህተት አልታደገም፡፡
ሀትሪክ፡- የበረኞች እጥረት አለብንብለው ያስባሉ ?
ሽፈራው፡- በኔ እምነት የስልጠናና የምልመላ ስርዓታችንን መመርመር አለብን፡፡ በሚገባ ተሰጥኦ ያለበት ቦታ ነው ጥሩ ጥሩ በረኞች አሉንኮ፡፡ እነ ጀማል ጣሰው ጌትነት የመሳሰሉ ፈርተዋል፤ ነገር ግን በብዛት የሉንም እንደ ባለሙያ ስንመለምልና ወደ ስልጠና ስናስገባ ግን ችግር ያለብን ይመስላል የሆነ አንድ ስህተት ያለው ይሄ ይመስለኛል የውጪ በረኛ አይምጣ ብሎ መጮህ እንዳንሰራ ሰበብ ይሆነናል ብዬ እሰጋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- የመን፣ ግብፅ፣ ሳዑዲ አረቢያና ቻይና በረኛ ከውጭ አያስፈርሙም… ለኛ ሲሆን ለምን አይሰራም ከውጪ በረኛ መቅረት አለበት የሚሉ አሉና ምን ማለት ይቻላል?
ሽፈራው፡- ከውጪ በረኛ አያስፈልግም ከተባለ የሀገር ውስጥ በረኞችን በጥራትና በብዛት ሊኖረን ይገባል፡፡ ፕሪሚየር ሊግ ላይ ብቻ ቢከለክልና 16 በረኞች ቢኖሩን ለብሔራዊ ቡድኑ ጥንካሬ ይፈጥራል ምክንያቱም ማች ፊትነሳቸው አሪፍ ስለሚሆን… ያም ቢሆን ግን ጊዜያዊ መፍትሔ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ በስራ አስኪያጅ፣ በአሰልጣኝና በተጨዋችነት ቦታ ተፎካካሪ ማድረግ እንጂ ለማንኛውም ሰው ክፍት በሆነ ስራ ላይ ገደብ በማድረግ ለውጥ መጠበቅ ልክ አይሆንም፡፡ ታች የሚጠበቅብን ሥራ እንዳትሰራ ነው የሚያደርግህ… እሺ በእግዱ እንስማማ የልምድ ልውውጡስ አቅም የመኮራረጅስ ከየት ይመጣል? ይሄም ራሱን የቻለ ጥያቄ ነው ተጨዋቾቹ ከውጪ መጥተው እልህ ውስጥ እንዲያስገቧቸው ማድረግ እንጂ መዝጋት ትክክል አይደለም ባይ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ጀማል ጣሰው ጋር ስናወራ የኢትዮጵያ አሰልጣኞች ለሀገር ውስጥ በረኞች እምነቱ የላቸውም አለ ይሄስ ትልቅ ችግር አይመስልዎትም?
ሽፈራው፡- አሰልጣኞች የሚፈልጉት ውጤት ነው፤ የኢትዮጵያ በረኛ ጎበዝ ሆኖ የውጪ ሀገር በረኞችን የሚያስገባበት ምክንያት የለውም፡፡ ሀገራቸው ግን ጥሩ በረኛ መሆን ሲያቅታቸው ወደዚህ ይመጡና የተሻለ ሆነው ተገኝተው የመሰለፍ እድል ያገኙ ይመስለኛል፡፡ አሰልጣኞቹ በፍጥርሃትና በጥላቻ ተሞልቶ የኢትዮጵያዊን በረኞች ይገፋል ብዬ አላምንም፡፡ በውበቱ ጊዜ ፋሲል ሁለቱንም በረኞች አፈራርቆ አጫውቷል፤ ከቻሉ ይጫወታሉ በኔ እምነት የበረኞችን አናሊስስን ብሰራ በትኩረትና በጊዜ አጠባበቅ የወጪዎቹ ከኛዎች ይሻላሉ፡፡ የብሔራዊ ቡድን በረኛ ለመሆን የግድ የፕሪሚየር ሊግ በረኛ መሆን አይገባም፡፡ መቐለ 7ዐ እንደርታ ለዋንጫ ሲፎካከር ስለነበር ብዙ ጨዋታ ያደረገን በረኛ ለመቀየር ይከብዳል፤ ማንኛውም በረኛ በብቃቱ እንጂ በቀለሙና በፓስፖርቱ ልዩነት ቦታ ይኖረዋል ማለት አይቻልም፡፡ ልክም አይመስለኝም፤ ለምንስ የኛ አሰልጣኞች በሀገር ውስጥ በረኞች እምነት አጡ የሚለው መመርመር አለበት ባይ ነኝ፡፡ ለምንስ 3 ወይም 4 ብቻ ጎበዝ በረኞች እንጠቅሳለን? ለምን 2ዐ ወይም 3ዐ በረኛ አይኖረንም? እንግሊዞች በረኛ አልወጣ ብሏቸው ሲጨንቃቸው ከስፔን በረኛ ዜግነት ሊያስቀይሩ ሁሉ ነበር ጀርመኖች ደግሞ በረኞች እንደአሸን እየፈሉላቸው ነው፤ በቃ ጥሩ የሰሩ ይደምቃሉ ያልሰሩት መድመቅ አይችሉም ጣሊያን የአለም ምርጥ በረኞች መገኛ ነበረች፡፡ አሁን ደግሞ ስፔኖች ተቆጣጥረውታል፤ በአጠቃላይ ለመናገር የሰራነውን ልክ ነው፤ የምናገኘውና ለዘላቂ ድል ከታች ከታዳጊዎች ስልጠና ብንነሣ ይሻላል፡፡ የውጪ በረኛ መከልከል አያዋጣም ለማለት ነው፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport